– 45 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት የህንዱ ልብስ ፋብሪካ ሥራ ጀምሯል
በመጪው ሚያዝያ ሊጠናቀቅ እንደሚችል በሚነገርለት የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የውጭ ኩባንያዎች የማምረቻ ቦታ መያዝ ጀመሩ፡፡ የቻይናው ኢንዶቻይን ኩባንያ ሁለት የማምረቻ ሼዶችን ለመከራየት ጫፍ ደርሷል፡፡
ኢንዶቻይን አፓረል የተባለው የቻይና ኩባንያ በሐዋሳ እየተገነባ በሚገኘው ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለ11 ሺሕ ካሬ ሜትር የማምረቻ ቦታ ማግኘቱን፣ የኩባንያው ጊዜያዊ ኃላፊ አኒላ ኩራላንቴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ኩባንያው ዝቅተኛውን 200 ሺሕ ዶላር ካፒታል በብሔራዊ ባንክ በኩል በመክፈል ወደ ኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተቀላቅሏል፡፡
ይሁንና ኩባንያው ተጨማሪ አምስት ሺሕ ካሬ ሜትር ማምረቻ እንዲሰጠው ድርድር ላይ እንደሚገኝ ያስታወቁት ኩራላንቴ፣ ስምምነት እስከሚፈጸም ድረስ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት እንደሚቆጠቡ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ፋብሪካው አልባሳትን የማምረት፣ የማቅለምና የላውንድሪ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችሉትን ማምረቻዎችን እንደሚተክል ገልጸው፣ ከ2,000 እስከ 3,000 ለሚገመቱ ዜጎች የሥራ ዕድል ሊያስገኝ እንደሚችልም አስታውቀዋል፡፡ ከ90 ከመቶ በላይ ሥራው የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችን ከሌሎች አምራቾች በመግዛት ማከፋፈል የሆነው ኢንዶቻይን ኩባንያ፣ ይህም ሆኖ ከቻይና ባሻገር በካምቦዲያና በቬትናም ማምረቻ ፋብሪካዎች እንዳሉት ኩራላንቴ ጠቅሰዋል፡፡
በመጀመሪያ የግንባታ ምዕራፉ በ100 ሔክታር መሬት ላይ ግንባታው እየተካሄደ ከሚገኘው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተጨማሪ በድሬዳዋ፣ በኮምቦልቻ፣ በመቀሌ፣ በአዳማና በጅማ ሌሎች ፓርኮች እንደሚገነቡና ለኢንቨስተሮች ዝግጁ እንደሚደረጉ ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል በ45 ሚሊዮን ዶላር በቢሾፍቱ ከተማ የተገነባው የህንዱ ካኖሪያ አፍሪካ ቴክስታይልስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ጥቅምት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በተደረገ ሥነ ሥርዓት በይፋ ሥራ መጀመሩን አብስሯል፡፡ ኩባንያው ሥራ ከጀመሩ ትልልቅ አልባሳት ገዥዎች ምርቱን እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ለሪፖርተር የገለጹት የኩባንያው የገበያ ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ጃይ ሶያንታር ናቸው፡፡
ካኖሪያ በአብዛኛው የጅንስ ጨርቆችን በማምረት ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ሲጠበቅ ከወዲሁ ፒቪኤች፣ ቪኤፍ ኮርፖሬሽን እንዲሁም ጄ.ሲ. ፔሪ የተባሉ የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያዎች ለመግዛት እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ሶያንታር አስታውቀዋል፡፡ በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ሜትር በላይ የጅንስና የሌሎች አልባሳት ጨርቆችን በማምረት ለገበያ የማቅረብ አቅም ያለው ፋብሪካ መሆኑም ተነግሮለታል፡፡