Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርማን ነው ምስክሩ?

ማን ነው ምስክሩ?

ቀን:

የአገራችን የዕድገት ጉዞ ዓለም እየመሰከረለት፣ ልበ ቅኖች እያጨበጨቡለት፣ ግፉበት ቀጥሉበት እያሉ ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ ይህ ዕውን እንዲሆን ካገዙት ትልልቅ የመንግሥት የቤት ሥራዎች መካከል ገቢን በቻለው አቅም መሰብሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ለልማቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በሰበሰበው የገቢ መጠን ስለሚለካ ነው፡፡ ይህ የሚያግባባን እውነት ከሆነ፣ በየዘርፉ ከሚስተዋሉ የልማት ውጤቶችና የዕድገት ከፍታዎች ጀርባ የገቢው ዘርፍ ወይም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አለ ማለት ነው፡፡

የሩቁን እንተወውና በ2003 ዓ.ም. መጀመርያ (የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መተግበር ሲጀምር) በአገሪቱ ይሰበሰብ የነበረው የገቢ መጠን 32  ቢሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ በአምስት ዓመቱ ማብቂያ 128 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ የሥራችን ድምር ውጤት ገቢውን የማሳደግ ጉዳይ ሆኖብን መነሻዬ ላይ ላስቀምጠው እንጂ የዚህ ውጤት መገኘት መንስዔዎቹ በርካታ የማሻሻያ ሥራዎች ናቸው፡፡ ከግብር ከፋዩ ጋር የተፈጠሩ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች የአንድ ዓላማ እኩል ባልደረባነት ስሜቶች መጉላታቸው ነው፡፡

ግብር ከፋዩ መጉላላቱ እንዲቀርለት በኤሌክትሮኒክስ ግብር የማሳወቅ (ኢፋይሊንግ)፣ በኤሌክትሮኒክስ ግብር ክፍያ (ኢፔይመንት) ሥራዎች ተዘርግተዋል፡፡ የግብር ከፋዮች ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ታይተው ምላሽ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ለዚህም የትርፍ ክፍፍል ጉዳይን፣ የአስጐብኚ ድርጅቶችንና የልኳንዳ ቤት ባለቤቶችን ጉዳይ ለአብነት ማንሳት ይችላል፡፡

ከእነዚህና ከተለያዩ ዘርፎች ጋር በአሠራር ምክንያት የተፈጠሩ ክፍተቶች በገቢ አሰባሰቡ ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳርፉ ጥረት ተደርጓል፡፡ ውጤትም ተገኝቶባቸዋል፡፡ ይህ የገቢ አስተዳደር ባለሥልጣኑ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ከሚያደርጋቸው ጥረቶች አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ምንም እንኳ እንዲህ ዓይነት ሥራዎች መሥራት ኃላፊነቱ ቢሆንም፣ ከፍ ባለ ደረጃ ለመፈጸም በቻለው መጠን እየጣረ ነው፡፡ ለዚህም ነው የአገሪቱ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ከፍ ያለው፡፡ ለዚህም ነው በራሳችን አቅም የምንሠራቸው በርካታና ግዙፍ ፕሮጀክቶች ዕውን የሆኑት፡፡ ለዚህም ነው ከድህነት እየተላቀቅን ስለመሆኑ የልማት አውታሮቻችን የአደባባይ ምስክር እየሆኑ የሚገኙት፡፡

ይህ ሁሉ በሆነበት ተቋም ውስጥ ሁሉንም ነገር በዜሮ አጣፍቶ በደምሳሳው የመንግሥት ደካማ ተቋም ሊሰኝ የሚችልበት አግባብ የለም፡፡ በሪፖርተር እሑድ ጥቅምት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. የዋለው ዕትም ርዕስ አንቀጽ ይዘቱን በዚህ ሊያስተካክል ወይም ሚዛናዊ አድርጎ ሊያስነብበን ይገባው ነበር፡፡

‹‹ተቋሙ ደካማ በሆነበት እንዴት የአገር ዕድገት ፈጣንና ቀጣይ ይሆናል?›› የሚለውን ጥያቄ ማንሳትም ተገቢ ነው፡፡ የራሳችንን ወጪ በራሳችን ገቢ በመደጎም ከነበረበት ዝቅተኛ አፈጻጸም ወደ 79 በመቶ ያደገው በደካማ አፈጻጸም ነው ሊባል አይችልም፡፡ ምንም እንኳ እጥረት የለውም ለማለት ባንደፈርም፡፡

የነጮችን ወይም የመጽዋቶችን እጅ እያየን የእነሱ የፖሊሲ ማራገፊያ እንዳንሆን ከሀቀኛ ግብር ከፋዮች ጋር በጋራ እየሠራ ያለ ተቋም ቢኖር የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ነው፡፡ እናም ስለምን ደካማ ተቋም ሊባል ይችላል?

የአገሪቱ ኢኮኖሚ በሚፈቅደው ልክ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የአገራችን ሀብት እንዲሆኑ፣ ለአሠራሩም አጋዥ በማድረግ የተቻላቸውን እየጣሩ ካሉት ተቋማት መካከል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አንዱ ነው፡፡

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ግብር ከፋዮቹ እንዳይንገላቱበት ዓመቱን በተለያዩ ግብር መክፈያ ወቅቶች ከፋፍሎ ግብር ከፋዮችን ‹‹ባመናችሁት ክፈሉ›› እያለ እየሠራ ያለ ተቋም ነው፡፡ ይህ የበለጠ ቀላልና ምቹ እንዲሆን ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ባሉበት ሆነው ግብራቸውን እንዲያሳውቁ የሚያስችል ሥርዓት ዘርግቷል፡፡ ይኽም ለግብር ከፋዩና ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ዕፎይታን ፈጥሯል፡፡

ከሌሎች ግብር ከፋዮችም ጋር አለመግባባት እንዳይኖር በየጊዜው ገጽ ለገጽ እየተገናኘ ደረጃ በደረጃ ችግሮችን እየፈታ ያለ ተቋም ነው፡፡ በዚህ የእውነት ማዕቀፍ ውስጥ ግብር ከፋዩ ስለምን ተቋሙን ያማርራል? ስለምንስ ደካማ ሊለው ይችላል? ይህ ማማረር የማን ነው? በአሠራሩ የረኩ ዜጐችስ የሉም? የትኞቹ ያመዝናሉ? ብሎ መመዘን ያለበት ነው፡፡ ግብር ለመሰወር ወይም ለማጭበርበር የሚጥሩ ጥቂት ግለሰቦች የሚሉትን በደፈናው ተቀብሎ ማናፈስን ምን ይሉታል?

ተቋሙ የአገር አለኝታነቱንና ሕዝባዊነቱን የበለጠ ለማጉላት ደግሞ በቅርቡ የተገልጋዮች ቻርተርን አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል፡፡ ይህ በደካማ ተቋም ውስጥ ሊተገበር አይደለም ታሳቢ ሊሆንም አይችልም፡፡ በሪፖርተር ርዕስ አንቀጽ፣ ይህ መረጃ ተደብቀው ወይም ሳይታወቁ ቀርተው አይደለም፡፡ ርዕስ አንቀጹ በተጻፈበት ዕትም  ቀደም ብሎ ባለው ዕትም (ጥቅምት 7 ቀን 2008 ዓ.ም.) የተቋሙን ዋና ዳይሬክተር አነጋግረው ያወጡትን እውነታ በጥቂቱም ቢሆን እዚህ ላይ መጥቀስ አልወደዱም፡፡

የአገር አቅም ሊለካባቸው ከሚችሉ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አቅም ያለበት ደረጃ እንዱ መስሎ ስለታየን ነው ይህን ሁሉ ማለታችን፡፡

ለአንባቢዎችም ሆነ የጋዜጣውን ዝግጅት ክፍል ፖሊሲ ለሚያንፀባርቀው ርዕሰ አንቀጽ እውነታውን ማስረዳት የሚቻለው የተቋሙን ስም እየጠቀሱ ደካማ በማለት ብቻ አይደለምና የደከመበትን ነገሮች ከነተግባሩ ለለውጥ በሚያግዝ መልኩ ለተደራሲያኑ ማቅረብ ጥቅሙ የጋራ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አሠራሮችን በመገምገም ደካማ የሆንኩባቸው ጉዳዮች ናቸው ብሎ የለያቸውን ስድስት የትኩረት መስኮችን አውጥቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዘርፉ ምንም እንኳ ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጠ ቢሆንም፣ ጠንካራ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ችግሩንና ተጋላጭነቱን ለመቀነስ ጥረት በማድረግ እየታገለ ያለ ተቋም ነው፡፡ በዚህም ይበል የሚያሰኝ ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡ ይህንን ስንል ተቋሙ ጉዞውን የጨረሰ ጠንካራ ተቋም ነው ማለታችን እንዳልሆነ አንባቢያን ትረዱናላችሁ፡፡ ይሁንና በአገሪቱ ቀጣይ ዕድገት ውስጥ የባለሥልጣኑ እጅ በረዥሙ ስላለበት ድክመቱን በጥንካሬ እየተካ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ ለዚህ ሁሉ ምስክሩ ሕዝባዊ የልማት ውጤቶቻችን ናቸውና ወደፊት በጥራትም፣ በቁጥርም ጨምረው እንዲገኙ ተቋሙ ጥረቱን ይቀጥላል፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ትምህርትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

*********

ዘገባው ይታረም

በሪፖርተር ቅጽ 21 ቁጥር 1614፣ ጥቅምት 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በወጣው ዕትም ገጽ 1 ላይ ‹‹አክሰስ ሪል ስቴት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ባለመጀመሩ ደንበኞች ሥጋት ውስጥ ገብተዋል›› በሚል ርዕሰ ዜና መቅረቡ ይታወሳል፡፡

በዚህ ዜና ሥር ክፍል 1 ገጽ 54 (በዜናው ዘጠነኛ አንቀጽ) ‹‹ለአክሰስ ሪል ስቴት ግንባታዎች፣ … የአፈር ፍተሻና የሕንፃ ዳግም ዲዛይን ሥራ እንዲሠራ ኢቲጂ ተመርጧል፡፡ ኢቲጂ ይኼንን ሥራ በብድር ለመሥራት የተስማማ መሆኑ ምንጮች ገልጸዋል፤›› የሚል የኩባንያችንን ስም የሚጠቅስ ሐሳብ ተጽፏል፡፡ ይሁን እንጂ ዜናው ከእውነት የራቀ በመሆኑ ይህን ደብዳቤ ለመጻፍ ችለናል፡፡

በዚህ መሠረት ኩባንያችን ኢቲጂ ዲዛይነሮችና አማካሪዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ከአክሰስ ሪል ስቴት ጋር የአፈር ፍተሻና የሕንፃ ዳግም ዲዛይን ሥራ ለመሥራት የተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድና የውል ስምምነት የሌለ መሆኑን፣ እንዲሁም የአንድ ወገን የተዛባ መረጃ ይዞ የኩባንያችንን ይሁንታ ሳይጣራ የተዘገበ ዜና በመሆኑ የተሰማንን ቅሬታ እንገልጻለን፡፡ ኅብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ የማስተካከያ ዕርማት ማሰራጨት አስፈላጊ መሆኑን መግለጽ እንወዳለን፡፡

ስለሆነም ኩባንያችንን አስመልክቶ በዚህ ዜና ውስጥ የቀረበው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን መግለጽ እንወዳለን፡፡

ኢቲጂ ዲዛይነሮችና አማካሪዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...