ለ81 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ ሠዓሊ ወርቁ ማሞ ምስጋና ለማቅረብ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ጥቅምት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት ላይ በወግና ባህል ቡና የቡና ግብዣ ተደርጐ ነበር፡፡ በሥነ ሥርዓቱ በባህላዊ መንገድ የተዘጋጀው ቡና ከ500 በሚበልጡ ሲኒዎች ተደርጐ ለታዳሚው ቀርቧል፡፡ ቡናውን የቀዱትም ሦስት ሴቶች ብቻ ናቸው፡፡
***********
ሞኝ እንደነገሩት
‹‹ፍቅር ያሸንፋል›› ስትለኝ አምኜህ
በጦርነት ሁሉ ልሰለፍ አብሬህ
ደብተሬን ቀድጄ
አድርቄ ወጥሬ ጋሻ ሠርቼበት
ብዕሬን ፈልፍዬ ጦር አስቀርጬበት
ጠላትን ወግቼ
ለፍቅር ደምቼ…
ካቀረቀርኩበት ቀና ብል የለህም
ያሸንፋል! ባልከኝ አንተ አልተሸነፍክም
እኔ ነኝ ብቻዬን ፍልሚያውን አውጄ
ጦሬን አበጅቼ
እኔው ተማርኬ ራሴን የሰጠሁ
ሙሉው ጦርነቴን
ሙሉ መሸነፌን
ሙሉ መሰጠቴን
ያንተ ድርሻ ቢኖር ልቤን የሰወረው
‹‹ፍቅር ያሸንፋል!›› ማለትህ ብቻ ነው፡፡
- ብሩክታይት ጎሳዬ፣ ጾመኛ ፍቅር 2007
********
የድመቶች ባህሪ ከቀለማቸው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው
‹‹የመጽሐፍን ይዘት በሽፋኑ መገመት አይገባም›› የሚል አባባል ቢኖርም ይህ ለድመቶች እንደማይሠራ ሳይንቲስቶች እየተናገሩ ነው፡፡ ሳይንቲስቶች የድመቶች የቁጠኝነት ባህሪ ከቀለማቸው ጋር እንደሚያያዝ መናገራቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡ ነብርማ ቀለም ያላቸውና በአሜሪካ ካሊኮ በመባል የሚታወቁት ድመቶች ቁጡ መሆናቸው ይነገራል፡፡ እንዲህ ዓይነት ቀለም ያላቸው ድመቶች በቀላሉ ሰው የማይቀርቡና ቁጡም መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ይሄ ቀደም ሲል ጀምሮ ይባል የበረ ነገር ሲሆን በቅርቡ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በድመቶች የፀጉር ቀለምና በባህሪያቸው ቀጥተኛ ግንኙነት መኖሩን ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡
ተመራማሪዎቹ ባካሄዱት ጥናት 1,274 ድመት አሳዳጊዎችን መጠየቅ ያስሞሉ ሲሆን፣ ድመቶቻቸው በቤት ውስጥ እንዲሁም ወደ እንስሳት ሐኪም ሲወሰዱ በምን ያህል ደረጃ ቁጡነት እንደሚታይባቸው እንዲገልጹ ተደርጓል፡፡ በጥናቱ መሠረት ዥንጉርጉር፣ ጥቁርና ነጭ እንዲሁም ግራጫና ነጭ ድመቶች ከሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ከሌሎች ድመቶች ይልቅ ቁጡዎች ናቸው፡፡
*************
ቸኮሌት በመሥረቋ 330 ፓውንድ ለተፈረደባት ሴት እየተደረገ ባለው የገቢ ማሰባሰቢያ የተገኘው ገንዘብ 14 ሺሕ ፓውንድ ደረሰ
ቸኮሌት በመሥረቋ 330 ፓውንድ ቅጣት ለተጣለባት እንግሊዛዊት ሎዊዛ ስዌል እየተደረገ ባለው የገቢ ማሰባሰቢያ የተገኘው ገንዘብ ከ14 ሺሕ ፓውንድ በላይ መድረሱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ስዌል፣ የሠረቀችው ቸኮሌት በጣም ርካሽ የሚባል እንደሆነና ለቀናት ምግብ ባለመብላቷ ድርጊቱን መፈጸሟን ለፍርድ ቤት አስረድታለች፡፡ እንግሊዛዊቷ ለቀናት ምግብ ያልበላችው ከመንግሥት የምታገኛቸው ጥቅማ ጥቅሞች በመታገታቸው መሆኑንም ለፍርድ ቤት ገልጻ ነበር ፡፡
ፍርድ ቤቱ ቸኮሌቱ ለተሠረቀበት መደብር ካሳ፣ ፍርድ ቤት ክስ የተመሠረተበትንና የፍርድ ሒደት ወጪን አስልቶ ነው ስዌል ላይ የ330 ፓውንድ ቅጣት የጣለው፡፡
በገቢ ማሰባሰቢያው የተገኘው ትርፍ ገንዘብ ድህነት ላይ ለሚሠራ በጎ አድራጎት ድርጅት እንደሚሰጥ ዘገባው ያመለክታል፡፡
***********
አወዛጋቢው አሻንጉሊት
የተለያዩ ዕውቅና ያላቸውን ሰዎችን በአሻንጉሊት መልክ በመሥራት ዝናን ያተረፈው የቻይናው አሻንጉሊት አምራች ድርጅት፣ በጀርመናዊው የማንችስተር ዩናይትድ አማካይ ተጨዋች ባስቲያን ሸዋንስታይገር ክስ ተመሠረተበት፡፡
ሸዋንስታይገር በአሻንጉሊት አምራቹ ላይ ክስ የመሠረተው፣ ድርጅቱ የተጨዋቹን ምሥል በአሻንጉሊት መልክ ቀርጾ የናዚ አለባበስ አጎናጽፎ ለገበያ በማቅረቡ ነው፡፡
ስካይኒውስ እንደዘገበው፣ ድርጅቱ የቀድሞው የሶቪየት ኅብረት መሪ ጆሴፍ ስታሊን፣ የቀድሞው የእንግሊዝ የጦር መሪ ዌንስተን ቸርችል እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ አምሳያዎችን በአሻንጉሊ በመቅረፅ ለገበያ ያቀርባል፡፡
ድርጀቱ፣ የሸዋንስታይገርን አምሳያ የናዚ ወታደር ልብስ አልብሶ በአሻንጉሊት መልክ መሥራቱ፣ ተጨዋቹን ለመጉዳት አስቦ አለመሆኑንና አለባበሱም የአጋጣሚ መሆኑን ቢገልጽም፣ የጀርመን ሚዲያዎች ጉዳዩን አራግበውታል፡፡
‹‹ጀርመኖች በሙሉ ናዚ ናቸው ወደሚለው ድምዳሜ ይወስዳል፡፡ ባስቲያን የሚለው ስም ደግሞ በጀርመን የተለመደ በመሆኑ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው፤›› ሲሉም አንዳንድ ጀርመናውያን ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጀርመን የሚዲያ ሕግ አማካሪው ኡሪክ አመሉንግ እንደሚሉት፣ ‹‹የቻይናው ኩባንያ የሠራው አሻንጉሊት፣ የሸዋንስታይገርን መብት የጣሰ፣ ስም ያጠፋ ስድብ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ሆኖም በድረገጽ አሻንጉሊቶችን ለመግዛት የተሳተፉ ደንበኞች፣ ስለአሻንጉሊቱ ያላቸውን ቀና አስተሳሰብ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኔ የሸዋንስታይገር አምሳያ ያለበትን አሻንጉሊት ወድጀዋለሁ፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዷ ነገር ጥሩ ተደርጋ ተሠርታለች›› ስትል ማይላላን የተባለች ገዢ ተናግራለች፡፡