– ለ13 ዓመታት የዘለቀው የኬንያ የበላይነት ያበቃበት
ፍራንክፈርት ማራቶን በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የላቀና የወርቅ ደረጃ ያለው ውድድር ነው፡፡ ከ35 ዓመታት በፊት በፊት በተጀመረው ዓመታዊ ውድድር ኢትዮጵያ ድል ማድረግ የጀመረችው ከአራት ዓመት ቆይታ በኋላ ነበር፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሆኖ ድሉን ግንቦት 11 ቀን 1976 ዓ.ም. የተቀዳጀው ደረጀ ነዲ ባሸናፊነት የገባበት ጊዜም 2 ሰዓት 11 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ ነበር፡፡ ይህም በወቅቱ የቦታው ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ከታዋቂው ደረጀ ድል በኋላ ኢትዮጵያና ፍራንክፈርት ማራቶን (በወንዶች) በድል ሳይተዋወቁ ከሦስት አሠርታት በላይ ተቆጥሯል፡፡
ዘንድሮ ይህን ታሪክ የለወጠ ክስተት ባለፈው እሑድ ጥቅምት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ተከስቷል፡፡ ለ34ኛ ጊዜ በተካሄደው ውድድር ሲሳይ ለማ የኢትዮጵያን የፍራንክፈርት ማራቶን የድል ጥማት ተወጥቷል፡፡ የአሸናፊነትን አክሊል ጨብጧል፡፡
በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማኅበር ድረ ገጽ እንደተዘገበው፣ የመጨረሻውን ኪሎ ሜትር በሁለት ኬንያውያን ታጅቦ የሮጠው ብልሁ ሲሳይ ለማ ኬንያውያኑን ተቀናቃኞች ላንቲ ሩቶ እና አልፈርስ ላጋትን ያሸነፈው፣ በ2 ሰዓት 06 ደቂቃ 26 ሰከንድ ነው፡፡ የራሱንም ምርጥ ጊዜ በ40 ሰከንድ አሻሽሏል፡፡ ሩቶ እና ላጋት ሁለተኛና ሦስተኛ የሆኑትም የየራሳቸውን ምርጥ ጊዜ 2 ሰዓት 06 ደቂቃ 36 ሰከንድ እና 2 ሰዓት 06 ደቂቃ 48 ሰከንድ በማስመዝገብ ነው፡፡
ለጋዜጠኞች በአሸናፊነቱ መደሰቱን የገለጸው የ24 ዓመቱ ሲሳይ ውድድሩን በ2 ሰዓት 05 ደቂቃ ለማጠናቀቅ አስቦ እንደነበር ሳያወሳ አላለፈም፡፡
ኢትዮጵያውያቱ የነገሡበት ውድድር
በፍራንክፈርት ማራቶን ለኢትዮጵያ የተመዘገበው አዲስ ታሪክ በሁለቱ ጾታዎች ለመጀመርያ ጊዜ ድርብ ድልን ማግኘቷ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ጉሉሜ ቶሎሳ በ2004፣ 2005፣ እና 2007 ዓ.ም. በማሚቱ ደስቃ፣ መሰለች መልካሙና አበሩ ከበደ በተከታታይ የተገኙትን ወርቃዊ ድሎች አስቀጥላለች፡፡
የውድድሩን 30ኛ ኪሜ በ1 ሰዓት 41 ደቂቃ 36 ሰከንድ ተነጥለው ያለፉት ሦስቱ ኢትዮጵያውያት ጉሉሜ ቶሎሳ፣ ድንቅነሽ መካሻና ኮሬን ጀሌላ ፉክክሩን ያካሄዱት እርስ በርስ ነበር፡፡ ፍጻሜው መስመር ላይ ተያይዘው የገቡት ጉሉሜና ድንቅነሽ በእኩል ሰዓት 2 ሰዓት 23 ደቂቃ 12 ሰከንድ ቢገቡም ባገባብ ጉሉሜ አሸንፋለች፡፡ በአራተኛነትና በስድስተኛነት ሩሲያዊቷ ሳርዳና ትሮፌሞቫእና ጀርመናዊቷ ሊዛ ሃህነር ጣልቃ ገቡ እንጂ አምስተኛና ሰባተኛ ሆነው የፈጸሙት ሌሎቹ ኢትዮጵያውያት መሠረት ቶልዋክ እና መሠረት መንግሥቱ ናቸው፡፡
ከመጀመሪያዎቹ አስሩ ፈጻሚዎች ግማሾቹ ኢትዮጵያውያት በሆኑበትና በነገሡበት ውድድር ያሸነፈችው ጉሉሜ፣ ‹‹በጥሩ አቋም ላይ ስለምገኝ ከመጀመሪያዎቹ ሦስቱ አንዷ እንደምሆን አስብ ነበር እንጂ አሸንፋለሁ ብዬ አልገመትኩም፤›› ስትል ለጋዜጠኞች ተናግራለች፡፡
ባለወርቅ ደረጃው የፍራንክፈርት ማራቶን የዘንድሮ 34ኛ ውድድር 14,565 ሯጮችን የሳበ ሲሆን በመነሻው ላይ በተለያዩ ምድቦች በጠቅላላው 25,547 ተሳታፊዎች ተገኝተውበታል፡፡ እስካሁን በተደረጉት ውድድሮች ኬንያ በሴቶች አምስት ጊዜ፣ በወንዶች 15 ጊዜ አሸንፋለች፡፡ በተለይ ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ ለ13 ዓመታት ያለማቋረጥ ኬንያውያን በርስትነት የያዙትን ድል ዘንድሮ ሲሳይ ለማ የኔ ሲሳይ ነው ብሎ ድሉን ለኢትዮጵያ አምጥቶላታል፡፡
የፍራንክፈርት ማራቶን ክብረ ወሰንን በሴቶች የያዘችው ኢትዮጵያዊቷ መሰለች መልካሙ ስትሆን፣ በ2005 ዓ.ም. ስታሸንፍ ያስመዘገበችው 2 ሰዓት 21 ደቂቃ 01 ሰከንድ ነበር፡፡ በወንዶች ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕሳንግ 2 ሰዓት 03 ደቂቃ 42 ሰከንድ አስመዝግቧል፡፡
ፋና ወጊው ደረጀ ነዲ
የፍራንክፈርት ማራቶን በ35 ዓመት ታሪኩ ውድድር ያላካሄደው ለአንድ ዓመት ብቻ ነበር፡፡ ከ1973 ዓ.ም. እስከ 1977 ዓ.ም. ድረስ የተካሄዱትን አምስት ውድድሮች ያከናወነው በግንቦት ወር ውስጥ ነበር፡፡ ውድድሩ እ.ኤ.አ. በ1986 (በ1978/9 ዓ.ም.) ሳይካሄድ ተዘልሎ በ1980 ዓ.ም. ዳግም የቀጠለው በየዓመቱ በጥቅምት ወር እንዲከናወን በመወሰን ነው፡፡
በ1976 ዓ.ም. በተካሄደው አራተኛው የፍራንክፈርት ማራቶን ኢትዮጵያ ባለድል እንድትሆን ያደረጋት እውቁ ደረጀ ነዲ፣ በ1972 ዓ.ም. የሞስኮ ኦሊምፒክ በማራቶን 7ኛ ሆኖ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ ቀደም ብሎም በአልጀርስ በ1970 ዓ.ም በተካሄደው ሦስተኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በማራቶን የብር ሜዳሊያ፣ በ1973 ዓ.ም የቶኪዮ ማራቶን 3ኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ በ1976 ዓ.ም. በተካሄደው የሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ የሶቪየት ኅብረት አጋር ሆና አልካፈልም በማለቷ በነበረው ከፍተኛ ብቃት ለወርቅ ይጠበቅ የነበረው ደረጀ ነዲ ሕልሙ እውን ሳይሆንለት ቀርቷል፡፡
የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረትና ሌሎች ስምንት አገሮች ከሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክ ራሳቸውን ማግላለቸው ተከትሎ ሶቪየቶች ለኦሊምፒኩ ምትክ እንዲሆን ‹‹ስፖርት ወዳጅነትና ሰላም›› በሚል መሪ ቃል ‹‹የሞስኮ የወዳጅነት ጨዋታዎች›› ሲያዘጋጁ፣ በሞስኮው ‹‹አማራጭ ኦሊምፒክ›› 50 አገሮች ተካፍለውበታል፡፡ የሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክ ተሳታፊ አንዳንድ አገሮች በተገኙበት መድረክ በአትሌቲክስ በማራቶን ደረጀ ነዲ ወርቅ ሜዳይ ያገኘው የራሱን ምርጥ ጊዜ 2 ሰዓት 10 ደቂቃ 32 ሰከንድ በማስመዝገብ ነበር፡፡