Tuesday, December 5, 2023

ልማታዊ ዴሞክራሲ መቶ በመቶ ፓርላማውን ከተቆጣጠረ በኋላ ያነጣጠረበት ሌላው ዘርፍ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹ምርጫ 2002 በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዝቡ በዴሞክራሲያዊ አካኋን ፀረ ሕገ መንግሥት ኃይሎችን ማርጅናላይዝ (ጥግ ማስወጣቱ) ማድረጉና ተመልሰው የሚያገግሙበትን ዕድል በጣም ጠባብ መሆኑን ማረጋገጡ አንድ አዲስ ስትራቴጂካዊ ምዕራፍ መጀመሩን ያሳያል፡፡ … በምርጫ 2002 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ የማይሆኑበት ደረጃ ላይ ስላደረስናቸው ሥራችን ተጠናቋል አልቋል ማለት አይደለም፡፡ ፀረ ሕገ መንግሥታዊ አቋማቸውን እስካልቀየሩ ድረስ መብታቸውን በጥብቅ አክብረን በማያቋርጥ ዴሞክራሲያዊ ትግል አሁን ከደረሱበት ደረጃ እንዳያልፉና እንዳያንሠራሩም በርትተን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡››

ከላይ የተገለጸው መግቢያ የተወሰደው ኢሕአዴግ ለልሂቃን አባላቱ በሚያሳተመው አዲስ ራዕይ መጽሔት የሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም. ዕትም ነው፡፡ ይህም ማለት በግንቦት ወር 2002 ዓ.ም. የተካሄደው አራተኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢሕአዴግና አጋሮቹ 99.6 በመቶ የፓርላማውን መቀመጫዎች ማሸነፋቸው ከተረጋገጠ በኋላ በመጽሔቱ ዋና አዘጋጅና በአገሪቱ የቀድሞ ጠቅላይ ማኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የተጻፈ የፓርቲው አቋም ነው፡፡

በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥም ይህ የፓርቲው አቋም ሥር ሰዶ የፓርላማውን 547 መቀመጫ ሙሉ በሙሉ ከአገሮቹ ጋር በመሆን ተቆጣጥሮታል፡፡

ይህንን በፓርላማ ውስጥ ካጠናቀቀ በኋላ ደግሞ ፓርቲው የያዘውን የልማታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮት (የኢኮኖሚ ሞዴል) በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለ ሥጋት ማስረፅን ይፈልጋል፡፡

በዚህ እምነት የተንቀሳቀሰው ገዥው ፓርቲ ቀጣይ ትኩረቱን ወደ አገሪቱ መገናኛ ብዙኃን አድርጓል፡፡ ለዚህም ይረዳው ዘንድ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መገናኛ ብዙኃን ፖሊሲን በረቂቅ ደረጃ አዘጋጅቷል፡፡

የዚህ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ መነሻና መድረሻም፣ ይኼንን የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ልዕልና የማስጠበቅና የሕዝብ የነቃ ተሳትፎን ማቀጣጠል መሆኑን ይገልጻል፡፡

የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ይዘት

በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የሥርዓቱ ማኅበራዊ መሠረቶች ሰፊው የአርሶና የአርብቶ አደር ማኅበረሰብ፣ በከተማ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪ አንቀሳቃሾች፣ ላብ አደሮች፣ በመንግሥት ሥራ ላይ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ልማታዊ ባለሀብቱ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለው የኢኮኖሚ አሠላለፍ ሲመረመር አሠላለፉ ልማታዊ የዕድገት አማራጭ አስፈላጊነት የግድ የሚልበት ሁኔታ ውስጥ መሆኑን ይገልጻል፡፡

በዚህ የልማታዊ ዴሞክራሲ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ውስጥ የኒዮሊበራል የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲን ይዞ መቀጠል አዋጭ እንዳልሆነ ረቂቁ ያስረዳል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የኒዮሊበራል አቅጣጫ ለጥቂት ቱጃሮች ጥቅም የቆመ በመሆኑ፣ ዋነኛ የሕዝብ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ሊያገለግል የሚችልበት ዕድል ከአፈጣጠሩና ከሚወክለው ማኅበራዊ መደብ አንፃር ጠባብና ዝቅተኛ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍን ቀጣይ አቅጣጫ ለመተለም ከገዥው የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት መሠረታዊ አቅጣጫዎችና ከማኅበራዊ መሠረት አወቃቀር ጋር የተመጋገበና የተጣጣመ ሆኖ የበላይነቱን ይዞ መቀጠሉ የማይቀር መሆኑን ይገልጻል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ በቀጣይ እንዲፈጠር የሚፈለገው የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መገናኛ ብዙኃን ተልዕኮ አብዛኛው ሕዝብ በመሠረታዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የጋራ አመለካከት እንዲይዝ ወቅታዊና ተከታታይ መረጃዎችን በማሠራጨት የሕዝቡን በመረጃ ላይ የተመሠረተ ንቅናቄና ሁለገብ ንቁ ተሳትፎ እንዲቀጣጠል ማድረግ ነው ይላል፡፡ በዚህም ሕዝቡን ለልማት፣ ለዴሞክራሲና ለመልካም አስተዳደር ተግባራዊነት ማነሳሳት አንደኛው ነው፡፡ በሌላ በኩል በአፈጻጸም ሒደት የሚከሰቱ ድክመቶችንና ውስንነቶችን ነቅሶ በማውጣት፣ ችግሮቹንና ውስንነቶቹን ከነምንጮቻቸውና የመፍትሔ አቅጣጫዎቻቸው ተንትኖ በማስቀመጥ፣ የሥርዓቱ ፖለቲካዊ ጤንነት ተጠብቆ እንዲጓዝ የሕዝብ ዓይንና ጆሮ ሆኖ ማገልገል እንደሆነ ይጠቁማል፡፡

የፖሊሲ ረቂቁ ከላይ የሰፈረውን ይበል እንጂ በሌላ በኩል ደግሞ የጋዜጠኝነት መርህን እንደሚጠብቅ ይገልጻል፡፡ ዜጐች ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን ሐሳብንና አመለካከትን በነፃነት የመግለጽ መብቶች ሳይደፈቁ በማናቸውም የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች እንዲሠራጩና እንዲተላለፉ ማድረግ፣ በዘርፉ ተቀባይነት ያላቸውን የሚዛናዊነት፣ የሀቀኝነትና የትክክለኝነት መርሆዎች ላይ ተመሥርተው ማናቸውም ሐሳቦች እንደሚንፀባረቁ ይገልጻል፡፡   

ስለሆነም በኢትዮጵያ የሚገኘው የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ አገሪቱ አሁን የተያያዘችውን የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቀጣይነት ለማረጋገጥና ርዕዮተ ዓለሙ በአብዛኛው ኅብረተሰብ ክፍል አስተሳሰብ ላይ ልዕልና እንዲያገኝ ቁልፍ ሚና መጫወት እንደሚኖርበት ያስረዳል፡፡

‹‹በማንኛውም አገር የሚገነባውና ሊገነባ የሚታሰበውም የመገናኛ ብዙኃን ኢንዱስትሪ በሥርዓቱ ዋነኛ ምሰሶና ማገር በሆነው የፖለቲካል ኢኮኖሚ መስመር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በወቅቱ የበላይነት ያገኘውን የፖለቲካል ኢኮኖሚ አስተሳሰብና ርዕዮተ መሸከም የማይችልና መስመሩን የህልውናው መሠረት አድርጐ የማያንቀሳቅስ የመገናኛ ብዙኃን ኢንዱስትሪ፣ አገሪቱ ዕውን ለማድረግ የምትረባረብበትን የህዳሴው መስመር ዋነኛ ግቦች የሆኑትን የጋራ ብሔራዊ መግባባትና የገጽታ ግንባታ ግቦች በፍፁም ሊያሳካ አይችልም?›› በማለት አፅንኦት ይሰጣል፡፡

ይህንን መሠረት በማድረግም በኢትዮጵያ የሚገነባው የመገናኛ ብዙኃን ተቋም ይህንኑ ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ ተገንዝቦ ለመፋለም መዘጋጀትና ቁልፍ ተልዕኮው አድርጐ ሊወስደው እንደሚገባ ያሰምርበታል፡፡

የሕዝብ (የመንግሥት) የመገናኛ ብዙኃን ቀጣይ የዕድገት አቅጣጫ ከመንግሥት የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫዎችና ከሥርዓቱ ልዩ ባህሪያት ጋር የተጣጣመና ተመጋጋቢ ሆኖ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባው፣ የግል መገናኛ ብዙኃን ህልውናም ቢሆን ከሥርዓቱ ቀጣይነት ጋር የተሳሰረ መሆኑን በአግባቡ ተቀብሎ እንዲንቀሳቀስ እንደሚጠበቅበት በአቋም ደረጃ ያስቀምጣል፡፡

ይህ ፖሊሲ ገና በረቂቅ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም የተለየ ለውጥ እንደማይመጣ ደግሞ፣ ሰሞኑን በውይይት ላይ የሚገኘው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ያስረግጠዋል፡፡

‹‹የከፍተኛ ትምህርትና የሥልጠና ተቋማት ሥርዓተ ትምህርት ላይ ፈጣን ማስተካከያ በማድረግ በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የታነፁ የኮሙዩኒኬሽን፣ የሚዲያና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን በማፍራት የብሔራዊ መግባባት ተቋማት ከኒዮሊበራል አስተሳሰብ ተፅዕኖ የተላቀቀ የሰው ኃይል እንዲኖራቸው የማድረግ ሥልት መከተል ወሳኝ ነው፡፡ የመገናኛ ኢንዱስትሪው በስፋትና በጥራት ወደ አዲስ ምዕራፍ በማሸጋገር የልማታዊ የዴሞክራሲ አስተሳሰብና በጐ አገራዊ ገጽታ መገንባት፤›› የአምስት ዓመቱ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መሆኑን ያብራራል፡፡

ሲንጋፖር

የሩቅ ምሥራቋ አገር ሲንጋፖር ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በኋላ ከማሌዥያ ፌዴሬሽን ተላቃ እ.ኤ.አ. በ1965 ‹‹ሪፐብሊክ ኦፍ ሲንጋፖር›› ተብላ ሉዓላዊ መንግሥት መመሥረት ችላለች፡፡

የአገሪቱ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትና አገሪቱን እ.ኤ.አ. እስከ 1990 ድረስ ለ31 ዓመታት የመሩት ሊኩዋን የው የልማታዊ መንግሥት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ርዕዮትን በመተግበር፣ በዓለማችን በአገልግሎት ዘርፍ ላይ መሠረት ያደረገ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበች አገር አድርገዋታል፡፡ ይሁን እንጂ በፕሬስ ነፃነት ከ180 አገሮች 153ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በአገሪቱ ሕገ መንግሥቷ ሐሳብን በነፃነት የማራመድና የመናገር መብቶች የአገርን ጥቅምና ብሔራዊ ደኅንነትን እስካልጐዳ ድረስ የተጠበቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተግባር ግን ከዚህ በተቃራኒ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ከገዥው ፒፕልስ አክሽን ፓርቲና ከባለሥልጣናቱ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡

አገሪቱ የውጭ የሚዲያ ተቋማት በግዛቷ የሚዲያ ሥራ ውስጥ እንዲሳተፉ ብትፈቅድም፣ በሕግ ደረጃ በውስጣዊ የሲንጋፖር የፖለቲካ ሁነቶች ላይ መዘገብ ተከልክለዋል፡፡ የአገሪቱ የኮሙዩኒኬሽን ሕጐች መደበኛ የመገናኛ ብዙኃንን ከመቆጣጠር አልፈው፣ የኢንተርኔትና የማኅበራዊ ድረ ገጾች አጠቃቀም ሕጐችንም በመቅረፅ የአገሪቱን ልማታዊ እንቅስቃሴ የሚፃረሩ መልዕክቶችን ያሠራጫሉ ባሏቸው ላይ ሕጋዊ ዕርምጃዎችን ይወስዳሉ፡፡

ሲንጋፖር ይህንን የሚዲያ ፖሊሲና ሕግ ለመቅረፅ መነሻዋ የልማታዊ መንግሥት ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌሎች የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ከተከተሉት የልማታዊ መንግሥት ፖለቲካዊ ጽንሰ ሐሳብ ላይ ዴሞክራሲን በመጨመር፣ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ጽንሰ ሐሳብን የመከተልና የማስፋፋት ሥራ ጀምራለች፡፡ በዚህ ዴሞክራሲን እንደ መሠረቱ በሚቀበል ልማታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮት ሥር እየተቀረፀ ያለው ልማታዊ ዴሞክራሲ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ መስመር ዴሞክራሲያዊነቱ ግን አጠያያቂ ሆኗል፡፡

የፖሊሲው መስመር ትክክለኛነት

የልማታዊ ዴሞክራሲ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ አቅጣጫ ትክክለኝነትን ለመለካት በዋነኝነት መሣሪያ ሊሆን የሚችለው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጥርት አድርጐ ሐሳብን በነፃነት የመያዝና የመግለጽ መብቶችን ያንፀባረቀ ነው፡፡

በተለይ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ አራት በዋነኝነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ‹‹ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሐሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል፤›› በማለት ይደነግጋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ይህንን ይበል እንጂ የልማታዊ ዴሞክራሲ የመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ ፖሊሲው ‹‹የኢትዮጵያ ብዝኃነት ለተለያዩ ኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶች ምርጥ መሸሸጊያ በመሆን፣ ከውጭው የኒዮሊበራሊዝም ዘመቻ ጋር ተደርቦ እጅግ ከፍተኛ ፈተና የሚፈጥር ነው፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ የሚገነባው የመገናኛ ብዙኃን ተቋም ይህንኑ ነባራዊ ዓለም አቀፍና ውስጣዊ ተግዳሮቶችን፣ እንዲሁም የሥርዓቱን አደጋዎችና መገለጫዎቹን በጥልቀት በመረዳትና የዕለት ተዕለት የሥራው አካል በማድረግ በአግባቡ ለልማታዊ አስተሳሰብ ልዕልና ያለመታከት የሚሠራ ሊሆን ይገባዋል፤›› ይላል፡፡

ፖሊሲው ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ አሁን በአገሪቱ ያሉ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት አደረጃጀትና አፈጣጠር እንደማይጠቅመው በመለየት መውጫ መንገዱን ይቀይሳል፡፡

ስትራቴጂውም በአማተር ጋዜጠኝነት፣ በፊልም፣ በማስታወቂያና በተመሳሳይ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶች የተፈጥሮ ስጦታቸውን ማውጣት እንዲችሉ በጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ አንዱ መንገድ ነው፡፡

በልዩ ልዩ የወጣትና የሴት ማኅበራት ተደራጅተው በጋዜጠኝነት ለመሰማራት ፍላጐት ያላቸውን በመመልመልና በማሠልጠን በኅትመትም ሆነ በጋዜጠኝነትና በዘጋቢነት ሙያ፣ እንዲሁም በብሮድካስት ኢንዱስትሪው በስፋት እንዲሰማሩ ልዩ ድጋፍ ማድረግ ሌላኛው መንገድ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ፋኩልቲ ዲን የነበሩት ዶ/ር አብዲሳ ዘረዓይ የተጠቃለለ የሚዲያ ፖሊሲ በአገሪቱ ለማበልፀግ መሞከሩን በተገቢነት ያነሳሉ፡፡

ማንኛውም የሚዲያ ፖሊሲ መነሻ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ነው የሚሉት ዶ/ር አብዲሳ፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የመነጋገርና ሐሳብን በነፃነት የመያዝ መብቶችንና የፕሬስ ነፃነትን አስመልክቶ የያዘው ድንጋጌ፣ ማንኛውም የሊበራል ዴሞክራሲ ሕገ መንግሥት የሚይዛቸውን መሠረታዊ ግብዓቶች ያካተተ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የሚዲያ ነፃነትን የሚደነግጉ ጠቃሚ ነጥቦች፣ ከልማታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰቦች ጋር በከፍተኛ ደረጃ የሚቃረኑ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

‹‹የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አስተሳሰብን መሠረት አድርጐ የሚዘጋጅ አጠቃላይ የሚዲያ ፖሊሲ እንዴት አድርጐ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ላይጥስ (ላይቃረን) እንደሚችል አይታየኝም፤›› ብለዋል፡፡

መሆን የሚገባውን በተመለከተም ተጠይቀው የልማታዊ ዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ ወደ አገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ መንፈስ መምጣት ይኖርበታል እንጂ፣ ሕገ መንግሥቱን ወደ ልማታዊ ዴሞክራሲ ማምጣት ተገቢ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡

‹‹የሚቀረፀው ፖሊሲ የልማታዊ ዴሞክራሲን ጽንሰ ሐሳብ ለመገንባት ከሆነ ይህ አካሄድ የሕገ መንግሥቱ የነፃ ሚዲያ ድንጋጌዎች ፍፃሜ ጅማሮ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ተገቢው መንገድ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ጠብቆ ማበረታቻዎችን ብቻ በመስጠት፣ የሚዲያ ተቋማት ፈልገው ወደ ልማታዊ ዴሞክራሲ እንዲመጡ ማድረግ ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡   

  

  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -