Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለተሿሚዎች መኖርያ ቤት ማቅረብ የተሳነው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ነባር ተከራዮች ሥጋት ገብቷቸዋል

ለተሿሚዎች መኖርያ ቤት ማቅረብ የተሳነው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ነባር ተከራዮች ሥጋት ገብቷቸዋል

ቀን:

ለከፍተኛ ባለሥልጣናት መኖርያ ቤት ማቅረብ የተሳነው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ፣ ባለፈው እሑድ ጥቅምት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በሲኤምሲ አፓርታማዎች ላይ ድንገተኛ ቅኝት አካሄደ፡፡ ኤጀንሲው ባካሄደው ቅኝት ምክንያት የአፓርታማው ነዋሪዎች የመፈናቀል ሥጋት እንዳደረባቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከ30 በላይ የሚሆኑ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ሠራተኞች በአፓርታማው ቅጥር ግቢ ተገኝተው፣ ተከራዮችን የተለያዩ ጥያቄዎችን በመጠየቅ መረጃዎችን ሲሰበስቡ ውለዋል፡፡

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የአፓርታማው ተከራይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኤጀንሲው ሠራተኞች ጥያቄ የሚያነጣጥረው ስህተት ፍለጋ ላይ ነው፡፡ ‹‹ይህ ደግሞ ያለበቂ ምክንያት እኛ የአፓርታማው ነዋሪዎችን በማፈናቀል ቤቶቻችን ለመንግሥት አዳዲስ ተሿሚዎች ለመስጠት ያለመ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ይህ ዓይነቱ አሠራር በፍጹም ተቀባይነት የለውም!›› በማለት እኚህ ተከራይ የኤጀንሲው የበላይ የሆነው መንግሥት ጉዳዩን በድጋሚ እንዲያጤነው ጠይቀዋል፡፡ በደርግ ዘመን ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ተብሎ 507 የአፓርትመንት ቤቶች መገንባታቸው ይታወሳል፡፡ ግንባታው እንዲካሄድ ያደረገው ደርግ በመውደቁ፣ ቀደም ሲል የነበረው ዓላማ ተሰርዞ ቤቶቹ አቅም ላላቸው ተከራዮች እንዲከራዩ ተወስኗል፡፡

በዚህ መሠረት አቅም ያላቸው ግለሰቦች ቤቶቹን ተከራይተው ኑሮአቸውን በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ላለፉት 24 ዓመታት ከቤት ግንባታ ውጪ የተደረገው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ፣ ለመንግሥት ሹማምንት የሚያቀርባቸው የመኖርያ ቤቶች እጥረት እየገጠመው በመሆኑ፣ ካሉት የሲኤምሲ አፓርትመንቶች መካከል 40 ያህሉን በተለያዩ ጊዜያት አስለቅቆ ለሚኒስትር ዴኤታዎች አከፋፍሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ 50 ያህል ቤቶች ደግሞ ለተለያዩ ሥራዎች አዲስ አበባ ከተማ የሚመጡ የሚድሮክ እንግዶች የሚያርፉባቸው ናቸው፡፡ የቤቶቹ ተከራይም ሚድሮክ ኢትዮጵያ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የተቀሩት ቤቶች በተለያዩ ግለሰቦች የተያዙ ሲሆን፣ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በግለሰቦች የተያዙ አፓርትመንቶች ላይ ትኩረት ማድረጉን የኤጀንሲው ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ኤጀንሲው ከአፓርትመንቶች በተጨማሪ በመኖሪያ ቪላዎች ላይም ዘመቻ መጀመሩ ይነገራል፡፡ በተለይ በሚኒስትር ደረጃ ለሚገኙ ባለሥልጣናት የሚቀርበው መኖርያ ቤት ደረጃውን የጠበቀ መሆን ስላለበት ቪላና ከዚያ በላይ የሆኑ ቤቶችን ለማስለቀቅ ኤጀንሲው የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

ለዓመታት ከኖሩበት እንዲፈናቀሉ እየተደረጉ ያሉ ነዋሪዎች ከኤጀንሲው ጋር ከፍተኛ ግጭት ውስጥ እየገቡ ሲሆን፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተከራዮች እንዲለቁ የሚደረግበት ምክንያት ትርጉም የሌለው መሆኑ እንደሚያበሳጫቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ነባር ደንበኞችን አፈናቅሎ ለባለሥልጣን ቤት መስጠት ምን ዓይነት አሠራር ነው?›› በማለት የሚጠይቁት እነዚህ ነዋሪዎች፣ ይህ አሠራር ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም ይላሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ካቢኔያቸውን መመሥረታቸው ይታወሳል፡፡ በአዲሱ ካቢኔ አዳዲስ ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች የተሾሙ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላም በርካታ ሹመቶች ይጠበቃሉ፡፡

ቀደም ሲል የነበረውን የባለሥልጣናት የቤት ጥያቄን ሳይጨምር 630 አዳዲስ የመኖርያ ቤቶች ጥያቄ ለኤጀንሲው መቅረቡ ታውቋል፡፡ እነዚህ ቤቶች በቀጥታ የሚቀርቡት ለመንግሥት ተሿሚዎች ብቻ ነው፡፡

ኤጀንሲውም እነዚህን የመኖርያ ቤቶች ጥያቄዎች ለመመለስ ያቀደው ነባር ደንበኞቹን በማፈናቀል መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ግንባታ ሳያካሂድ 24 ዓመታት የተቆጠሩ ከመሆኑም በላይ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ያሉት መኖርያ ቤቶች በልማት ምክንያት እየፈረሱ ይገኛሉ፡፡

በቅርቡ በግዮን ሆቴል በተደረገ ስብሰባ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይለ ማርያም ዓለም ሰገድ፣ ‹‹የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ከዚህ በኋላ መኖርያ ቤት የሚያቀርበው ለመንግሥት ተሿሚዎች ብቻ ነው፤›› በማለት በግልጽ በስብሰባው ለታደሙ ባለድርሻ አካላት ተናግረዋል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር አስተያየት እንዲሰጡ ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...