የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማስተካከያ ለማካሄድ የሚያስችለው የኢነርጂ ሥራዎች ረቂቅ ደንብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡
የግል ባለሀብቶች በኢነርጂ ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ቢፈልጉ የተከለከለ ባይሆንም፣ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ግን ዝቅተኛ በመሆኑ በዘርፉ ለመሰማራት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ዘገምተኛ ሆኖ መቆየቱ ይነገራል፡፡
በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የግል ባለሀብቶች በኤሌክትሪክ ማመንጨት ዘርፍ እንዲሰማሩ፣ መንግሥት የተለያዩ ማበረታቻዎችን እንደሚሰጥ ተጠቅሷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ፣ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ከሆነ ለጋሾች ጋር በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡
በኢትዮጵያ በኢነርጂ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ ኢንቨስተሮች ያሏቸው አገሮች ተወካዮች፣ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚገባና ማሻሻያው ከተደረገ በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጐት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሰጡት ምላሽ በውኃ፣ በጂኦተርማል፣ በፀሐይ፣ በንፋስና በመሳሰሉት ኃይል ማመንጫዎች ግንባታ ማካሄድ ለሚፈልጉ ኢንቨስተሮች የመንግሥት በር ክፍት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዘርፉ የሚሰማሩትንም ባለሀብቶች መንግሥት እንደሚያበረታታ ተናግረዋል፡፡
በዋናነት የኢንቨስተሮች ትኩረት ግን የታሪፍ ማሻሻያው ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ሞገስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢነርጂ ሥራዎች ረቂቅ ደንብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
ይህ ደንብ ስለኤሌክትሪክ ማመንጨት፣ ማስተላለፍ፣ ማከፋፈል፣ መሸጥ፣ ማስመጣት ወይም መላክ በጥልቀት ይተነትናል፡፡ በእርግጥ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ቁጥሮች ከዚህ ደንብ በኋላ በሚወጣው መመርያ የሚገለጹ ቢሆንም፣ አቶ ጌታሁን እንዳሉት ግን በመመርያው የሚወጣው ታሪፍ የኢንቨስትመንት ወጪን መሸፈን በሚያስችል ደረጃ የተቃኘ ነው፡፡
ኢነርጂ ለማመንጨት የሚሰጥ ቀነ ገደብ በረቂቅ ደንቡ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ ከውኃና ጂኦተርማል የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የተሰጠው የባለቤትነት ጊዜ 25 ዓመት ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ውጭ ለመላክም ሆነ ለማስመጣት የተሰጠው ፈቃድ ጊዜ ለአሥር ዓመት ነው፡፡
በእነዚህ ሕግጋት ወደ ኢንቨስትመንት የሚገቡ ባለሀብቶች የሚያመነጩትን የኤሌክትሪክ ኃይል በመመርያ በሚገለጸው ታሪፍ፣ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ይሸጣሉ፡፡ አቶ ጌታሁን እንዳሉት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ ደንቡን ያፀድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡