ጥቅምት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ረፋዱ ላይ ሰባራ ባቡር አካካቢ ከሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በመከላከያ ምስክርነት ሊቀርቡ ከነበሩት ሦስት እስረኞች መካከል፣ ሁለቱ የማምለጥ ሙከራ ሲያደርጉ አንዱ ሲገደል አንዱ ማምለጡ ተገለጸ፡፡
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሕዝብ ግንኙነት ተወካይ ምክትል ሰርጀንት ሳህለ ገብርኤል ይትባረክ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እስረኞቹ ያመለጡት ፍርድ ቤት ደርሰው ለመውረድ ሲቃረቡ የመኪና በር በመስበር ነበር፡፡ በተለያዩ የውንብድና ወንጀሎች 31 ዓመት የተፈረደበት አንደኛው እስረኛ ሲያዝ፣ በተመሳሳይ ወንጀል የዘጠኝ ዓመት ከስድስት ወራት ፍርደኛ የሆነውና ተጨማሪ ሦስት ክሶች የነበሩበት ሁለተኛው እስረኛ ለማምለጥ ባደረገው ሙከራ ተገድሏል፡፡
እስረኛውን አሳዶ ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ቢሆንም መንደር ውስጥ በመግባቱ ሁኔታዎች አስቸጋሪ በመሆናቸው፣ በመጨረሻ መተኮስ ግድ እንደነበር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ ‹‹እስረኛውን ረዥም ርቀት ተከታትለነዋል፡፡ ላለመተኮስ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን መንደር ውስጥ በመግባቱ የተወሰደው ዕርምጃ የግድ የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡
ለማምለጥ ከሞከሩት ሁለት እስረኞች ጋር በአንድ መኪና ውስጥ የነበረው ሌላ እስረኛ ለመንቀሳቀስ ምንም ዓይነት ሙከራ አድርጎ እንዳልነበር የገለጹት ምክትል ሰርጀንት ሳህለ ገብርኤል፣ ያመለጠውን እስረኛ ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ክትትሉ እየተደረገ ያለው ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ጋር መሆኑንና የእስረኛው ፎቶግራፎችም መበተናቸውንም አክለዋል፡፡
አልፎ አልፎ እስረኞች ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ሲሉ የማምለጥ ሙከራ እንደሚያጋጥም፣ ነገር ግን እስካሁን አምልጦ ሳይያዝ የቀረ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ሪፖርተር የእስረኞቹን ሙሉ ስም በሚመለከት መረጃ ያለው ቢሆንም የሕዝብ ግንኙነት ተወካዩ እንዳይገለጽ ጠይቀዋል፡፡