Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክለሴቶች መብት መከበር የመቆም ፈተና

ለሴቶች መብት መከበር የመቆም ፈተና

ቀን:

ገነት በሽር (ስሟ ለጽሑፉ የተቀየረ) መንግሥት ለዜጎቹ ካስተላለፋቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ ባለድል ናት፡፡ ከድህነቷ የተነሳ በጊዜው ሊከፈል የሚገባውን ቅድመ ክፍያ መክፈል አልቻለችም፡፡ የቅርብ ዘመድም ሆነ አጋር ለችግሯ አልደረሰላትም፡፡ ያላት አማራጭ ሌሎች ተመሳሳይ ድህነት ላይ የሚገኙ ዜጎች ዕጣው ሲደርሳቸው የሚፈጽሙትን ማድረግ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት አንድ ሰውዬ ብር 3,000 ሊሰጣትና ለሁለት ዓመት ቤቱን ያለ ኪራይ እንዲኖርበት በውል ተስማማ፡፡ ሰውዬው ለሁለት ዓመታት በቤቷ ከኖረ በኋላ ለገነት መልሶ ለማስረከብ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ስለዚህ ወደ ፍርድ ቤት ክሷን ይዛ መሄድ ብቸኛ መፍትሔ ሆነ፡፡ የሴቶች ተከራካሪ ድርጅት ረድቷት ክሷን ስትመሠርት ሰውዬው በሰጠው የመከላከያ መልስ ብር 400,000 ስለተበደረች እንድትከፍል የሚል የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ አቀረበ፡፡ ሰውዬው ተጨማሪ ሁለት የብድርና የስጦታ ውል አስፈርሟት ስለነበር እነዚህን ውሎች ማስፈረስ የድርጅቱ ነፃ የሕግ ባለሙያዎች ሥራ ነበር፡፡ ሦስት ዓመታትን ከፈጀ በኋላ በማጭበርበር የተፈፀሙት ሦስት ውሎች እንዲፈርሱ ተደርገው ገነት ቤቷን ተረክባ አዲስ ሕይወት ጀመረች፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ከሚደርስባቸው የመብት ረገጣዎች አንዱን ጠቀስን እንጂ በየዕለቱ የምንሰማው ጥቃትና የመብት ረገጣ ሥራ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው የገነትን ጉዳይ በጽናት በመከታተል ፍትሕ እንድታገኝ የረዳትን የበጎ አድራጎት ድርጅት ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ይባላል፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት መውጣትን ተከትሎ በአገራችን ከተቋቋሙና በስፋት ከሚግታወቁ ተራማጅ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ውስጥ ቀዳሚው ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1995 ተቋቁሞ በ1996 ሥራ የጀመረው ማኅበሩ ያነገበው ራዕይ የኢትዮጵያ ሴቶች በሕገ መንግሥቱና በሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች የተረጋገጡላቸው መብቶች በተጨባጭ ተከብረው ከወንዶች ጋር በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ሁኔታቸው እኩል ሆኖ ማየት ነው፡፡ ራዕዩን ለማሳካትም የሴቶችን መብቶች የሚጥሱ ሕግጋትና ልማዶችን በጥናት ፈትሾ እንዲሻሻሉ ግፊት አድርጓል፣ ኅብረተሰቡ ስለ ሴቶች መብት እንዲያውቅ አያሌ የሥልጠናና የማኅበረሰብ ውይይት ሥራዎችን አከናውኗል፤ ገነትን የመሰሉ አቅም የሌላቸውን ሴቶች ነፃ የሕግ ምክርና በፍርድ ቤት ጥብቅና ቆሞላቸዋል፡፡ ማኅበሩ እነዚህን ሥራዎች የሚሠራው በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳር፣ በአሶሳ፣ በሐዋሳ፣ በአዳማ፣ በድሬዳዋና በጋምቤላ ባሉ ቅርንጫፎቹ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 20 የሕግ ባለሙያዎች ከ280 በላይ በጎ ፈቃደኞች በሥሩ አቅፏል፡፡

ማኅበሩ ከተቋቋመ 20 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በዚህ ሳምንት ዕለቱን በተለያዩ መርሃ ግብሮች አሳልፎታል፡፡ ማኅበሩ አገራችን የሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ባልነበረባት ጊዜያት ለሴቶች መብት የቆመ፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፋዊና አኅጉራዊ ጥምረቶች የወከለ፣ በተባበሩት መንግሥታት የሚቀርቡ የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርቶችን ያዘጋጀና ዝግጅት ላይ የተሳተፈ፣ የምርምር ውጤቶቹን በጆርናል መልክ በማሳተም ፈር ቀዳጅ የሆነ፣ ከብዙ የውጭ ለጋሽ አገሮች ጋር በታማኝነት የሠራና ለብዙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች መብት መመኪያ የሆነ ስለሆነ 20 ዓመቱ ሞልቶ መጎርመሱ ውዳሴ ይገባዋል፡፡

በዚህ ጽሑፍ ማኅበሩ የሠራቸውን ሥራዎች፣ ተፅዕኖአቸውንና ያመጣውን ለውጥ ከመገምገም ይልቅ ጸሐፊው ማኅበሩ ያጋጠሙት ችግሮች ላይ የግል ምልከታ ለማድረግ አስቧል፡፡ በ20 ዓመት የሥራ ዘመኑ የማኅበሩ ፈተናዎች በሁለት ሊካፈሉ ይችላሉ፤ ውስጣዊና ውጫዊ በመባል፡፡ ከውስጣዊ ችግሮች ውስጥ የአባላት ተሳትፎና ቁርጠኝነት ማነስ፣ ማኅበሩ ሥራውን የሚያሰፋበትን አሠራርና የቢሮ ሁኔታ የበጎ አድራጎት ሕጉ እንደሚወጣ ከታሰበበት ጊዜ ጀምሮ በፍጥነት አለመተግበር፣ ተወዳዳሪ ሠራተኞቹን በሥራ ላይ ለማቆየት አለመቻልና የሰው ኃይል ፍሰት ማብዛት፣ የጅማሬውን ያህል በስፋትና በንቃት የግፊት ሥራ አለመሥራት ወዘተ. ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ማኅበሩን እጅጉን የፈተነውና አሁን ድረስ ህልውናውን የሚገዳደረው ውጫዊ ምክንያት ሲሆን፣ በተለይ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት በማኅበሩ ላይ የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ማኅበሩ በካሚላትና በመሳሰሉት ጉዳዮች ኅብረተሰቡን በማንቀሳቀስ በፈፀማቸው የቅስቀሳ ሥራዎች ለተወሰኑ ጊዜያት መታገዱ ይታወሳል፡፡

በጸሐፊው እምነት ግን ማኅበሩ ሥራውን እንደቀድሞው እንዳይሠራ ፈተና የሆነበት ዋና ውጫዊ ችግር በ2001 ዓ.ም. የወጣው የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ ሲሆን፣ አዋጁን ተከትሎ ማኅበሩ 70 በመቶ ሠራተኞቹን ቀንሷል፡፡ ሥራዎቹን አጥፏል፣ እንቅስቃሴውም መቀነሱ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት የራሱ ቢሮ ኖሮት ሥራውን በጥንካሬ እንዳይሠራ ደግሞ የበጎ አድራጎት ኤጀንሲው ያጠራቀመውን ገንዘብ ማገዱ፣ ፍርድ ቤቶችም የኤጀንሲውን ዕርምጃ መደገፋቸው ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የአዋጁን ጠንካራነት ያለርህራሄ በማስፈጸም የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን የጎዳውን ታሪካዊ የሰበር ፍርድ ለመመልከት እንሞክር፡፡

ሕጉና ማኅበሩ

የበጎ አድራጎት ሕጉ ምርጫ 1997 ተከትሎ ከታዩ የሕግ ለውጦች አንዱ ሲሆን፣ አሁን ድረስ ከሕገ መንግሥቱና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ጋር በመጣረሱ ሰፊ ትችት ይደርስበታል፡፡ ሕጉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንና ማኅበራትን ‹‹የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት››፣ ‹‹የኢትዮጵያ ነዋሪዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት›› እና ‹‹የውጭ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› በሚል በሦስት ይከፍላቸዋል፡፡ ክፍፍሉ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አገልግሎታቸውን ለሚፈጽሙበት የሚጠቀሙበትን የገቢ ምንጭ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ወይም ማኅበራት የሚባሉት የገቢ ምንጫቸው ከአገር ውስጥ እንዲያገኙ የተወሰነ ሲሆን እስከ 10 በመቶ ብቻ የሚሆነውን ከውጭ ምንጭ እንዲያገኙ ሕጉ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ሌሎቹ ማኅበራት ግን የገቢ ምንጭ ገደቡ አይመለከታቸውም፤ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት እንዲሠሯቸው የተፈቀዱትን የሰብዓዊና የዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ የሃይማኖት፣ የብሔርና የፆታ እኩልነት፣ የሕፃናትና የአካል ጉዳተኞች መብቶች፣ የግጭት አፈታትና የፍትሕና የሕግ ማስፈፀም አገልግሎቶችን ቀልጣፋነት ማጠናከር ሥራዎችን መሥራት አይችሉም፡፡

የበጎ አድራጎት ሕጉ እንደወጣ 17 አካባቢ የሚሆኑ ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ ተቋማት ሥራቸውን ለውጠዋል፡፡ ማኅበሩና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ ግን አዋጁ የሚያመጣባቸውን ተፅዕኖ ተቋቁመው በተመሠረቱባቸው ዓላማዎች ለመጽናት ወስነዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር አዋጁ በረቂቅነት ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ በሴቶች መብት ላይ በመሥራት ለመቀጠል በመወሰኑ በአዲሱ አዋጅ የተሻለ አገልግሎትን ለመስጠት የተወሰኑ ዝግጅቶችን ጀምሮ ነበር፡፡ ከእነዚህ ሥራዎቹ ዋናው ዕቅድ ከውጭ ለጋሾች ገንዘብ በማሰባሰብ አገልግሎቱን ለማስቀጠልና ወጪ ለመቀነስ የሚያስችለውን የራሱን ቢሮ ለመግዛት ወይም ለመገንባት ማሰቡ ነበር፡፡ በዚሁ መሠረት በጊዜው ወደ 12 ሚሊዮን ብር ያሰባሰበ ሲሆን፣ ቢሮውን ለመግዛት በመንቀሳቀስ በነበረበት ወቅት በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ገንዘቡ እንዳይንቀሳቀስ ታገደበት፡፡ ማኅበሩ ገንዘቡ እንዲለቀቅለት ለኤጀንሲው ቦርድ ያቀረበ ቢሆንም ተቀባይነትን ባለማግኘቱ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት በመጨረሻም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርቦት ተፈርዶበታል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በሰበር መዝገብ ቁጥር 75877 መስከረም 23 ቀን 2005 ዓ.ም. የመጨረሻውን አስገዳጅ ፍርድ የሰጠ ሲሆን፣ ፍርዱ የበጎ አድራጎት ሕጉን በመተርጎም ረገድ ቀዳሚ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ሰበር ችሎቱ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ ላይም ተመሳሳይ ፍርድ በመዝገብ ቁጥር 74036 በተመሳሳይ ቀን የሰጠ ሲሆን፣ በዚህ ጽሑፍ በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ላይ የተሰጠውን ፍርድ መነሻ በማድረግ የተወሰነ ምልከታ ለማድረግ ይሞከራል፡፡ በፍርድ ሒደቱ ከመሰማት መብትና ከኤጀንሲው ቦርድ ሥልጣን ጋር የተያያዙ ጭብጦች የተነሱ ቢሆንም፣ የጉዳዩ ዋና ጭብጥ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001 ዓ.ም. የመፈፀሚያ ጊዜ መቼ ነው? የሚለው በመሆኑ ምልከታው በዚሁ ነጥብ ዙሪያ ይሆናል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ

ጉዳዩ የጀመረው በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር አመልካችነት ለኤጀንሲው ቦርድ በቀረበ አቤቱታ ነው፡፡ ማኅበሩ ከውጭ ካገኘው እስከ 12 ሚሊዮን ብር በጀት በመጠቀም በበጎ አድራጎት አዋጁና ደንቡ መሠረት እስከመጨረሻው መንቀሳቀሱን ገልጾ፤ ኤጀንሲው ታኅሳስ 14 ቀን 2002 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ በማኅበሩ የባንክ ሒሳብ ከነበረው ገንዘብ ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ እንዳገደበት እና 1.6 ሚሊዮን ብር የሚሆነውን እንደለቀቀለት በማመልከቻው ገልጿል፡፡ የበጎ አድራጎት ሕጉ የካቲት 6 ቀን 2002 ዓ.ም. በኋላ ተፈጻሚ እንደሚሆን በኤጀንሲው ተገልጾ፣ በደንቡ አንቀጽ 10 ተረጋግጦ የአዋጁ አፈጻጸም መሸጋገሪያ ጊዜ ተሰጥቶ ባለበት ሁኔታ ኤጀንሲው የማኅበሩን ገንዘብ ማገዱ አግባብነት የለውም በተጨማሪም ማኅበሩ አዋጁ ማኅበሩ ለተገልጋዮች ነፃ አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችለውን ንብረት ለመግዛት ብር 8.6 ሚሊዮን እንደሚያስፈልገው ለኤጀንሲው አቅርቦ እያለና ቀድሞ ይህን እንዳይፈጽም ፍትሕ ሚኒስቴር ምዝገባ በማቆሙ አለመቻሉን ገልጾ፣ በመሸጋገሪያ ጊዜ ለመጠቀም ያቀዳቸውን ተግባራት የኤጀንሲው ዕግድ ያስተጓጎለበት መሆኑን በመግለጽ ዕግዱ ተነስቶ ገንዘቡን እንዲጠቀምበት ይወስንለት ዘንድ ዳኝነት ጠይቋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ተጠሪ የሆነው የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ በበኩሉ በሰጠው መልስ ማኅበሩ በአዋጁ መሠረት የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ሆኖ መመዝገቡንና በመግለጹ አዋጁ ከአሥር በመቶ በላይ ከውጭ ገቢ ምንጭ መጠቀም እንደማይችል ገልጿል፡፡ ማኅበሩ አዋጁ ካፀናበት ከየካቲት 6 ቀን 2001 ዓ.ም. በፊትና በኋላ በርካታ ገንዘብ ከውጭ የገቢ ምንጮች የሰበሰበ መሆኑን፤ አዋጁ ከፀናበት ከዚሁ ጊዜ በኋላ በቀድሞ ሕጎች የተገኙ መብትና ግዴታዎች ተፈጻሚ የሚሆኑት አዋጁን እስካልተቃረኑ ከሆኑ ብቻ ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 111(1) መደንገጉን ገልጾ ገንዘቡን ለተሰማራበት ዓላማ መጠቀም የማይችል መሆኑን ተከራክሯል፡፡ ኤጀንሲው ማኅበሩ ከገንዘቡ ውስጥ በየዓመቱ ከአገር ውስጥ የሰበሰበውን መጠን አሥር በመቶ ከታገደው ገንዘብ እንዲጠቀም መፍቀዱን ገልጾ ማኅበሩ ገንዘቡ እንዲለቀቅለት ያቀረበው ክስ ተገቢ አለመሆኑን ተከራክሯል፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅት ኤጀንሲ ቦርድ የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ የአመልካችን (የማኅበሩን) ክርክር ውድቅ በማድረግ የኤጀንሲው ዕርምጃ ሕጋዊ ነው በማለት ወስኗል፡፡ ማኅበሩ ይግባኙን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን አከራክሮ የቦርዱን ውሳኔ አጽንቷል፡፡ በመጨረሻም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቧል፡፡

የሰበር ችሎቱ አቋም

ጉዳዩን በመጨረሻ የተመለከተው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአብላጫ ድምፅ የሥር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጽንቷል፡፡ ችሎቱ በዋናነት አከራካሪ የነበረውን የበጎ አድራጎት ሕጉ የተፈጻሚነት ጊዜ ከአዋጁ፣ ከደንቡና ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስቴር መጋቢት 16 ቀን 2001 ዓ.ም. በአዋጁ መሠረት ዳግም ምዝገባ እስከሚጀምር የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በነበሩበት እንዲቀጥሉ የጻፈውን ደብዳቤ መሠረት አድርጎ ጉዳዩን መርምሮታል፡፡ አብላጫው ድምፅ ትንተናውን የሰጠው ማኅበሩ መሠረት የሚያደርጋቸው የሕግ ድንጋጌዎች ማለትም የበጎ አድራጎት ሕጉ አንቀጽ 111 እና የደንቡን አንቀጽ 10(2) ነው፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 111(1) ርዕሱ ‹‹የመሸጋገሪያ ድንጋጌዎች በሚል የተቀመጠ ሲሆን ቀድሞ በነበረው ሕግ የተገኘ መብትና ግዴታ አዋጁን እስካልተቃረነ ድረስ እንደሚቀጥል ሲያስቀምጥ ንዑስ ቁጥር ሁለት ደግሞ ቀደም ሲል የተመዘገቡ ማንኛውም የበጎ አድራጎት ድርጅት አዋጁ ከፀናበት ከየካቲት 6 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደገና መመዝገብ ያለባቸው ስለመሆኑ በአስገዳጅ መልኩ ደንግጓል፡፡ የደንብ ቁጥር 168/2001 አንቀጽ 10(2) ደግሞ የድጋሚ ምዝገባ ውጤት ተግባራዊ የሚሆነው ምዝገባው በተጠናቀቀበት ጊዜ ሳይሆን አዋጁ ከፀናበት ከአንድ ዓመት በኋላ ይሆናል ሲል ያስቀምጣል፡፡ ሰበር ችሎቱ እነዚህን ድንጋጌዎች በማገናዘብ ድንጋጌዎቹ ሲታዩ ቅራኔ ያላቸው ናቸው ለማለት የሚቻል ሳይሆን እርስ በርሳቸው የተጣጣሙ እንደሆኑ ይገልጻል፡፡ ‹‹… በመሸጋገሪያ ጊዜው ውስጥ አንድ ኢትዮጵያዊ የሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማኅበር ከውጭ ምንጭ በሕጉ ከተመለከተው የገንዘብ መጠን በላይ እንዲሰበሰብ የሚፈቀድበት አግባብ የለም፡፡ ምክንያቱም የመሸጋገሪያ ድንጋጌ ዓይነተኛ ዓላማ ቀደም ሲል በነበሩ ሕጎች የተገኙ መብቶችና ግዴታዎች አዲስ ሕግ ሲወጣ አከራካሪ እንዳይሆኑ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ግልጽ ምላሽ ለመስጠት ነው ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን፣ ድንጋጌዎቹ አንድ ላይ ሲታዩ ቀደም ሲል ለተገኙት መብቶችና ግዴታዎች ተፈጻሚነት ያጣው ሕግ ተፈጻሚ እንዲሆን ማድረግ  ሳይሆን በአዲሱ ሕግ  እንዲሸፈኑ መደረጉን የሚያስገነዝቡን ናቸው፡፡››

በዚህ መሠረት የሰበር ችሎቱ አራት ዳኞች የበጎ አድራጎት ኤጀንሲው ማኅበሩ በአዋጁ የመሸጋገሪያ ጊዜ ከውጭ ምንጭ በማሰባሰብ ነፃ አገልግሎት ለመስጠት ቢሮ ለመግዛት ማሰቡ አዋጁን የሚቃረን እንደሆነ መደምደሙና ይሄው ገንዘብ ታግዶ በየዓመቱ ማኅበሩ ከአገር ውስጥ የሰበሰበውን ገንዘብ አሥር በመቶ እንዲወስድ ማድረጉ ተገቢ ነው ሲል አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡

የሰበር ችሎቱ የልዩነት ሐሳብ

አብላጫው ድምፅ ከወሰነው ፍርድ በተለየ የልዩነት ሐሳባቸውን በፍርዱ ያሰፈሩት ዳኛ ግራ ቀኙን ባከራከሩት ሁሉም ጭብጦች ላይ ሳይሆን በጉዳዩ ዓቢይ ጭብጥ በሆነው የመሸጋገሪያ ድንጋጌና ሊተረጎምበት የሚገባውን የሕግ አግባብ በሰፊው ተንትነዋል፡፡ የልዩነት ሐሳባቸውን ባሰፈሩት ዳኛ መሠረት የሕግ አውጭው የበጎ አድራጎት ሕጉን ተፈጻሚነት ከነባር ማኅበራትና እንደ አዲስ ከሚመዘገቡት አንፃር የተመለከተው ሲሆን፣ ለነባሮቹ አዋጁ ተፈጻሚ የሚሆነው ከፀናበት ጊዜ ከአንድ ዓመት በኋላ በመሆኑ የችሮታ ጊዜ ሰጥቷቸዋል፡፡ አዋጁን ለማስፈፀም የወጣውም ደንብ በአንቀጽ 10(2) አዋጁ ከመጽናቱ በፊት በተመዘገቡ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ላይ በአዋጁ መሠረት የሚፈፀመው ድጋሚ ምዝገባ ውጤት ተግባራዊ የሚሆነው ምዝገባው በተጠናቀቀበት ጊዜ ሳይሆን አዋጁ ከፀናበት ከአንድ ዓመት በኋላ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ከዚህ አንፃር ዳግም የሚመዘገቡ ነባር የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ላይ አዋጁ ተፈፃሚ የሚሆነው ሕጉ ከፀና ከዓመት በኋላ ማለትም ከየካቲት 6 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ ነው የሚሉት ዳኛው ማኅበሩ በችሮታው ጊዜ የውጭ የገንዘብ ምንጭን መጠቀሙን ሕጉ እንደማይከለክል ይተነትናሉ፡፡››

የልዩነት ሐሳባቸውን ያሰፈሩት ዳኛ ተጨማሪ ሦስት ምክንያቶችን በመግለጽ ማኅበሩ በችሮታ ጊዜው ያሰባሰበውን ገንዘብ ኤጀንሲው ማገዱ ተገቢ አለመሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ የመጀመሪያው የሕግ አውጭው የመሸጋገሪያ ጊዜውን የሰጠበትን ዓላማ በመተንተን ነው፡፡ እንደ ዳኛው አገላለጽ ሕግ አውጭው ሕጉን ያወጣው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 31 መሠረት የተደራጁ ማኅበራት በቀድሞው ምዝገባቸው መሠረት በአጭር ጊዜ የሚያጠናቅቋቸውን ተግባራት እንዲያጠናቅቁ፣ በሕግ ወይም በውል ያገኟቸውን መብትና ግዴታዎች እንዲፈጽሙ ለማስቻል፣ ከአዋጁ በፊት ያፈሩትን ንብረት በድጋሚ ለሚመዘገቡበት ዓላማ ለማመቻቸት እንዲችሉ እንዲሁም ከመመዝገባቸው በፊት ያከናወኗቸውን ተግባራት፣ የሰበሰቡትን ገንዘብና ያለባቸውን ዕዳ በባለሙያ አስጠንተው ግልጽ መረጃ ለማቅረብ እንዲችሉ የችሮታ ጊዜ የሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ይላሉ ዳኛው ሕግ አውጭው ነባር ማኅበራት ፈርሰው እንደ አዲስ እንዲመዘገቡ ባስገደደ ነበር፡፡ ሆኖም የችሮታ ጊዜው ዓላማ ማኅበሩ የሰራውን ዓይነት ዝግጅት እንዲያደርጉ ነው፡፡ ሁለተኛው ዳኛው የኤጀንሲውን ድርጊት በአዋጁ ከተገለጹት ሦስት ዓላማዎች አንፃር ተመልክተውታል፡፡ የአዋጁ ዓላማ ሕገ መንግሥታዊ የዜጎች የመደራጀት መብትን መተግበር፣ ድርጅቶችን መደገፍና ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ማቋቋም ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አዋጁ የችሮታ ጊዜ (የሽግግር ጊዜ) የሰጠው ማኅበራቱ ከአዲሱ አዋጁ ጋር በሚጣጣም መንገድ እንዲደራጁ ነው፡፡ የደንቡም ዓላማ ተመሳሳይ መሆኑን ዳኛው ያብራራሉ፡፡ በዚህ መነሻነትም አዋጁ ተፈፃሚነቱ ለአንድ ዓመት ያህል ማዘግየት ያስፈለገው በመሸጋገሪያ ጊዜ ማጠናቀቅ የሚገባቸውን ተግባር እንዲያጠናቅቁ ዕድል መስጠት መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ ዳኛው በሦስተኛ ደረጃ የሚያነሱት አዋጁ አዲስ ማኅበራት ብር 50,000 ብቻ ማሰባሰብ እንደሚችሉ ሲገልጽ የቆዩ ማኅበራትን በተመለከተ ድጋሚ ሲመዘገቡ በንብረትነት ይዞት ለመመዝገብ ስለሚችለው የገንዘብና የንብረት መጠን የሚገድብ ድንጋጌ አላካተተም፡፡ ከዚህ አንፃር ይላሉ ዳኛው ‹‹በድጋሚ ምዝገባው ማኅበሩ የነበረውን ንብረትና ያጠራቀመውን ገንዘብ ይዞ በድጋሚ ሊመዘገብ እንደሚችልና ኤጀንሲው በሕግ ያልተገደበን ገደብና ሁኔታ ማኅበሩ በድጋሚ ከመመዝገቡ ከአንድ ቀን በፊት በመጣል የአመልካችን ገንዘብ ያገደ መሆኑን ያሳያል፤›› በሚል ፍርዱ ለኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ሊሆን እንደሚገባ በልዩነት ሐሳባቸውን አስፍረዋል፡፡

በፍርዱ ላይ የቀረበ አጭር ምልከታ

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርንና የበጎ አድራጎት ድርጅትና ማኅበራት ኤጀንሲን የሚያከራክራቸው ዋና ነጥብ የአዋጁ የመሸጋገሪያ ድንጋጌ ነው፡፡ አዋጁ በአንድ በኩል ቀደም ሲል የተመዘገቡ ማንኛውም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ይህ አዋጅ ከፀናበት ጊዜ ጀምሮ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደገና መመዝገብ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹አዋጁ ከመወጣቱ በፊት ቀድሞ በነበረው ሕግ የተገኘ መብት ይህን አዋጅ እስካልተቃረነ ድረስ   ይቀጥላል፤›› በሚል ይደነግጋል፡፡ ይህ ድንጋጌ ምክንያታዊና አወንታዊ ትርጉም እንዲኖረው ለማድረግ ከተሞከረ ተፈጻሚነቱ በአዲሱ አዋጅ መሠረት እንደገና በተመዘገቡ ማኅበራት ላይ ከሆነ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ማኅበራቱ ከተመዘገቡ በኋላ በቀድሞው መሠረት የሚቀጥሉላቸው መብቶች በዳግም ምዝገባው ወቅት በአዋጁ ያልተከለከሉት ከሆነ ነው፡፡ ለዳግም ምዝገባ በተቀመጠው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ስለሚኖሩ ወይም ስለሚቀጥሉት መብቶችና ግዴታዎች የሚለው ነገር የለም፡፡ አዋጁ ባልተመዘገቡት ላይ ተፈጻሚነት ስለማይኖረው በተጨማሪም በቀድሞው ሕግ መሠረት ተመዝግበው ይሠሩ የነበሩት እንዲፈርሱ ወይም ሥራቸውን እንዳይቀጥሉ የሚያደርግ ድንጋጌ ባለማስቀመጡ ድርጅቶቹ ባልተሻረው ሕገ ደንባቸውና ከውጭ የተገኘ ገንዘብ ላይ ገደብ በማያደርገው የፍትሐ ብሔር ሕግ መሥራት መቀጠል እንደሚችሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ዳግም ምዝገባ ላከናወኑት ግን የአዋጁ አንቀጽ 111(1) መሠረት መብትና ግዴታው ከአዋጁ እስካልተቃረነ ድረስ መቀጠል እንደሚችል ነው፡፡ ይህ ትርጉም አከራካሪ የሆነውን የአዋጁን አንቀጽ 111 ገጸ ንባብ በመከተል ማንም ሰው ሊደርስበት የሚችል ነው፡፡

አዋጁን ለማስፈፀም የወጣውም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 168/2001 ዓ.ም. የአዋጁ ድንጋጌዎች በቀድሞ ሕግ መሠረት ሲሠሩ የነበሩ በሽግግር ጊዜው ያልተመዘገቡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንና ማኅበራትን በተመለከተ ዝምታ መምረጡን ተከትሎ ጉዳዩን ግልጽ ለማድረግ ድንጋጌ ቀርጿል፡፡ ደንቡ በአንቀጽ 10(2) ‹‹አዋጅ ከመጽናቱ በፊት በተመዘገቡ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ላይ በአዋጁ መሠረት የሚፈፀመው ድንጋጌ ምዝገባ ውጤት ተግባራዊ የሚሆነው ምዝገባው በተጠናቀቀበት ጊዜ ሳይሆን አዋጁ ከፀናበት ጊዜ ከአንድ ዓመት በኋላ ይሆናል፤›› በሚል በተሻለ ግልጽነት ደንግጎታል፡፡ ከዚህ አንፃር ደንቡ ያልተመዘገቡ ግን በቀድሞ ሕግ መሠረት ሥራቸውን ለሚሠሩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች አዲሱ አዋጅ እንደማይሠራ ከመግለጽ ባለፈ በአዲሱ አዋጅ በተመዘገቡትም ላይ ቢሆን ከፀናበት ከአንድ ዓመት በኋላ እንጂ ከተመዘገቡበት ጊዜ ጀምሮ ተፈጻሚ እንደማይሆን ግልጽ አድርጎታል፡፡ ከዚህ አንፃር በአዋጁና በደንቡ መካከል የይዘት ቅራኔ አለመኖሩን የሰበር ችሎት አብላጫው ድምፅ መደምደሙ ተገቢነት ያለው ቢሆንም፣ በሽግግሩ ጊዜ አዲሱ አዋጅ ተፈጻሚ እንደሚሆን የያዘው አቋም ግን በሁለቱም ሕግጋት ያልተገለጸ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ጉዳይን ከፍሬ ነገሩ ለመረዳት እንደሚቻለው ገንዘቡን አሰባስቦ ቢሮ ለመግዛት ባቀደበት ጊዜ በአዲሱ አዋጅ መሠረት ዳግም ምዝገባ አለማከናወኑን ነው፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር የማኅበሩን የሕግ ሰውነት ያላደሰበትን ወራትን ጨምሮ ከታደሰም በኋላ ማኅበሩ ከውጭ ምንጭ ገንዘብ ሲያሰባስብ ይገዛበት የነበረው የፍትሐ ብሔር ሕጉ ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ድንጋጌዎች መሠረት ደግሞ ማኅበሩ ሙሉውን በጀት ከውጭ ምንጭ እንዲያገኝ ስለሚፈቅድለት ገንዘብ መሰብሰቡም ሆነ ቢሮ ለመግዛት መንቀሳቀሱ በሕግ አግባብ የተፈፀመ ነው፡፡

የሽግግሩን ጊዜ ዓላማና በሽግግር ጊዜው ሊፈፀሙ ስለማይገባቸውና ስለሚገባቸው ድርጊቶች አዋጁ የሚለው ነገር የለም፡፡ ከዚህ አንፃር ነባር ያልተመዘገቡ ማኅበራት ሥራቸውን መሥራት የሚቀጥሉ ሲሆን፣ አዋጁ ያልሸፈናቸው በአዲሱ አዋጅ መሠረት ዳግም የተመዘገቡትም አዋጁ ተፈጻሚ የሚሆንባቸው በደንቡ በተደነገገው መሠረት አዋጁ ከፀናበት ከአንድ ዓመት በኋላም ማለትም ከየካቲት 6 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ የሽግግር ጊዜውን ዓላማ ለመረዳት የአዋጁን መግቢያ፣ ከአዋጁ በፊት በመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኅብረት የተደረጉ ውይይቶችን እንዲሁም የፍትሕ ሚኒስቴር በመጋቢት 16 ቀን 2001 ዓ.ም. የጻፈውን ደብዳቤ መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡ በሐሳብ የተለዩት ዳኛ በጥሩ ሁኔታ በተነተኑት መልኩ የአዋጁ መግቢያ የሕጉ ዓላማ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚሠሩትን ሥራ ማጠናከርና የመደራጀት ሕገ መንግሥታዊ መብትንም ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሽግግር ጊዜውም ዓላማ ከዚሁ ጋር ተጣጥሞ መተግበር ይኖርበታል፡፡ የሽግግር ጊዜው በጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲጠፉ፣ እንዲከስሙና ያለሀብትና ንብረት በአዲሱ አዋጅ እንዲገዙ ማድረግ አለመሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡ አዋጁ በይዘቱ ከጨመራቸው የፖሊሲ አቅጣጫ ለውጥ ውጪ በጎ አድራጎት ድርጅቶችን ወዲያውኑ እንዲፈርሱ፣ ያለመ ድንጋጌ ያልያዘ መሆኑን ሁሉም ሊያረጋግጠው ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ የሰበር ችሎቱ ፍርድ ማኅበሩን ቀድሞ ያለውን ሀብት የሚያሳጣ፣ የሰበሰበውን ገንዘብ እንዳይጠቀም የሚከለክል በመሆኑ የአዋጁን ዓላማ የሚያደናቅፍ ነው፡፡

አዋጁ በረቂቅነት በነበረበት ወቅት የተደረጉ ውይይቶች ተመሳሳይ አቋምን የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከቀድሞ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ውይይት በሕጉ የተቀመጠው የአንድ ዓመት የሽግግር ጊዜ የበጎ አድራጎት  ደርጅቶቹ ለአዲሱ አዋጅ አፈጻጸም ራሳቸውን ለማዘጋጀት ተብሎ የተደነገገ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚህ መነሻነት የበጎ አድራጎት ድርጅቶቹ የጀመሩዋቸውን ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ የሽግግሩ ጊዜ እስከ ሦስት ዓመት እንዲራዘምላቸው የጠየቁ ቢሆንም፣ መንግሥት ሳይቀበለው እንደቀረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በዚህ መድረክ እንደተንፀባረቀው የሽግግር ጊዜው ዓላማ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲዘጋጁ ማስቻል እንጂ ባዶ እጅና እግራቸውን ይዘው አዋጁ ጋር እንዲጋፈጡ አለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሰበር ችሎቱ የአብላጫ ድምፅ አቋም መንግሥትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶቹ ከአዋጁ መውጣት በፊት የደረሱበትን መተማመን የሚጥስ ነው፡፡

በመጨረሻም የፍትሕ ሚኒስቴርን ደብዳቤ ለመረመረ የሽግግሩ ጊዜ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚሠሩትን ሥራ እየሠሩ እንዲቀጥሉና በአዲሱ አዋጅ መሠረት የበጀት ምንጭ ጥያቄ በፌዴራልም ሆነ በክልሎች እንዳይነሳባቸው ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኤጀንሲው የማኅበሩን ገንዘብ አዋጁ መፈፀም ሳይጀምር ለመቆጣጠር ጥረት ማድረጉ፤ ድርጊቱንም የሰበር ችሎቱ አብላጫ ድምፅ መደገፉ አግባብነት የለውም፡፡

በአጠቃላይ ሰበር ችሎቱ በማኅበሩ ላይ የሰጠው ፍርዱ የበጎ አድራጎት አዋጁን ከሕግ አውጭው መንፈስ በራቀ መልኩ የተረጎመ ነው፡፡ የሐሳብ ልዩነታቸውን ያሰፈሩት ዳኛ ከድንጋጌዎቹ ይዘት፣ ከወጡበት ዓላማ እንዲሁም ከሕገ መንግሥቱ የመደራጀት መብት አንፃር የተነተኑት አቋም ለጸሐፊው የተሻለ አሳማኝ ነው፡፡ ፍርዱ ታሪካዊ ነው፡፡ የበጎ አድራጎት ሕጉ የሚሰጥበትን የሰላ ትችት የበለጠ ፍርድ ቤት ያጠበቀው መሆኑን አስረጂ ነው፡፡ ፍርዱ ፍትሐዊ ሆኖ በሐሳብ የተለዩትን ዳኛ አቋም ቢከተል ኖሮ ማኅበሩ ለጭቁን ሴቶች የሚሠራውን ሥራ በተሻለ ባስቀጠለ ነበር፡፡ ያ ግን አልሆነም፡፡ ለጸሐፊው ይህ ፍርድ ማኅበሩ ከገጠሙት ፈተናዎች ሁሉ የከፋው እንደሆነ ያምናል፡፡ ያለፉት ሰባት ዓመታት ማኅሩን በቀድሞው ጥንካሬና ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ ያላየነው በፍርዱ ምክንያት መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ መንግሥት ግን ከፍርድ ቤት አቋም መለስ ለጭቁን ሴቶቹ በማሰብ ለመብታቸው የሚከራከረውን ማኅበሩን የሚያግዙ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ማኅበሩ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕፃናት ከለላ ፕሮጀክት፣ ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ከዓለም ባንክና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የሚተገብራቸው ፕሮጀክቶች ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ በተለይ የዓለም ባንክና የአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ እንደ አገር ውስጥ የገንዘብ ምንጭ መቆጠራቸው ማኅበሩ በቀጣዮቹ ዓመታት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲወጣ እንደሚያደርገው ጸሐፊው ያምናል፡፡        

ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...