‹‹አሜሪካ በአካባቢያችን ውጥረት የምታነግሥ ከሆነ የቻይና ምላሽ ከሚታሰበው በላይ ይሆናል››
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሉ ካንግ፣ አሜሪካ በቻይና ሰው ሠራሽ ደሴት አካባቢ የባህር ኃይል የጦር መርከቧን ማሰማራቷን በተመለከተ ከሰጡት ማስጠንቀቂያ የተወሰደ፡፡ አሜሪካ ማክሰኞ ዕለት በደቡባዊ ቻይና ባህር የጦር መርከቧን ማንቀሳቀሷ በቻይና ላይ ከፍተኛ ቁጣ ፈጥሯል፡፡ ከቻይና ደሴት 12 ኖቲካል ማይል ርቀት ላይ በታየው የአሜሪካ የጦር መርከብ ምክንያት፣ በሁለቱ አገሮች መካከል አደገኛ ፍጥጫ ይፈጠራል ተብሎ ተሠግቷል፡፡ ሚስተር ኩንግ አገራቸው የማንንም አገር ትንኮሳ እንደማትታገስ አስታውቀው፣ አሜሪካ በሰላማዊ መንገድ ችግሩን እንድታስወግድ ጠይቀዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አገራቸው በአካባቢው ያላትን ወታደራዊ ጥንካሬ ታሳያለች ብለዋል፡፡ ይህም ከሚገመተው በላይ እንደሆነ አስጠንቅቀዋል፡፡ አሜሪካ ግን በቻይና ባህር አካባቢ ነፃ የናቪጌሽን እንቅስቃሴ መኖር ስላለበት ይህም በተከታታይ ሳምንታት ይቀጥላል ብላለች፡፡ ፊሊፒንስም አሜሪካን መደገፏ ተሰምቷል፡፡ ቻይና ግን ፍጥጫው ጥሩ ባይሆንም ተጠንቀቁ እያለች ነው፡፡ በምሥሉ ላይ የሚታየው ዩኤስኤስ ላሰን የተባለው የአሜሪካ የጦር መርከብ በቻይና ባህር ሲቀዝፍ ነው፡፡