Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅእየሱሰ ክርስቶስ በተጠመቀበት ዮርዳኖስ ወንዝ ከማርቆስ ወንጌል 1፤9-11 የተወሰደው ጥቅስ በተለያዩ ቋንቋዎች...

እየሱሰ ክርስቶስ በተጠመቀበት ዮርዳኖስ ወንዝ ከማርቆስ ወንጌል 1፤9-11 የተወሰደው ጥቅስ በተለያዩ ቋንቋዎች ተጽፎ ይገኛል፡፡ አማርኛና ትግርኛም ከቋንቋዎቹ ይጠቀሳሉ፡፡

ቀን:

    ባለልኳንዳ

አላየህ ሆኖ’ንጂ ከብት ሆኖ ሲነዳ

ዛሬ ጊዜ ጥሎት ቢሰቀል ልኳንዳ

አጥንቱን ፈላልጠህ አሳየኸው ፍዳ!

ምነው ጨከንክበት?

ከተከትከው በግፍ – በመጥረቢያ ጉልበት

እንዳንተው ፍጡር ነው – ቢነሳው አንደበት

ይታመማል ስጋው፣ ስሜቱ ሲደበት፡፡

ከቶ ማነህ አንተ? ነፍሱን የምትቀማ

በድን አደረከው ‹‹እምቧ!›› ሲል ብትሰማ?

እንዲህ እንደጨከንክ!

ሥጋውን በጣጥሰህ፣ ደሙን እንዳፈሰስክ፣

ለበላተኛ ከርስ – ነፍሱን እንዳፈረስክ፣

ስለት እንደሞረድክ – በጉልበታም ብልጫ

የሥራህን ከፋይ – ለቀረጥከው ቅርጫ

አጥንትህን ከትካች – ይመጣል በሩጫ፡፡

ካሳሁን ወ/ዮሐንስ፣ ማርገጃ፣ 2006 ዓ.ም.

* * *

የሳዑዲ ተዋናይ በሴት አድናቂዎቹ ምክንያት ለእስር በቃ

ኑሮውን ኩዌት ላይ ያደረገው ታዋቂው ሳዑዲ ዓረቢያዊው ተዋናይና የቲቪ ፕሮግራም አቅራቢ አብዱል አዚዝ ካሳር፣ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ሳዑዲን በጐበኘበት ወቅት አንድ የገበያ ማዕከል ውስጥ የሴት አድናቂዎች አጀብ አብዝተሃል በሚል ታስሮ እንደነበር ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡

ካሳር በሪያድ ጉብኝቱ በሴት አድናቂዎቹ ምክንያት ግርግር ተፈጠረበት የተባለውን አል ናኪል የገበያ ማዕከልን እንደሚጐበኝ ቀድሞ በማኅበራዊ ድረ ገጾቹ ላይ አስታውቆ የነበረ ሲሆን፣ አድናቂዎቹ ሌላ ጥሩ የሚሉትን የገበያ ማዕከል እንዲጠቁሙትም ጠይቆ ነበር፡፡

‹‹የገበያ ማዕከሉ ውስጥ እንደገባሁ በአድናቂዎች ተከበብኩኝ፣ በመጨረሻም አንድ ሰው ይዞኝ ከአንድ ክፍል ውስጥ አስገባኝ፤›› ያለው ካሳር፣ መጀመሪያ ስልኩ መወሰዱንና ከዚያም በቁጥጥር ሥር ውሎ በመጨረሻ በዋስትና መለቀቁን ገልጿል፡፡   

* * *

የናይጄሪያ ፖለቲከኞች የአዕምሮ ሕክምና እንዲደረግላቸው ተጠየቀ

የሌጎስ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ምክትል ቻንስለር ፕሮፌሰር ኦይ ኢቢዳፖ ኦቤ፣ ታዋቂው የሬጌ አቀንቃኝ ማጄክ ፋሼክ እንዲሁም በማኅበር የተደራጁ ሳይኪያትሪስቶች፤ የናይጄሪያ ፖለቲከኞች የአዕምሮ ሕክምና እንዲደረግላቸው ጠየቁ፡፡ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ ምሁራኑ ጥያቄያቸውን ለናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሐማዱ ቡሃሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ለፖለቲከኞችና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለሚሠሩ ሠራተኞች የአዕምሮ ሕክምና ማድረግ ግዴታ እንዲሆንም አሳስበዋል፡፡

ፕሮፌሰር ኢቢዳፖ ኦቤ እንደሚሉት፣ የአዕምሮ ሕክምና በማድረግ ማን በሕዝብ አገልግሎት ተቋማት የመሥራት አቅም አለው? የሚለውን መለየት ይቻላል፡፡ ከዚህ ባለፈም ሙስና የአዕምሮ ህመም ምልክት በመሆኑ በፖለቲከኞችና በመንግሥት የሥራ አስፈጻሚዎች ላይ በሚደረግ የአዕምሮ ሕክምና ሙስናን መቀነስ ይቻላል፡፡

* * *

አብዝቶ ቴሌቪዥን ማየት ለሞት እንደሚያጋልጥ በጥናት ተረጋገጠ

‹‹አብዝተው ቴሌቪዥን ባዩ ቁጥር በማንኛውም ምክንያት የመሞት ዕድልዎትን እየጨመሩት እንደሚሄዱ አውቀው ጥንቃቄ ያድርጉ፤›› ሲል የአሜሪካ ናሽናል ካንሰር ኢንስቲትዩት ያደረገውን ጥናት ዋቢ አድርጐ አሳውቋል፡፡

በአሜሪካ ጆርናል ኦፍ ፕሪቬንታቲቭ ሜድስን ጆርናል የሰፈረው ጥናት እንደሚያሳየው፣ በቀን ከሦስት እስከ አራት ሰዓት ቴሌቪዥን የሚያዩ ሰዎች በማንኛውም ህመም የመሞት ዕድላቸው 15 በመቶ ሲሆን፣ በቀን ሰባት ሰዓት የሚያዩት ደግሞ የመሞት ዕድላቸው 47 በመቶ ነው፡፡ ረዥም ሰዓት መቀመጥ በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ሰዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ይመክራል፡፡ ሆኖም ቴሌቪዥን ከመመልከት ጋር ተያይዞ የሚመጣ የጤና ችግርን ለመከላከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዋጋ እንደሌለውና ይልቁንም ቴሌቪዥን ረዥም ሰዓት ከማየት መቆጠብ ወሳኝ እንደሆነ ጥናቱ አመላክቷል፡፡

በጥናቱ ከ50 እስከ 71 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 221 ሺሕ ሰዎች ተሳታፊ ሲሆኑ፣ ሁሉም የጐላ የጤና እክል እንዳልነበረባቸው ዘ ኢንዲፐንደንት ዘግቧል፡፡  

* * *

በቻይና ሁለት ልጅ መውለድ ተፈቀደ

በቻይና እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር ለመቀነስ ታስቦ እ.ኤ.አ. በ1980 የፀደቀው ‹‹አንድ ልጅ ለአንድ ቤተሰብ›› ፖሊሲ ተቀይሮ አንድ ቤተሰብ ሁለት እንዲወልድ ተፈቀደ፡፡

በ2013 ሕጉን በማላላት ለቤተሰባቸው አንድ የሆኑ ልጆች ሁለት እንዲወልዱ የተፈቀደ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ግን ሙሉ ለሙሉ ሕጉ ተቀይሯል፡፡

ፖሊሲው በሥራ ላይ እያለ ሁለት የወለዱ ሰዎች ልጃቸው ተወስዶ የገንዘብ ቅጣትም ይጣልባቸው ነበር፡፡ ከ30 ዓመት በላይ ሲተገበር የቆየው ፖሊሲ፣ በቻይና ልጆች በብቸኝነት እንዲያድጉና ማኅበራዊ ሕይወታቸው እንዲቃወስ መንገድ ይፈጥር ነበር፡፡ የፖሊሲው መሻሻል የታዳጊዎች ባህሪ የተሻለ እንዲሆን እንደሚያግዝ ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡

* * *

የግብርና መንፈሳዊ አባቶች

በኾንሶ ጥብቅ የሆነ የአዝመራ ሥርዓት አለ፡፡ ለመዝራት፣ ለማረም፣ የወፍ ጥበቃ፣ ግሽበት ለመከላከል፣ የእሸት እንኩቶ ለመሰብሰብ፣ ለመውቃት የየራሱ የሆነ ሥርዓቶች አሉት፡፡ ይህንንም የሚከታተሉና የሚያስፈጽሙ፣ ሥርዓቶችንና ወቅቶችን የሚከታተሉ፣ የሚወስኑና የሚያስተባበሩ የግብርና መንፈሳዊ አባቶችና ኤክስፐርቶች አሉ፡፡ ማንኛውም ገበሬ ከዚህ ሥርዓትና ከግብርና መንፈሳዊ አባቶች ውጪ አይሄድም፡፡ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡

  1. ከታ (ባህላዊ የእምነት ሥርዓት የሚመራ)፡- አዝመራ ከተዘራበት ጊዜ ጀምሮ አዝመራ እስከሚወቃበት ጊዜ ድረስ ሥጋ መብላት፣ መታጠብ፣ ፀጉሩን መቁረጥ፣ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም፣ ከራሱ ፓሌታ (የመኖሪያ አካባቢ) ክልል ውጪ መሽናትና ማደር የተከለከሉ ናቸው፡፡ ይህም የሚሆነው ፀረ አዝመራ የሆኑ ነፍሳትን፣ አዕዋፋትን፣ እንስሳትን፣ አውሬዎችን በጸሎትና በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ለመቆጣጠርና ለመከላከል ነው፡፡ ማናቸውም ፀረ ሰብል በአንድ ማሳ ውስጥ ሲከሰቱ ለምን ተከሰተ? መፍትሔውስ ምንድነው? ብሎ ይመረምራል፡፡ ያስመረምራል፡፡ መፍትሔውንም ይፈልጋል፡፡

በፓሌታ ደረጃ አንድ ከታ ይኖራል፡፡ የከታነት ማዕረግ የሚተላለፈው በዘር ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ጥብቅ መስፈርት አለው፡፡ ጨዋ የሆነ ሰው፣ የሰው ነፍስ አጥፍቶ የማያውቅ (የጠላትም ቢሆን)፣ በአካሉ ላይ ፍንክትና ሽርክት የሌለው፣ አካለ ሙሉ የሆነ፣ ማናቸውንም የርክሰት ጸባዮችና ባህሪያት የሌሉበት ተብሎ ይፈተሻል፡፡

በዘር ሲተላለፍ ተተኪው ይህንን የማያሟላ ሰው ከሆነ ከቤተሰቡ ሌላ ሰው ይመረጣል፡፡ መተካካቱንና ምርጫውን የሚያካሂዱት አፓ – ቲምባው (ተወካይ)፣ ኼላው (የወጣት ትልውድ)፣ ሰንቀሊታው (የወጣት መሪ)፣ ኼሊታዎችና የአካባቢ ሽማግሌዎች ናቸው፡፡

  1. ሱጋ፡- የከታ ረዳት ነው፡፡ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከታው የሚፈጽማቸውና የሚያስፈጽማቸው መንፈሳዊና አካላዊ ሥርዓቶች እንዳይቋረጡ ተክቶ ይሠራል፡፡ ከታው ኃላፊነቱ በሚወጣበት ወቅትም በተቻለ መጠን የማገዝና የመርዳት ሥራዎችን ይሠራል፡፡ ሥርዓቱንም ከሞላ ጎደል ይፈጽማል ወይም ይጠብቃል፡፡
  2. ቆሎታ፡- ኅብረተሰቡም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ መሆን አለመሆኑን የሚከታተል፣ መረጃ የሚሰበስብ፣ ሥርዓቱን የሚተላለፍ ሰው ሲገኝ ለከታው የሚያሳውቅ ሰው ነው፡፡ የሚኖረው ከኅብረተሰቡ ጋር ነው፡፡ ከታና ሱጋ የሚፈጽሟቸው መንፈሳዊና አካላዊ ሥርዓቶችን መፈጸም አይጠበቅበትም፡፡
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...