Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየፋቡላ ህልም

የፋቡላ ህልም

ቀን:

የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የቴአትር ጥበባት ተማሪ የነበሩ ሰባት ወጣቶች ይሰበሰባሉ፡፡ ወጣቶቹን አንድ የሚያደርጋቸው ለትውፊታዊ ተውኔቶች ያላቸው ፍቅር ነበር፡፡ ሊመረቁ የወራት ዕድሜ ሲቀራቸው ከስሜታቸው በዘለለ ትውፊታዊ ድራማዎችን አዘጋጅተው ለማቅረብ ወጥነውም፣ ‹‹ፋቡላ›› የተሰኘ የጥበባት ማኅበር አቋቋሙ፡፡ ተማሪዎቹ በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ቀዳሚ እንደሆነ የሚነገርለትን ‹‹ፋቡላ፤ የአውሬዎች ኮሜዲያ››ን ታሳቢ አድርገው በሰየሙት ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ትውፊቶችን ያስሱም ጀመር፡፡

የበጅሮንድ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ቴአትር ‹‹ፋቡላ፤ የአውሬዎች ኮሜዲያ›› በወቅቱ ለእይታ የበቃው ሆቴል ውስጥ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ የተለያየ ዘውግ ያላቸው ቴአትሮች እየተሠሩ በአገሪቱ ልዩ ልዩ ሥፍራዎች ለተመልካች ደርሰዋል፡፡ ፋቡላ የሚለው የቡድኑ ስያሜ መሠረት ይህ ነው፡፡

የፋቡላ የመጀመሪያ ሥራቸው ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ያዘጋጁት ትውፊታዊ ድራማ ሲሆን፣ የተለያዩ ብሔረሰቦች ተጣምረው የሚፈጥሯትን ኢትዮጵያ የሚያሳይ ነበር፡፡ ድራማውን ለማዘጋጀት የነበራቸው ጊዜ አጭር ነበርና በየብሔረሰቡ ተዘዋውሮ ጥናት ማካሄድ አልተቻለም፡፡ አባላቱ እንደ አማራጭ የወሰዱት ከየክልሉ የተውጣጡ ተማሪዎች ወደሚማሩበት ትምህርት ቤት ሄዶ በአጭር ጊዜ ባህላቸውን ማጥናትን ነበር፡፡ በስብሰባ ማዕከል የቀረበው ድራማው በወቅቱ ተወዳጅነት አትርፏል፡፡ ድራማው ከሕዝብ የተዋወቁበት ከመሆኑ ባሻገር፣ የተከፈላቸው 10,000 ብር መቋቋሚያ ሆኗቸዋል፡፡ ከዚያም ላለፉት ዓመታትም በብዙ መድረኮች ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡

ከሰባቱ መሥራቾች አምስቱ ከማኅበሩ ጋር ዘልቀዋል፡፡ ድራማዎች ሲያዘጋጁ የሚያሳትፏቸው አባላት ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ከአባላቱ ብዙዎቹ የቴአትር ጥበባት ምሩቃን ሲሆኑ፣ ትእይንት ሲኖራቸው ይሰባሰባሉ፡፡ በተቀሩት ጊዜአት ደግሞ በየፊናቸው ይሯሯጣሉ፡፡ ከመሥራቾች ሁለቱ በሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር ከፍተኛ የቴአትር ባለሙያ ሒሩት ይርዳውና የካፍደም ሲኒማ ሥራ አስኪያጅ ስንታየሁ ታዬ ናቸው፡፡

ከሥራዎቻቸው ‹‹ባህልን ለልማት›› በሚል ያዘጋጁት የሦስት ቀን ፌስቲቫል ይጠቀሳል፡፡ የደራሼ፣ ዋግህምራና ወለጋ የሠርግ ሥነ ሥርዓትን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር፣ ስብሰባ ማዕከልና ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አሳይተዋል፡፡ በየትኛውም አካባቢ ያለ ነዋሪ በሌላ ቦታ ስላሉ ማኅበረሰቦች ባህል አካባቢው ድረስ ሳይሄድ እንዲያውቅ ከሚያስችሉ መንገዶች መካከል ትውፊታዊ ድራማ ይጠቀሳል፡፡ ባህልን ተመልካች ያለበት ድረስ ያመጣሉ፡፡

‹‹ከራሱ ብሔረሰብ ውጪ ስለሌላውም ብሔረሰብ እሴት መናገር የሚችል ትውልድ መፍጠር አንዱ ዓላማችን ነበር፤›› ትላለች ሒሩት፡፡ የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ አማርኛ በመሆኑ ሥራዎቻቸውን በአማርኛ ቢያቀርቡም፣ የተለያዩ ብሔረሰቦችን ባህል እንደሚያሳዩ ታስረዳለች፡፡ ይዘው የተነሱት ዓላማ ሙሉ በሙሉ ተሳክቷል ማለት ባይቻልም፣ ለውጦች እንዳስተዋለ ስንታየሁ ይናገራል፡፡ ስብጥር ያላቸው ተመልካቾች በታደሙባቸው መርሐ ግብሮች ሥራቸውን አቅርበው ጥሩ ምላሽ ማግኘታቸውን እንደ ስኬት ይጠቅሳል፡፡

ፋቡላ በአንድ ወቅት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ያዘጋጃቸው በነበሩ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች ሥራዎቻቸውን ያቀርቡ ነበር፡፡ በፑሽኪን (የሩሲያ ባህል ማዕከል) በየሦስት ወሩ የተለያዩ ብሔረሰቦችን ትውፊታዊ ሥራዎች አቅርበዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ሥራዎቻቸው የጦቢያ ግጥምን በጃዝ ወርኃዊ ምሽቶች ይጠቅሳሉ፡፡ ሻደይ፣ አሸንዳና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የባህል ጥናት ከጀመሩባቸው ጥቂቱ ናቸው፡፡

ዓላማዎቻቸውን ከግብ እንዳያደርሱ በርካታ ችግሮች እየተፈታተኗቸው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ዋነኛው የፋይናንስ እጥረት ነው፡፡ የአባላቱን መሠረታዊ ፍላጐቶች ለማሟላት የሚያስችል ገቢ ስላልተገኘ አልባሳትና ሌሎችም ግብአቶችን ከቴአትር ቤቶች በውሰት ለመውሰድም ተገደዋል፡፡ መለማመጃ ቦታ ስለሌላቸው፣ ትእይንት ባሰናዱ ቁጥር ፊታቸውን ወደሚተባበሯቸው ተቋማት ያዞራሉ፡፡

ስንታየሁ እንደሚለው፣ የማኅበሩ መሥራቾች ያላቸው ዝንባሌም እውቀትም ቴአትር ተኮር በመሆኑ በአስተዳደርና አቅም ግንባታ ረገድ በምን አቅጣጫ መሄድ እንዳለባቸው ሳይገነዘቡ ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከታደሙባቸው መድረኮች ያገኙትን ተሞክሮ በመመርኮዝ የማኅበሩን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ፈር ማስያዝ እንዳለባቸው ያምናል፡፡

ስለትውፊታዊ ድራማ ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች ውስን መሆናቸው ሌላው ችግር ነው፡፡ አንድ ድራማ ለመሥራት የትውፊቱ ባለቤት ከሆኑ ማኅበረሰቦች ጋር ተቀራርቦ ባህላቸውን ማጥናት፣ መጻሕፍትና ጥናቶችን ማገላበጥም ግድ ይላል፡፡ ቢሆንም ረዥም ጊዜ ወስደው ላዘጋጁዋቸው ትውፊታዊ ድራማዎች መድረክ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት አለመሳካት ተስፋ አስቆራጭ የሆነበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም፡፡

በሌላ በኩል ማኅበሩን ግብአት በማቅረብ፣ በተለያዩ መድረኮች እንዲሳተፉ በመጋበዝና በሌላም መንገድ ድጋፍ የሚያደርጉላቸው ግለሰቦች መኖራቸው ደግሞ ተስፋቸውን ያለመልመዋል፡፡ ሥራዎቻቸው ለሌሎች የኪነ ጥበብ ውጤቶች መነሻ ሆነው ማየታቸው ዘወትር እንደሚያበረታታቸው ሒሩት ትናገራለች፡፡ እንደ ምሳሌ የምትጠቅሰው ለኢትዮጵያ ሚሊኒየም ያቀረቡት ትእይንት በብሔር ብሔረሰቦች የሙዚቃ ቪዲዮ ተቀንጭቦ መካተቱን ነው፡፡

ሒሩት ኢትዮጵያ ውስጥ ባህል ተኮር ኪነ ጥበባዊ ሥራዎችን መሥራት ከባድ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ኃላፊነት ለመውሰድ ፈቃደኛ የሆኑ ተቋማት ውስን መሆናቸውንም ታክላለች፡፡ ‹‹ትውፊታዊ ድራማዎች ካላቸው ማኅበረሰባዊ ፋይዳ አንፃር ተገቢው ትኩረት አልተሰጣቸውም፤›› በማለት ዘርፉ በውጣ ውረድ የተሞላ መሆኑን ታስረዳለች፡፡ አንድ ሥራ ለእይታ ከበቃ በኋላ አድናቆታቸውን የሚገልጹ እንጂ ደፍረው ኢንቨስት የሚያደርጉ ጥቂቶች ቢሆኑም ‹‹ገንዘብ ስላላገኘን አንቆምም፤›› ይላል ስንታየሁ፡፡

ፋቡላዎች ለዘርፉ መስዋዕትነት መክፈላቸው ነገ በተመሳሳይ ሙያ ለሚሰማሩ ወጣቶች ነገሮችን እንደሚያቀል ያምናሉ፡፡ እነሱን የገጠሟቸው መሰናክሎች ተስተካክለው ትውፊታዊ ድራማዎች አልያም ተውኔቶች በስፋት ለተመልካች የሚደርሱበትን ቀን ለማየትም ይናፍቃሉ፡፡ መሥራቾቹ፣ ከተነሱበት ጊዜ ጀምሮ የገጠሟቸው ፈተናዎች ማኅበራቸውን እንዳደከሙት ቢናገሩም፣ ለሙያው ያላቸው ፍቅር ዳግም ለመነሳት ምርኩዝ እንደሆናቸው ይናገራሉ፡፡

‹‹ሁሌም አዳዲስ ነገሮችን ለመሥራት ተነሳሽነት አለን፤›› የሚሉት መሥራቾቹ፣ የማኅበራቸውን ክፍተት የሚሞሉ ግብአቶችን በማቅረብ አልያም መድረክ በማመቻቸት የሚያግዟቸው ቢያገኙ በርካታ ትውፊታዊ ድራማዎችን ለሕዝብ እንደሚያቀርቡ በማመን ነው፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በየክልሉ ያሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች፣ የየክልሉ ልማት ማኅበሮች እንዲሁም የባህል ጉዳይ የሚቆረቁሯቸው በሙሉ እንዲያግዟቸም ጥሪ ያቀርባሉ፡፡

ሒሩት ‹‹ፋቡላ ማለት መገለጫዬ ነው፤ መስዋዕትነት የከፈልኩበት ማኅበር ነው፤›› በማለት ትገልጸዋለች፡፡ ስንታየሁ በበኩሉ ፋቡላ ስሜቱን የሚገልጽበት፣ ታሪኮችን የሚናገርበት መንገድ እንደሆነ ያምናል፡፡

ትውፊታዊ ድራማ ታሪክ ከሚተላለፍባቸው መንገዶች አንዱ በመሆኑ ትኩረት እንዲቸረው የሚያሳስበው ስንታየሁ፣ ማኅበራቸው አሁን ካለው የተለመደው የቴአትር አቀራረብ የተለየ ቅርጽ ያላቸው ሥራዎች የሚወጡበት እንዲሆን ተስፋ ያደርጋል፡፡

ፋቡላዎች አንድ ኢትዮጵያዊ ከራሱ ብሔረሰብ ውጪ ስለሌሎችም ግንዛቤው ኖሮት ማየት ህልም አላቸው፡፡ ቴአትር፣ ፊልምና ሌሎችም የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች በጉጉት የሚታደመው ተመልካች ለትውፊታዊ ድራማም ተመሳሳይ ምላሽ የሚሰጥበት ቀን እንደሚመጣም ያምናሉ፡፡         

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...