Wednesday, October 4, 2023

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የመጀመርያ ዓመት የፓርላማ ውሎ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ማክሰኞ ጥቅምት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በፓርላማ ተገኝተው ከአባላቱ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች ውስጥ ለዋና ዋናዎቹ የሰጡትን ምላሽ ዮሐንስ አንበርብር እንደሚከተለው አሰናድቶታል፡፡

ኮንስትራክሽንና ቤቶች

  • የኮንስትራክሽን ዘርፍ አቅም የማዳበር እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም የአሜሪካ ኩባንያዎች በሜጋ ፕሮጀክቶች እንዲሳተፉ፣ ዩኒቨርሲቲዎች በዲዛይንና ማማከር በክልልና በፌዴራል መንገዶች ፕሮጀክት ውስጥ እንዲሳተፉ፣ ጠንካራ ሥራ በዚህ ዓመት ይጀመራል፡፡

የዓለም አቀፍ የግንባታ ደረጃ የሚያሟሉ በጣት የሚቆጠሩ አገር በቀል ኮንትራክተሮችን ባለፉት ዓመታት አይተናል፡፡ ይህንን የማስፋት ሥራ ነው የሚጠበቅብን፡፡ ከ20 እስከ 30 የሚቆጠሩ አገራ በቀል ኮንትራክተሮችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማብቃት አለብን፡፡ መዋቅራዊ ችግሩን መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ነው የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተቋቋመው፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለኪራይ ሰብሳቢነት ተጋላጭ የሆነ ዘርፍ ነው፡፡ ይህንን የሚያደርቅ ትግል ያስፈልጋል፡፡ በከተሞች የቤት ልማት ፕሮግራሞችን በተመለከተ ሦስት ዓይነት ፕሮግራሞች አሉ፡፡

በግል ጥረት የመሳተፍና የቤት ባለቤት የመሆን፣ በግል አልምቶ ለሌሎች የማከራየት አንዱ ፕሮግራም ነው፡፡ ሁለተኛው በመንግሥት የሚሠሩ የቁጠባ ቤቶች ፕሮግራም ነው፡፡ ሦስተኛው በባለሀብቶች የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ እነዚህ ሦስቱ በጣምራ ነው የቤት ችግሩን ሊቀርፉ የሚችሉት፡፡

በየትም አገር በመንግሥት ብቻ የቤት ፍላጎትንና አቅርቦትን ማሳካት አይችልም፡፡ መንግሥት የራሱን ድርሻ መጫወት አለበት፡፡ ነገር ግን መላው በዚህ ዙሪያ መሳተፍ ያለባቸው በሙሉ ሲሳተፉ ብቻ ነው ችግሩ ሊቀረፍ የሚችለው፡፡

በግል ጥረት ቤት የመገንባት ጉዳይን በተመለከተ በሁለት መልኩ የሚታይ ነው፡፡ አንደኛው ገንዘብና ሀብቱ ያላቸው መንግሥት በሚያመቻቸው የሊዝ ጨረታ በመሳተፍ ቤት የሚያለሙበት ሁኔታ ነው፡፡ ሌላውና ሁለተኛው በተለይም መካከለኛና አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በተደራጀ መንገድ የቤት ሥራ ማኅበራትን በማደራጀት መንግሥት መሬት በነፃ እያቀረበላቸው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይኼ ገቢያቸው አነስተኛ ለሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ገቢያቸው ሻል ያሉትን ደግሞ የአካባቢ መለስተኛ የሊዝ ዋጋ በመክፈል የሚሳተፉበት አሠራር ነው የሚኖረው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የቤት ልማት ፕሮግራም ውስጥ የግል ባለሀብቶች በሊዝ መሬት አግኝተው ቤት የሚገነቡ አሉ፡፡

ሁለተኛ መካከለኛ ገቢ ያላቸው በማኅበር የተደራጁና የአካባቢውን መለስተኛ የሊዝ ሒሳብ በመክፈል መሬት ወስደው የሚሠሩ ማኅበራት አሉ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ መንግሥት በቁጠባ መልክ የሚያቀርበው አለ፡፡ አራተኛ የግል ሪል ስቴት አልሚዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የቤት ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

በእንደዚሁ ዓይነት ተሳትፎ ካልሆነ በስተቀር የቤት ፍላጎቱን ማሟላት ያስቸግራል፡፡ በመንግሥት የሚቀርበው የቤት ፕሮግራም በተለያዩ ደረጃዎች የተከፋፈለ ነው፡፡

የእነዚህ ቤቶች የግንባታ ፍጥነትና የጥራት ጉዳይ ተገቢና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ አሁን በደረስንበት ደረጃ በተለይ 20/80 ቤቶች ፕሮግራም ጥራት እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ መንግሥት ይህንን ፕሮግራም በሚቀርፅበት ጊዜ ቤት የማልማት ብቻ ሳይሆን ወጣቶችና ሴቶች ከፍተኛ የሥራ ዕድል እንዲያገኙም ተብሎ የተቀረፀ ነው፡፡

ከመክፈል አቅም አኳያ የገመገምናቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ስለዚህ ለእነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሆኑ ዋጋቸው አነስ ያሉ ቤቶች እንዴት ተደርጎ ዲዛይን ማድረግ ይቻላል የሚለውን ከተለያዩ አገሮች ልምድ በመነሳት እየሠራንበት ነው ያለው፡፡ ይህ በሚጠናቀቅበት የቤቶቹ ግንባታ ከዋጋ አንፃር የሚያወጣውን ለውጥ ማየት ይቻላል፡፡ ሁለተኛው የቁጠባ ቤቶች ፕሮግራም የተወሰነ መነሻ ክፍያ ከተደረገ በኋላ በሞርጌጅ ሥርዓት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የሚተሳሰር ሥርዓት ነው፡፡

ስለዚህ የተወሰኑ ዓመታትን በተከታታይ መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ የመጀመርያዎቹ አካባቢዎች ችግር ሊከሰት ይችላል፡፡ ምክንያቱም የተቆጠበ ነገር ስለሌለ፡፡ በሒደት ግን ቁጠባው ባልተቆራረጠ መንገድ የሚከናወን ስለሚሆን ችግሩ ይቃለላል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የመንግሥት ሠራተኞችን ጉዳይ ለየት ባለ መልኩ ማየት ያስፈልጋል፡፡

የቁጠባ ፕሮግራሙ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ባገለገሉበት ጊዜያት በውል መሠረት ሊስተናገዱ የሚችሉበት ሁኔት እየተጠና ነው ያለው፡፡ በተመሳሳይ መንገድ የግል ባለሀብቶች ስንል በሁለት መንገድ ነው የሚታየው፡፡ አንደኛው የሪል ስቴት አልሚዎችን የሚመለከት ነው፡፡ ሌላኛው የግል ባለሀብቶች የራሳቸውን ሠራተኞች ቤት እንዲኖራቸው የሚያደርጉበት አሠራር ነው፡፡ በተለይ አሁን ወደ ኢንዲስትሪ ሽግግር በሚደረግበት ወቅት በርካታ ኩባንያዎች ወደ ኢንዲስትሪ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚሳተፉ ስለሚሆን ለሠራተኞቻቸው ቤት አልምተው የሚያስተናግዱበት ሥርዓት ይፈጠራል፡፡

የቤት ፕሮግራማችን በፍላጎት ላይ የተመሠረተ መሆን ስለሚገባው በክልሎች የተመረጡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሚገነቡባቸው አካባቢዎች የቤቶች ልማት ይካሄድባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል መታየት ያለበት የቤቶች ፍላጎት አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት መመደብ የሚችለው አቅም አለ፡፡ እነዚህ ሁለቱ ተጣጥመው መሄድ አለባቸው፡፡ ሌላው ከንግድ ባንክ በዓመት ምን ያህል መበደር ይችላል የሚለውን ማየት ተገቢ ይሆናል፡፡ አሁን በደረስንበት ሁኔታ ለዚህ ዘርፍ ወደ አሥር ቢሊዮን ብር ብድር ተመቻችቶ ነው ያለው፡፡ ዜጎች የሚቆጥቡትን ሳይጨምር፡፡ አሁን ከዚህ በላይ ለመመደብ መንግሥት አቅሙ የለውም፡፡

ኢኮኖሚ

የውጭ ንግድ ሚዛን ካልተስተካከለ ኢኮኖሚዎችን ውስጥ ምስቅልቅል ነው የሚፈጥረው፡፡ በወጪ ንግድና በገቢ ንግድ መካከል ያለውን ሚዛን ለመጠበቅ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በከፍተኛ ደረጃ ይሠራል፡፡ ወደ አገር ውስጥ ለልማታችን የምናስገባቸውን ዕቃዎች የምንሸፍንበትን የውጭ ምንዛሪ በኤክስፖርት መሸፈን ካልቻልን ወደፊት ኢኮኖሚያችን ተንገራግጮ የሚቆምበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡

ሁለት ጉዳዮች ላይ አትኩረን እንሠራለን ብለን ነው ያሰብነው፡፡ አንደኛው ከወጪ ንግዳችን ውስጥ 70 በመቶውን የሚይዘው የግብርና ዘርፍ ነው፡፡ ይህ ከሆነ የግብርና ዘርፍ ምርቶችን መጨመር በጣም አንገብጋቢ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ የማስፋት ስትራቴጂያችንን ተግተን መተግበር ይኖርብናል፡፡

ይኼ ለሁለት ጉዳዮች ይጠቅመናል፡፡ አንደኛው የገቢ አቅማችንን ያሳድግልናል፡፡ ሁለተኛው በብዛት ባመረትን ቁጥር ከዋጋ መውደቅ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ጉዳት ለመቋቋም ያስችለናል፡፡ ሁለተኛው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ምርቶች ናቸው፡፡ በዚህ ዘርፍ በጥራት ማምረት ነው፡፡ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በዚህ ዘርፍ እንዲጨምር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ከማዕድን ምርቶቻችን ጋር በተያያዘ በተለይም ደግሞ ባህላዊ የወርቅና የጌጣጌጥ ምርቶቻችንን ካለማን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ማግኘት ይቻላል፡፡

ከአገራችን የዕዳ መጠንና ጫና ጋር በተያያዘ አገሮች የዕዳ ጫና ውስጥ ገብተዋል የሚባልበት የተለምዶ መስፈርት አለ፡፡ አንዱ ትልቁ ሚና የሚጫወተው የኤክስፖርት ግኝት ነው፡፡ የኤክስፖርት ግኝት መቀነሱ የዕዳ ጫና ያመጣል፡፡ የአገራችን የዕዳ ጫና ግን ከሌሎች አገሮች ለየት የሚልበት የራሱ ባህሪ አለው፡፡ አገራችን የምትበደራቸው ብድሮች የሚሄዱት ለመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ኮርፖሬሽኖች ነው፡፡ ሌሎች አገሮች ግን ለደመወዝ ክፍያና ለመንግሥት ሥራ ማስኬጃ ነው የሚበደሩት፡፡ ስለዚህ በሁለታችን መካከል ያለው የብድር አወሳሰድ መሠረታዊ ልዩነት አለው፡፡

ለቴሌኮም፣ ለመሠረተ ልማት፣ ለኃይል ማመንጫ ግድቦች የመሳሰሉት ነው የምንበደረው፡፡ ስለዚህ ፕሮጀክቶቹ ራሳቸው መልሰው የሚከፍሉት ነው የሚሆነው፡፡ ፕሮጀክቶቹ የውጭ ምንዛሪንም ጭምር ለማስገባት ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ለስኳር የተወሰደው ብድር ስኳር ኤክስፖርት በማድረግ መመለስ የሚቻል ነው፡፡ ለባቡር የተወሰደውም ብድር የተወሰነ መንግሥት የሚደጉመውም ቢሆን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ራሱ የሚሸፍነው ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ የምንወስደው ብድር ለልማት ብቻ የሚውልና ተቋማቱ ራሳቸው ሊከፍሉት የሚችሉት ነው፡፡ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር በቅርቡ የተቋቋመበትም ምክንያት ሁሉም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም አሁን ደግሞ የኢትዮ ቴሌኮም በሚሄዱበት ጥሩ የኮርፖሬት ፋይናንስ ደረጃ ለማድረስ ነው፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ መንግሥት ምንም ዓይነት ዋስትና ሳይገባ ኩባንያዎቹ በራሳቸው የሚበደሩት ነው የሚሆነው፡፡

በመጨረሻም መንግሥት እስከዛሬ የወሰዳቸው ብድሮች ለዕዳ ጫና የሚዳርጉት አይደሉም፡፡ ማኑፋክቸሪንግን በተመለከተ አገር በቀል ኩባንያዎች ተሳትፎ ውስን መሆን ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ ማንኛውም አገር ዘላቂ ዕድገት ሊያስመዘግብ ከፈለገ ግብርና ከሚመራበት ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ በመቀጠልም ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ መሸጋገር አለበት፡፡ ይኼን ሳያደርግ ያደገ አገር የለም፡፡ ከዚህ አኳያ አገራችን ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ ካስፈለገ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ መጎልበት አለበት፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እንዲጎለብት ካስፈለገ ደግሞ ዘላቂ ዕድገት ሊያመጡ የሚችሉት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ናቸው፡፡

የውጭ ባለሀብቶች ሚና ድጋፍ ማድረግ ነው መሆን ያለበት፡፡ አሁን ያለንበትን ደረጃ በምንመለከትበት ጊዜ የአገራዊ ባለሀብቶቻችን ተሳትፎ ውስን ነው፡፡ የአገር ውሰጥ ባለሀብቶችን ወደዚህ ዘርፍ የማስገባት ጉዳይ የፍላጎት ሳይሆን የግዴታ ጉዳይ ነው፡፡ የህልውና ጉዳይ ነው ቢባል የሚያንስበት አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ዕድገታችን የሚንጠለጠለው በእነርሱ ላይ ስለሆነ፡፡ ልምድ ማነስና ድፍረት ማጣት ነው ዘርፉን እንዳይቀላቀሉ ያደረጋቸው፡፡ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት፣ በንግድ ዘርፎች ያሉ ኩባንያዎች ደረጃ በደረጃ ወደዚህ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገቡ የግድ ነው፡፡ ሥራቸውን ትተው ይግቡ ማለት ሳይሆን ተደፋፍረው ወደዚህ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሸጋገር ይጀምሩ ነው፡፡ ምክንያቱም የእነሱ መኖር የሞት የሽረት ጉዳይ ነው፡፡ ድፍረት እንዲያኙ፣ ኪሣራ እንገባለን ብለው እንዳይሰጉ የሚያደርጉ ማበረታቻዎችን መንግሥት ያደርጋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ዘላቂ ያልሆነ በአቋራጭ የሚገኝ ሀብት በአገራችን አለ፡፡ ስለዚህ የግል ባለሀብቶች ወደዚህ የሚያመዝኑበት ዕድል አለ፡፡ የግል ባለሀብቶቹ ችግር አይደለም፡፡ የፖለቲካ ኢኮኖሚው የፈጠረው ችግር ነው፡፡ እነዚህን የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮች ማድረቅ ያስፈልጋል፡፡

በእኛ አገር ያለው የትርፍ ህዳግ ከ50 በመቶ ካልበለጠ በስተቀር ትርፍ አገኘው ብሎ አያስብም፡፡ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ አየር በአየር ያስለመደው አጥፊ ፀረ ልማት ንግድ ነው፡፡ ስለዚህ የትርፍ ህዳጉ ከአሥር በመቶ ባልበለጠበት ሁኔታም ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በአቋራጭ ትርፍ ማግኘት መንገድ ከተዘጋ ልማታዊ ባለሀብቶች እየተፈጠሩ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚሄዱበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

  •  

መንግሥት ሰሞኑን በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ዙሪያ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቷል፡፡ በሚያስማሙን ጉዳዮች ላይ ለመግባባት በማያስማሙን ጉዳዮች ላይ ደግሞ ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ እየተባበርን የምንቀጥልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መድረክ ተከፍቶ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በዚህ መድረክ ሁሉም በአገራችን ያሉ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ መንግሥት ማድረግ የሚችለው ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች መጋበዝ እንዲሁም ያዘጋጀናቸውን ዶክመንቶች ቀድሞ መላክ በመሆኑም አንብባው ተዘጋጅተው ከእኛ ጋር እንዲወያዩ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ አድርገናል ሰነድም ተልኳል፡፡ የተወሰኑት አልመጡም እጅግ አብዛኞቹ ግን ተገኝተዋል፡፡ ያልመጡት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመገናኛ ብዙኃን የሰጡት ምክንያት ውኃ የሚቋጥር አይደለም፡፡ ይኼ መንግሥት በሕጋዊ መንገድ ያልተመረጠ ስለሆነ በሕጋዊ መንገድ ካልተመረጠ መንግሥት ጋር አንወያይም ነው ያሉት፡፡ እንግዲያው የትኛው መንግሥት እያስተዳደረ እንደሚመጡ እናያለን፡፡

ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጋር ባደረግነው ውይይት በብዙ ጉዳዮች ላይ የሚያግባባን ነገር እንዳለ ገምግመናል፡፡

ወደፊትም እንቀጥላለን፡፡ ክፍት የቴሌቪዥን የፖሊሲ ክርክሮች ይኖሩናል፡፡ ሌሎች መድረኮችም ይኖሩናል፡፡ በተለያዩ ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ እንወያያለን፡፡ የፓርቲዎች የጋራ መድረክ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ተስማምተናል፡፡ ስለዚህ ቢሳተፉ ለእነሱም ለእኛም በአጠቃላይ ለአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጠቃሚ ይሆናል፡፡

አገራችን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ አሳሳቢ እንደሆነ ከማንም በላይ የምታውቅ አገር ናት፡፡ ስለዚህ ይህንን ጉዳይ ለመፍታት በአንድ በኩል የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ ፕሮግራምና ስትራቴጂ ቀርጻ የምትሄድ አገር ናት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአየር ንብረት ተፅዕኖ የሚያመጣውን ዳፋ ለመቀነስ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ቀርጻ የምትንቀሳቀስ አገር ናት፡፡

ይህንንም ለዓለም ቀድማ ያሳወቀች አገር ናት፡፡ አሁን የተከሰተው የአየር ለውጥ መዛባት እንደሚመጣ ይታወቃል፡፡ ከአምና በልግ ጀምሮ ነው የተስተዋለው፡፡ ነገር ግን የምግብ ዋስትና ፕሮግራማችን አቅም ገንብቶ የቆየ በመሆኑ ባለው ውኃና በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ፕሮጀክቶቻችን አማካይነት ስንከላከል መጥተናል፡፡ የሆነው ሆኖ ለተከታታይ ዓመታት በሚሆንበት ጊዜ ይህ አቅም እየተሟጠጠ መሄዱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ የተለያዩ ድጋፎችን ይጠይቃል፡፡ ሌላው የዝናብ ዕጥረቱ የተከሰተበት አካባቢ የአርብቶ አደሩ አካባቢ ነው፡፡

በዚህ አካባቢ የመኖ ልማት አቅርቦት ሥራችን ረዥም ጊዜ የሚወስደን ሆኖ አልተገኘም፡፡ ለአጭር ጊዜ ለመከላከል ዕድል የሰጠንም ቢሆን ለረዥም ጊዜ የሚያቆየን አልሆነም፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ለረዥም ጊዜ የሚቆይ በመስኖ ላይ ያተኮረ የመኖ ልማት ሥራ መሥራት እንዳለብን ተገንዝበናል፡፡

የሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ሳይደርስ ለመከላከል ችለናል፡፡ ከእንስሳት ሀብት ጋር በተያያዘ ግን ጉዳት ደርሷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቀድመን የያዝነው የመጠባበቂያ እህል ክምችት እነዚህ አካባቢዎች ላይ ጉዳት ሳይደርስ ለማሰራጨት ችለናል፡፡ ከአሁን በኋላም በከተማው ሕዝብ ላይ የምግብ እጥረት እንዳይከሰት ለማድረግ በሚያስችል ደረጃ መንግሥት የእህል ግዢ እያካሄደ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ያለምንም መንገራገጭና የዋጋ ንረት በማያሳስብበት ሁኔታ ችግሩን ለመቆጣጠር እየተሠራ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -