Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አልሚዎች ትኩረት የነፈጉት የአትክልትና ፍራፍሬ ሀብት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዶ/ር ኢዶሳ ኢቲሳ ላለፉት 23 ዓመት በአቮካዶ ላይ ምርምር ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡ በሌሎች የሞቃት ፍራፍሬ በሚባሉ ዝርያዎች ላይ እንደ አናናስ፣ ሙዝና ማንጎ የመሳሰሉ ፍራፍሬዎች ላይ ጠለቅ ያለ ጥናት ማድረጋቻውም ይነገርላቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የሞቃት ፍራፍሬና አትክልት ምርምር ብሔራዊ አስተባባሪ ናቸው፡፡

ከሁለት አሥርት በፊት አቮካዶ በኢትዮጵያ ብዙም ጥቅም ላይ እንደማይውል የሚገልጹት ተመራማሪው፣ በአሁኑ ወቅት የአቮካዶ ምርት በስፋት ከመታወቅ አልፎ ጥሩ ተቀባይነት እንዳለው ይገልጻሉ፡፡

አቮካዶ በአገሪቱ ከቆላ እስከ ደጋ ባለው አካባቢ እየተመረተ ሲሆን፣ ከአገሪቱ በምርቱ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም አሥረኛ ለመሆን እንደበቃችም ያክላሉ፡፡ ነገር ግን ከአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ አገሪቱ በአግባቡ እየተጠቀመች እንዳልሆነ ዶ/ር ኢዶሳ ገልጸዋል፡፡

‹‹በአገራችን ዓመቱን ሙሉ አቮካዶ ማምረት እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአቮካዶ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ሰፊ እርሻ የለም፡፡ ግለሰቦች በመኖሪያ አካባቢያቸው አምስትና ስድስት ዛፍ እየተከሉ ያመርቱታል፡፡ ነገር ግን በአግባቡ ስለማይንከባከቡት ምርታማ ሊሆን በሚያስችለው አቅም አይመረትም፤›› ብለዋል፡፡

አገሪቱ ስላሏት የአቮካዶ ዝርያዎች፣ የምርቱ ተስማሚነትና በአግባቡ ስለመመረቱ ነጥቦች ከሪፖርተር ለተነሳላቸው ጥያቄ የዶ/ር ኢዶሳ በእነዚህ ሁሉ ደካማ ውጤት እንደሚታይ ያብራራሉ፡፡

‹‹አቮካዶ በተፈጥሮው የተለያየ ባህሪይ አለው፡፡ ለምሳሌ ከአንድ ዛፍ 1,000 የአቮካዶ ዘር ቢዘራ የተለያየ ዓይነት ምርት ነው የሚሰጠው፡፡ ነገር ግን በምርጥ ዘር ቢዘራ እጅግ ብዛትና ጥራት ያለው አቮካዶ ይወጣዋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ለምግብነት ከሚውለው ባሻገር ለመዋቢያነት የሚያገለግሉ ቅባቶችና ዘይቶችን ጨምሮ ሌሎችም ምርቶችን ለማምረት የሚያስችል ጥቅሞች ያሉት ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን ገና ብዙ አልተሠራበትም ሲሉ ተመራማሪው ይስማማሉ፡፡

‹‹በዓለም አቀፍ ገበያም ፍላጎቱ አለ፡፡ ወደዚህ ምርምር ማዕከል እንኳ ከተለያዩ አገሮች ስልክ እየደወሉ የብዙ ሺሕ ቶን ሙዝ፣ አቮካዶና አናናስ እንደሚፈልጉ ይገልጹልናል፡፡ ነገር ግን በአገራችን ያንን ያህል የሚያመርት እርሻ ስለሌለን ማግኘት የምንችለውን ያህል የውጭ ምንዛሪ እያገኘን አይደለም፤›› ዶ/ር ኢዶሳ በቁጭት ከሚገልጹት ፋይዳ መካከል ይጠቀሳል፡፡

የግሉ ዘርፍም ለምን ወደዚህ ሥራ መግባት እንዳልቻለ ግራ እንደሚገባቸው ገልጸው፣ እርግጥ ዘርፉ ውጤት እስኪያገኝ ጊዜ ሊፈጅ እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

አቮካዶ ምርት ለመስጠት እስከ ሦስት ዓመት ይፈጅበታል፡፡ የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት ቢሆንም አንዴ ለምርት ከደረሰ በኋላ ግን ከማንኛውም ሰብል በተሻለ በዓመት ለአራት ጊዜ ምርት መሰብሰብ ይቻላል የሚሉት ተመራማሪው፣ ከዚህ በተጨማሪም ከወይን እርሻ በዓመት አራት ጊዜ ምርት ማንሳት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

ስለ አናናስ  ምርት ሲያብራሩም፣ አገሪቱ በዓለም ላይ ከሚገኙ ምርጥ የአናናስ ዝርያዎች መካከል የተሻሉት እንደሚገኙባትና በሙዝ ዝርያም እንዲሁ በዓይነቱም ሆነ በጥራቱ ተወዳዳሪነት እንደሌላት ሲያብራሩ በቁጭት ነው፡፡

አንድ የሙዝ ግንድ ከ46 እስከ 60 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሙዝ ያመርታል፡፡ በዓመትም አራትና አምስት ጊዜ ያመርታል፤›› በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የምርምር ማዕከሉ በቂ አቅም ቢኖረውም ለዘርፉ ፍላጎት ኖሮት ወደ ማዕከሉ በመምጣት ምክር የሚጠይቅ የግል ባለሀብት እንደሌለ የገለጹት ዶ/ር ኢዶሳ፣ ማዕከሉ ለገበሬዎች ዝርያዎችን በማቅረብና በመስጠት የአመራረት አተገባበሩን በማሳየት እያገዘ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ግሎባል ጋፕ በተባለው የእንግሊዝ ተቋም በኩል ኢትዮጵያ ፍራፍሬ ወደ ውጭ ገቢያ እንድትልክ ሙከራ ተደርጓል፡፡ ከዚህም በላይ የአውሮፓን ጨምሮ ከመቶ በላይ አገሮች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ሊልኩ እንደሚችሉ ዶ/ር ኢዶሳ ሲያስረዱ፣ በግሎባል ጋፕ በኩል በኢትዮጵያ የሚመረተው ጥራቱን የጠበቀና ከማንኛውም ኬሚካል የፀዳ በመሆኑ እስካሁን ገበሬዎች ብቻ ሲያመርቱት የቆየው አሠራር ብቻውን ፋይዳ እንደማይኖረውና ማኅበራትንና የኅብረት ሥራ ዩኒየኖችን ማጠናከር፣ በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ በየትኛውም የአየር ፀባይና የመሬት አቀማመጥ የፍራፍሬ ምርት በስፋት መመረት ይችላል፡፡ ከአራት በማይበልጥ ጥቂት ዓመታት ከአገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለተለያዩ አገሮች የተትረፈረፈ ምርት ማቅረብ ይቻላል፡፡ ከዓረብ አገሮች እስከ አውሮፓ እንዲሁም እስከ እስያ ማዳረስ የሚችል አቅም አለን፡፡ ነገር ግን የአገራችን ፍራፍሬ አምራቾች እጅግ ውሱን በመሆናቸው ዘርፉ ምንም እንዳልተሠራበት መናገር ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

በገበያ በኩል ያለውን ፍላጎት ትኩረት ያደረጉበት ዶ/ር ኢዶሳ፣ እያመረቱ ባሉት አርሶ አደሮች የሚመረተው ምርት ለመቆረጥ ሳይደርስ በማሳ ላይ ተሸጦ እንደሚያልቅ በዋቢነት አሳይተዋል፡፡

‹‹እኛ  በቅርበት የምንከታተላቸው አርሶ አደሮች ፓፓያ ሲደርስ ከአንድ ሔክታር በሳምንት ሦስት ጊዜ አይሱዙ ተጭኖ ይወጣል፡፡ ከዚህም እስከ 110 ሺሕ ብር ሲያገኙ ይታያል፤›› የሚሉት ዶ/ር ኢዶሳ፣ አንድ ኪሎ ወይን ከ200 ብር ያላነሰ ዋጋ እያወጣ መሆኑም የፍራፍሬ ዘርፍ ምን ያህል አዋጭ እንደሆነ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

‹‹ሙዝና አቮካዶ በማምረት በቀላሉ በከፍተኛ ገቢ ማግኘት እየተቻለ ነው የሚሉት ተመራማሪው፣ ‹‹የፍራፍሬ ዘር አባዝቶ የሚያከፋፍል ከየት ይገኛል? የተገኘውን ዘርስ ማን ተረክቦ ያምርት? የሚሉ ጥያቄዎች ግን ተመራማሪው የሚያቀርቧቸው ናቸው፡፡ የምርምር ማዕከሉ ዘርን የማሻሻል ኃላፊነት ብቻ ያለበት መሆኑን በማስታወስ በመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ብቻ የሙዝ፣ የአቮካዶ፣ የማንጎና የወይን ዝርያዎችን ጨምሮ ከ30 በላይ ዝርያዎች ተሻሽለው እንደወጡም ገልጸዋል፡፡

ዘር በማከፋፈል በኩል ችግር መኖሩን የሚገልጹት ዶ/ር ኢዶሳ፣ ‹‹ትኩረቱ ሁሉ በሰብል ላይ ብቻ ነው፤›› በማለት የፍራፍሬ ዘርፍ ቸል እንደተባለ ጠቁመዋል፡፡  

ማዕከሉ የገንዘብ እጥረትና የአቅም ውሱንነት እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን፣  ከምርምር ሥራው ውጪ ዘር አባዝቶ መሥራት ከኃላፊነቱ ውጪ በመሆኑ ይልቁንም መንግሥት አቅሙ ያላቸው የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች፣ መሬቱ ያላቸውና ለማምረት የሚችሉ የከተማም ሆነ የገጠር ነዋሪዎች ፊታቸውን ወደ ፍራፍሬ እንዲያዞሩ መገፋፋት ይጠበቅበታል ሲሉ ይመክራሉ፡፡

አነስተኛ ባለሀብቶች እንዲያለሙ እስከ አሥር ሔክታር መሬት ላይም ኢንቨስት እንዲደረግ መፈቀድ እንዳለበት ያስባሉ፡፡ ትልልቅ ኢንቨስተሮች በግንባታም ሆነ በሌላ ሥራ ላይ ከቀረጥ ነፃ ዕቃዎችን እንዲያስገቡ እንደተፈቀደው ሁሉ የግብርና ዕቃዎች፣ ውኃ መሳቢያም ሆነ ትንንሽ የግብርና ማሽኖች ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ መደረግ አለበት የሚል አቋም አላቸው፡፡ ሰፋፊ እርሻ ያላቸው አርሶ አደሮች እያለሙ ቢሆን ደላላ እየጎዳቸው በመሆኑ፣ ደላሎች ከገበያው እንዲወጡ ለገበሬውም ጥበቃ ሊደረግ እንደሚገባ በመጠቆም የግብይት ሰንሰለቱን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡   

በግብርና ምርምር የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ዶ/ር አስናቀ ፍቅሬ  እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር አቀማመጥ ለፍራፍሬ ምርት ብቻም ሳይሆን ለአውሮፓም ሆነ ለምሥራቅ አፍሪካ ቅርብ በመሆኑ ምርቱን በተፈለገው መጠን ለማቅረብ የሚመች እንደሆነና በኢትዮጵያም ፍራፍሬው ላይ በደንብ መሥራት እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ በፍራፍሬ ምርት ትልቅ ድርሻ እንዳላትና የውጭ ገበያዋም ሰፊ መሆኑን ዶ/ር አስናቀ ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያም ከፍተኛ የማምረት አቅም እንዳላት በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ከልማቱ ጋር በተመጣጠነ መልኩ ፍራፍሬ ላይ ተሠርቷል ማለት አይቻልም፡፡ ምርቱ ዕውቀት ከመፈለጉም በላይ እንደ ንግድ ወዲያው የሚያተርፍ አይደለም፡፡ ነገን የሚያስብ የፍራፍሬ አምራችና ለገበያ አቅራቢ ባለሀብት ያስፈልጋል፡፡ የግል ባለሀብቶች ገበያ ላይ ሊሳተፉና እሴት ጨምረው ሊልኩ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምርጥ ዘር ብዜትና ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ዶ/ር አበበ አጥላው በበኩላቸው፣ ፍራፍሬ ላይ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር አተኩሮ መጠራት ይጠበቅበታል ይላሉ፡፡ ሥራ አጥ ወጣቶች ዘሩን እንዲያባዙ መደረግ አለበት የሚሉት ዶ/ር አበበ፣ ባለሀብቶች ፎቅ ገንብተው ሆቴል መሥራት ብቻ ሳይሆን ፍራፍሬው ላይም ቢሰማሩ አገርን የበለጠ ተጠቃሚ ማድረግ ይችላሉ ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ለማምረት ያለው ችግር ከዕውቀት በተጨማሪ ካፒታል እንደሆነ ገልጸው፣ መሬትና ውኃ እንዲሁም አየሩ ምቹ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ ባለሀብቱ አንጡራውን አፍስሶ፣ ባለሙያ ቀጥሮ ካመረተ የማያተርፉበት ምክንያት የለም፡፡ ግብርና ምርምርም የፍራፍሬን ዘር በማሻሻል እጅግ ምርታማ የሆኑ ዘሮችን ማቅረብ ስለሚችል በቴክኖሎጂ በኩል ችግር የለም፡፡ ችግር ቢያጋጥምም ወዲያው የሚፈታ በመሆኑ ‹‹ባለሀብቶቻችን እባካችሁ ፍራፍሬ ላይ ተሠማሩ፤›› በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡                      

በመንግሥት ይፋ የተደረገው የመጀመርያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸምና የሁለተኛው ዕቅድ ረቂቅ ሰነድ ላይ ለዘርፉ የተያዘውን የልማት ፕሮግራም በተመለከተ ካሰፈረው ለማየት እንደተቻለው፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ በመጀመርያው የአምስት ዓመት አፈጻጸሙ ደካማ ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን፣ ከታቀደው እጅግ ወደኋላ ቀርቶ መፈጸሙንም ያሳያል፡፡

ከ2003 እስከ 2006 ዓ.ም. ባሉት የመጀመርያው አራት ዓመታት በአትክልት ዘርፍ የባለሀብቶች ተሳትፎ 11,591 ሔክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዶ 807.3 ሔክታር ወይም የዕቅዱን ሰባት በመቶ ብቻ ሆኗል፡፡ በምርት ረገድም ቢሆን ከዘርፉ 310 ሺሕ ቶን ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ በአራተኛው ዓመት የተገኘው የዕቅዱን ስድስት በመቶ ብቻ ነው፡፡

በፍራፍሬው ዘርፍ በተመሳሳይ 11513 ሔክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዶ ነበር፡፡ በአራት ዓመት የተሸፈነው 10,707 ሔክታር ወይም የዕቅዱን 93 በመቶ ነው፡፡ በምርት ረገድም 310 ሺሕ ቶን ለማምረት ሲታቀድ፣ የአራት ዓመት አፈጻጸሙን ግን የዕቅዱን ስድስት በመቶ ብቻ አሳክቷል፡፡

የአበባ፣ የመድኃኒትና የዕፅዋትን ጨምሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ንዑስ ዘርፎች ከአገር ውስጥና ከውጭ ባለሀብቶች፣ ከክልሎችና ከፌዴራል መንግሥት ባጠቃላይ 3.4 ሚሊዮን ሔክታር መሬት የተላለፈ ቢሆንም፣ በባለሀብቶች መልማት የቻለው 840 ሺሕ ሔክታር ብቻ እንደነበር ረቂት ሰነዱ ያሳያል፡፡ ለዚህ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን ደግሞ ባለሀብቶች የማልማት ሥራቸውን ማቋረጣቸው አንዱ ምክንያት እንደሆነ ሰነዱ ይጠቅሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች