Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየተጨቆኑ ቴአትሮች

የተጨቆኑ ቴአትሮች

ቀን:

በበጎ አድራጎት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነፃ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡ ለሕክምና ወደ ተቋሙ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ የቀዶ ጥገና ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው ይገለጽላቸዋል፡፡ በቀዶ ጥገናው አንድ ኩላሊታቸው እንደሚሠረቅ በአሁኑ ወቅት በብሔራዊ ቴአትር በመታየት ላይ ያለው ‹‹ቅጥጥል ኮከቦች›› ይሳያል፡፡ የኩላሊት ስርቆት የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና በሚሰጥባቸው እንደ ህንድ ባሉ አገሮች በስፋት የሚታይ ነው፡፡

በአገራችን ይህ ሕክምና ከተጀመረ የተቆጠሩት ገና ሳምንታት ብቻ ቢሆንም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ተመሳሳይ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ከማንሳት በዘለለ በቀጣይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የኅብረተሰቡን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት አጀንዳ የሚያደርጉ ቴአትሮች ጉዞ ግን ውጣ ውረድ የተሟላ ነው፡፡ በተመሳሳይ የሚጠቀሰው ‹‹ሰማያዊ ዓይን›› ዘወትር ቅዳሜ አመሻሽ በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት ይታያል፡፡

 ቴአትሩ ትኩረቱን በሙስና ላይ አድርጎ፣ በተለይም መሬትን በሕገወጥ መንገድ ከመሸጥ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡ በቴአትሩ ካሉ ገፀ ባህሪያት አንዱ በከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ይሠራል፡፡ ከመሥሪያ ቤቱ የግለሰቦች ፋይል ሲሰረቅ፣ ባልተገባ መንገድ ግለሰቦች የመሬት ባለቤት ሲሆኑና ሌሎችም ከመሬት ጋር የተያያዙ ውጣ ውረዶች ሲከሰቱ ይታያል፡፡

ቴአትሩን ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተመለከቱት ሙናና አሮን  ደሳለኝ ስለ ቴአትሩ የተለያየ አስተያየት ይሰነዝራሉ፡፡ ‹‹ሰማያዊ ዓይን›› ያነሳው ርዕሰ ጉዳይ ወቅታዊና የአብዛኛው ማኅበረሰብ ጥያቄ የሚንፀባረቅበት እንደሆነ አሮን ይናገራል፡፡

የቴአትሩ ጭብጥ ቁም ነገር አዘል ከመሆኑ ባሻገር የቀረበበት መንገድ የተመልካችን ቀልብ የሚስብ ነው ይላል፡፡ ‹‹ቴአትሩ ሕመማችንን ነው የተናገረልን ከቴአትር ቤቱ ስወጣ ከተማችን ውስጥ ምን እየተከናወነ ነው? ብዬ ራሴን እየጠየኩ ነበር፤›› ሲል ስለ ቴአትሩ ይገልጻል፡፡ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ቴአትሮች በብዛት ቢመለከትም ደስተኛ ነው፡፡

በሌላ በኩል ሙና ቴአትሩን የተመለከተችው አዝናኝ ስለሆነ እንጂ የተነሳው ርዕሰ ጉዳይ እንዳልሳባት ትናገራች፡፡ ቴአትር የምታየው መንፈሷን ዘና ለማድረግ  በመሆኑ ቀለል ያለ ጭብጥ ቢነሳ ትመርጣለች፡፡ በቴአትሮች አስቂኝ ምልልስ ወይም ድርጊት ጣል ካልተደረገ ተመልካቹ ውስን እንደሚሆን ታምናለች፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቴአትር ዙሪያ ከሚነሱ ጉዳዮች አንዱ አብዛኞቹ ለመድረክ የሚበቁ ሥራዎች የኮሜዲ ይዘት ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉ ሥራዎች በስፋት ለተመልካች ሲቀርቡ አይስተዋልም፡፡ ቢቀርቡም እንኳን ምን ያህል ተመልካች ያገኛሉ? ምን ያህልስ ይበረታታሉ? የሚሉ ጥያቄች ይነሳሉ፡፡

አስቂኝ ቴአትሮች ከማዝናናት ባለፈ ቁም ነገር አዘል የሚሆኑበት ጊዜ መኖሩ እሙን ነው፡፡ ቁም ነገር አዘል ሥራዎችም በኮሜዲ ተዋዝተው ይቀርባሉ፡፡ ይዘታቸው ምንም ይሁን ምን መልካም ቦታና ምላሽ ይሰጣቸዋል? የሚለው ጥያቄም ተያይዞ ይነሳል፡፡

አንዳንድ ባለሙያዎች ዘርፉ ክፍተት የሚሰጠው ለአስቂኝ ቴአትሮች እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በተቃራኒው በተለያየ ጊዜ የተሠሩና አስቂኝ ባይሆኑም ለረዥም ጊዜ ተወደው የታዩ ቴአትሮች መኖራቸውን በማጣቀስ፣ ማንኛውም ዓይነት ይዘት ያለው ሥራ አቀራረቡ ካማረ ተወዳጅነት እንደሚያተርፍ የሚያምኑም አሉ፡፡

አሮን አዘውትሮ ቴአትር ይመለከታል፡፡ አንድ ቴአትር ማንኛውንም ዓይነት ጉዳይ ቢያነሳ አቀራረቡ ተመልካችን የሚገዛ ካልሆነ ተቀባይነት እንደማይኖረው ያምናል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ተመልካቾች አስቂኝ ወይም አሳዛኝ ነገር ብቻ ነው የሚስባቸው ብሎ መደምደም ተገቢ አይደለም፡፡ ‹‹ኦቴሎ››፣ ‹‹የጠለቀች ጀንበር››፣ ‹‹ውበትን ፍለጋ›› ማኅበረሰባዊ ጉዳዮችን ካነሱ፣ ‹‹ህንደኬ›› እና ‹‹ቴዎድሮስ›› ከታሪካዊ ቴአትሮች ይጠቅሳል፡፡

 ተመልካች ትኩረት የሚሰጠው ለቴአትር አቀራረብ እንጂ ለሚነሳው ጉዳይ ቅለት ወይም ክብደት እንዳልሆነም ገልጾ፣ ‹‹ባለሙያዎች ተመልካች የሚያዘነብለው ወደ አስቂኝ ቴአትር ነው ብለው ማሳቅ ላይ ብቻ ማተኮር የለባቸውም፤›› ይላል፡፡

 ሙና፣ በተለይ ወጣቶች ቀለል ያለ ይዘት ያላቸውን ቴአትሮች ይወዳሉ ብላ ታምናለች፡፡ በቀደሙት ጊዜያት ቁም ነገር አዘል ጉዳይ የሚያነሱ ቴአትሮች ቢሠሩም፣ አሁን ላይ ቦታ የሚያገኙት ቀለል ያሉት ናቸው ብላ ታስባለች፡፡ ‹‹ፍሬሽ ማን›› እና ‹‹የቀለጠው መንደር›› ከምታነሳቸው ቴአትሮች መካከል ናቸው፡፡

አንዳንዶች አዝናኝ የሆኑ ቴአትሮች እንደሚያስፈልጉ ሁሉ ቁም ነገር አዘል ቴአትሮችም መዘጋጀት እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ደግሞ ከአስቂኝ ቴአትሮች ውጪ ያሉ ሥራዎች ቢቀርቡም እንደማይበረታቱ ያስረዳሉ፡፡ የአብዛኛውን ማኅበረሰብ ነባራዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቁና ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፍን ዓላማ ያደረጉ ሥራዎች የዕይታ ጊዜአቸው አጭር ይሆናል፡፡ የሚያስገኙት ገቢም አነስተኛ ነው ይላሉ፡፡

በ‹‹ሰማያዊ ዓይን›› ከሚተውኑ አንዱ መለሰ ወልዱ፣ አስቂኝ ያልሆነ ነጥብ የሚያነሱ ቴአትሮች ትርፋማ እንደማይሆኑ መታሰብ የለበትም ይላል፡፡ መሰል ቴአትሮች ተመልካች በማይሰላችበት መንገድ ከቀረቡ ትርፋማ የማይሆኑበትም ምክንያት እንደሌለ ይናገራል፡፡ በሙያው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የታሪክ ፍሰትና ቴክኒኮች ናቸው፡፡ በተጨማሪም የአንድ ቴአትር ታሪክ ሁሉንም ሰው የሚነካ ጉዳይ ላይ ሲያጠነጥን ለረዥም ጊዜ ይታያል፡፡

ቴአትር ቤቶች 70/30 የተሰኘ አሠራር አላቸው፡፡ 70 በመቶ በቴአትር ቤቱ ባለሙያዎች የተሠሩ ቴአትሮች ቀርበው፣ የቀረው 30 በመቶ ከቴአትር ቤቱ ውጪ ላሉ ይሰጣል፡፡ መለሰ እንደሚለውም፣ በዚህ ስብጥር አስቂኝ ብቻ ሳይሆኑ የተለያየ ይዘት ያላቸው ቴአትሮች ይበረታታሉ፡፡

ጸሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ጠንካራ ይዘት ያላቸው ቴአትሮች መበረታታት አለባቸው ይላሉ፡፡ መንግሥትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን የመሰሉ ተቋማት ዕውቀት ማስጨበጥ፣ ታሪክ መንገርና መሰል ዓላማ ያላቸው ቴአትሮችን መደገፍ አለባቸው፡፡

እሳቸው ‹‹ኪነ ጥበብ ሕዝቡን መምራት አለበት፤ ባለሙያው ከኅብረተሰቡ ቀድሞ አቅጣጫ ማሳየት አለበት፤›› ይላሉ፡፡ በልዩ ልዩ መንገድ ለማስተላለፍ ተሞክረው ያልተሳኩ መልዕክቶች በኪነ ጥበብ ሲነገሩ ጆሮ ያገኛሉ ብለውም፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ተጠቃሽ የሆኑ ቁም ነገር አዘል ቴአትሮች እንዳሉም ይናገራሉ፡፡

ዛሬ ዛሬ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ከመዝናናት ላለፈ ዓላማ የመጠቀሙ ነገር በመንግሥት፣ በባለሙያውና በተመልካቹም ዘንድ እንደተዘነጋ፣ ለሕዝቡ ጠቀሜታ ያላቸው ሥራዎች እንዲቀርቡ በማድረጉ መንግሥትም ጥበበኞችም የራሳቸውን ድርሻ መውሰድ እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ ተመልካቾችም የሚያዩትን ቴአትር መርጠው፣ ቁም ነገር መቅሰምን አንድ ግብ አድርገው ወደ ቴአትር ቤት ማምራት አለባቸው፡፡

የደራሲያን ሚናን በተመለከተም፣ ‹‹ገንዘብ እናገኝበታለን እንጂ ሕዝብ እናስተምራለን ብሎ የሚነሳ የለም፤›› በማለት ገንዘብ የማግኘት ጥያቄ የቴአትሮችን ይዘት እየወሰነ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሌሎች አገሮች ኪነ ጥበብ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ ከኢትዮጵያ ጋር በማነፃፀርም፣ በአገራችን የኪነ ጥበብ ተልዕኮ ምን እንደሆነ ያጠያይቃል ይላሉ፡፡

አርቲስት አዜብ ወርቁ በበኩሏ፣ የቴአትር ይዘት ባለሙያው ካለው በጀት ጋር እንደሚያያዝ ትናገራለች፡፡ የአገርና የማኅበረሰቡን ችግር የሚያነሱ ባለሙያዎች ድጋፍ ስለማያገኙ ስኬታማ ሲሆኑ አይታይም፡፡ ባለሙያዎች በገቢ ወደሚያዋጣው ዘርፍ የሚሄዱትም አማራጭ በማጣት እንደሆነ ትናገራለች፡፡

የተለየ ይዘት ያላቸው ቴአትሮችን ለማዘጋጀት ከፍተኛ በጀት ያስፈልጋል፡፡ ከተሠሩ በኋላም የሚወጣባቸውን ያህል ትርፋማ አይሆኑም፡፡ ‹‹በጀትና መሰል ጥያቄዎች የደራሲውን ዕይታ ይገድባሉ፤ ቴአትሮቹ ቢበረታቱ ግን ባለሙያውም ለሌላ ሥራ ይነሳሳል፤ አዳዲስ ሐሳብ ላይ ያተኮሩ ሥራዎችም ለተመልካች ይቀርባሉ፤›› ትላለች፡፡

እንደ ‹‹የቴድሮስ ራዕይ›› ያሉ ታሪካዊ ይዘት ያላቸው ቴአትሮችን እንደ ምሳሌ የምትጠቅሰው አዜብ፣ ወጪና ገቢያቸው ሳይመጣጠን አጭር ጊዜ ታይተው ከመድረክ የሚወርዱበት አጋጣሚ እንደተፈጠረ ትናገራለች፡፡ በቀላሉ ሊወደዱ የሚችሉ አስቂኝ ሥራዎች የተበራከቱት በመሰል ቴአትሮች ካለው አሉታዊ ተሞክሮ በመነሳት ነው፡፡ ቴአትሮች አስቂኝ ሳይሆኑ ተመልካች ያገኙበትን ጊዜ በማስታወስም፣ ባለሙያው በድፍረት ሠርቶ ተመልካች ፊቱን አስቂኝ ወዳልሆኑ ቴአትሮች እንዲመልስ ማድረግ እንዳለበት ታምናለች፡፡

አርቲስት ቴዎድሮስ ተስፋዬ በአንድ ወቅት ቴአትር ቤቶች በአጠቃላይ አስቂኝ ቴአትሮችን ብቻ ያሳዩ እንደነበር ጠቅሶ፣ አሁን ለውጥ እየመጣ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በእሱ እምነት፣ የባለሙያዎችም የተመልካቹም አመለካከት እየተቀየረ መጥቷል፡፡

ማኅበረሰባዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ሥራዎች የተሻለ ተቀባይነት እያገኙ ነው፡፡ እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው በቤተሰብ መሀል ስለሚፈጠር መቃቃር የሚያወሳውን ‹‹ከትዳር በላይ›› እና ‹‹ቅጥልጥል ኮከቦች››ን ነው፡፡ እነዚህን ለመሰሉ ቴአትሮች ተመልካች አይገኝም የሚለው አመለካከትም ቀስ በቀስ እየተቀረፈ ነው፡፡ አበረታች ድባብ መኖሩ ሥራዎቻቸው አስቂኝ ስላልሆኑ ገበያውን ሰብረው እንደማይገቡ በማመን ወደ ኋላ ያሉ ደራሲያንንም እንደሚያነሳሳ ይናገራል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡን ባለሙያዎችና ተመልካቾች የተለያየ ይዘት ያላቸው ቴአትሮች ትኩረት ሳቢ ሆነው መቅረብ እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ ቴአትሮች ያላቸው ፋይዳ በይዘት መወሰን እንደሌለበት ይገልጻሉ፡፡ ማኅበረሰቡን ያማከሉና አንገብጋቢ የሚባሉ ጉዳዮችን የሚያነሱ ቴአትሮች እንደሌሎች ሥራዎች መድረክ ቢያገኙ መልካም ነው የሚል ሐሳብም አላቸው፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...