በአለቃ ጌታቸው
አገራችን የተያያዘችው የዕድገትና ልማት እንቅስቃሴ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ድህነትን ለማስወገድ ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ መድረሱን ሁሉም የሚቀበለው ገሃዳዊ እውነት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ መንግሥት ይህ ተስፋ ሰጪ የልማትና የዕድገት እንቅስቃሴ ይበልጥ ጎልብቶ ኢትዮጵያን ከድህነትና ከኋላቀርነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማላቀቅ ቁርጠኛ አቋም ይዞ፣ በሁሉም ዘርፍና ሴክተር የተቀናጀ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡
ይህ በአገሪቱ የተቀጣጠለው የዕድገት ተስፋ ወደኋላ እንዳይንሸራተትና ጨርሶም እንዳይቀለበስ፣ በተለይም በአመራር አቅምና በመልካም አስተዳደር ረገድ ሰፊ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ መንግሥት በማመኑ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለችግሮቹ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሁኔታውን ለማሻሻል ቀን ከሌት እየለፋ ይገኛል፡፡
በርካታዎቹ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ውጤቶችም ይህንኑ ተረድተው መንግሥት የጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ግቡን እንዲመታ ከጎኑ በመቆም በሙያቸው የተቻላቸውን እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ መሰል የሙያው በጎ ተግባራት መካከልም የሪፖርተር ጋዜጣ ሳይታክትና ሳያሰልስ እያበረከተ ያለው አስተዋጾኦ ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
ጋዜጣው በዚህ መልኩ ለንባብ ካበቃቸውና ኃላፊነቱን በአግባቡ ከተወጣባቸው መጣጥፎች አንዱ ባለፈው መስከረም 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በቅጽ ቁጥር 1609 ‹‹ልናገር›› ዓምዱ በአቶ ታደሰ ዓለሙ የተጻፈ ጽሑፍ ተጠቃሽ ነው፡፡
ይህ ጽሑፍ የአገሪቱ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት ምን ያህል በአመራር ብቃት ማነስ፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር እንዲሁም በመልካም አስተዳደር ዕጦት እየዘቀጠ እንደሚገኝ ያመላከተ በመሆኑ፣ በዘርፉ የተሰማራውን ባለድርሻ አካል ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚ የሆነውንም የኅብረተሰብ ክፍል ያስደሰተና የዘርፉን ሁለንተናዊ ችግሮች ያመላከተ በመሆኑ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡
አቶ ታደሰ ዓለሙ ያደረጉት ነገር ቢኖር በጽሑፉ ላይ የተጠቀሱት ችግሮች በተለያዩ ዘርፉን በተመለከተ በተደረጉ ስብሰባዎች ላይ የቀረበ፣ ለሚመለከተው የመንግሥት አካልና በሕዝብ ማመላለሻ ዘርፍ ላይ የተሰማራ ባለድርሻ አካል ሁሉ የሚያውቃቸው ሆኖ፣ አሁን ግን ጸሐፊው መላው የኅብረተሰብ ክፍል እንዲያውቀው ያደረጉ እውነተኛ የዘርፉ ተቆርቋሪ መሆናቸውን ነው፡፡
ያም ሆኖ አቶ ታደሰ ዓለሙ የጻፉትንና በበሳል ሙያዊ ብቃት የተቀነባበረው ይህ እውነት ያላስደሰታቸውና በችግሮቹ መካከል በተፈጠረ ቀዳዳ ከግል ጥቅማቸው ጋር የሚያያይዙ አካላት፣ ‹‹የአቡዬን ግብር የበላ ሳይጠይቁት ያስለፈልፈዋል›› እንዲሉ አሁንም እንደ ወትሯቸው እውነቱ ተድበስብሶ እንዲቀር በሪፖርተር ጋዜጣ ቅጽ 2 ቁጥር 1613 ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በወጣው ዕትም ላይ ‹‹የሰሙትን ከማስተጋባት ያዩትን መናገር ለእውነት ይቀርባል›› በሚል ርዕስ በአቶ ታደሰ አለሙ የቀረበውን የዘርፉን አጠቃላይ ችግሮች የሚዳስስ ጽሑፍ እነሱን የማይወክልና የተዛባ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የሚዲያውን ሙያዊ ብቃት የሚያጥላላ ጹሑፍ የሁሉም ትራንስፖርት ማኅበራት አቋም አስመስሎ በማዘጋጀት ለንባብ አብቅተዋል፡፡ ስለእውነት እንነጋገር ከተባለ የጸሐፊው ስህተት ምኑ ላይ ነው?
አቶ ታደሰ ዓለሙ በበሳል ጽሑፋቸው ባቀረቡት መጣጥፍ ላይ በሕገወጥ መንገድ የበለፀጉ ጥቂት ግለሰቦችን የሚኮንኑ የትራንስፖርት ዘርፍ በልምድ እንጂ በሲስተም የሚመራ አለመሆኑ፣ እስካሁን ለውጥ ሳያመጡ ዘርፉን ለረጅም ጊዜ የመሩትን አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ለሕዝብ ያጋለጠ ጽሑፍ ሆኖ ሳለ፣ ይህንን ለማድበስበስ የቡድን ጸሐፊዎች የጻፉትን ማስተባበያ አንብቤ እኔ እውነቱን መመስከር አለብኝ ከሚል ስሜትና ቁጭት በመነሳት ‹‹እንዳልናገረው ጉዱ ብዙ ሆኖ፣ እሆዴ ያለው ጭስ ገደለኝ አፍኖ›› በማለት ለዘመናት የያዝኩትን እውነት በዚህ ጽሑፍ ለአንባቢያን አቅርቤአለሁ፡፡
የቡድን ጸሐፊው እንድል ያስቻለኝ ጽሑፉ የቀረበው ከአገር አቋራጭ የትራንስፖርት ማኅበራትና ድርጅቶች መሆኑን በርዕሱ ላይ የተቀመጠ ቢሆንም፣ የትራንስፖርት ባለሥልጣንን መከላከል ባስመሰለ መልኩ ጽሑፉ ያትታል፡፡ ማንኛውም ተቋምም ሆነ ግለሰብ በሠራው ሥራ ተጠያቂ ላለመሆን ራሱ መልስ መስጠት ሲገባው፣ በሌሎች ተንተርሶ መልስ ለመስጠት መሞከሩ በአቶ ታደሰ ዓለሙ የቀረበው ጹሑፍ ተቋሙ ምን ያህል የወረደ ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያሳይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የዚህ ጹሑፍ አቅራቢ ያረጋገጠው እውነት ቢኖር ዘርፉን የሚመሩ የትራንስፖርት ባለሥልጣንና የቅርብ ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ለእንደዚህ ዓይነት ተግባር ከሕግ ውጪ ያደራጇቸው ጥቂት ማኅበራትን በማሰባሰብ የማስተባበያ ጽሑፉን ካዘጋጁ በኋላ፣ ሌሎችን ማኅበራት ማኅተም እንዲያደርጉ በማስገደድ ማኅበራቱም ከዕለት ሕይወት ፍራቻ በመነሳት ጹሑፉን እንዳዘጋጁ በመቁጠር በመሸኛ ወረቀቱ ላይ ብቻ በግዳጅ ማኅተም እንዲያደርጉ መገደዳቸውን ነው፡፡ የትራንስፖርት ማኅበራት በጉዳዩ ላይ የጋራ እምነትና የተጻፈው ጽሑፍ እውነትነት ከሌለው በራሳቸው መድረክ ተሰብስበው ጸሑፉን ገምግመው በቃለ ጉባዔ በተደገፈ መልኩ ማስተባበያ ማቅረብ ሲቻል፣ ሁሉንም ባልወከለ መንገድ በህቡዕ በመንቀሳቀስ በጥቂት ጥቅማቸው በተነካባቸውና ተጠያቂ እንዳይሆኑ በሰጉ ግለሰቦች የተጻፈ ጽሑፍ መሆኑን ታዝቤአለሁ፡፡ የጽሑፉ አብዛኛውን ቦታ የያዘው አቶ ታደሰ ዓለሙ ለጻፉት ጽሑፍ እውነተኛና በመረጃ የተደገፈ መልስ ከመስጠት ይልቅ፣ የትራንስፖርት ታሪካዊ አመጣጥን ለጥናት በሚመስል መልኩ የተጻፈና ከሌላ ተገልብጦ የመጣ መሆኑን ያሳያል፡፡
የቡድን ጸሐፊዎች ከጻፉት ነጥብ ላይ አንዱ በአቶ ታደሰ ዓለሙ የቀረበው ጹሑፍ በመረጃና በእውነተኛ ማስረጃ ያልተደገፈ መሆኑ ተጨባጭ እውነታዎችን መመስከር እንዳልቻሉ ይገልጻሉ፡፡ በዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮችን ዓይቶ ለመመስከር ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ የሚቻል ቢሆንም፣ አቶ ታደሰ ዓለሙ ከገለጿቸው ነጥቦች በተጨማሪም አንባቢያን እንዲረዱት ለማድረግ የሚከተሉትን ጭብጥ ማስረጃዎች ከበቂ በላይ ይሆናሉ በሚል ለአንባቢ አቅርቤአለሁ፡፡
ማስረጃ አንድ፡- የኢትየጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን መስከረም 29 እና 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በቴሌቪዥን ዜና ዕወጃው በአዲስ አበባ ከተማ በፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ሥር የሚተዳደሩ መናኸሪያዎች ያሉበትን አስከፊ ደረጃ በምሥል በመደገፍና ከተጠቃሚውና ከራሱ ከትራንስፖርት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች መብራት፣ አጥር፣ መዝናኛ፣ ፅዳት፣ የእንግዶች ማስተናገጃ፣ የመፀዳጃ ቤቱን የፅዳት ጉድለት፣ ወዘተ በተመለከተ ግልጽ መረጃ ተሰጥቷል፡፡ ከዚህም በላይ መናኸሪያዎቹ ለመንገደኛ ምቹ ያለመሆናቸውንና ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የመናኸሪያዎቹን ደረጃ እንዲያሻሽል ቢነገረውም ያልሠራ መሆኑን ከዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኃላፊ በግልጽ ቋንቋ ተነግሯል፡፡ የአቶ ታደሰ ዓለሙ ጽሑፍ በእጃችን የሚገኙትን መናኸሪያዎች እንደ አቅማችን በአግባቡ ጠግነንም ሆነ አስተካክለን መሠረታዊ የሆኑ ፋሲሊቲዎች ተሟልተውላቸው ከአቧራና ከቆሻሻ የፀዳ፣ በቂ መፀዳጃ ያለው፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለአረጋዊያን ምቹ የሆነ መናኸሪያ ሊኖረን ይገባል፡፡ አለመታደል ሆኖ እንጂ አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ የዕድገት ሒደቷ በየሴክተሩ እጅግ ብዙ የሆኑ ዕቅዶች ታቅደው በተግባርም የታዩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች፣ ኤርፖርቶች፣ ስታዲየሞች፣ ወዘተ በክልልም ደረጃቸውን የጠበቁ መናኸሪዎች እየተገነቡ የሚታይ ሀቅ ሲሆን፣ የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣንን ለረጅም ጊዜ የመሩ የአመራር አካላት አቅዶ የመሥራት፣ ዕቅድን የማስፈጸም፣ ክትትልና ጥናት ባለመኖሩ እስካሁን ደረጃውን የጠበቀ መናኸሪያ በፌደራል ደረጃ ሊኖረን አላስቻሉንም፡፡
ነገር ግን በየዓመቱ በሚያቀርቡት ሪፖርት መሬት ላይ የሌለን ነገር ብዙ እንደሠሩ እየተደረገ እንደሚቀርብ የሚታወቅ ነው፡፡ የቡድን ጸሐፊዎች ግን የሐሰት ምስክር ሆነው ሲቀርቡ ይታያል፡፡ ሆኖም በቀጣይ መንግሥት በወጠነው የሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮት ደረጃ ስንደርስ፣ የዘርፉን ችግሮች ሙሉ በሙሉ ተቀርፎ የመናኸሪያ ደረጃችንም ሆነ አጠቃላይ የዘርፉ ዕድገት በዚያው መልኩ የሚያድግ መሆኑን፣ እስካሁን አንድ በፌደራል ደረጃ የአገሪቱን ዕድገት የሚመጥን መናኸሪያ አልኖረንም የሚል መልዕክት የያዘ ነው፡፡ የቡድን ጸሐፊዎች ራስን ለመከላከል እንጂ እውነታውን በአግባቡ የገለጹት አልመሰለኝም፡፡ ከማንም በላይ አሁን ያሉት መናኸሪዎች የአገልግሎት ደረጃ ምስክርነት የሚሰጠው ሕዝቡ ምን እንደሚል በኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን በቀረበው የቴሌቪዥን ዜና ዕወጃ ላይ ተገልጿል፡፡
ማስረጃ ሁለት፡- በትራንስፖርት ባለሥልጣን የሕዝብ ትራንስፖርት ሞደርናይዜሽን የጥናት ሰነድ በራሱ በትራንስፖርት ባለሥልጣን ባለሙያዎች በጷጉሜን 2006 ዓ.ም የቀረበው ሰነድ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፣ በክፍል ሁለት ‹‹በሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ነባራዊ ገጽታዎችና መሠረታዊ ችግሮች›› በሚል ርዕስ ሥር፣
- አሁን ያለው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ከኅበረተሰቡ መንቀሳቀስ ፍላጎት ጋር አብሮ ሊያድግ ያልቻለና በዕድሜ ጠገብ ችግሮች የታነቀ መሆኑ እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ አለመሆኑ፣
- ዘርፉ አሁንም ቢሆን በተለምዶአዊ አሠራር የሚመራ በመሆኑ ከነባር ችግሮች ለመላቀቅ በሚደረግ ጥረቶች የአመለካከት፣ የክህሎትና የአቅም ውስንነት ፈታኝ እንቅፋቶች ሆነው የሚስተዋሉ ችግሮች እንደሆኑ፣
- የሕዝብ ትራንስፖርት የአገልግሎት መስጫ ቦታዎች ደረጃቸውን ያልጠበቁና አስፈላጊው አገልግሎት መሟላት ያልቻሉ በደካማ አቅርቦት መገለጫ የሚፈረጁ ሲሆኑ ተጠቃሚውን ለወከባና ለእንግልት የሚያጋልጡ ቦታዎች ሆነው እንደሚስተዋሉ፣
- ዘርፉ በቴክኖሎጂ ያልተደገፈ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የአገልግሎት ጥራት ጉድለት፣ ለቅልጥፍና ችግር የተጋለጠ ስለሆነ የተጠቃሚውን ኅብረተሰብ ፍላጎት በሚፈልገው መልኩ ሊያረካ የሚችል አቅም መፍጠር እንዳልቻለ፣
- በአገሪቱ በርካታ የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ተቋማዊ የአገልግሎት መሻሻል እያታየ ባለበት በአሁኑ ወቅት የትራንስፖርት ዘርፍም ተመጋጋቢ ለውጥ ለማድረግ በርካታ ጅምር ሥራዎች እያከናወነ ቢሆንም፣ በአገልግሎት ሰጪውና በአመራሩ በሚታዩ በርካታ የአመለካከት ክፍተቶች ወደ ዘርፉ የሚገባ የኢንቨስትመንት መጠን ዝቅተኝነት ምክንያት የሚጠበቀውን ያህል ለውጥ ማምጣት አለመቻሉ በአግባቡ የተገለጸ ሲሆን በዚህ ሰነድ በተጨማሪ ሲብራራ፣
በሕዝብ ትራንስፖርት ማኅበራት አደረጃጀት በሚል ርዕስ ሥር
- ከተጠቃሚው ፍላጎት ጋር አብሮ የሚያድግ አቅርቦትና የአገልግሎት ጥራት ለመፍጠር የዘርፉን ሁለንተናዊ አቅም በማጎልበትና ተደራሽ በመሆን፣ አገሪቱ የምትጠብቀውንና የምትጠይቀውን የትራንስፖርት ፍላጎት መመለስ የሚያስችል አደረጃጀት አለመኖሩ፣
- አደረጃጀቱ ለሦስተኛ ወገን የተጋለጠ መሆኑን፣
- የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ኦፕሬተሮች ዘርፉን ለመለወጥ አደረጃጀታቸው አመቺ አለመሆኑን ሰነድ ሲገልጽ በተጨማሪ፣
በሕዝብ ትራንስፖርት መስጫ ቦታዎች በሚለው ርዕስ ሥር የዘርፉን ችግር በደንብ ሲገልጸው፣
- መናኸሪያዎቹ ደረጃቸውን ያልጠበቁና አስፈላጊውን አገልግሎት ማሟላት ያልቻሉ መሆናቸው፣
- ተጠቃሚው ለወከባና ለእንግልት የሚያጋልጡ የአሠራር ሥርዓት መኖሩን፣
- በቴክኖሎጂ ያልተደገፈ በመሆኑ ለአገልግሎት ጥራት ጉድለት ለቅልጥፍና ችግር የተጋለጡ መሆኑን ዘርዝሮ፣ በዚሁ ሰነድ ላይ ደግሞ
የአመለካከት ችግር በሚል ርዕስ ሥር
- በዘርፍ ዘለቄታዊ ዕድገትን ከማምጣት ይልቅ በአቋራጭ ትርፋማ ለመሆን የእርስ በርስ መጠላለፍ መኖሩን፣
- እንደ አንድ የሥራ ዘርፍ ቆጥሮ ከመያዝ ይልቅ በአማራጭ የሥራ ዘርፍ በመያዝ ሙሉ በሙሉ አቅም ወደ አገልግሎት ለመግባት ትኩረት አለመስጠት፣
- በዘርፉ አዋጭነት ላይ አመኔታ ማጣትና ያለመተማመን፣
- አገልግሎት ተኮር ሳይሆን ገቢ ተኮር መሆኑ፣
- የአገልጋይነት ሳይሆን የተገልጋይነት ስሜት መኖሩና በተጨማሪም፣
በፈጻሚው አካል በኩል
- የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት፣
- የጠባቂነት መንፈስ፣
- ራስን አለማብቃት፣
- ኪራይ ሰብሳቢነትን በቁርጠኝነት አለመታገል፣
- የግንዛቤ እጥረት መኖሩን፣
- የአቅም ውስንነት መኖሩን፣
- ራስን በማብቃት ክህሎትን በማዳበር ለውጥን ተግባራዊ ለማድረግ ያለው ቁርጠኝነትና ዝግጁነት አናሳ መሆኑን፣
- በአስፈጻሚውና በፈጻሚው መካከል የቅንጅታዊ አሠራር ችግሮች መኖራቸው ራሱ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በሰነዱ ላይ በስፋት ያስቀመጠውና መሬት ያለ (Surface) እውነት እንደሆነ ሲያጠቃልላቸው
በአጠቃላይ በዘርፉ በኩል የሚታዩ ደካማ ጎኖቹ በሚል ርዕስ ሥር ችግሩን፡-
- የተበጣጠሰ የትራንስፖርት ማኅበራት አደረጃጀት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ፣
- ዘርፉ በአግባቡ በወጥነት መመራት አለመቻሉ፣
- በዘርፉ በበቂ ሁኔታ የሠለጠነ የሰው ኃይል አለመኖሩ፣
- ዘርፉ በቴክኖሎጂ ያልተደገፈ መሆኑ፣
- አገልግሎቱ ደንበኛ ተኮር አለመሆኑ፣
- ተጠቃሚው በቂ መረጃ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል አሠራር አለመመቻቸቱ የሚታዩ ደካማ ጎኖች መሆናቸውን ነው፡፡
በአጠቃላይ ዘርፉ በብዙ ችግሮች የተወሳሰበ መሆኑ የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት በራሱ ባለሙያዎች አስጠንቶ ለባለድርሻ አካላት ያቀረበው ከነመፍትሔው የተቀመጠ ሰነድ መኖሩን የቡድን ጸሐፊዎች ዘንግተውት ይሆን? ወይስ ሰነዱ ለሕዝብ ዕይታ ስለማይቀርብ እውነታን በሐሰት ደፍጥጠን እንለፈው ከሚል በመነጨ ስሜት ተተብትበው ይሆን? አቶ ታደሰ ዓለሙን የሚተች ጹሑፍ ለመጻፍ የተገደዱት፣ በዚህም ረገድ ሌላም በርካታ የሰነድ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡
ማስረጃ ሦስት፡- የትራንስፖርት ሚኒስቴር ‹‹በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት ዙሪያ የተካሄደ ዳሰሳ›› በሚል ርዕስ የፖሊሲና የሕግ ጉዳዮች ዳሬክቶሬት መጋቢት 2005 ዓ.ም. ለባለድርሻ አካላት በቀረበው ሰነድ ላይ በዝርዝር እንደተቀመጠው፣
- የትራንስፖርት ማኅበራት ለክትትልና ለድጋፍ እጦት መጋለጥ፣
- የቁጥጥር ማነስና ኢፍትሐዊ የተሸከርካሪ የሥምሪት ምደባ፣
- ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ተሸከርካሪዎች ላይ የሚደረግ የቴክኒክ ቁጥጥር ችግሮች፣
- የአመራር ብቃትና የቡድን አሠራር ዕጦት፣
- የክትትልና ቁጥጥር ደካማ አፈጻጸም፣
- በመመርያዎችና ደንቦች አተገባበር ላይ ያሉ ችግሮች፣
- የትራንስፖርት ማኅበራት የአፈጻጸም ጉድለት፣
- የመናኸሪያ አገልግሎት አሰጣጥ ኋላቀርነት በተመለከተ በሚሉ ነጥቦች ላይ በዝርዝር የዘርፉን ጉድለቶች በተጨባጭ ማስረጃ በመተንተን ችግሩን ለመፍታት የመፍትሔ ሐሳቦችን በመጨመር፣ ግዮን ሆቴል ለባለድርሻ አካላት ያቀረቡት ሰነድ ጉልህ ማስረጃ ይሆናል፡፡ እነዚህ የማስተካከያ ነጥቦች ግን በባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት በኩል እንደ በጎ ግብዓት ሳይቆጠሩ እንዲያውም በችግሩ ገፍተውበት ይገኛሉ፡፡
ማስረጃ አራት፡- በአዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 20 ቀን 2007 ዓ.ም. በ74ኛ ዓመት ቁጥር 020 ላይ በመጀመሪያ ገጹ ‹‹የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች በባለድርሻ አካላት አለመናበብ እስከ መቼ ይጎዳሉ?›› በሚል ርዕስ ሥር በዝርዝር የዘርፉንና የተቋሙን ጉልህ ችግሮች በበሳል ጹሑፍ አስቀምጧል፡፡ ይህም በተማሪ መግቢያና መውጫ ሰዓት የሚፈጠረው የትራንስፖርት ችግር ምን ያህል ከዓመት ዓመት ተማሪውን የሚያሳስበውና የሚያስጨንቀው መሆኑን በጽሑፉ ገልጿል፡፡ ይኸውም መፍትሔ ሳይፈለግለት በየዓመቱ እየተደጋገመ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና ተገልጋዩን ኅብረተሰብ እየጎዳ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ ከቡድን ጸሐፊዎች እንደተገለጸው አቶ ታደሰ ዓለሙ ምንም ዓይነት ጭብጥ መረጃ እንደሌላቸው የሰሙትን ብቻ እንደጻፉ አድርገው ማቅረባቸው፣ ዘርፉ በተሻለ ጎዳና ላይ እንደሚገኝ አስመስለው ለማቅረብ የሞከሩትን ሐሳብ ከዚህ በላይ ዘርፉ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ በገሃድ የሚያሳይ ምን ዓይነት የማስረጃ ሰነድ ሊቀርብ ይችላል? አንባቢያን እውነቱን ይፍረዱ?
የቡድን ጸሐፊዎች ስለሠራተኞች ሥነ ምግባር ሲገልጹ ለሥነ ምግባር ጉድለቱ መንስዔ አገልጋዩ ብቻ ሳይሆን የተገልጋዩም አስተዋጽኦ እንዳለበት፣ ክቡር ደንበኛ የሆነውን ተገልጋይ ኅብረተሰብም ጭምር ሊወቅሱት ይሞክራሉ፡፡ በዘመናዊ የንግድ አሠራር ምንም አለ ምን ደንበኛ ሁሌም ትክክል ነው በሚል መርህ አገልግሎት ለመስጠት የተቸገሩና ትናንትም ዛሬም እንደሚያደርጉት ሁሉ ነገም በደንበኛው ላይ ጫና ለማሳደር ምን ያህል ፍላጎትና የኋላቀርነት አስተሳሰብ እንዳላቸው የሚያሳይ ገሃድ የወጣ ጽሑፍ ነው፡፡ የቡድን ጸሐፊዎች እንዳሉት ከሚሠሩ ይልቅ ብዙ ከሚያወራ ብዙ ስህተት እንደሚኖር፣ የሚሠራ ግን ስህተቱን አርሞ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እንዲጓዙ ልብ ሊሉት ይገባ ነበር፡፡ ‹‹ጧት ከቤትህ ስትወጣ ያደነቃፈህ ድንጋይ ማታ ወደ ቤት ስትመለስ ደግሞ ካደናቀፈህ እንቅፋቱ ድንጋዩ ሳይሆን አንተ ነህ›› የሚለውን ብሂል የቡድን ጸሐፊዎች አስተውለውት ይሆን?
ስለሕገወጥ የሥምሪት እንቅስቃሴ በተመለከተ የቡድን ጸሐፊዎቹ እንደሚሉት፣ ሕገወጥነትን ለመግታት ያልተቻለው ዋነኛው ምክንያት በሕገወጥነት የሚያደራጀውን ተዋናይ በቀላሉ ለመለየት አለመቻሉ መሆኑን ትክክለኛ ጽሑፍ አስነብበዋል፡፡ እውነት ነው ሕገወጥ ሥራን የሚሠሩት ዘርፉን ከሚመሩ አካላት የቅርብ ግንኙነት ያላቸው ተለጣፊ ጋሻ ጃግሬዎቻቸው በመሆናቸው፣ እንዴት እነዚህን አካላት አጋልጠው ይስጡ? ለማስቆምስ ምን ዓይነት ሞራል ይኖራቸዋል?
ከአዲስ አበባ – ጅጅጋ ያለውን የጉዞ መስመር ከቦሌ ሩዋንዳ ላይ ሕገወጥ መናኸሪያ መነሻ በማድረግ ለዓመታት ያህል በሕገወጥ መንገድ ከመናኸሪያ ውጪ በደረጃ 1 አገር አቋራጭ ተሽከርካሪ ከተተመነለት ታሪፍ በላይ አገልግሎት ሲሰጥ እየሰሙ፣ እያዩ ማስቆም ያልቻሉ የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ተቆርቋሪ የቡድን ጸሐፊዎች ይህንን ሀቅ እንዴት ማስተባበል ይችላሉ? በሁሉም መናኸሪያዎች ጀርባ በሕገወጥ መንገድ በየዕለቱ ሥምሪት ሲሰጥ እያዩ መለየት ተሳነን የሚሉ አካላትን ምን እንበላቸው? በመልካም አስተዳደርና በኪራይ ሰብሳቢነት እንነጋገር ከተባለ በአገር አቋራጭ ዘርፍ የተሠማሩ ባለሀብቶች ከጥቂት ማኅበራት በስተቀር የሠሩበትን የኮንትራት ሒሳብ በአግባቡ ለባለንብረቱ የሚከፍሉ ስንቶች ናቸው? ምንም ዓይነት ዕውቅና በሌለው ሕጋዊ ባልሆነ የአክስዮን ማኅበር ስም ደረሰኝ በማሠራት ገንዘብ ሰብስቦና በአክስዮን ስም የተሰበሰበው ገንዘብ የት እንደደረሰ እንኳን ግልጽ የሆነ መረጃ ያልተደራጀበት የማኅበር አመራር የለም ለማለት ነው?
የጥቂት ማኅበራት ውስጣዊ አደረጃጀታቸው፣ የሒሳብ አሠራራቸው፣ የሠራተኛ አቀጣጠራቸው፣ በትክክል ራሳቸው ባወጡት መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ተፈጻሚ የሚያደርጉ ማኅበራት እስኪ ይፈተሹ? ለህዳሴ ግድብ ተብሎ ከባለሀብቱ የተሰበሰበን ገንዘብ ለይቶ በራሱ አካውንት ከፍተው ማስቀመጥ ያልቻሉና እንደ ማኅበሩ የራሱ ገቢ አድርገው ለሥራ ማስኬጃ የተጠቀሙ ማኅበራት የሉም? ይህንንስ የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት እያወቀው የወሰደው ዕርምጃ ምንድነው? በደንብ የቡድን ጸሐፊዎች ሊገልጹ ያልቻሉት መራራ እውነት ነው! የትራንስፖርት ባለሥልጣን ደብዳቤ ለማኅበራቱ ከመጻፍ ውጪ በተግባር ይህንን ጥፋት የፈጸሙ ማኅበራትንም ሆነ ግለሰቦችን ተጠያቂና ገንዘቡን ለታለመለት ዓላማ እንዲመለስ አላደረጉም፡፡ ዛሬ መንግሥት ምንም የሌላቸውን ሥራ አጥ ወገኖች በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ እያደራጀ ባለሀብት እንዲሆኑ ባደረገበት ወቅት ትናንት ባለሀብት የነበሩ፣ ዛሬ ግን በትራንስፖርት ባለሥልጣን የአመራርና የአፈጻጸም ችግር ምክንያት ከ300 በላይ የሚሆኑ የአገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች መሥራት እየቻሉ እንዳይሠሩ ተከልክለው ቄራና ሱማሌ ተራ አካላቸው ተበታትኖ ለመለዋወጫ በዝቅተኛ ዋጋ ተሸጠው ባዶ እጃቸውን ቁጭ ያሉ ባለሀብቶች ጥቂቶች አይደሉም፡፡ የትራንስፖርት ባለሥልጣን እነዚህ ባለሀብቶች ከሥራ እንዳይወጡ ሌሎች አማራጮችን ፈልጎ (Exit strategy) ነድፎ ማሠራት ቢችልና በተለይ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር እንዲፈቱ ሁኔታዎች እንዲመቻችላቸው ትልቅ ሥራ ቢሠራ ኖሮ፣ ባለሀብቱም ዛሬ በችግር ላይ ባልተገኘና የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግርንም ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽ ባደረገ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የስንቱ ቤት ተበትኖ ስንቶቹ ባለሀብት የነበሩ ሥራ አጥ እንደሆኑ ቤቱ ይቁጠረው! በዚህ ጉዳይ ላይ ከባለድርሻ አካላት አውቶቡሶች ከሥራ ውጪ ከመሆናቸው በፊት ዕቅድ ወጥቶላቸው ቀለማቸውን ባለሀብቱ ቀይሮ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሰርቪስ አገልግሎት በተመጣጣኝ ክፍያ እንዲሰጡ እንዲደረግ ተደጋጋሚ ሐሳብና አስተያየት ቢቀርብም ምላሽ አልተገኘም፡፡ በዚህ ግድየለሽና ኃላፊነት በጎደለው አመራር ከፍተኛ የአገር ሀብት ለብክነት ከመዳረጉም ባሻገር፣ በርካታ ቤተሰብ ተበትኗል፡፡ ከዚህ በላይ የመልካም አስተዳደር ችግር ገላጭ ነገር ምን ይመጣ ይሆን፡፡ ማንኛውም አገልግሎት ሰጪ የሚወጣውና የሚወርደው አገልግሎት የሚሰጠውን የኅብረተሰብ ፍላጎት ለማማሏትና በተጓዳኝ ራሱን ተጠቃሚ ሆኖ ቤተሰቡን ለመርዳት፣ ከተቻለም የተሻለ ዕድገት ለማግኘት ነው፡፡ ነገር ግን በሕዝብ ማመላለሻ ዘርፍ ላይ አሁን ካለው የመለዋወጫ፣ የጎማና አስተዳደራዊ ወጪዎች አንፃር ታይቶ የታሪፍ ማስተካከያ እንዲደረግ ባለሀብቱ ቢጠይቅም፣ ለራሳቸው በሥልጣን መቆየት እንጂ የበላድርሻ አካሉን ችግር በአግባቡ ለመፍታት ፍላጎት በሌላቸው ጥቂት የትራንስፖርት ባለሥልጣን ኃላፊዎች ተፅዕኖ ታሪፍን ለማስተካከል ፍላጎት ባለማሳደራቸው፣ በዘርፉ የተሠማሩ ባለሀብቶች በኪሳራ እየሠሩ ባሉበት ሁኔታ ለአራት ዓመታት የታሪፍ ማሻሻያ አልተደረገም፡፡ በ2002 ዓ.ም. ዕቅዳቸው ጀምሮ በአራት ወሩ የታሪፍ ክለሳ እንደሚያደርጉ በወረቀት ቢያስቀምጡትም በተግባር ግን አልፈጸሙትም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለሴክተሩ የሚወጣው ኢንቨስትመንት በጣም በከፍተኛ ደረጃ ማደጉ እየታወቀ ምላሽ አለመሰጠቱ ዘርፉን የሚመሩት አካላት የባለድርሻ አካሉን ጥያቄ ያለመቀበል ችግር እንዳለባቸው የሚያመላክት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለድርሻ አካላቱ ከትራንስፖርት ባለሥልጣን አልፈው ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አቅርበው ቀደም ሲል ምላሽ ሳያገኙ ለረጅም ዓመታት የቆዩትን የዘርፉን ችግሮች፣ አሁን ሰሚ አግኝተው ክቡር የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ለታሪፍም ሆነ ለአጠቃላይ የሴክተሩ ችግሮች ትኩረት በመስጠት መፍትሔ እንዲያገኙ በየደረጃው የሚያደርጉትን ክትትልና ቁጥጥር የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አድናቆቱን ሊገልጽ ይወዳል፡፡ እነዚህ ችግሮችም ሙሉ በሙሉ ይፈታሉ የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ፡፡
አንድ እውነት መናገር ይቻላል፡፡ የሕዝብ ማመላለሻ ዘርፉን ብዙ ጊዜ የመሩ ተሿሚዎችም ሆነ ጥቂት የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ተቀጣሪ ሠራተኞች ብዙ ጊዜ ዘርፉን የመሩ፣ ነገር ግን ምንም ዓይነት ተጨባጭ ውጤት ወይም ለውጥ ያላመጡ በመድረክና በሪፖርታቸው ላይ ብቻ እኛ ይህንን አደረግን በማለት የሚደሰኩሩ ሲፈልጉ የሚሰጡ ሳይፈልጉ የሚነሱ በተቋሙ ለረጅም ጊዜ የቆዩ በመሆናቸው፣ መሥሪያ ቤቱን እንደ ግል ድርጅታቸው የሚያዩ የፈለጉትን ከሕግ ውጭ የሚጠቅሙ ያልፈለጉትን መመርያና ደንብ እየፈቀደም የሚጎዱ መሠረታዊ የሆኑትን የሥነ ምግባር መመርያዎች የማይከተሉ ሲሆኑ እውነቱ ሲገለጥ ግን ይህ ነው፡፡
- ኅብረተሰቡ ያልረካበት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑ፣
- የወረደ መናኸሪያ ይዘው መቆየታቸው፣
- ባለሀብቱ ብቁ ተወዳዳሪ አድርገው ያልመሩና ያላደራጁ መሆናቸው ነው፡፡
በጥቅሉ የቡድን ጸሐፊዎች እንደሚሉት ሳይሆን በዘርፉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መኖሩን ከማንም በላይ ምስክርነት የሚሰጠው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ይኼውም መስከረም 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀን በሸገር ሬድዮ ‹‹አንዳንድ ነገሮች›› በሚል ፕሮግራም ላይ የተሰጡ የሕዝብ አስተያየቶች ምስክሮች ናቸው፡፡ በዚህ በኩል በተለያዩ ሚዲያዎች የሚያቀርቡትን የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የመናኸሪያ ችግር፣ ወዘተ በየጊዜው ቅሬታና አቤቱታ እየቀረበ እንዴት በዘርፉ ችግር የለም? የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ሊወቀስ አይገባውም? ብለው የቡድን ጸሐፊዎች ምስክርነት ይሰጣሉ? ይህ የሚሳየው የቡድን ጸሐፊዎች ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ወይም ለወከላቸው ባለሀብትና አገልግሎት ለሚሰጡት የትራንስፖርት ተጠቃሚ ኅብረተሰብ መብት ከመቆርቆር ይልቅ፣ ለጥቂት ኃላፊዎች ተጠያቂ እንዳይሆኑ የቆሙ መሆኑ ነው፡፡
በሕዝብ ክምችት ሥምሪት ወቅት ያለውን የአሠራር ሒደት አቶ ታደሰ ዓለሙ በአግባቡ የገለጹት ሲሆን፣ የቡድን ጸሐፊዎች በመናኸሪያው በእውነት የሚታየውን የታሪፍ አገልግሎት አሰጣጥ ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ ለኅብረተሰቡ ያሰቡ በሚመስል ሁኔታ ለመጻፍ ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የመናኸሪያው ማኅበረሰብና ራሱ የትራንስፖርት ተጠቃሚው ኅብረተሰብ የሚያውቀውን እውነታ ግን በምሳሌ መልክ ለአንባቢ ግልጽ እንዲሆን ላቅርብ፡፡
ከአዲስ አበባ – ሆሳዕና በአገር አቋራጭ ከመደበኛ መስመር ውጪ በሚደረግ ጉዞ ተመላሽ ስለማይገኝ 50 በመቶ ባለሀብቱ ከስሮ 50 በመቶ ሕጉ በሚፈቅደው በገበያ መርህ መሠረት በ150 በመቶ ታሪፍ ብር 112.50 ሲሆን፣ ይህንን ታሪፍ ለመፍቀድ በቅድሚያ ከመናኸሪያ ውጪ በሕገወጥ መንገድ የሚጭኑት እስከ ብር 200.00 እያስከፈሉ መንገደኛውን ያጓጉዛሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ለኅብረተሰቡ ያሰቡ ይመስል የትራንስፖርት ባለሥልጣን ኃላፊዎች የትራንስፖርት ተገልጋዩን አቅም ባገናዘበ አኳኋን እንዲጓጓዝ አድርገናል የሚል ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ እንዲሉ ሕዝብ የሚያውቀውን እውነት ሊያስተባብሉ ይሞክራሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የትራንስፖርት ሚኒስቴር የፖሊሲና የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ባቀረበው የዳሰሳ ጥናት፣ በሕዝብ ክምችትና በበዓላት ወቅት እስከ 200 በመቶ ኅብረተሰቡ ከፍሎ በሕገወጦች እንደሚጓጓዝ በግልጽ ከኅብረተሰቡ ባገኘው መረጃ እውነታውን አስቀምጧል፡፡
ማንም የሚያውቀውን ለሕገወጦች ሊጠቅም የሚችል የአሠራር ሒደት እየተከተሉ በጽሑፋቸው ግን ይህንን ለማስተባበል መሞከራቸው እውነት የመናኸሪያው ኅብረተሰብና ባለሀብቱ አያውቀውም በሚል ነው? ወይስ አንባቢያንን ለማሳሳት? ግልጽ አይደለም?
በአጠቃላይ ስለትራንስፖርት ዘርፍ ችግሮች ከዚህ ጸሐፊ በበለጠ የትራንስፖርት ባለሥልጣን ሞደርናይዜሽን የጥናት ሰነድ፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን የመስከረም 19 እና 20 ቀን 2008 ዓ.ም. የዜና ዘገባ፣ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ቁጥር 020 ዕትም፣ ከሁሉም በላይ ዘርፉን በበላይነት የሚመራው የትራንስፖርት ሚኒስቴር የፖሊሲና የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ያቀረበው ጥናት ከበቂ በላይ የገለጹት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የቡድን ጸሐፊዎች ከላይ የተገለጹን የጥናት ሰነዶችን በእጃቸው የሚገኝና የዜና ዘገባውንም ያደመጡት በመሆኑ በሰጡት የማስተባበያ ጽሑፍ በእጅጉ ሊያፍሩበት ይገባል፡፡
በቡድን ጸሐፊዎች በሪፖርተር ጋዜጣ ጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. በወጣው ጽሑፍ ላይ እንደተገለጸው ቀደም ሲል በነበረው የደርግ ሥርዓት ይከፈል የነበረውን የአገልግሎት ኮሚሽን 12 በመቶ እንደነበር፣ አሁን ግን እንዲቀንስ በማድረግ ይህንን እንደ ትልቅ ለውጥ በማየት የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ያስገኘው ትልቅ ጥቅም እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በመሠረቱ ይህ ለውጥ ዛሬ አገሪቱን የሚመራው መንግሥት ያስገኘው አጠቃላይ የአገርና የሕዝብ ጥቅም እንጂ፣ ተቋማዊ ለውጥ ተደርጎ እንደ ትልቅ ምስክርነት ለወሰድ አይገባም፡፡ በአንፃሩ ግን የቡድን ጸሐፊዎች ያልገለጹትና ራሳቸውን የሚነካ እውነታ ግን ዛሬ ላይ የሚከፈለው አነስተኛ የአገልግሎት ክፍያ ጥቂት የማኅበራት ኃላፊ ተጠቃሚ አመራሮች፣ በሕገወጥ መንገድ ሲጠቀሙበትና እንደ ግል ኩባንያቸው እንደፈለጉ ሲያዙበት የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት የሚመለከተው የሥራ ክፍል እያወቀ በሕግ የተሰጠን የመቆጣጠር ሥልጣን በመተው፣ ሕገወጦችን ሲደግፉ ይታያል፡፡ አስረጂ የሚሆነው በሕግ ወይም በመመርያ የፈረሱ ማኅበራትን ገንዘብና ንብረት በፍትሐ ብሔር ሕግ መሠረት ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ መሆን ሲገባው፣ ይህንን ተከታትሎ ተፈጻሚ ሳያደርግ የግለሰቦች መጠቀሚያ እንዲሆን መተባበሩ የቡድን ጸሐፊዎችን ይህንን ለማስተባባል መሞከራቸው ‹‹ከባለቤቱ ያወቀ ምንድነው እንዲሉ››፣ በጥቅም ምን ያህል የተሳሰሩ መሆናቸውን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው፡፡
በመጨረሻም ለማንሳት የምፈልገው ሀቅ ቢኖር ከአቶ ታደሰና ከቡድን ጸሐፊዎቹ የቀረበውን ጽሑፍ እውነተኝነት ለማጣራትና አንባቢያንም ግራ እንዳይጋቡ የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያዎች መንግሥት በሰጣቸው ትልቅ ኃላፊነት መሠረት፣ የምርመራ ዘገባ አድርገው እውነቱን አፍረጥርጠው ለሕዝቡና ለመንግሥት ሊያሳውቁ ይገባል፡፡ ዘርፉን የሚመራውና ሌሎች የሚመለከታቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አሁን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ባለበት፣ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን በቁርጠኝነት ለመቅረፍና የትራንስፖርት ሴክተሩን ለመታደግና ለማዘመን የችግሮቹን መንስዔና ተጠያቂ የሆኑትን አካላት በሚገባ በመለየትና ተጠያቂ በማድረግ ዘርፉ ወደ ትክክለኛ የአገልግሎት አሰጣጥ ምህዋር እንዲገባ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አምናለሁ፡፡ ይህም እንቅስቃሴ የተሻለ ውጤት እንደሚያሳይ ክቡር የትራንስፖርት ሚኒስትሩ የጀመሩት ሒደት አመላካች እውነት ነው፡፡
በመጨረሻም የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በጽሑፉ ላይ የጠቀሳቸውን የሰነድ ማስረጃም ሆነ ሌሎች በርከት ያሉ ማስረጃዎች ለሚዲያ ክፍሉም ሆነ ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ ፈቃደኛ መሆኔን እየገለጽኩ የተጀመረውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ ሁሉም ኅብረተሰብ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል በማለት ጽሑፌን አጠቃልላለሁ፡፡ ቸር እንሰንብት!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡