Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ለፈቃድና ዕድሳት የተቀመጠውን ጊዜ እንደማይራዘም አስጠነቀቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ለፈቃድና ዕድሳት የተቀመጠውን ጊዜ እንደማይራዘም አስጠነቀቀ

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ የንግድ ፈቃድና ዕድሳት መጠናቀቅ ያለበት እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ በመሆኑ ከዚያ በኋላ የሚመጡ ነጋዴዎች ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ያሳሰበው ንግድ ቢሮው፣ ነጋዴዎች የሚደርስባቸውን እንግልት ለመፍታት ሲዘጋጅ መቆየቱን አስታውቋል፡፡ ዓምና የዕድሳትም ሆነ የምዝገባ ጊዜ ተራዝሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከ264,464 በላይ የተመዘገቡ ነጋዴዎች በሚገኙባት አዲስ አበባ በየዓመቱ የንግድ ፈቃድ ለማሳደስም ሆነ ምዝገባ ለማካሄድ በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ግርግርና ትርምስ ይስተዋላል፡፡ በየዓመቱ የንግድ ፈቃድ ማሳደሻ ጊዜ፣ በአዋጅ ቁጥር 686 መሠረት ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ እስከ ጥቅምት 30 መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ዋና ሥራ ሒደት መሪ አቶ ልመነው ታደሰ አብራርተዋል፡፡ ‹‹ባልታደሰ ንግድ ፈቃድ ምንም ዓይነት የንግድ ሥራ መሥራት፣ ለጨረታ መወዳደር አይቻልም፤›› ያሉት አቶ ልመነው፣ ባልታደሰ ንግድ ፈቃድ ሲነግድ የተገኘ ነጋዴ የሚቀጣበት አግባብም ለየት እንደሚል አሳስበዋል፡፡

ወቅቱ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ የሚሰጥበት በመሆኑና ነጋዴዎች የመጨረሻውን ሰዓት ጠብቀው ከመምጣት ይልቅ በጊዜ እንዲመዘገቡ፣ ንግድ ፈቃዳቸውን እንዲያድሱ ለማሳሰብ ሰኞ፣ ጥቅምት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. አራዳ ሕንፃ ላይ በሚገኘው ንግድ ቢሮ፣ የቢሮውና የገቢዎችና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የኃላፊው ተወካይ አቶ ግዛቸው አሊ እንዳስታወቁት፣ ባለፈው ሳምንት በተደረገ ስብሰባ ከሚመለከታቸው ብቃት አረጋጋጭ ተቋማት ጋር ውይይት መደረጉንና ነጋዴውን በአፋጣኝ እንዲያስተናግዱ ተነግሯቸዋል፡፡ በመሆኑም ንግድ ቢሮ ለዕድሳት የሚመጡ የንግድ ፈቃዶችን ለማስተናገድ በተጠንቀቅ እየጠበቀ እንደሚገኝና እስካሁንም በማስተናገድ ላይ እንደሚገኝ ኃላፊዎቹ ይናገራሉ፡፡

እስከ 2003 ዓ.ም. በነበረው መረጃ መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ የነበረው የነጋዴ ቁጥር 84,893 ብቻ እንደነበር የገለጹት አቶ ግዛቸው፣ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ግን ከ264,464 በላይ ነጋዴ በመመዝገቡ ከ179 ሺሕ በላይ ነጋዴ በአራት ዓመታት ውስጥ መመዝገቡን አቶ ግዛቸው አብራርተዋል፡፡

የነጋዴው ጥያቄዎች

ነጋዴዎች ቀድመውም ዘግይተውም ሲመጡ በወረዳና በክፍለ ከተማ ደረጃ የሚያገኟቸው መስተንግዶዎች፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይጎላሉ፡፡ በመስከረም ወር በተደረገ ጥናትና ከነጋዴው ጋር በተደረገ ምክክር እንደታየው፣ ለነጋዴዎች የብቃት ማረጋጋጫ የሚሰጡ ተቋማት የሚፈጥሩት እንግልትና መጓተት ይጠቀሳል፡፡ አንዳንዱ መሥሪያ ቤት አታካች መመዘኛዎችን ሲተገብር፣ ሌሎች ደግሞ መስፈርቱን የማያሟላ ቢሆንም ትብብር ይደረግለት እያሉ ደብዳቤ የሚጽፉ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ብቃት የሚያረጋግጡ ተቋማት ነጋዴውን እንዳያጉላሉ፣ አሠራራቸውን እንዲያስተካክሉ ተደርጓል ያሉት የንግድ ቢሮው ኃላፊዎች፣ ከዚህ ቀደም ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ያልተዛመዱ፣ የተጋነኑ መጠይቆችን በማውጣት ብቃት የመስጠት ቢሮክራሲውን ሲያንዛዙ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ ሲብስም አንድ ነጋዴ ወይም ኩባንያ እንደተሠማራበት ዘርፍ ከበርካታ ብቃት አረጋጋጭ ተቋማት ዘንድ ፈቃድ ለማግኘት ደጅ ለማንኳኳት ሲገደድ ቆይቷል፡፡ ኃላፊዎቹ እንደሚገልጹት ይህ አዝጋሚ አሠራር ተፈትሾ ማስተካከያ የተደረገበት በመሆኑ፣ በቀረው ጊዜ ነጋዴውም ድርጅቶችም ንግድ ፈቃድ እንዲያሳድሱና ግብር እንዲከፍሉ ጥሪ እየቀረበ ነው፡፡

ነጋዴዎችም ሆኑ የንግድ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ ከሚያገኙባቸው ተቋማት መካከል የምግብና መጠጥ ጤና አጠባበቅና ቁጥጥር ኤጀንሲ፣ የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ፣ የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ፣ የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ ንግድ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን ይጠቀሳሉ፡፡ ለአብነት ያህል የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ለጋራዦችና ጎሚስታዎች የሚጠይቀው የብቃት ማረጋገጫ መሥፈርት ከአቅም በላይ ለመሆኑ አስርጅ ከተደረጉት መካከል የሚጠየቀው የመሬት ስፋትና የሙያተኞች የትምህርት ማስረጃ ከአቅም በላይ ሆነው መገኘታቸውን ንግድ ቢሮው አስፍሯል፡፡ ሌሎችም በርካታ የአሠራርና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በንግድ ቢሮው ተዳስሰዋል፡፡

ከንግድና ከንግድ ድርጅት ስያሜ ጋር በተያያዘ ሲቀርቡ የነበሩ አቤቱታዎች መፈታታቸውን አቶ ልመነው ከሪፖርተር ተጠይቀው አብራርተዋል፡፡ ነጋዴዎችም ሆኑ ኩባንያዎች ለንግድ ፈቃድ ሲያመልክቱ ያቀረቧቸው ስያሜዎች ውድቅ እየተደረጉባቸው በተደጋጋሚ መቸገራቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ የወል ስሞችን ለንግድ ስያሜነት መጠቀም አይቻልም እየተባሉ የሚጉላሉ ነበሩ፡፡ ለምሳሌም ዓባይ የሚለውን ስያሜ ለንግድ መጠቀም አይቻልም ሲባል ቆይቷል፡፡ ይኸውም ዓባይ የሚለው ስም ለዓባይ ወንዝ ብቻ የተተወ ስያሜ መሆን ስለሚገባው፣ የንግድ ምልክት ተደርጎ መወሰድ የለበትም ወዘተ. የሚሉ ክርክሮች ሲነሱ ቆይተዋል፡፡ እንዲህ ላሉት ጥያቄዎች ምላሽ መሰጠቱን አቶ ልመነው ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን ነጋዴዎች የንግድ ፈቃድ ለማሳደስም ሆነ የምዝገባ አገልግሎቶችን ለማግኘት ከሚቸገሩባቸው መካከል የሊዝ ጊዜያቸውን የጨረሱ መደብሮችን ለማሳደስ የሚገጥማቸው ውጣ ውረድ፣ የሕንፃ መጠቀሚያ ፈቃድ፣ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ወይም የውል ማስረጃ ለማቅረብ መቸገርና ሌሎችም ከንግድ መሥሪያ መደብሮች ጋር በተያያዘ ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮች መሆናቸውን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በጥናት አረጋግጬ መፍትሔ እየሰጠሁ ነው ይላል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ በነጋዴዎችና በባለሙያዎች የሚቀርበው አስተያየት ደግሞ ንግድ ፈቃድ ማሳደስ በደቦ ከሚሆን ወይም ሁሉም በጅምላ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ እንዲያሳድስ ከሚደረግ ይልቅ እያንዳንዱ ነጋዴም ሆነ ተቋም ፈቃድ ባወጣበት ቀን በየዓመቱ እንዲያሳድስ ቢደረግ የብዙዎችን ራስ ምታት እንደሚያስቀር ነው፡፡

ገቢዎች ስለነጋዴው ከሚናገረው

ነጋዴዎች ለግብር መክፈያ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ግብርና ታክስ ከፍለው ከዕዳ ነፃ ወይም ‹‹ክሊራንስ›› በመውሰድ ንግድ ፈቃዳቸውን ማሳደስ ይጠበቅባባቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አታክልቲ ገብረ እግዚአብሔር በበኩላቸው ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ወይም ደረጃ ‹‹ሀ›› መካከል ከሐምሌ 1 እስከ ጥቅምት 30 ግብር መክፈል ከሚጠበቅባቸው ውስጥ እስካሁን የመጡት 55 ከመቶ ያህል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የደረጃ ‹‹ለ›› ወይም መካከለኛ ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ ጳጉሜን ጨምሮ የሁለት ወር የግብር መክፈያ ጊዜ ገደብ ተቀምጧል፡፡ ለአነስተኛ ግብር ከፋዮች ወይም የደረጃ ‹‹ሐ›› ለሚባሉት የተቀጠው የግብር መክፈያ ጊዜ የሐምሌ ወር ብቻ ነው፡፡

ንግድ ቢሮ ፈቃድ የማይሰጣቸውን እንደ ትራንስፖርት ያሉ ዘርፎችን ጨምሮ ገቢዎች የመዘገባቸው ነጋዴዎች ቁጥር 336 ሺሕ እንደሆኑ የጠቀሱት አቶ አታክልቲ፣ ከእነዚህ ውስጥ 28,913 ነጋዴዎች ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ናቸው፡፡ 229 ሺሕ ግብር ከፋዮች በአነስተኛ ግብር ከፋይነት ሲመደቡ፣ የተቀሩት ነጋዴዎች በመካከለኛ ግብር ከፋይነት ይመደባሉ፡፡ ይሁንና ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ምድብ ውስጥ ከ55 ከመቶ በላይ እስካሁን ግብር ለመክፈል እንዳልመጡ አቶ አታክልቲ አስታውቀው፣ ለዚህ ምክንያት ከሚደረጉት መካከል ነጋዴው የሚጠበቅበትን ግብር ለሥራ ማስኬጃነት በመጠቀም በመጨረሻው ሰዓት ላይ መክፈልን የሚመረጥ መሆኑ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ሌላኛው ግን ሒሳብ ለማወራረድና ለማጠናቀር ሲባል ነጋዴው በወቅቱ እየመጣ እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡ ይሁንና ከሐምሌ ወር እስከ መስከረም መጨረሻ በነበረው ሩብ ዓመት ውስጥ እንዲሰበሰብ ከሚጠበቀው 5.9 ቢሊዮን ብር ታክስና ግብር ውስጥ 5.6 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዓመት ከታክስና ግብር ለአዲስ አበባ ከተማ ይሰበሰባል ተብሎ የሚጠበቀው ገቢ 22.8 ቢሊዮን ብር መሆኑን አቶ አታክልቲ አስታውሰዋል፡፡

በሌላ በኩል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በአዲስ አበባ ከሚተችባቸው አሠራሮች መካከል የጉልት ቸርቻሪዎችን ሳይቀር በየወረዳውና በየክፍለ ከተማው ከአቅም በላይ ታክስ ሲያስከፍል በአንፃሩ ሕንፃ እያከራዩ፣ ቪላዎችን፣ አፓርታማዎችንና ኮንዶሚኒየም ሳይቀር በዶላር እያከራዩ ገንዘብ የሚያጋብሱትን ችላ ማለቱ ነው፡፡ በየመንደሩ ከሚገኙ ሕንፃ አከራዮች መካከል ከአነስተኛ ግብር ከፋዮች ጋር እየተሰለፉ ዝቅተኛ ግብር የሚከፍሉ መኖራቸውም በአደባባይ የሚታይ ተግባር ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ከሪፖርተር የተጠየቁት አቶ አታክለቲ፣ በ1996 ዓ.ም. የወጣው የቁርጥ (ግምት ግብር) በ2003 ዓ.ም. ቢሻሻልም በተለይ በኪራይ ግብር ላይ ትልቅ ችግሮች እንደሚታዩና ገቢዎች ተገቢውን ግብር ማግኘት እንዳልቻለ ይናገራሉ፡፡ በአከራይና ተከራይ መከካል የሚደረጉ የኪራይ ውሎች ወደ ገቢዎች እንደማይመጡና የሚመጡትም ቢሆኑ ተጭበርብረው ከገበያ ዋጋ አኳያ እጅግ አነስተኛ በሆነ መጠን እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች