Wednesday, September 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ጠንካራ ተቋማትና አመራሮች በሌሉበት መንግሥት እንዴት ውጤታማ ይሆናል?

  መንግሥት ውጤታማ ሆኖ የሕዝብ እርካታ መፍጠር የሚችለው ጠንካራ ተቋማትና ብቁ አመራሮች ሲኖሩት ነው፡፡ የሕዝብ እርካታ የሚለካባቸው በርካታ አገልግሎት መስጫ ተቋማትና አመራሮቻቸው፣ ምን ያህል ዝግጁ ናቸው ተብሎ በጥናት ላይ የተመሠረተ ፍተሻ መደረግ አለበት፡፡ በተለይ አሁን አዲሱ ካቢኔ ተመሥርቶ በየደረጃው አመራሮች በተሰየሙበትና የተወሰኑ የመንግሥት መዋቅሮችም እንደ አዲስ ሲደራጁ፣ የተቋማት ጥንካሬና የአመራሮች ብቃት በሚገባ መገምገም አለበት፡፡ በተነፃፃሪ ሕዝብ በየትኞቹ ተቋማት የተቀላጠፈ አገልግሎት እያገኘ ነው? የትኞቹስ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እያስተጓጎሉ ነው? ተብሎ መፈተሽ አለበት፡፡ በርካታ የተዝረከረኩ ነገሮች አሉ፡፡

  የተቋማትንና የአመራሮቻቸውን ጥንካሬና ብቃት ጥያቄ ውስጥ ከሚከቱ ችግሮች መካከል አንዱ፣ የቢሮክራሲው መንቀራፈፍና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅም ማነስ ነው፡፡ ቢሮክራሲው አዝጋሚ ከመሆኑ የተነሳ የብዙዎቹ ተቋማት ውጤታማነት የወረደ ነው፡፡ መንግሥት ውጤታማ ነኝ ብሎ መኩራራት የሚችለው ሕዝብ በሲቪል ሰርቪሱ የአገልጋይነት መንፈስና ጥራት ላይ እርካታ ሲኖረው፣ ሲቪል ሰርቪሱ ከማናቸውም የፖለቲካ ተፅዕኖዎች ነፃ ሆኖ ሲሠራ፣ መንግሥት ፖሊሲዎችን ሲቀርፅና ተግባራዊ ሲያደርግ ጥራትን መነሻ ሲያደርግና ፖሊሲዎችን የማስፈጸም ተነሳሽነቱ በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ሲያገኝ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ አካሄድ የተቋማት ቢሮክራሲ አፈጻጸም ሲፈጥን፣ አመራሮችም ንቁ ይሆናሉ፡፡ በብዙዎቹ ተቋማት ግን ይህ እርካታ ፈጣሪ መሠረታዊ ጉዳይ ተግባራዊ ባለመሆኑ፣ ሕዝብ በመልካም አስተዳደር እጦት አበሳ ያያል፡፡

  የመንግሥት ውጤታማነት ከሚገለጽባቸው መሠረታዊ ከሚባሉ አገልግሎቶች መካከል የትምርት ሥርዓቱና ጥራቱ፣ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ተደራሽነትና ጥራት፣ የንፁህ ውኃ መጠጥ አቅርቦትና ጥራት፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ጥራት፣ የሕዝብና የጭነት ትራንስፖርት አቅርቦትና የአገልግሎት ጥራት፣ የበጋና የክረምት መንገዶች ብዛትና ጥራት፣ የደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ አገልግሎት ጥራት፣ የበጀትና የፋይናንስ አስተዳደር የጥራት ደረጃ፣ የገቢ አሰባሰብ ብቃት፣ ውጤታማ የሆነ የሕዝብ አስተዳደር፣ ወዘተ. ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከላይ በተጠቀሱት የተለያዩ መስኮች ውስጥ የሕዝብ እርካታ ምን ይመስላል? እንዴትስ ይለካል? ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡

  በተቋማት ደረጃ ሕዝብ በጣም የሚማረርባቸው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፣ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የስልክ፣ የመገናኛና ትራንስፖርት፣ የመሬት አስተዳደር፣ የግንባታ ፈቃድ፣ የንግድ ፈቃድ ምዝገባና ዕድሳት፣ ገቢዎችና ጉምሩክ፣ ወረዳና ክፍለ ከተማዎች፣ ወዘተ. ተቋማዊ ጥንካሬያቸውና የአመራሮቻቸው ብቃት ምን ይመስላል? ከዘመኑ ቴክኖሎጂና ዕውቀት ጋር የሚመጣጠን ቅልጥፍና ለምን የላቸውም? ተቋማቱን በማዘመንና የአመራሮቻቸውን አቅም በመገንባት ወይም የተሻሉ አመራሮችን በመሾም ውጤታማ ለማድረግ ለምን ጥረት አይደረግም? እስከ መቼ በአፈጻጸም ድክመት እየተሳበበ ሕዝብ እንዲጎሳቆል ይደረጋል? መንግሥትስ እስከ መቼ በእነዚህ ደካማ ተቋማትና አመራሮች ምክንያት ይወቀሳል? ከፍተኛ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡

  የመንግሥት ተቋማትና አመራሮች ድክመት ጉዳይ ችላ በተባለ ቁጥር አደጋው ለራሱ ለመንግሥት ነው፡፡ ሕዝቡ በየደረሰበት አስተዳደራዊ በደሎች ሲፈጸሙበትና የአገልግሎቶች መስተጓጎል ሲደርስበት፣ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት ይጠፋል፡፡ ይህ ደግሞ ለአመፅ፣ ለብጥብጥና ለሁከት በር ይከፍታል፡፡ ችግር ሲፈጠር ሕግ ለማስከበር አዳጋች ይሆናል፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ይከሰትና ለሞትና ለንብረት ውድመት በር ይከፍታል፡፡ ዜጎች መሠረታዊ የሆኑ የፍጆታ ዕቃዎችን ማለትም ምግብ፣ ውኃ፣ ኤሌክትሪክና የመሳሰሉትን በአግባቡ ማግኘት ሳይችሉ ሲቀሩ ከባድ ነው፡፡ የመጠለያና የመሠረተ ልማት አገልግሎቶችን አለማግኘትም እንዲሁ፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ሲፈጠሩ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል አመራሮች ፈጣን ምላሽ ሲጠፋ ደግሞ ችግሩ የከፋ ይሆናል፡፡ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡

  የብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማትና አመራሮች ዘገምተኝነት ድንገተኛ የሆኑ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ ይታያል፡፡ ወትሮም እንደነገሩ የሆኑት እነዚህ ተቋማት ለድንገተኛ አደጋዎች ያላቸው ዝግጁነት በጣም ደካማ በመሆኑ ማንም አይተማመንባቸውም፡፡ ሌላው ቀርቶ በስግብግብ ነጋዴዎች ምክንያት ሕዝብ ላይ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት ሲፈጠር ፈጣን ምላሽ ሲሰጥ አይታይም፡፡ ገበያውን ሥርዓት አልበኞች እንደፈለጉ ሲፈነጩበትና ሕዝቡን ግራ ሲያጋቡት የሚመለከታቸው ተቋማት የሚባንኑት በርካታ ሕገወጥ ተግባራት ከተከናወኑ በኋላ ነው፡፡ በእነዚህና በሌሎች ችግሮች ሳቢያ ሕዝብ እንኳን ሊረካ እንባውን እያዘራ ነው፡፡ ይህም ልዩ ትኩረት ይሻል፡፡

  በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የሚታዩ አሳዛኝ ተግባራት ለብዙዎቹ ሰቆቃ እየሆኑ ነው፡፡ አንድ ወንጀል ሲፈጸም ፖሊስ እንዴት ነው የሚመረምረው? ዓቃቤ ሕግስ እንዴት ነው ክስ የሚያደራጀው? ከሳሽና ተከሳሽ በፖሊስና በዓቃቤ ሕግ ዘንድ እንዴት ነው የሚስተናገዱት? ገንዘብ ፍትሕን የሚጠመዝዝበት ዘመን ላይ ሆነን እነዚህን ጥያቄዎች ስናነሳ፣ ሕዝቡ ውስጥ የሚነገረው ነገር ለጆሮ ይዘገንናል፡፡ መንግሥት በአመዛኙ አሸናፊ በሚሆንበት የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ፣ ዜጎች በግል በሚያጋጥሟቸው ጉዳዮች ወደ ፍትሕ አካላት ሲሄዱ ከሳሽ ከመሆን ይልቅ ተከሳሽ መሆን ይሻላል እያሉ ነው፡፡ ገንዘብ ያለው ገንዘብ የሌለውን በግፍ የሚረታበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ሰሞኑን እንደሰማነው ፍትሕ የብሔር ግንኙነትና የወሲብ ሰለባ ሆኗል፡፡ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና ዳኛ ሥራቸውን በነፃነት እያከናወኑ ሕዝቡን መታደግ ካቃታቸው ማዘን ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በጣም አስፈሪ ነው፡፡

  በብዙዎቹ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ መረን የተለቀቀው ሙስና ጉዳይ ብዙ ተብሎበታል፡፡ ነገር ግን ሙስና ገንፍሎ በተዝረከረከበት በዚህ ወቅት ተቋማቱና አመራሮቹ ካልታደሱ በስተቀር ለአገር መከራ ነው፡፡ ከትንሹ የጉቦ መደራደሪያ እስከ ትልቁ ግዥና ጨረታ ድረስ በየቦታው የሚታየው ዓይን ያወጣ ዝርፊያ፣ የመንግሥትን ውጤታማነት ችግር ውስጥ እየከተተው ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ የሚቀረፅባቸው የትምህርት ተቋማት ሳይቀሩ የሙስና መናኸሪያዎች ሆነዋል፡፡ የጤና ተቋማት ሌቦች በርክተውባቸዋል፡፡ ሕዝብ አገልግሎት ፍለጋ የሚሄድባቸው ብዙዎቹ ተቋማት ‘ጉዳይ ገዳይ’ በሚባሉ የሙስና አቀባባዮች ተወረዋል፡፡ ለስሙ በየተቋማቱ የተገተሩት የሥነ ምግባርና የአገልጋይነት መርሆዎች የተጻፉባቸው ሰሌዳዎች ስንቱን ነገር እየታዘቡ ይሆን? በንፅህና ሕዝባቸውን እያገለገሉ የሚገኙ ሠራተኞች እንዴት እየተሸማቀቁ ይሆን? ሙሰኞች ከንፁኃን በላይ እየተንጎራደዱ አገር ሲያጠፉ እንዴት ውጤታማ መሆን ይቻላል? ሁኔታው አስፈሪ ነው፡፡

  መንግሥት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አገር ለማስተዳደር ቆርጬ ተነስቻለሁ ሲል፣ የተቋማቱንና የአመራሩን ጉዳይ ሊያስብበት ይገባል፡፡ የሙስናው ደን ጥቅጥቅ ከመሆኑ የተነሳ ብዙዎች መሽገውበታል፡፡ አቅም የሌላቸውና ደንታ ቢሶች ደግሞ በየቦታው ተሰግስገዋል፡፡ በስመ የድርጅት አባልነት ዕውቀትም ሆነ የረባ ልምድ ሳይኖራቸው ተቋማትን እየመሩ ያሉ ሰዎች ብቃት ባላቸው ካልተተኩ መዘዙ የከፋ ነው፡፡ በየተቋማቱ ውስጥ ያለው የተዝረከረከ አሠራር መፍትሔ ይፈለግለት፡፡ ስለውጤታማነት መነጋገር የሚቻለው ሕዝብ እርካታ አግኝቶ መንግሥትን ማመስገን ሲጀምር ብቻ ነው፡፡ እርካታ በሌለበት ስለውጤታማነት መነጋገር ካለመቻሉም በላይ፣ የአገሪቱም ሆነ የመንግሥት ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ጠንካራ ተቋማትና ብቃት ያላቸው አመራሮችን በመያዝ ውጤታማ ለመሆን መነሳት ያስፈልጋል! እነዚህ በሌሉበት ግን እንዴት ውጤታማ መሆን ይቻላል?   

        

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

  ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

  የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በተመድ ጉባዔ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች

  በስዊዘርላንድ ጄኔቭ እየተካሄደ በሚገኘው 51ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ‹‹ለሰላምና ለዕርቅ መሸነፍ የለብንም›› ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ

  የሰው ልጅ ጠብን በዕርቅ፣ በደልን በይቅርታ፣ ድህነትን በልማት፣ ክህደትን...

  መፍትሔ አልባ ጉዞ የትም አያደርስም!

  ኢትዮጵያ ችግሮቿን የሚቀርፉ አገር በቀል መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡...

  ጦርነቱና ውስጣዊ ችግሮች

  መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው...

  መኖሪያ ሸጦ መዞሪያ!

  እነሆ ከመካኒሳ ወደ ጀሞ ልንጓዝ ነው። ቀና ሲሉት እየጎበጠ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መፍትሔ አልባ ጉዞ የትም አያደርስም!

  ኢትዮጵያ ችግሮቿን የሚቀርፉ አገር በቀል መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡ ከዚህ ኢፍትሐዊ ዓለም መፍትሔ ይገኛል ብሎ መጠበቅ የማይቻልበት ጊዜ ላይ እየተደረሰ ነው፡፡ የዓለምን ሚዛን ያስጠብቃሉ...

  ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

  በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ...

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...