Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹በጥቅምት አንድ አጥንት››

‹‹በጥቅምት አንድ አጥንት››

ቀን:

በመላው ዓለም የተለያዩ ፌስቲቫሎች ሲከበሩ ይታያል፡፡ በስፔን የሚካሄዱት ከኮርማ ጋር የሚደረግ ፍልሚያና የቲማቲም ውርወራ ድብድብ በርካታ ተመልካቾችን ያፈሩ ፌስቲቫሎች ናቸው፡፡ መሰል ፌስቲቫሎችም በተለያዩ አገሮች ሲካሄዱም ይስተዋላል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በኢትዮጵያም የተለያዩ ፌስቲቫሎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ቴስት ኦፍ አዲስና ኦክቶበር ፌስት በኢትዮጵያ በቅርቡ ከተጀመሩ ፌስቲቫሎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የተከበረው ‹‹በጥቅምት አንድ አጥንት›› የተሰኘው የጥሬ ሥጋ ፌሲቲቫልም አዲስ ብቅ ካሉት መካከል ነው፡፡ ቅዳሜ ጥቅምት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በኤግዚቢሽን ማዕከል የተከፈተው ፌስቲቫሉ፣ ከመግቢያው ጀምሮ ደመቅመቅ ብሎ ነበር፡፡ የጥሬ ሥጋ ፍቅር ያላቸው፣ በመሰል ዝግጅቶች መሳተፍ የሚያስደስታቸው፣ የውጭ አገር ዜጎችና ሌሎችም የፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች ዝግጅቱን አድምቀውት አምሽተዋል፡፡

አብዛኛዎቹም ጥሬ ሥጋ ይመገቡ ነበር፡፡ መደዳውን የተደረደሩት ልኳንዳ ቤቶችም በዛ ያለ ሥጋ ይዘዋል፡፡

እያንዳንዳቸውም እስከ 30 የሚሆኑ አስተናጋጆች አስከትለዋል፡፡ ሁሉም ትዕዛዛቸውን ለማድረስ ከወዲያ ከወዲህ ይሯሯጣሉ፡፡ ሥጋ ቤቶቹም ስያሜያቸውን ከላይ ለጥፈዋል፡፡ ከርቀት የሚታየው ‹‹ኃይሉ ጮማ›› የተሰኘው ልኳንዳ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም ሲሳተፉ ሁለተኛ ጊዜአቸው እንደሆነ ሥጋ ቤቱን ወክለው የተገኙት አቶ ወንድሙ ወልደመስቀል ናቸው፡፡

‹‹ሰው ተሰብስቦ ሲበላና ሲጠጣ ማየት ደስ ያሰኛል›› የሚሉት አቶ ወንድሙ፣ አጋጣሚው ገበያቸው እንዲደራ በማድረጉም በየዓመቱ የመሳተፍ ፍላጎት አድሮባቸዋል፡፡ ‹‹በፌስቲቫሉ ብዙ ደንበኞች እናገኛለን፡፡ በቀን እስከ ሁለት ከብት እንጨርሳለን፡፡ ይህም በሌላው ጊዜ ከምንሸጠው ከእጥፍ በላይ ነው፤›› በማለት አጋጣሚው የፈጠረላቸውን ሰፊ ገበያ ገልጸዋል፡፡ ዋጋውን በተመለከተም በኪሎ እስከ 250 ብር የሚሸጡ ሲሆን፣ ከሴንቸሪ ፕሮሞሽን ጋር በጋራ ፌስቲቫሉን ያዘጋጀው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ለተጠቃሚው 100 ብር ስፖንሰር በማድረጉ በ150 ብር ሸጠዋል፡፡ የቦታ ኪራይ ስለማይከፍሉም በአጋጣሚው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከቁርጥ ባሻገር ጥብስ፣ በርገር፣ ፒዛና ሎሎችም የምግብ ዓይነቶች ተዘጋጅተዋል፡፡ ለሕፃናትም አይስክሬምና የተለያዩ መዝናኛዎችም ነበሩ፡፡

በሱዳን፣ ሊቢያና ግብፅ እንደኖሩ የሚናገሩት የ44 ዓመቱ አቶ አማረ ተክለሃይማኖት፣ በጀርመን ሃውስ ባርና ሬስቶራንት ሼፍ ናቸው፡፡ በተለይም ከዶሮ ሥጋና ከፉርኖ ዱቄት ቂጣ የሚሠራውን ሻዎሮማ የተባለ ምግብ ያበስላሉ፡፡ በቆይታቸው ሁሉ ይሠሩ የነበረው ሻዎሮማን ነበር፡፡ ‹‹በጥቂት ጊዜ ገንዘብ ለማካበት ዓይነተኛ መንገድ ነው፡፡ በዚህም ላይ ጣፋጭ በመሆኑ ተመራጭ ነው፤›› ሲሉ አዋጭነቱን ይገልጻሉ፡፡

በአገር ውስጥ ብዙ አለመለመዱን የሚናገሩት አቶ አማረ፣ በፌስቲቫሉ የተሳተፉት ሻዎርማ እንዲለመድ ለማድረግ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እንደ ቁምሳጥን የቆመው የብረት መጥበሻ በእጅጉ ግሏል፡፡ በእንጨት መሳይ ነገር ተሰክቶና ተደራርቦ ብረቱ መካከል የተቆለለው የዶሮ ሥጋ በግለቱ ተጠብሷል፡፡ መዓዛው ያውዳል፡፡ በዙሪያው የተቀመጡ ተጠቃሚዎችም በላይ በላይ እያዘዙ ይመገቡ ነበር፡፡ በመጠበስ ላይ የነበረው የዶሮ ሥጋ ቢያንስ እስከ 30,000 ብር ድረስ እንደሚያወጣም ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ አንዱን ሻዎሮማ በ50 ብር በመደበኛ ሽያጭ ደግሞ እስከ 90 ብር ይሸጣል፡፡ ‹‹ዋጋውን የቀነስነው ኅብረተሰቡ እንዲለምደው ብለን ነው፡፡ ለኛ የተሰጠን ልዩ ማበረታቻ አልነበረም፤›› የሚሉት አቶ አማረ፣ ምግቡ ይበልጥ እንዲለመድላቸው ዋጋ መቀነሳቸውን ተናግረዋል፡፡

አንዳንዶች መሰል ፌስቲቫሎች ቢለመዱ አዳዲስ የምግብ ጣዕሞችን ለማጣጣም ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ ከምግቡ ጎን ለጎን ቢራም ቀርቦ ነበር፡፡ ብዙዎችም ቁርጥ አልያም ጥብስ ተመግበው ያወራርዱ የነበረው በቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ነበር፡፡

ለሁለት ቀናት በቆየው ፌስቲቫል የተሰኘው አባቶች ‹‹በጥቅምት አንድ አጥንት›› ይሉት የነበረውን ብሂል ለማስታወስ ታልሞ እንደሆነ የተናገሩት የሴንቸሪ ፕሮሞሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘውገ ጀማነ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ስምንት ሥጋ ቤቶችና ሌሎች  ሬስቶራንቶች በፌስቲቫሉ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡

የፌስቲቫሉ ተባባሪ አዘጋጅ የነበረው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በሒልተን ሆቴል ይዘጋጅ የነበረውን ኦክቶበር ፌስት ስፖንሰር ያደርግ ነበር፡፡ በዚያ ፕሮግራም ላይ ከነበረው የመግቢያ ገንዘብ አንፃር መካከለኛ ገቢ ያላቸው ግለሰቦች መገኘት ይከብዳቸው ነበር፡፡ በቢጂአይ ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ የሽያጭ ክፍል ኃላፊ አቶ ኢሳያስ አባተ እንደሚሉት፣ በጥቅምት አንድ አጥንት የሚለውን ፌስቲቫል ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ማክበር የተጀመረው አቅምን ባገናዘበ መልኩ ነው፡፡ በዘንድሮው ዝግጅትም 1.6 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...