Monday, December 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የድርቁ ጫና የዋጋ ግሽበት እንዳያባብስ!

በክረምት ዝናብ ሥርጭት ላይ በተፈጠረው መዛባት ምክንያት ከ8.3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡ መንግሥት አሥር ቢሊዮን ብር በመመደብ በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕርዳታዎችን በማዳረስ ላይ መሆኑን እያስታወቀ ሲሆን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤትም ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡ ምንም እንኳ ለጋሽ አገሮች ለተረጂዎች ድጋፋቸውን ለማድረግ ቃለ የገቡ ቢሆንም፣ በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለው ክፍተት አሁንም ሰፊ መሆኑ እንዲሁ ተገልጿል፡፡ በዚህ የድርቅ ጫና ምክንያት በመላ አገሪቱ የዋጋ ግሽበት እንዳይባባስም ሥጋት አለ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ማክሰኞ ጥቅምት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ፣ ድርቁ የምግብ ዋጋ ግሽበትን እንዳያባብስ መንግሥት በስፋት ምግብ ከውጭ እያስገባ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም በዝናብ እጥረት ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን የምግብ እጥረት ለመቆጣጠርና ለመቋቋም፣ ችግሩ በተከሰተባቸው ቦታዎች በተለይም በአርብቶ አደሮች አካባቢ የውኃ ጉድጓዶችን በማዘጋጀት በቶሎ የሚደርሱ ሰብሎች እየተመረቱ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ መንግሥት በእርግጥም በዚህ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ ከሆነ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን መንግሥት የድርቅን ጫና እየተቋቋመበት ያለው ፍጥነትና ተረጂዎችም በአግባቡ አስፈላጊውን ዕርዳታ እያገኙ ስለመሆናቸው አሠራሩ ግልጽ ሆኖ መታየት አለበት፡፡

የክረምቱ ዝናብ ሥርጭት ከመስተጓጎሉ ቀደም ብሎ የበልግ ዝናብ በመቅረቱ ችግር የከፋ ሊሆን እንደሚችል ይታወቅ ነበር፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ኤልኒኖ በተባለው የአየር ፀባይ ምክንያት ድርቅ በምሥራቅ አፍሪካና በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚከሰት ይታወቅም ነበር፡፡ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ባለሥልጣን የአየር ትንበያም ይኼንኑ እውነታ የሚጋራ ነበር፡፡ በመሆኑም የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማትም ሆኑ ዓለም አቀፍ ተባባሪዎች ድርቁን አስመልክቶ ያደረጉት ዝግጅት ምን ያህል እንደነበር ሲወሳ አይሰማም፡፡ መንግሥት መጀመርያ በራሱ አቅም ብቻ ሊወጣው እንደሚችል፣ ቆየት ብሎ ደግሞ ለለጋሾች ጥያቄ መቅረቡ አይዘነጋም፡፡ አሁን እንደሚታየው ግን የለጋሾች እጅ በበቂ ሁኔታ አልተዘረጋም፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ጫናው ሙሉ በሙሉ መንግሥት ላይ ያርፋል ማለት ነው፡፡ ሸክሙን ያከብደዋል፡፡

የዘንድሮው በጀት ሲታቀድ መንግሥት ለመጠባበቂያ ብሎ የያዘው ገንዘብ አንድ ቢሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ ይኼ የመጠባበቂያ ገንዘብ ድርቁን ማዕከል ያደረገ ነበር ለማለት ያዳግታል፡፡ ምክንያቱም መጀመርያ የአስቸኳይ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር 4.5 ሚሊዮን መሆኑ ሲነገርና ከዚያም ቁጥሩ ወደ 7.5 ሚሊዮን ማደጉ ሲሰማ የመንግሥት ዝግጅት ከ700 ሚሊየን ብር የዘለለ አልነበረም፡፡ ቁጥሩ አሻቅቦ 8.3 ሚሊዮን መድረሱ ታውቆ የለጋሾች ምላሽ ሲጠፋ ነው መንግሥት አሥር ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡን ያስታወቀው፡፡ ይህ ገንዘብ ደግሞ በዘንድሮ በጀት ውስጥ የተተከለ ሳይሆን፣ በቀጥታ ለልማት ከሚውለው ላይ የተነሳ ነው፡፡ አገሪቱ ባለፉት ሦስት ወራት ከሰበሰበችው 34 ቢሊዮን ብር ላይ የተቀነሰ ነው፡፡

በቅርቡ በእንግሊዝ ከኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አባላት ጋር የተወያዩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ከተሳታፊዎች መካከል ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ የድርቁ ጉዳይ ነበር፡፡ ጠያቂው መንግሥት ለድርቁ ተጎጂዎች ምን እያደረገ ነው? በውጭ ያሉ ወገኖችስ ምን ማድረግ አለባቸው? የሚል ነበር፡፡ እሳቸው በሰጡት ምላሽ መንግሥት ለልማት ከመደበው በጀት ላይም ቢሆን በመውሰድ ድርቁ ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ጉዳት እንዳያደርስ ዕርዳታና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው መንግሥት በስፋት ከውጭ የምግብ ግዥ ላይ የተሰማራው፡፡ መንግሥት ድርቁ ባልጠበቀው መንገድ ዱብ ዕዳ ስለሆነበት ርብርብ በማድረግ ላይ መሆኑ ቢታወቅም፣ በፍጥነት ለተረጂዎች ዕርዳታው እየደረሰ ነው የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ተረጂዎች በተገቢው መንገድ ዕርዳታ ካላገኙ መፈናቀል ይከተላል፡፡ በተጨማሪም የከተማ ነዋሪዎች ለችግር ይጋለጣሉ፡፡ ወትሮም እንደነገሩ የሆነው ግብይት ይናጋና የዋጋ ግሽበት ይከሰታል፡፡

ድርቁ ከተከሰተ ወዲህ ካለፈው ሰኔ ወር 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ባለሁለት አኃዝ መሆን የጀመረው የዋጋ ግሽበት፣ በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ 11.9 ደርሷል፡፡ መንግሥት በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ በተጠናከረ ሁኔታ ከማቀላጠፍ በተጨማሪ፣ ከተሞች በዋጋ ግሽበት እንዳይመቱ በመሠረታዊ ምግቦችና በፍጆታ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ማረጋጋት ሥራ ማከናወን አለበት፡፡ የዕርዳታ ምግቡ ሥርጭት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን፣ መንግሥት በጠቅላይ ሚኒትሩ አማካይነት እንደገለጸው መጠነ ሰፊ የምግብ ግዥና አቅርቦት መፍጠር አለበት፡፡ ይህ ሕይወት አድን ሥራ በደካማው የመንግሥት ቢሮክራሲ የተተበተበ አሠራር እንዳይደናቀፍ ማድረግም የግድ ይላል፡፡

ከመንግሥት ጥረት በተጨማሪ የለጋሾችና የሰብዓዊ ድርጅቶች ተሳትፎም በተጠናከረ መንገድ እንዲጠናከር አስፈላጊው ሥራ መከናወን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ ልምዶች እንደሚያሳዩት ለጋሾችና ሰብዓዊ ድርጀቶች የዕርዳታ አቅርቦታቸው ስለሚዘገይ፣ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ሁኔታዎች ካልተሻሻሉ የተረጂዎች ቁጥር ይጨምራል የሚል ሥጋት አለ፡፡ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብም የራሱ ጉዳት አለው፡፡ በሶማሌ ክልል በሸበሌ ዞን ምሥራቅና ምዕራብ ኢሚ ወረዳዎች የዋቢ ሸበሌ ወንዝ ሞልቶ ከክትሩ በመውጣቱ፣ ለችግር የተጋለጡ ወገኖች በውኃ ተከበዋል፡፡ የወንዙ ሙላት በመጨመረ ቁጥር በሌሎች ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎችም ለችግር መጋለጣቸው አይቀርም፡፡ ይህንና መሰል ችግሮች በመንግሥት ላይ ጫና በፈጠሩ ቁጥር፣ ችግሩም እየከበደ ይሄዳል፡፡ በዕርዳታ አቅርቦት ላይም መስተጓጎል ይፈጠራል፡፡

በድርቁ ምክንያት ከፍተኛ ርብርብ መደረግ ያለበት ዜጎች ለሕልፈት እንዳይዳረጉ፣ ከቀዬያቸው እንዳይፈናቀሉ ወይም እንዳይሰደዱና ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ላይ እንዳይስተጓጎሉ ጭምር ነው፡፡ ለተረጂዎች የሚላክ የዕርዳታ ምግብ የሚዘርፉ፣ ለፖለቲካ ዓላማ የሚያውሉና ሕገወጥ ተግባር የሚፈጽሙ ለሕግ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ በብቃት ማነስና በቸልተኝነት በሚፈጠር መዘግየት የሰው ልጅ ሕይወት ለአደጋ እንዳይጋለጥ ከፍተኛ ትኩረት ይደረግ፡፡ በሌላ በኩል የድርቁ ጫና በአገሪቱ ዜጎች ላይ የበለጠ ችግር እንዳይፈጥር ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል አስተዋጽኦ ያበርክት፡፡ ኃላፊነቱን መንግሥት ላይ ብቻ በመጣል ሸክሙን ሳይጋራ ዳር ሆኖ መተቸት ተገቢ አይደለም፡፡ ነውር ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሰው ሕይወት ላይ የሞት አደጋ ለመድረሱ የተጨበጠ መረጃ ባይኖርም፣ በርካታ እንስሳት ግን በተለያዩ አካባቢዎች ሞተዋል፡፡ የድርቁ መጠን በጨመረ ቁጥር ሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይህንን ቀውስ መታደግ የሚቻለው ደግሞ ሰብዓዊ ተግባራትን በፍጥነትና በተቀናጀ አኳኋን መምራት ሲቻል ነው፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴም በግልጽነት ሲከናወን ነው፡፡ የድርቁ ጫና በጨመረ ቁጥር መፈናቀልና መሰደድ ይጀመራል፡፡ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ሁኔታ ኑሮውን የሚመራው የከተማና ከተማ ቀመስ አካባቢ ነዋሪ ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ ለዚህም ሲባል ነው የድርቁ ጫና የዋጋ ግሽበት እንዳያባብስ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...