Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊመንግሥት የሰጠው ድጐማ በአርበኞች ማኅበር አባላት መካከል አለመግባባት ፈጠረ

መንግሥት የሰጠው ድጐማ በአርበኞች ማኅበር አባላት መካከል አለመግባባት ፈጠረ

ቀን:

መንግሥት ለጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር በ2007 ዓ.ም. 1.5 ሚሊዮን ብር፣ በ2008 ዓ.ም. ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ብር በሰጠው ድጎማ ምክንያት በአባላቱ መካከል አለመግባባት ተፈጠረ፡፡

መንግሥት የኑሮ ውድነቱንና የአርበኞችን የማይረሳ የጀግንነት ተግባር ከግምት ውስጥ በማስገባት የተጠቀሰውን ገንዘብ ድጐማ ቢያደርግም፣ የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚዎች ለሚገባቸው አርበኞች አደላድለው መስጠት ሲገባቸው እንዳላከፋፈሉ ቅሬታቸውን የገለጹት አቶ ወርቅነህ ተገኝ፣ አቶ ደስታ ኤርቤሎ፣ ሻለቃ ሰይፉ ኃይሉ፣ መሪጌታ አምዴ ገሠሠ፣ አቶ ጥላሁን ኃይለኛው፣ አቶ ሸዋንጣሰው ደምለው፣ አቶ አስታጥቄ፣ አቶ አዳሙ አሰጋኸኝ፣ ደጃዝማች ይፋት አሰግድ፣ አቶ ወንድይፍራው ታረቀኝ፣ አቶ ሙሉጌታ ዳምጠውና አቶ መላኩ ሙሉጌታ ናቸው፡፡

የማኅበሩ አባላት እንደሚሉት፣ በማኅበሩ ውስጥ ሕገወጥ አሠራርና ብልሹ አስተዳደር ሰፍኗል፡፡ ሥራ አስፈጻሚዎቹ ቢያንስ ቢያንስ መንግሥት የደጎመውን ገንዘብ እንኳን ለአርበኞቹ ማከፋፈል ሲገባቸው የት እንዳደረሱት እንደማይታወቅ፣ የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚዎች እየፈጸሙ የሚገኙትን ሕገወጥ ተግባር በሚመለከት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በማስረጃ ማቅረባቸውን፣ ጥፋቶቹ እንዲታረሙ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ የተሰጠ ቢሆንም እስካሁን ሊታረም እንዳልቻለ አባላቱ ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

ሌላው የማኅበሩ አባላት የሚያነሱት ቅሬታ፣ በአርበኞች ሀብት የተገነባውና አራት ኪሎ ፓርላማ ፊት ለፊት የሚገኘው የአርበኞች ሕንፃን የሚመለከት ነው፡፡ ሕንፃው በወር ከ80,000 ብር በላይ ተከራይቶ ለአርበኞች ገቢ እያስገኘ ቢሆንም፣ የማኅበሩ አመራሮች ተከራዮችን በሕገወጥ መንገድ በማስወጣት የአርበኞቹ ጥቅም እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን አባላቱ ይናገራሉ፡፡

ከማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ ውጪ ሕገወጥ ጨረታ በማውጣት በዕድሳት ስም እንዲፈርስና ቅርስነቱን እንዲያጣ እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ፣ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ እንዲያስቆምላቸው ጠይቀዋል፡፡

በ1990 ዓ.ም. ማኅበሩ ካወጣው መተዳደሪያ ደንብ ውጪ ምርጫ መካሄዱንና በደንቡ አንቀጽ 18 መሠረት የማኅበሩ ከፍተኛና የበላይ ሥልጣን የጠቅላላ ጉባዔ መሆኑ ተደንግጐ እያለ፣ ምርጫ የተካሄደው በሕገወጥ መንገድ መሆኑን በመግለጽ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለፌዴራል ጉዳዮችና አርብቶ አደሮች ልማት ሚኒስቴር፣ ለአዲስ አበባ ከንቲባና ለሌሎችም የመንግሥት አካላት ማሳወቃቸውን ተናግረዋል፡፡

የማኅበሩ አባላት የሚያቀርቡትን ቅሬታ በሚመለከት ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ ‹‹አባት አርበኞች እንዲጠቀሙ ከማድረግ ባለፈ ሕገወጥ ተግባርም ሆነ ብልሹ አሠራር በእነሱ ላይ አይፈጸምም፤›› ብለዋል፡፡ በ2007 በጀት ዓመት መንግሥት የደጐመውን 1.5 ሚሊዮን ብር ለ1,195 አባላት ማከፋፈላቸውንም አስረድተዋል፡፡ በሁሉም ክልሎች ለሚገኙትና በጣም በዝቅተኛ ኑሮ ላይ በሚገኙት ደግሞ የተሻለ ክፍያ እንዲያገኙ ማድረጋቸውንም አክለዋል፡፡

በ2008 በጀት ዓመት መንግሥት ሁለት ሚሊዮን ብር በድጐማ መልክ መስጠቱን ያረጋገጡት ፕሬዚዳንቱ፣ የማከፋፈል ሒደቱ በተጠና ሁኔታ መጠናቀቁንና ከሐምሌ ወር 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ወደኋላ በመሄድ በቅርቡ ክፍያ እንደሚፈጸም ጠቁመዋል፡፡

ጥቂትና ዝም ብለው መንግሥትንና ሕዝብን የሚያስቸግሩ አባላት እንዳሉ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ የፍሳሽ ማስወገጃዎቹ የተበላሹ፣ የኤሌክትሪክ መስመሮቹ ዝርጋታቸው ትክክል ያልሆነና ከተገነባ ከ50 ዓመታት በላይ የሆነን ሕንፃ ለማደስ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማስቆም እየተሯሯጡ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ሕንፃው እጅግ በጣም ዝቅተኛ በሆነ ኪራይ ከመከራየቱም በተጨማሪ፣ ከበስተኋላው ወደታች እየሰመጠ የሚገኝ በመሆኑ ታድሶ መስተካከልና በአካባቢው ዋጋ መከራየት ስላለበት፣ ሕጋዊ ጨረታ አውጥተው በማሳደስ ላይ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ጥቂት አባላት ከተከራዮች ጥቅም ስለሚያገኙ በየመገናኛ ብዙኃኑና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመዘዋወር አላሠራ እንዳሏቸው፣ ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቃቸውን ፕሬዚዳንቱ አቶ ዳንኤል ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ ተከራዮችም የአባላቱን ግፊት በመከተል እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ሊለቁላቸው እንዳልቻሉ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ይኼንን የሚያደርጉት አባላት ጥቅሙ የእነሱም ጭምር መሆኑን ተረድተው በሥራው ቢተባበሩ ይሻል እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ሕንፃው እንዲታደስ የተደረገውም ከ150 በላይ የማኅበሩ አባላት በተገኙበት ስብሰባ ላይ ግልጽ በሆነ መንገድ ተወያይተውና በቃለ ጉባዔ ተስማምተው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ምርጫን በሚመለከት በዋናነት የሚመለከተው የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ የሚያውቀው በመሆኑ እሱ ቢናገር እንደሚመርጡ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...