የጀርመን አፍሪካ የንግድ ማኅበርና የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሁለቱን አገሮች ንግድና ኢንዱስትሪ ለማስተሳሰር ያስችላል የተባለውን የመግባቢያ ሰነድ ሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ተፈራረሙ፡፡ በመጠጥ ኢንዱስትሪ፣ በእርሻ፣ በእንስሳት መኖ፣ በዱቄት ምርትና በሌሎችም ዘርፎች ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው የጀርመን ኩባንያዎችም ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር የንግድ ግንኙነት ለመፍጠር ተነጋግረዋል፡፡
ከሳምንት በፊት 20 ኩባንያዎች ይዞ አዲስ አበባ የገባው የጀርመን ልዑክ፣ ከኢትዮጵያ የንግድ ተቋማት ጋርም ተወያይቶና ግንኙነት መሥርቶ ነበር፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ስንመጣ የመጀመርያ ጊዜያችን ነው፡፡ በኢትዮጵያ መሥራት የሚፈልጉ ኩባንያዎችንም አምጥተናል፤›› ያሉት ጁዲዝ ሆፍማን የጀርመን-አፍሪካ የንግድ ማኅበር ኃላፊ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ለመሥራት ፍላጎት ካሳዩ የጀርመን ኩባንያዎች መካከል እ.ኤ.አ. በ1960 የተቋቋመው ብሩክነር ማሽንቧ የተሰኘው የፕላስቲክ ማሸጊያ ጥሬ ዕቃዎችን የሚያመርተው ኩባንያ ይገኝበታል፡፡
ጀርመን ሲድ አልያንስ የተባለው ሌላው ፍላጎት ያሳየ ኩባንያ ሲሆን፣ በቅባት እህሎች፣ በድንች፣ በበቆሎና በሱፍ ምርቶች ይታወቃል፡፡ ዓመታዊ ሽያጩ አሥር ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን፣ በእርሻ ሥራ ከተሰማሩ ተቋማት፣ ከመጠጥ ኢንዱስትሪዎችና ጥናትና ምርምር ከሚያደርጉ አገር በቀል ተቋማት ጋር አብሮ መሥራት እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ እንዳሉት ስምምነቱ የሁለቱን አገሮች የንግድ ትስስር ያጠናክራል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ጥቂት የማይባሉ የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2008 እስከ 2014 ባለው ጊዜ ውስጥም 344 የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለመሥራት ፈቃድ አግኝተዋል፡፡ በእርሻ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በሆቴል፣ በግንባታ፣ በሪል ስቴትና በሌሎችም ዘርፎች ፈቃድ ከወሰዱት ውስጥ ሥራ የጀመሩት ግን ሰማንያ ስምንቱ ብቻ ናቸው፡፡
የተቀሩት ወደ ሥራ ያልገቡበት ምክንያት በአገር ውስጥ ካለው የአሠራር ችግር ጋር በተያያዘ መሆኑን የገለጹት ጁዲዝ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ኢንቨስት የሚያደርጉ የጀርመን ኩባንያዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ ጥቂት የማይባሉት ፈቃድ ካገኙ በኋላ ከቀረጥ ጋር በተያያዘ እንዲሁም በተንዛዛ አሠራርና ቢሮክራሲ ምክንያት ሁሉም መሥራት አልቻሉም፡፡ በሌላ በኩል የኃይል መቆራረጥ፣ መሬት የማግኘት ችግርና ሌሎችም እንዳይሠሩ ማነቆ እንደሚሆኑ ሰምቻለሁ፤›› ብለዋል፡፡