የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሦስት አዲስ ሚኒስትር ዴኤታዎችን ሾመ፡፡ በዚህም መሠረት በሚኒስቴሩ የአሜሪካ ጉዳዮች ጄኔራል ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ አገሪቱን ለረጅም ዓመታት በዲፕሎማሲው መስክ ያገለገሉትንና በአሜሪካና በአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር የነበሩትን፣ አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስን በመተካት ተሹመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የቀድሞው የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ዮናስ ዮሴፍና የቀድሞው የሐረሪ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ረጋሳ ከፋለ አቶ ከድር ደዋኖንና በአዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ካቢኔ በሚኒስትር ማዕረግ የብሔራዊ ፕላኒንግ ኮሚሽን ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙትን፣ ዶ/ር ይናገር ደሴን በመተካት የሚኒስትር ዴኤታ ሹመት አግኝተዋል፡፡
በተመሳሳይ የፌደራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ሁለት ሚኒስትር ዴኤታዎች የተሾሙለት ሲሆን፣ አቶ ሙሉጌታ ውለታው ባሉበት እንደሚቀጥሉ ታውቋል፡፡
ለሚኒስቴሩ አዲስ የተሾሙት ሁለቱ ሚኒስትር ዴኤታዎች ደግሞ የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝና የቀድሞው የአዋሽ አርባ ከተማ አስተዳዳሪ አቶ አወል አርጊሶ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት አቶ ካይዳኪ የታዳጊ ክልሎችና የአርብቶ አደር ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሲሆኑ፣ አቶ አወል ደግሞ የብዙኃን፣ የሙያ ማኅበራትና የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ሆነዋል፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ደግሞ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ሁለት ሴት አመራሮች የተመደቡለት ሲሆን፣ የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ኃላፊ ወ/ሮ ፍሬሕይወት አያሌውና የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወርቅነሽ ብሩ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ረዳት ሆነው የተሾሙትን አቶ እውነቱ ብላታንና አቶ ሽመልስ ከማልን እንደሚተኩ ታውቋል፡፡
ዶ/ር ዋቅጋሪ ፉሪ ደግሞ የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲሾሙ፣ በዚህ ቦታ ሲያገለግሉ የነበሩት ዶ/ር ዓለሙ ስሜ ደግሞ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ተሾመዋል፡፡ ዶ/ር ዓለሙ የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ሆነው በመሥራት ማገልገላቸው የሚታወስ ነው፡፡
የቀድሞው የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ በየነ ገብረ መስቀል ደግሞ፣ አዲስ የተቋቋመው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ተሾመዋል፡፡
ቀደም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ደዋኖ ከድርና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል፣ በየትኛው የሥራ መደብ እንደተሾሙ ወይም እንደተመደቡ ለማወቅ አልተቻለም፡፡