Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አንበሳ አውቶቡስ ድርጅት ከዓለም ባንክ የ18 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አገኘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት አሠራሩን በዘመናዊ የትራንስፖርት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ግንባታ ለመከወንና ለዴፖዎች ማስፋፊያ፣ ከዓለም ባንክ የ18 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቱን ገለጸ፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ በድሉ አሰፋ ይህን ለሪፖርተር የገለጹት፣ ማክሰኞ ጥቅምት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሆቴል በተዘጋጀው የድርጅቱ የ2008 የበጀት ዓመት ዕቅድ ላይ፣ ከሕዝብ ክንፍ ተወካዮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በተካሄደ ውይይት ላይ ነው፡፡

በዚህም መሠረት ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት የሚያስተዳድራቸውን ሦስት ዴፖዎችን ዘመናዊ ለማድረግና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አንድ አዲስ ዴፖ ለመገንባት የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ፣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አቶ በድሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹አሁን የተሻለ የሚባለው የካ የሚገኘው ጋራዥ ነው፡፡ ሸጎሌና መካኒሳ የሚገኙት ጋራዦች የዛሬ አርባና ሃምሳ ዓመት በቆርቆሮ እንደተሠሩ ሜዳቸው በፀሐይና በአቡዋራ በክረምት ጭቃ ስለሚሆን በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድም አውቶቡሶቹ በየጊዜው የሚሰባበሩብን በዚህ ችግር ምክንያት ነው፡፡ እርሱን አሳይተን የከተማ አስተዳደሩም በቅርበት ሠርቶበት የገንዘብ ድጋፍ እንዲገኝ አድርጓል፡፡ ይህም አሠራሩን ለማዘመን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

አቶ በድሉ፣ ‹‹አሁን ዘመናዊ ፋሲሊቲ የምናገኝበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ የፕሮጀክት ቀረፃው ተጠናቋል፡፡ በፕሮጀክቱ መሠረት የሚያስፈልገው ገንዘብ ሁሉ ተመድቧል፡፡ አሁን የማማከርና የሥራ መዘርዝር (ToR) ሥራ እየተከናወነ በመሆኑ፤ በቅርቡ ወደ ግዥውና ሥራው እንገባለን፤›› በማለት አክለው አስረድተዋል፡፡

ድርጅቱን ወደ ኤሌክትሮኒክ ክፍያ የማስገባት ዕቅድና አሠራር በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ከዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ጋር በተያያዘ እኛ መጀመሪያ ጥናት ስንሠራ አስበነው የነበረውና ገበያ ላይ የነበረው የኤሌክትሮኒክ ቲኬቲንግ ዋጋ እጅግ በጣም የተለያየ ነበር፡፡ እንዲሁም ያስፈልጋል ያልነው ገንዘብና በኋላ የደረስንበት ዋጋ ግን ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑም ሌላኛው ችግር ነበር፡፡ ሆኖም አሠራር ሆኖ ስለተገኘ አሁን የዓለም ባንክ በፈጠረልን አቅም የሚፈጸም ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

በአውቶቡሶቹ ላይ በብዛት የሚታየው ማስታወቂያ የድርጅቱን ታዋቂ ቀለምና ምልክት ያበላሻል የሚል አስተያየት ከብዙ ሰዎች ስለሚሰማ ለዚህ የሚሰጡት ምላሽ ምንድነው? በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹እኛ እንደ ኢንተርፕራይዝ ገቢ የሚያስገኝ ማንኛውም ነገር ካለ እንሠራለን፡፡ ማስታወቂያው ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገባ መሆኑን ስላወቅን በዚህ ምክንያት ነው የምንጠቀምበት፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከማስታወቂያ የተገኘውን ገቢ በተመለከተም፣ ‹‹ጥሩ ገንዘብ እናገኛለን፡፡ ባለፈው ዓመት ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር አካባቢ አግኝተናል፡፡ ይህ ማለት የአንድ ዓመት የጐማ ወጪ ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ በኋላ የተሰባሰቡ የወታደር ማጓጓዣ ካሚዮኖች የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንዲያስችላቸው አግዳሚ ወንበርና የቆርቆሮ መጠለያ ተደርጐላቸው፣ በ1935 ዓ.ም. በወቅቱ አጠራር በሥራና መገናኛ ሚኒስቴር ሥር አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት መቋቋሙ ይታወሳል፡፡ በአምስት ‹‹ትሬንታ ኳትሮ›› ተሽከርካሪዎች በ40 ጣሊያናውያንና ለሥልጠና በተመለመሉ 80 ኢትዮጵያውያን ሥራውን የጀመረው አንበሳ አውቶቡስ ድርጅት፣ ባለፈው ዓመት 185 ሚሊዮን መንገደኞችን ማጓጓዙ ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የአውቶቡሶቹ ቁጥርም 814 መድረሳቸውን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች