Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መስማትስ መርጦ ነው!

እነሆ መንገድ። ከስታዲየም ወደ ቦሌ ድልድይ ልንጓዝ ነው። ይቀሰቅሰናል፣ የጎዳናው ወኔ የመንገዱ ፋኖ። መጓዝ ወዲያ ማዶ መራቅ የትናየት። አንድም ለመታወስ አንድም ለመረሳት፣ አንድም ለመወደድ አንድም ለመጠላት። ‹‹ሾፌር አስነሳው እንጂ ሞተሩን›› ይላል እንደ ጩልሌ ዓይኖቹ እዚህም እዚያም እየቃበዙ ጋቢና የተቀመጠ ሾፌሩን ዕረፍት የሚነሳ ተሳፋሪ። ‹‹አልሞላም እኮ! አንተ አትጠራም? ሞት ይጥራህና…›› ሾፌሩ ወያላው ላይ አንባረቀ። ወያላው ሞትም ሕይወትም አልጠሩትም። መሀል ላይ ነው። መሀል መንገድ። ግራ እጁ ላይ ያሰራትን አንፀባራቂ ‹ራዶ› ሰዓት ይነካካል። ‹‹አንተን እኮ ነው?›› ሾፌሩ ተተኮሰ። በረገገና ሰዓቱን መነካካቱን ትቶ መጮህ ጀመረ። ‹‹ምናለበት እስከዚያ ብታስነሳው?›› ችክ ማለት ይወዳል አንዳንዱ ሰው። ‹‹ወንድሜ ነዳጁስ? በውኃ አይሠራም እኮ?›› ሾፌሩ ከፊል ትህትና ከፊል አሽሙር ቀላቅሏል። ‹‹ጃንቦ ጄት አደረግከው እንዴ?›› ሆዱን ይዞ ይስቃል ጋቢናውና አካባቢውን በጩኸቱና በቀዥቃዣ ዓይኖቹ የተቆጣጠረው ተሳፋሪ።

‹‹አንዳንዱ ሰው ያለቦታው ሲገኝ ግን አይገርምም? ምናለበት ሰውነቱን ትቶ ‹ራዳር› ቢሆን ይኼ ሰውዬ?›› ይለኛል ቀጠን ረዘም ያለ ወጣት አጠገቤ እየተቀመጠ። ‹‹ . . . ደግሞ በውኃስ ቢሆን? ያው አይደለም እንዴ? የውኃና የነዳጅ ሠልፍ የሚለየው በምን እንደሆነ ታውቃለህ? ነዳጅ ማደያ መኪና ይዘህ ትሠለፋለህ። ቧንቧ ተራ ደግሞ ጀሪካን ይዘህ ትሠለፋለህ። እባክህ ያው ነው። እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ ብሎ ምን እንደነበረ ታውቃለህ? ቆርጠው አውጥተውት ነው ይባላል። የምሬን ነው! ‹እግዚአብሔር ሰማይና ምድር ፈጠረ› ብሎ ‹በኢትዮጵያም ምድር የፈጠረው ነገር ሁሉ በሠልፍ እንዲገኝ አደረገ› የሚል ነበረበት። ክብር ምሥጋና ለእሱ!›› ያለማቋረጥ ያነበንባል። ‹ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም በማነብነብም ጭምር እንጂ› የሚልም ነበረ እንዳይለን እንጂ እንደፈቀደው። መርጦ መስማት ነው ጎበዝ!

ጉዟችን ተጀምሯል። ሾፌራችን ፊት ነስቶ ዝም እንደማስባል፣ ‹‹ጃንቦ ጄት እንዴት ያለ ነው?›› እያለ ያን አፈ ነበልባል ያስቀድድብናል። ‹‹ጃንቦ ጄት አታውቅም? ‹ኦ ማይ ጋድ!› እውነትም የትምህርት ጥራት ወርዷል። ኢሕአዴግ ግን ምን እንደሚሠራ ይታወቀዋል?›› ሲል ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠች ወጣት፣ ‹‹የባሰ አታምጣ ስንለው አይሰማም እንዴ?›› ብላ ከጎኗ የተቀመጠው ጎልማሳ ላይ አፈጠጠችበት። ‹‹ማን?›› ጎልማሳው ግራ ተጋብቷል። ‹‹ተወው ግድ የለም! አንድ አስመጪና ላኪ አለ…›› ብላ ታጠፈችበት። ‹‹ዌል ጃንቦ ጄት ምን መሰለህ? . . .›› ‹ጃንቦ! ጃንቦ!› ሲል ሰውዬው መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ ወጣቶች ወያላውን ጠሩት። ምስኪኑ ወያላ ሐሳቡ ከሥራው ርቆ ያለው የእጁ ሰዓት ላይ ነው። አስግጎ ‹‹አቤት?›› ሲላቸው፣ ‹‹እስኪ ቀስ ብለሽ አጣሪ? ሰውዬው ዕድሜውን ድራፍት ቤት ነው ዩኒቨርስቲ የጨረሰው?›› አለ አንደኛው። ወያላው እንደተምታታበት ፊቱን አዞረባቸው።

መሀላቸው የተሰየሙ አዛውንት ፈገግ ብለዋል። ሦስተኛው ረድፍ ላይ ጥቁር የለበሰች ወይዘሮ አርፎ አልቀመጥ ያላትን ብላቴና ልጇን እየገሰፀች፣ ‹‹ዘንድሮ ድራፍት ቤት መጨረስና ዩኒቨርሲቲ መመረቅ ይነጣጠላል እንዴ? በየቀኑ ፓርቲ ቢደግሱ የማይወጣላቸው ሆነዋል የዛሬ ልጆች…›› እርግማን ቢጤ አጉተመተመች። አዛውንቱ ምክር ብጤ ሲሰጧት ጆሯችን ስለ ጃንቦ ጄት ወደሚሰጠው ‹ሌክቸር› ተመለሰ። ‹‹ . . . ጃንቦ ጄት ገና ስታስነሳው 4,000 ጋሎን ነዳጅ ምጥጥ ነው የሚያደርገው። ፉት ጭልጥ ያደርገዋል ታውቃለህ? እሱን ‹ፕላን› ሲያደርጉ የፈጁት የወረቀት ክብደት ከአውሮፕላኑ ክብደት ይበልጣል እኮ። ኢማጅን!›› ይላል አጭሩን ሾፌር ቁልቁል እያየ። ‹‹አሁን ይኼ ይገርማል? ዓባይን ለመገደብ እያሰብን የነጎዱት ዘመናት ‹ሴቭ› ቢደረጉ ፓስፊክን አይገድቡም?›› የሚለኝ ጎኔ የተቀመጠው ወጣት ነው። ‹ዕድሜ ግድብ ቢሆን ውኃ ዘንድ ምን አስኬደህ? ታሪካዊ ስህተቶቻችንን ብቻ ገድቦ ከትውስታችን ቢያጠፋልን አይበቃም ነበር?› ልለው አልኩና ምን አነጋገረኝ ብዬ ተውኩት። ነገር ቢረዝም ግድብ ይሆናል እንዴ?

ወያላው ሒሳብ መቀበል ጀመረ። ከጋቢና አንስቶ መጨረሻ ወንበር ወደ ተቀመጡት ወጣቶች እስኪደርስ ፀጥታ ታክሲያቺን ውስጥ ሰፍፎ ነበር። የወያላውም ሰዓት ያጥበረብር ነበር። ‹‹ፓ! ‹ራዶ› ሰዓት አስረህ ነው ወያላነት የምትሠራው? የኢኮኖሚ ዕድገት ይሏችኋል ይኼ ነው፤› አለ መስኮቱን ታኮ ተጣቦ የተቀመጠ ባርኔጣ የደፋ ወጣት። ‹‹ምን ታደርገዋለህ? አንዱ ሲንቀዠቀዥ አውልቆ ጥሎት ሄደና አነሳሁት። ግን አልሠራ ብሎ ያለፋኛል፤›› ወያላው በንፅህና የልቡን ያወራል። ‹‹አይዞህ ያንተ ሰዓት ብቻ አይደለም የቆመው። የብዙዎች ዕድሜና ሰዓት አይሠራም›› አዛውንቱ ናቸው መሀል ገብተው የሚቀኙት። ‹‹ሰው ሞባይል፣ ቁልፍ፣ ቦርሳ ይጥላል እንጂ እንዴት የእጁን ሰዓት ታክሲ ውስጥ ጥሎ ይወርዳል? የማይመስል ነገር አሉ፤›› ከአዛውንቱ በስተግራ የተሰየመች ጥርሰ ፍንጭት አስተያየት ሰጠች። ‹‹ሰው ቀን ሲጥለው እንኳን የእጁን ሰዓት ራሱን ይጥል የለም ወይ? እንዴት ያለ ነገር ነው እንግባባ እንጂ፤›› አዛውንቱ ሊያቃኗት ይደክማሉ።

ከእሷ በስተግራ ያለው ደግሞ ከአጀንዳ ውጪ፣ ‹‹ታክሲ ውስጥ የወደቀ ዕቃ ባለቤት እንደሌለው ተቆጥሮ ይወረሳል የሚል ማስታወሻ ተጽፎ ሊለጠፍልን ይገባል። አለበለዚያ እኮ ስናምናቸው የጣሉንን እያሰብን ጨርቃችንን ጥለን የምናብደው ታክሲ ውስጥ መሆኑ የማይቀር ነው፤ ይላል። ወዲያ ደግሞ ባለባርኔጣው፣ ‹‹ሥልጣን ብይዝ መጀመሪያ የማቋቁመው የሰዓት ሚኒስቴር ነው፤›› እያለ ይቀስቅሳል። ‹‹ምን ልታደርግ?›› አለች ባለፍንጭቷ በመገረም እያየችው። ‹‹የሚሠሩ ሰዓቶችን በሙሉ ሰብስቤ ለማስቆም ነዋ!›› ብሎ ሲል ተሳፋሪዎች ተንጫጩ። ‹‹ልማቱስ? የተጀመረው ሳያልቅ? ያሰብነው ሳይሳካ?›› ብላ ወይዘሮዋ ስትቆጣ፣ ‹‹የቆመ ሰዓት በቀን ቢያንስ ሁለቴ እውነት ይናገራል። ዕድሜ ልክ በተዛባ አቆጣጠር፣ ሙስና፣ አድር ባይነት፣ ማስመሰል እየተጫወቱብን ከመኖር በደቂቃ ዕድሜ ሀቅን ተሳልሞ ማለፍ አይሻለም?›› እያላት ባርኔጣውን አስተካከለ፡፡ ‹እንኳንም ሥልጣን አልኖረህ› አልነው በልባችን። ሠርተንና ቆጥረን አልደርስበት ብንል ደግሞ ብለን ብለን ጊዜን የሚያቆምልን ሚኒስቲር መሥሪያ ቤት ስንመኝ አንገርምም? ወይ ሐበሻ!

ጉዟችን ቀጥሏል። ወይዘሮዋ ከአዛውንቱ ጋር ተግባብታ ወግ ትሰልቃለች። ‹‹ታዲያ ደህና ሰንብተው ምን አገኛቸው?›› አዛውንቱ  መረጃ ተጠምተዋል። ‹‹ደህና ነበሩ አሉ። ማልደው ተነስተው በሉ ቁርስ አቅርቡልኝ፣ የመድኃኒት ሰዓቴ ደርሷል አሉ ነው የሚሉት። ለካ መድኃኒቱ አልቋል፤›› ወይዘሮዋ ሳግ እየተናነቀ ያቋርጣታል። ‹‹እሺ?›› አዛውንቱ ያረሳሳሉ። ‹‹ከዚያማ ልጃቸው ዘንድ ቢደወል ቢደወል እንዴት ትገኝ? ወርቅ የሆነች ልጅ አለቻቸው። ልጅ መቼም አንዴ ነፍስ ካወቀ በኋላ ለቤተሰቡ የማይሆነው የለም። ሲደወልላት ‹የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም› ነው መልሱ። እንዲያው በእንዲህ ያለ ሰዓት አለመገኘት ካለመፈጠር እኩል ሆነ እንጂ ‹የደወሉላቸው ደንበኛ አልተፈጠሩም› የሚል አለመቀረፁም አንድ ነገር ነው፤›› ብላ ስታበቃ ወይዘሮዋ አፍንጫዋን አስጓራችው። ይኼኔ ብላቴናው፣ ‹‹እማዬ ሞባይል አትገዢልኝም ግን?›› አሳቻ ሰዓት መርጦ መጠየቁ ነው። ‹‹የለም ጥሩንባ ይሻልሃል። መስሎን ነው እኛም እንጂ ጥሩንባ ምን አለን? ደህና ሲያሰማማን ሲያቀራርበን ነው የኖረው። ጥሩንባ አገልግሎት የማይሰጥበት ክልል የለም፤›› ብላ ከማይገባው ምፀት ጋር ከቦርሳዋ አውጥታ ፊሽካ ሰጠችው። ነገ የፊሽካ ገበያ ደራ ሲባል ብትሰሙ ታዲያ የእኛ ታክሲ ጉድ ነው። ቴሌ መቼም በካርድ የሚሠራ ፊሽካ መሥራት አያስብም አይደል? እስኪ ከፓሪስ ሲመለስ እንጠይቀዋለን!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። አዛውንቱ በአንዱ ጥግ ያወጋሉ። ወጣቶች ልብ ብለው ያደምጣሉ። ‹‹አንድ ሰውዬ በግ ሊገዛ ገበያ ወጣ፤›› ያቋርጣቸዋል ባርኔጣ የደፋው ወጣት። ‹‹መቼም በዛሬ ገበያ ባልሆነ?›› ስላቸው፣ ‹‹ቆይ ትደርስበታለህ። ምናለበት ለነገር ከምትቸኩሉ ጨዋታ ብታስጨርሱ?›› አዛውንቱ ወሬያቸውን ስላቁዋረጡዋቸው ደህና እንዳልተግባቡዋቸው  ወጣቶቹን ማማረር ጀመሩ። አጠገቤ የተቀመጠው ላጤ፣ ‹‹መጨረስ ምንድነው? ያስጨረሰንስ ማን ነው? የጨረሰን እንጂ የጨረሰልንስ አለ እንዴ?›› ሲለኝ ለካ ሰምተውታል። ‹‹እሱንስ ስታጨርሰኝ ታገኘው መስሎኝ? የልጅ ነገር አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ አሉ፤›› ተረቱ አዛውንቱ። ‹‹ተቀይሯል አባት። ለዛሬዎቹ አይሠራም፤›› አለቻቸው ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመችው ሴት። ‹‹እኮ ምን ተተረተባቸው?›› አዛውንቱ ሳያስቡት መስመራቸውን ሳቱ። ‹‹እነማን ላይ?›› ወይዘሮዋ ጠየቀች። ‹‹ስለእነማን ነው የምናወራው? ስለዛሬ ልጆች ነዋ፤›› ቁጣ ቁጣ አላቸው። ወይዘሮዋ ‹‹ዛሬ ደግሞ ምን ልጅ አለ? ገና ሳይወለዱ እየሸበቱ፤›› ማባዘት ወደፈለገችው ነገር ስትንደረደር አዛውንቱ ‹‹በይ ተይው›› ብለው ወደ በግ ገበያቸው ተመለሱ።

‹‹እና ምን እያልኳችሁ ነበር?  . . . አዎ፣ በግ ሊገዛ ገበያ ሄደ። አንዱን የሰባ ያለተለተ በግ አይቶ ወደ ባለበጉ ጠጋ አለና ‹ስንት ነው?› አለው። ‹60 ብር› ሲለው ነጋዴው፣ ‹60 ብር? በ20 ብር አህያ አልገዛም እንዴ?› እያለ ተነጫነጨበት። ታዲያ በግ ነጋዴው ምን አለው መሰላችሁ? ‹የሚጣፍጥህን አንተ ታውቃለህ› ጥልቅ ዝምታ ሰፈነ። ወያላው ‹አማሌሌሌሌን› ያፏጫል። ወጣቶቹ አዛውንቱ ያመጡዋት ምሳሌ አንድምታ ሰፍቶባቸው ያወጣሉ ያወርዳሉ። ወይዘሮዋ አንዴ የሟቹን ስም እያነሳች፣ አንዴ ረብሸኛ ልጇን አተኩራ እያየች ታገነግናለች። መውረጃችን ደርሶ ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን ሲከፍተው አዛውንቱ ወደ ወጣቶቹ ዞረው፣ ‹‹የዛሬን አያርገውና ይህቺ አገር ስንት ባለቅኔ፣ ስንት ነገር ፈቺ፣ ተፍጥሮን መርማሪ እንዳላመጠች ይህቺ ምሳሌ ቋጥኝ ትሁንባችሁ?›› ብለው እያዘኑ ተነሱ። ‹‹ብቻ ጊዜው አጭበርባሪ ነው። የትኛዋም አገር የወጣቶች ናት። ቢያጣምሙዋትም ቢያቀኑዋትም ኃይሉ አላቸው። ዋጋ መክፈል እየፈራችሁ ርካሽ ነገር አትምረጡ አደራ። ኤድያ የእኔ ነገር። ለካ ጊዜው የዴሞክራሲ ነው። የሚጣፍጣችሁን እናንተ ታውቀላችሁ። ብቻ ብቻ . . .›› እያሉ ወርደው በእግራቸው ብዙ ተጓዙ። ‹መራጭና አስመራጭ› መሆን ሲቸግር እንዲህ ነው ለካ። አንዳንዴ እኮ አሰስ ገሰሱን ከመስማት እንዲህ ዓይነቱን መርጦ መስማት አይሻልም ትላላችሁ? መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት