Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የውጭ ኩባንያዎችን በመኖርያ ቤቶች ግንባታ ለማሳተፍ የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ውስጥ የውጭ አገር ኮንትራክተሮችን ለማስገባት የወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ተገምግሞ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት፣ ለከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ተላከ፡፡

የጨረታውን ውጤት ሚኒስቴሩ የሚቀበል ከሆነ፣ 14 የውጭ ኩባንያዎች በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በተከፈተው ዓለም አቀፍ ጨረታ 28 የውጭ አገር ኩባንያዎች ፕሮፖዛላቸውን ይዘው በመቅረብ ተወዳድረው ነበር፡፡

ላለፉት ዘጠኝ ወራት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ኢንስቲትዩት ጨረታውን በተመለከተና የውጭ ኩባንያዎች በመኖርያ ቤት ግንባታ ውስጥ ሲሳተፉ የመጀመርያ ጊዜ በመሆኑ አሠራሩን ሲያጠና ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዮሴፍ ብሩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢንስቲትዩቱ ሥር የተዋቀረው ኮሚቴ ሥራውን ጨርሶ ለሚኒስቴሩ ልኳል፡፡

በግምገማ ሒደቱ በክፍያ ላይ መግባባት ላይ ያለመደረሱን ዶ/ር ዮሴፍ አስረድተው፣ የውጭ ኩባንያዎቹ ከራሳቸው የፋይናንስ ምንጭ ይዘው ይመጣሉ? ከመጡስ እንዴት ነው የሚከፈለው? መንግሥትስ በምን ዓይነት መንገድ ክፍያ ይፈጽማል? ክፍያ የሚፈጸመው በውጭ ምንዛሪ ከሆነ በአገሪቱ ላይ የምንዛሪ እጥረት አይፈጠርም ወይ? በሚሉት ጉዳዮች ኮሚቴው የጠራ አቋም አለመያዙን አስረድተዋል፡፡

የውጭ ኮንትራክተሮችን ወደ አገር ውስጥ አስገብቶ በመኖርያ ቤቶች ግንባታ ለማሰማራት የአገሪቱ ሕጎች የማይፈቅዱ መሆናቸው ተዘርዝሯል፡፡ ሚኒስቴሩ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የኮንስትራክሽን ግዢ የሚፈጽምበት ረቂቅ ሕግ ማዘጋጀቱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ዶ/ር ዮሴፍ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ከእነዚህ አማራጮች በተጨማሪ ኢንስቲትዩቱ ሌሎች የመኖርያ ቤቶች ግንባታ አማራጮችን ለማየት እየሞከረ ነው፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በቀረበለት ፕሮፖዛል ላይ ውሳኔ ከሰጠ፣ በዚህ ዓመት 14 የውጭ ኩባንያዎች 100 ሺሕ የሚጠጉ መኖርያ ቤቶች በአዲስ አበባ ከተማ እንዲገነቡ ይደረጋሉ ተብሏል፡፡ ኩባንያዎቹም የቤቶቹን ግንባታ በ18 ወራት እንደሚፈጽሙ ታምኗል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2007 ዓ.ም. ተጀምረው ያልተጠናቀቁ 50 ሺሕ ቤቶችን ጨምሮ፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 250 ሺሕ ቤቶችን የመገንባት ዕቅድ አውጥቷል፡፡

እስካሁን በአገር ውስጥ ኩባንያዎች አቅም እየተካሄደ ያለው የቤቶች ግንባታ በሚፈለገው ፍጥነት እየተካሄደና ለተጠቃሚው እየተላለፈ ባለመሆኑ ነዋሪዎች ቅሬታ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ መንግሥት የመኖርያ ቤቶች ግንባታ በአስቸኳይ ተካሂዶ ለኅብረተሰቡ መተላለፍ አለበት የሚል አቋም በመያዝ ለውጭ ኩባንያዎች በሩን ክፍት ማድረጉ በአዎንታዊ ጎኑ እየታየ ነው፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌም በቅርብ እንደተናገሩት፣ በተያዘው በጀት ዓመት የውጭ ኩባንያዎች በቤቶች ግንባታ እንዲሰማሩ ይደረጋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች