Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከ21 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያስፈልገው የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ

ከ21 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያስፈልገው የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ

ቀን:

በአገሪቱ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ የሚተገበረው የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አዳማ በሚገኘው ገልማ አባገዳ የስብሰባ አዳራሽ፣ ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ ይፋ ሆኗል፡፡ ዕቅዱን ለመተግበርም 21 ቢሊዮን 908 ሚሊዮን 225 ሺሕ ዶላር እንደሚያስፈልግ የዕቅዱ ሰነድ ያመለክታል፡፡

ከዚህም ገንዘብ ውስጥ 33.7 በመቶ ያህሉ ለሰው ሀብት ልማትና ማኔጅመንት፣ 34.7 በመቶ ለጤና መሠረተ ልማቶች እንዲሁም 19.7 በመቶ ደግሞ ለጤና አገልግሎት ጥራት ማሻሻያዎች እንደሚውሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሰባት ምዕራፎች 182 ገጾች ያሉት ሰነድ እንደሚያስረዳው፣ ለዕቅድ ማስፈጸሚያ የሚውለው ገንዘብ የሚገኘው መንግሥት ከሚመድበው በጀት፣ ማኅበረሰቡ በዓይነትና በገንዘብ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ፣ ከጤና ኢንሹራንስና ከውጭ የልማት አጋሮች ነው፡፡

- Advertisement -

የጤናውን ዘርፍ አገልግሎት በጥራት ለሁሉም ማዳረስ፣ የመረጃ አቅምን ማሳደግና በአግባቡ መጠቀም፣ በወረዳ ደረጃ ለውጥ ማስመዝገብ መቻል፣ የሕክምና ባለሙያዎች ሙያቸውን አክብረው ርህራሄና ጥንቃቄ የተሞላበት አገልግሎት ለተገልጋዩ እንዲያበረክቱ ማድረግ በዕቅዱ ከተካተቱ አበይት ጉዳዮች ይገኙበታል፡፡

በሕይወት የመኖር ዕድሜ ጣሪያ አሁን ካለበት 64 ዓመታት ወደ 69 ዓመታት እንዲሁም በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ትብብር አዲስ አበባ ውስጥ የሜዲካል ሲቲና ለሕፃናት ተርቸሪ ሆስፒታል ማቋቋም፣ ለመጀመርያ (ፕራይመሪ)፣ ለሁለተኛ (ሰከንደሪ) ለተርቸሪ (ሦስተኛ) ጤና ተቋማት ተፈላጊ መድኃኒቶች መቶ በመቶ ማሟላት የሚሉትም በዕቅዱ ተካተዋል፡፡

ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር እንዳብራሩት፣ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርማሽን ዕቅድ አካል የሆነው ይኸው የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተለጠጡ ግቦችን አስቀምጧል፡፡ የሕፃናትን ሞት በ70 ከመቶ፣ የእናቶችን ሞት በ75 ከመቶ ለመቀነስ ከ25 ዓመት በላይ የፈጀ ቢሆንም፣ በአምስት ዓመታት ውስጥ ይህን መጠን በግማሽ ለመቀነስ ታቅዷል፡፡

ከተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ወባን ለማጥፋት በዕቅዱ የተካተተ ሲሆን፣ ለተግባራዊነቱም አሠራሮች፣ ሥርዓቶች፣ የሰው ኃይል፣ የምርምርና አቅምን ማጎልበት ላይ የሚሠራ ይሆናል፡፡ የኤችአይቪ በሽታን አሁን ካለበት መጠን ለመቀነስ ማለትም 90 ከመቶ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎችን የመለየት፣ 90 ከመቶ ያህሉን ደግሞ በሕክምና ላይ የማስቀመጥ፣ በሕክምና ከሚቀመጡት መካከል ደግሞ 90 ከመቶ ያህሉን በደማቸው ውስጥ ያለው ቫይረስ በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ማድረግም ይገኝበታል፡፡

የቲቢ በሽታን በተለይም መድኃኒትን የተለማመደ ቲቢን የመለየትና የማከም፣ ይህንን ማድረግ የሚችሉ ተቋማትን የማስፋፋት ጉዳይ በሰፊው የሚሠራበት ሲሆን፣ የሥርዓተ ምግብን ጉዳይ በተመለከተ የዕድገት መቀንጨርን (ስታንቲንግ) በከፍተኛ ደረጃ የመቀነስ ግብ ተቀምጧል፡፡ በተቀመጠውም ግብ መሠረት እ.ኤ.አ. በ2030 ወይም ከ15 ዓመታት በኋላ አንድም ሕፃን የዕድገት መቀንጨር እንዳይገጥመው ወይም የመቀንጨሩ ሁኔታ ዜሮ እንዲሆን ታልሟል፡፡

ትኩረት የሚሹ የቆላና የሐሩር በሽታዎችን ወይም ኔግሌክትድ ትሮፒካል ዲዝዝ የሚባሉትን ትኩረት ሰጥቶ በመሠራት፣ በቀጣዩ አምስት ዓመታት አብዛኞቹን የማስወገድ የሚያደርሱትንም ትልቅ የጤና ችግር የመቀነስ ሥራ ይከናወናል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የትራኮማን በሽታ ተከትሎ የሚመጣና ለዓይነ ስውርነት ሊዳረግ ከሚችለው የዓይን ቆብ ሥር ፀጉር መብቀል ጋር በተየያዘ የቀዶ ሕክምና የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ሆኗል፡፡ በዚህም የተነሳ 670 ሺሕ የሚደርሱ ዜጎች በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ይህን የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ካላገኙ ለዓይነ ስውርነት ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡

ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች እያደጉ፣ ሥርጭታቸውም እያየሉ ነው፡፡ በተለይ በከተሞች አካባቢ ተላላፊ በሽታ ዋነኛ የጤና ችግር እየሆነ ነው፡፡ የተወሰኑት ደግሞ በገጠር አካባቢም ችግር ወደ መሆን ደርሰዋል፡፡ በመሆኑም የመከላከል ፖሊሲን መሠረት ያደረገ፣ በመጀመርያ ደረጃ ጤና አገልግሎት የሚሰጡ ሥራዎችን በሰፊው ለማከናወን በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ውስጥ ተካቷል፡፡

እነዚህ የተለጠጡ ግቦች ሊሳኩ የሚችሉት፣ ዘርፉ ስር ነቀል ለውጥ እንዲያመጣ ከተደረገ ነው፡፡ ለዚህም አራት የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች ተቀምጠዋል፡፡ የመጀመርያው የአገልግሎት ጥራትንና ፍትሃዊነትን ማረጋገጥ፤ ሁለተኛው ዕቅዱንና አገራዊ ስታንዳርዶችን መሠረት አድርጎ የጥራት ቁጥጥር ሥራዎች በየደረጃው እንዲተገበሩ ማድረግ፣ ሦስተኛው ተከታትይነት ያለው የጥራት ማሻሻያ ሪፎርሜሽን መገንባት ሲሆን አራተኛው ደግሞ በጤና ዙሪያ በቂ መረጃ ያለውን ማኅበረሰብ መፍጠር ናቸው፡፡

እስካሁን ድረስ የግል ሕክምና ተቋማት በየዓመቱ ፈቃድ ያወጣሉ፤ ያሳድሳሉ፡፡ ቁጥጥርም ይደረግባቸዋል፡፡ የመንግሥት ሕክምና ተቋማት ግን እንደፈለጉት ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ይቆማል፡፡ የመንግሥት ተቋማትም በየዓመቱ ፈቃድ እንዲያወጡ፣ በደረጃ መሠረት እየሠሩ ስለመሆናቸውም ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ ሙክታር ከድር የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ‹‹ቀጣዩ የአምስት ዓመት የጤና ሴክተር ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የጤናውን ዘርፍ ልማት ወደ ከፍተኛ ምዕራፍ ለማሸጋገር ወሳኝነት ያላቸውን ግቦች የያዘ ነው፡፡ እነዚህን ግቦች በሚገባ ለማሳካት መቻል ጥራቱ የተጠበቀና በላቀ ደረጃ የተደራጀ የጤና ሴክተር ልማትን ለማረጋገጥ ልዩ ትርጉም ያለው ነው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...