በሽብር ተግባር ላይ በመሰማራትና ራሱን አይኤስ (ኢስላሚክ ስቴት) በማለት የሚጠራውን ቡድን ለመቀላቀል ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉ 20 ተጠርጣሪዎች፣ ማክሰኞ ጥቅምት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
አዲስ አበባ ከተማን የሽብር ቡድኑ መቀመጫ አድርገው በመሰየም በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአማራ፣ በሶማሌና በሌሎች ክልሎች መዋቅራቸውን በመዘርጋት እነሱ ከሚከተሉት ክዋርጂያ አስተምህሮትና እምነት ውጪ ሌላ እምነት በኢትዮጵያ ሊኖር እንደማይገባ ለማድረግ መንቀሳቀሳቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡
በአዲስ አበባ በተለይ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ፣ በወለጋ፣ በሸዋሮቢት፣ በከሚሴ፣ በሰንበቴና በጅግጅጋ ከተሞች ይንቀሳቀሱ እንደነበር የተጠቀሱት ተከሳሾች አብዱል ዋህድ አብደላ፣ ናስር ደጉ፣ ሬድዋን ታኢ፣ ሼህ እድሪስ ሐሰን፣ አብዱ መሐመድ፣ ዛይድ ናስር፣ ኒዛሙ ሼዓ አብዱል ሐኪም፣ አብዱል ሐመድ፣ ተማም መኰንን፣ ኤልያስ ያሲን፣ ሐምዴ ይማም፣ ሸሪፍ ባሉዴ፣ እድሪስ መሐመድ፣ ሐሰን ሁሴን፣ አስራር ሐሰን፣ ሼክ ሚፍታህ አባራያ፣ ሼክ መሐመድ አባወርቁ፣ ሼህ መሐመድ ሳላህ፣ መሐመድ እድሪስና ሰዒድ ዓሊ ናቸው፡፡
ተከሳሾቹ መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል፣ የጦር መሣሪያዎችን ለመግዛትና የሥልጠና ቦታዎችን በመምረጥ ገንዘብ የሚያገኙበትን መንገድ እያፈላላጉ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ በጅማ አካባቢ ተሽከርካሪዎችን በማስቆምና ተሳፋሪዎችን በመግደል ንብረትና ገንዘብ መዝረፋቸውንም አክሏል፡፡
ተከሳሾቹ በሃይማኖታቸው መከሰስ የተከለከለ መሆኑን፣ ምስክር መሆን እንደማይቻል፣ የመንግሥት ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት መጠቀም እንደማይቻል፣ በመንግሥት ትምህርት ቤት መግባትና ሳይንሳዊ ትምህርቶችን መማር እንደማይቻልና ሌሎችንም መልዕክቶች በተለይ አንደኛ ተከሳሽ አብዱል ዋህድ አብደላ ያስተላልፍ እንደነበር ክሱ ያብራራል፡፡
ከ1999 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. በተጠቀሱት የተለያዩ ቦታዎች መንቀሳቀሳቸውንና ለጀመሩት የወንጀል ድርጊት ውጥን እንዲረዳቸው፣ ‹‹አልኩፋሩ ቢጣጉት›› የሚል መጽሐፍ እያነበቡ ይዘጋጁ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
አብዱል ዋህድ የተባለው ተጠርጣሪ የአሸባሪው አይኤስን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ግለሰቦችን እንዴት ወደርሱ አስተሳሰብ መለወጥ እንደሚቻል፣ እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት ስለሚደረገው ውይይት የተቀረፁ ድምፅና ምሥል የያዙ ሥራዎችን፣ ለዓላማቸው እንዲረዳቸው በንቃት ይመለከቱ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡
ተከሳሾቹ የአይኤስ ዘጋቢ ፊልሞችን የማየት ግዴታና ኃላፊነት እንዳለባቸውም በትኩረት ሲሠራ እንደነበር አክሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ መቅረባቸውን አረጋግጦ ክስ ለማንበብ ሲዘጋጅ አስተርጓሚ ባለመቅረቡ፣ ክስ ለማንበብ ለጥቅምት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡