ከዓለም ታላቅ አትሌቶች አንዱ የሆነው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በኒው ዮርክ ሮድ ረነርስ የሚዘጋጀው የአበበ ቢቂላ ሽልማት የዘንድሮ ተሸላሚ ሆነ፡፡ ከሠላሳ ሦስት ዓመት በፊት ተሸላሚ ከነበረው ኢትዮጵያዊው ማሞ ወልዴ ቀጥሎ ለዚህ ክብር የበቃ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ሆኗል፡፡
በዓለም በረዥም ርቀት ሩጫ ዓይነተኛና ወደርየለሽ አስተዋጽዖ ላበረከቱ እውቆች የሚሰጠው የአበበ ቢቂላ ሽልማት የዘንድሮ (እ.ኤ.አ. 2015) ተሸላሚው ኃይሌ በታሪክ የመጀመሪያው ማራቶንን ከ2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ በታች የገባ ተጠቃሽ አትሌት አድርጎታል፡፡ በ10 000 ሜትር አራት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን፣ ሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚና የክብረ ወሰን ባለቤትነትን የተቀዳጀው ኃይሌ፣ በአትሌቲክስ ሕይወቱ የዓለም ክብረ ወሰኖችን ከሁለት ደርዘን በላይ ሰባብሯል፡፡
ከረዥም ርቀት ወደ ማራቶን ሲሸጋገርም በአምስተርዳም (እ.ኤ.አ. 2005)፣ በርሊን (2006-2009)፣ ዱባይ (2008- 2010)፣ ፉኮካ (2006) በአሸናፊነት ሲዘልቅ፣ እ.ኤ.አ. በ2007 የኒው ዮርክ ግማሽ ማራቶንን በ59 ደቂቃ 24 ሰከንድ ያሸነፈበት ጊዜ እስካሁን አልተደፈረም፡፡ ኃይሌ ለረዥም ርቀት ሩጫ ስፖርት ላበረከተው እጅግ የላቀ አስተዋጽዖና በስኬታማ የቢዝነስ ሰውነቱ ለዓለም ሯጮች ተምሳሌት በመሆኑ የዘንድሮን የአበበ ቢቂላ ሽልማት እንዲቀበል አስችሎታል፡፡
እንደ ኮምፒተተር ዶት ኮም ዘገባ፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ላቅ ባለው የአትሌቲክስ ተግባሩና ሰብአዊ ክንዋኔው ይሁንታ በመስጠት የዘንድሮውን የአበበ ቢቂላ ሽልማት መስጠቱ እንዳስደሰተው፣ የኒው ዮርክ ሮድ ረነርስ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚሸል ካፒራስ ተናግረዋል፡፡
በሁለት ኦሊምፒኮች በሮም 1952 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1960) እና በቶኪዮ 1957 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1964) በማራቶን ሁለት ወርቅ ሜዳሊያ በድል አድራጊነቱ በተቀዳጀው በኩር (ሌጀንደሪ) አበበ ቢቂላ ስም የተሰየመውና በየዓመቱ የሚካሄደው ሽልማት የተጀመረው በ1971 ዓ.ም. ነበር፡፡ የአዘጋጁ ኒው ዮርክ ሮድ ረነርስ ቀዳሚው ተሸላሚ አሜሪካዊው ቴድ ኮርቢት ሲሆን፣ ከአሜሪካ ውጪ የመጀመሪያው አሸናፊ ቼኮዝሎቫኪያዊው ኤሜል ዛቶፔክ በ1972 ዓ.ም. ሽልማቱን ሲያገኝ፣ በአምስተኘው ዓመት ላይ ኢትዮጵያዊው ማሞ ወልዴ በ1975 ዓ.ም. ታላቁን ክብር አግኝቷል፡፡
ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በሜልቦርን ኦሊምፒክ በ1949 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1956) ስትካፈል ፋና ወጊ አትሌት ከነበሩት አንዱ የሆነው ማሞ ወልዴ የተወዳደረው በ800 ሜትርና በ4 በ400 ሜትር ዱላ ቅብብል ነበር፡፡ በቶኪዮ ኦሊምፒክ በ10000 ሜትር አራተኛ፣ በሜክሲኮ ኦሊምፒክ በ10000 ሜትር ብር ሜዳሊያ ያገኘው ማሞ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያውን አጥልቋል፡፡ በአጭር፣ በመካከለኛ፣ በረዥም ርቀትና በማራቶን ስመጥር አትሌት የነበረው ማሞ ወልዴ በአንድ ኦሊምፒክ ሁለት ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ በማስገኘት በር ከመክፈቱም በላይ በሙኒክ ኦሊምፒክ በ40 ዓመቱ ሮጦ የነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት ታሪክ መሥራቱ ይታወሳል፡፡
የአበበ ቢቂላ ሽልማት በሠላሳ ሰባት ዓመት ታሪኩ አንድ ጊዜ ብቻ (በ2000 ዓ.ም.) ያልተካሄደ ሲሆን፣ ከአፍሪካ እስካሁን ለዚህ ክብር የበቁት ከሻምበል ማሞ ወልዴና ከሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ሌላ ታንዛኒያዊው ጁማ ኢካንጋ (1987 ዓ.ም.)፣ ኬንያዊቷ ቴግላ ሎሩፔ (1992 ዓ.ም.) እንዲሁም ያገሯ ልጅ ፖል ቴርጋት (2003 ዓ.ም.) ይጠቀሳሉ፡፡