Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምአፍጋኒስታንንና ፓኪስታንን የመታው ርዕደ መሬት

አፍጋኒስታንንና ፓኪስታንን የመታው ርዕደ መሬት

ቀን:

ባለመረጋጋትና በጦርነት የምትፈተነውን አፍጋኒስታን ማዕከል ያደረገው ርዕደ መሬት በአፍጋኒስታንና በአካባቢው ለሚኖሩ፣ ከ350 ለሚበልጡ ነዋሪዎች ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ በሔክተር ስኬል መለኪያ 7.5 የሆነው ርዕደ መሬት፣ ሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በአፍጋኒስታን ቢከሰትም ምቱ ፓኪስታን፣ ታጃኪስታንና ህንድ ድረስ ዘልቋል፡፡

የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ የርዕደ መሬቱ መነሻ በሰሜን አፍጋኒስታን በምትገኘውና ፓኪስታንን፣ ታጃኪስታንና ቻይናን በምትዋስነው ባዳኪሽሃን ቢሆንም፣ ከፍተኛ ሞት የተመዘገበው ግን ፓኪስታን ውስጥ ነው፡፡

አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው፣ በርዕደ መሬቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር እስከ ማክሰኞ ድረስ 311 የደረሰ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 228 ሞት የተመዘገበው በፓኪስታን ነው፡፡ በፓኪስታን ከተመዘገበው ከፍተኛ ሞት በተጨማሪ ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ርዕደ መሬቱ በተነሳበት አፍጋኒስታን እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ 33 ሰዎች ሲሞቱ ከ200 በላይ በሚሆኑት ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በአፍጋኒስታን በተመዘገበው ሞት 12 ሴት ተማሪዎች እንደሆኑም ታውቋል፡፡

በህንድ ቁጥጥር ሥር በሚገኘው ካሽሚር ግዛት ውስጥ ሁለት ሞት የተመዘገበ ሲሆን፣ ርዕደ መሬቱ ካስመዘገበው 7.5 ሔክተር ስኬል ማለትም ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ አንፃር፣ የሞትና የጉዳት መጠን ሊጨምር እንደሚችል የፓኪስታንና የአፍጋኒስታን ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡

ከካቡል ሰሜን ምሥራቅ 160 ማይል ርቀት ላይ የተነሳው ርዕደ መሬት 132 ማይልስ ጥልቀት ያለው በመሆኑ፣ ተፅዕኖው እስከ ህንድ ኒው ዴልሂ እንደዘለቀ ተዘግቧል፡፡

በአፍጋኒስታን በ14 ከተሞች የሚገኙ 103 አካባቢዎች በርዕደ መሬቱ ሲመቱ፣ አራት ሺሕ የሚጠጉ ቤቶችም ወድመዋል፡፡ ዝናብ በመቀላቀሉም በብዙ ሥፍራዎች ላይ የመሬት መንሸራተት አስከትሏል፡፡

የአፍጋኒስታንና የፓኪስታን ባለሥልጣናት የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ቢጠይቁም፣ ለተጎጂዎች መድረስ ግን ቀላል አልሆነም፡፡ ዕርዳታ ለማድስ የተደረጉ ጥረቶችም በኤሌክትሪክና በስልክ መቋረጥ፣ እንዲሁም በመንገድ መፈራረስና ተራራማነት የተነሳ በአግባቡ ሊደርሱ አልቻሉም፡፡ በአፍጋኒስታን በተለይም ታሊባን ተደጋጋሚ ጥቃት በሚያደርስበት ሰሜናዊው ክፍል ደግሞ ዕርዳታ ማድረሱ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡

በሰሜን ፓኪስታን አብዛኞቹ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በጥራት ባለመገንባታቸው በርዕደ መሬቱ በቀላሉ ወድመዋል፡፡

በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል፣ በህንድ ዋና ከተማ ኒው ዴልሂ እንዲሁም በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢዝላማባድ የሚኖሩ ነዋሪዎች ርዕደ መሬቱ ዳግም ይከሰት ይሆን? የሚል ሥጋት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በኢዝላማባድ ሕንፃዎች ተሰነጣጥቀዋል፡፡ ሠራተኞችም ሕንፃዎችን ለቀው ወጥተዋል፡፡ በኒው ዴልሂ ርዕደ መሬቱ በተከሰተበት ዕለት የባቡር ትራንስፖርት ለ15 ደቂቃዎች ያህል አገልግሎት መስጠት አቁሞ ነበር፡፡

በርዕደ መሬቱ የተጎዱ የፓኪስታንና የአፍጋኒስታን ዜጎች ለመድረስ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ ርዕደ መሬቱ ባጠቃቸው ገጠራማ አካባቢዎች የደረሰውን የጉዳት መጠን ለማወቅም ሆነ ሥፍራዎቹን ለማየት አልተቻለም፡፡

በአፍጋኒስታን ተራራማ ሥፍራዎች በተከሰተው ጉዳት ዕርዳታ ለማድረስ የታሊባን ተዋጊዎች እንቅፋት ይፈጥራሉ የተባለ ቢሆንም፣ በርዕደ መሬቱ ከተጠቁ አካባቢዎች የተወሰነውን የተቆጣጠረው ታሊባን ዕርዳታ ሰጪዎች እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የታሊባን ተዋጊዎች የተጎዱ ሰዎችን እንዲያግዙ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ሲሆን፣ የዕርዳታ ኤጀንሲዎች እንዳያፈገፍጉና የዕርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉም ታሊባን ጠይቋል፡፡

በአፍጋኒስታን ላለፉት አራት ቀናት ከባድ ዝናብ መጣሉ ችግሩን አወሳስቦታል፡፡ ነዋሪዎችም ከቤት ወጥተው ደጅ ማደርን ተያይዘውታል፡፡ በአፍጋኒስታን ካናር ከተማ ፖሊስ አዛዥ አብዱል ሃቢብ ‹‹ሕዝቡ ደጅ ከማደር ባለፈም በቂ ምግብ የለውም፤›› ሲሉም መናግራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የማንቂያ ደወል

የደቡብ እስያ ክፍል ከዚህ ቀደምም ከባድ ርዕደ መሬት ደርሶበታል፡፡ ባለፈው ዓመት በኔፓል በተከሰተ ርዕደ መሬት ከዘጠኝ ሺሕ ዜጎች በላይ ሞተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2005 በካሽሚር በተከሰተውና 7.6 ባስመዘገበው ርዕደ መሬት ከ73 ሺሕ በላይ ሰዎች ሲሞቱ 69 ሺሕ ያህል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ቤት አልባ ሆነዋል፡፡

አካባቢው ለርዕደ መሬት ተጋላጭ የመሆኑን ያህል የየአገሮቹ መንግሥታት የአደጋ ጊዜ ዝግጁነታቸው ደካማ መሆኑ ይነገራል፡፡ በፓኪስታን አደጋን የመከላከልና የመቆጣጠር አቅም የተጠናከረ አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2005 በፓኪስታን ካሽሚር በተከሰተው ርዕደ መሬት ከዘጠኝ ሺሕ በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን ቢያጡም፣ ካለፈው ርዕደ መሬት የተወሰደ ትምህርት እንደሌለ የፓኪስታን ዴይሊ ታይምስ ዘግቧል፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም የማንቂያ ደወል ተደውሏል›› የሚለው ዘገባው፣ ርዕደ መሬቱ የተፈጥሮ አደጋ ቢሆንም የአደጋው ሰለባ የሆኑት ትምህርት ቤቶች በሙስና ምክንያት ደረጃቸውን ጠብቀውና ርዕደ መሬት የሚቋቋሙ ተደርገው አለመገንባታቸውን አውስቷል፡፡

ምክንያቱ ያልተገለጸ ርዕደ መሬት

አፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን፣ ህንድ ከዝቅተኛ እስክ ከፍተኛ ደረጃ በሚደርስ ርዕደ መሬት የመመታት ታሪክ አላቸው፡፡ ባለፈው ሰኞ በአፍጋኒስታን ሂንዱ ኩሽ ተራራ ላይ የተነሳው ርዕደ መሬት፣ ከመሬት በታች 200 ኪሎ ሜትር ዘልቆ የገባ ነበር፡፡ ርዕደ መሬቱ ማዕከል ካደረገው ሥፍራ በምዕራብ አቅጣጫ በሚገኙ አካባቢዎች 4.0 እና ከዚህ በላይ ሔክተር ስኬል ያላቸው ተከታታይ ርዕደ መሬቶች ተከስተዋል፡፡ ናሽናል ጂኦግራፊ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፣ ይህ ዓይነቱ ክስተት ለሳይንቲስቶችም ግልጽ አይደለም፡፡

ላለፉት 100 መቶ ዓመታት ከነበሩ ከባድ ርዕደ መሬቶች ሰባት ያህሉ የተከሰቱት ሂንዱ ኩሽ ተራራ ከሚገኝበት እስከ 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ባሉ ሥፍራዎች ቢሆንም፣ ይህ ለምን ሆነ የሚለው ሳይንሳዊ ምላሽ አላገኘም፡፡ አካባቢው ገጠራማ፣ ተራራማና ግጭት የሚበዛበት በመሆኑ ጂኦሎጂስቶች የርዕደ መሬቱን ምክንያት ለይተው ለማወቅ አለመቻላቸውን፣ በሳንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጂዮፊዚስት የሆኑት ግሬግ ቢሮዛ ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ደግሞ፣ ጥልቀት ያላቸው የርዕደ መሬት ክስተቶችን ለማጥናት ከባድ መሆኑን አስታውቋል፡፡

spot_img
Previous article
Next article
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...