Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉእስኪ በጂዲፒው ትንሽ እንቀልድ

እስኪ በጂዲፒው ትንሽ እንቀልድ

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

ጂዲፒ የሚለውን የእንግሊዝኛ ምህፃረ ቃል ምንነት ብዙ ሰው ያውቀዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ጂዲፒ (Gross Domestic Product-GDP) ማለት ሲሆን፣ የአማርኛ ትርጉሙ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ማለት ነው፡፡ እንደ እንግሊዝኛው አማርኛውንም በምሕፃረ ቃል አሳጥረን (ጥአውም) ብለን መጥራት እንችላለን፡፡ ይህ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ለሕዝቡ ቁጥር ሲካፈል የሕዝቡን ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢን (Per Capital Income) ይሰጠናል፡፡

ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢ ዋናው የድህነት ቅንሳ መለኪያ አመልካች መረጃ ስለሆነ፣ ከዚህ ቀልድ በኋላ ዘወትር የሚወራለትን የድህነት ቅነሳውን መጠን ያሰሉ ሰዎች ቀልዴን ማስተባበል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ግን የድህነት ቅነሳ መረጃቸውን የሚያምን የሐበሻ ልጅ የለም፣

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በአንድ በተወሰነ ወቅት ብዙ ጊዜ በዓመት በአገር ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች በገበሬው፣ በወዛደሩ፣ በፀጥታ አስከባሪው፣ በመከላከያ ሠራዊት አባሉ፣ በዳኛው፣ በጋዜጠኛው፣ በመምህሩ፣ በሐኪሙ፣ በቢሮ ሠራተኛው፣ በነጋዴው፣ በሙዚቀኛው፣ በፀጉር አስተካካዩ፣ በቤት ሠራተኛው፣ በሾፌሩ፣ በዘበኛው፣ በጫማ አሳማሪው፣ በዳንስ አስተማሪው፣ በጭፈራ ቤት ሥርዓት አስከባሪው፣ ወዘተ. ተመርቶ በሸቀጥ መልክ ለገበያ የቀረበ ወይም ለገበያ እንደቀረበ ተቆጥሮ ዋጋው የተተመነ ቁሳዊ ዕቃና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ነው፡፡

ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በገንዘብ ዋጋ በሁለት መልክ ይለካል፡፡ አንዱ ምርቱ በተመረተበት ዓመት የገበያ ዋጋ መለካት ሲሆን፣ ሁለተኛው የዋጋ ንረትን በምርቱ ልኬት ውስጥ ላለማስገባት በአንድ በተመረጠ ዓመት ቋሚ ዋጋ አማካይነት የተከታታይ ዓመታት ምርት መጠንን መለካት ነው፡፡

ምሥለ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (Nominal GDP) ምርቱ በተመረተበት ዓመት የገበያ ዋጋ (Current Market Price) የተለካ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ሲሆን፣ በየዓመቱ የሚከሰተውን የዋጋ ንረት ስለማይጨምርም በዋጋ ንረት ያልተበከለና ያላበጠ ምርት መጠን ነው፡፡

እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (Real GDP) በአንድ በተመረጠ ዓመት ቋሚ የቀድሞ ገበያ ዋጋ (Constant Market Price) የተለካ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ሲሆን፣ በየዓመቱ የሚከሰተውን የዋጋ ንረት ስለማይጨምርም በዋጋ ንረት ያልተበከለና ያላበጠ ምርት መጠን ነው፡፡

የሁለቱን ዓይነቶች ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን አለካክ አቅልሎ ለመረዳት በምሳኔ እንመልከት፡፡

አንድ ገበሬ አምና ስምንት ኩንታል ስንዴ አምርቶ እያንዳንዱን ኩንታል በአንድ ሺሕ ብር ቢሸጥ፣ የስምንት ሺሕ ብር ምርት አመረተ ማለት ነው፡፡ ዘንድሮ አሥር ኩንታል ምርት አምርቶ እያንዳንዱን ኩንታል በሺሕ ሁለት መቶ ብር ቢሸጥ፣ የአሥራ ሁለት ሺሕ ብር ምርት አመረተ ይባላል፡፡

የአምናው ኩንታል ምርት በአንድ ሺሕ ብር ዋጋ ተለክቶ የዘንድሮው ኩንታል ምርት በሺሕ ሁለት መቶ ብር ዋጋ መለካቱ፣ የዘንድሮውን ምርት መጠን የዋጋው ንረት አሳብጦታል፡፡

የአምናው ስምንት ኩንታል ምርትና የዘንድሮው አሥር ኩንታል ምርት በተመሳሳይ የአምና ቋሚ ዋጋ አንድ ሺሕ ብር ቢለኩ፣ ገበሬው ዘንድሮ ያመረተው ምርት መጠን አሥራ ሁለት ሺሕ ብር ሳይሆን አሥር ሺሕ ብር ነው፡፡ በአምናው ቋሚ ዋጋ የተለካው የዘንድሮ ምርት መጠን በዋጋ ንረት አልተበከለም፡፡

በኢትዮጵያ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ የየዓመቱ እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በ1992 ዓ.ም. ቋሚ የገበያ ዋጋ ሲለካ ቆይቷል፡፡ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ግን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ወደ 2003 ዓ.ም. ቋሚ የገበያ ዋጋ ተከልሷል፡፡

ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ ባሉት ዓመታትም እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት እየተለካ ያለው፣ በ2003 ዓ.ም. ቋሚ የገበያ ዋጋ አማካይነት ነው፡፡ የዚህ አንድምታ ምን እንደሆነ ቀጥለን እንመልከት፡፡

በጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ቋሚ ዋጋ ከ1992 ወደ 2003 ዓ.ም. መከለስ ምክንያት፣ የ2003 ዓ.ም. እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ከ1992 እስከ 2003 ዓ.ም. ነበሩት የየዓመታቱ ዋጋ ንረቶች ተበክሎ አብጧል፡፡

ስለሆነም በዋጋ ንረት ተበክሎ ያበጠው የ2003 ዓ.ም. እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት፣ በ1992 ዓ.ም. ቋሚ ዋጋ የተለካውን የ2003 ዓ.ም. እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ሦስት እጥፍ ሆኗል፡፡

እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በመነጨበት ዘርፍ በ1992 እና በ2003 ዓ.ም. ቋሚ ዋጋዎች በቢሊዮን ብር

 

ዘርፍ

የ2003 ዓ.ም. ምርት መጠን

የሁለት ልኬቶች ንፅፅር

 

በ1992 ዋጋ

 

በ2003 ዋጋ

ግብርና

64.7

212.5

3.3 እጥፍ

ኢንዱስትሪ

21.2

49.8

2.3 እጥፍ

አገልግሎት

73.4

207.2

2.8 እጥፍ

ጠቅላላ

157.5

469.5

3.0 እጥፍ

ነፍስ ወከፍ ገቢ

1946

6267

3.2 እጥፍ

 

   ምንጭ፡- የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

የሕዝቡ ኑሮ የአዲሱን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ያህል ሦስት እጥፍ አደገ ማለት ነው? ወይስ ለቆጠራ ያህል ብቻ የሚያገለግል የወረቀት ላይ ዳማ ጨዋታ ነው? ጥያቄ የሚያጭር ጉዳይ ነው፡፡ ባለሙያዎችም ሆኑ ሕዝብ አጽንኦት ሰጥተው ሊወያዩበት ይገባል፡፡

የአገር ውስጥ ምርቱ መለኪያ ቋሚ ዋጋ ከ1992 ወደ 2003 ዓ.ም. በመቀየሩ ምክንያት፣ በወረቀት ላይ በሚጻፉ ቁጥሮች ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ቅጽበታዊ ሦስት እጥፍ የዘለለ ነፍስ ወከፍ ገቢን ማሳደግና ድህነትን መቀነስ ይቻላል ማለት ነውን?

በሠንጠረዡ ላይ እንደተመለከተው የ2003 ዓ.ም. ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን በ1992 ዓ.ም. እና በ2003 ዓ.ም. ቋሚ ዋጋ አለካክ ሲነፃፀር የግብርናው ምርት መጠን በ3.3 እጅ በልጧል፡፡ የኢንዱስትሪው ምርት መጠን በ2.3 እጅ በልጧል፡፡ የአገልግሎት ምርት መጠን በ2.8 እጅ በልጧል፡፡ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን በ3.0 እጅ በልጧል፡፡ ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢ 3.2 እጅ በልጧል፡፡

ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሁሉም አገሮች በየተወሰኑ ዓመታት እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ቋሚ ዓመቱን ይከልሳሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የብሔራዊ ኢኮኖሚ ልኬት መርህም ተቀባይነት ያለው አሠራር ነው፡፡

ናይጄሪያም ካቻምና የቋሚ ዋጋ መለኪያ ዓመት ከልሳ 510 ቢሊዮን ዶላር እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን በማስመዝገብ፣ ቀደም ሲል በ375 ቢሊዮን ዶላር ከአኅጉሪቱ በአንደኝነት ደረጃ ስትመራ የነበረችውን ደቡብ አፍሪካን በልጣ፣ ከአፍሪካ ቁጥር አንድ ግዙፍ ኢኮኖሚ ተብላለች፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ጉዳይ እንመለስና ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠኑን ያሳበጠው የቋሚ መለኪያ ዓመቱ መከለሱ በራሱ ብቻ ሳይሆን፣ ከክለሳው በፊት የነበሩት እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ንረቶች በክለሳው ውስጥ በመካተታቸው ነው፡፡

የዋጋ ንረት መጠነኛ በሆነበት ኢኮኖሚ ውስጥ የመለኪያ ቋሚ ዓመቱ መከለስ ብዙ ለውጥ አያስከትልም፡፡ የዋጋ ንረት ከፍተኛ በሆነበት ኢኮኖሚ ውስጥ ግን የመለኪያ ቋሚ ዓመት ክለሳው የአገር ውስጥ ምርት መጠንን ከልክ በላይ ያሳብጠዋል፡፡

በሠንጠረዡ እንደምንመለከተው በተከለሰው በ2003 ዓ.ም. መለኪያ ዓመት ቋሚ ዋጋ የተለካው የ2003 ዓ.ም. 469.5 ቢሊዮን ብር እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት፣ በ1992 ዓ.ም. መለኪያ ዓመት ቋሚ ዋጋ ከተለካው የ2003 ዓ.ም. 157.5 ቢሊዮን ብር እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በሦስት እጥፍ ይበልጣል፡፡

በተከለሰው የ2003 መለኪያ ዓመት ቋሚ ዋጋ የተሰላውን የ2003 ዓ.ም. 6,267 ብር ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢ በ1992 ዓ.ም. መለኪያ ዓመት ቋሚ ዋጋ ከተለካው የ2003 ዓ.ም. 1,946 ብር ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢ ጋር ስናነፃፅር ልዩነቱ ከሦስት እጥፍ በላይ ነው፡፡

በቋሚ መለኪያ ዓመት ክለሳው ምክንያት ጥቅል የአገር ውስጥ ምርትና ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢ በወረቀት ላይ በሚታይ ቁጥር ደረጃ፣ ወደ መካከለኛ ኑሮ ደረጃ በፍጥነት እየተጠጋ ነው፣ ድህነትም በፈጥነት እየቀነሰ ነው፡፡

አብዛኛው ሕዝብ ግን በዋጋ ንረት ምክንያት ኑሮው በማዘቅዘቁ ከመካከለኛው ኑሮ ደረጃ እየራቀና እየደኸየም ነው፡፡ ወረቀቱ ነው ስለኑሯችን የሚመሰክረው? ወይስ የገሀዱ እውነታ ነው?

የየዓመቱ ገደብ የለሽ ዋጋ ንረቶች ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭንቀቶችና ስቃዮች ናቸው፡፡ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርትንና ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢን በፍጥነት አሳድገው በፍጥነት መካከለኛ ገቢ ውስጥ ለማስገባት ሆነ ድህነትንም ለመቀነስ፣ ሩቅ አልመው ሩቅ ለማደር ለሚተጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ባለሙያዎች በደስታ ጮቤ የሚያስረግጡ ናቸው፡፡

ቋሚ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ዓመት በየአሥር ዓመቱ ስለሚከለስም በ2013 ዓ.ም. እንደገና ተከልሶ፣ የምርት መጠኑና ነፍስ ወከፍ ገቢው ሦስትና አራት እጥፍ አድገው እንደታለመው በቅርብ ዓመታት ድህነትን ለማጥፋት ወደ መካከለኛ ገቢ መጠን መቃረብም ይቻላል፡፡

በ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት የኢትዮጵያ እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት አሥር ቢሊዮን ብር ገደማ ነበር፡፡ የ2003 ዓ.ም. 460.5 ቢሊዮን  ከ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት አሥር ቢሊዮን ብር አካባቢ ጋር ሲነፃፀር ሃምሳ እጥፍ ግድም እንደሆነ ይታያል፡፡

እንግሊዝ በኢንዱስትሪ አብዮቷ ዘመን ኢኮኖሚዋን እጥፍ ለማድረግ ስልሳ ዓመታት ፈጅቶባታል፡፡ አሜሪካ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ገደማ ኢኮኖሚዋ መመንጠቅ ሲጀምር፣ ኢኮኖሚዋን እጥፍ ለማድረግ ሃምሳ ዓመታት ፈጅቶባታል፡፡ በፍጥነት ያደጉት የምሥራቅና የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮችም ኢኮኖሚያቸውን እጥፍ ለማድረግ እስከ አሥር ዓመታት ፈጅቶባቸዋል፡፡

የእኛን አገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከእነዚህ አገሮች ዕድገት ታሪክ ጋር ስናነፃፀር የኤሊና የጥንቸል ሩጫ ውድድር ይመስላል፡፡ እነርሱ ኤሊዎቹ እኛ ጥንቸሏ ነን፡፡ ይህ የሚታመን መረጃ ነውን? በኢኮኖሚ ጥናት ሳይንስ ሊረጋገጥ ይችላልን?

የኃይሌ ገብረ ሥላሴና የኢትዮጵያ ታሪክ እየተመሳሰለ ነው፡፡ ኃይሌ አቅሙ ደክሞ ሩጫውን ሲያቆም የመኪና አስመጪ ኩባንያ ከፈተ፡፡ ኢትዮጵያም የኢኮኖሚ ዕድገት ሩጫዋን ጨርሳ ይሆናል፣ የመኪና አስመጪ ኩባንያ እየመሰለች ነው፡፡

እንደ የዓለም ባንከ፣ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሁኔታውን ያውቃሉ ወይስ አያውቁም? አውቀውስ ተቀበሉት ወይስ አልተቀበሉትም?

አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ከማወቅም አልፈው አምነው ተቀብለው መዝግበውታልም፡፡ የአገሮችን መረጃዎች አጣጥለው በዚህ ሳቢያ በትውውቅና በሹመት የተገኘ ሥራቸውንና ወፍራም ደመወዛቸውን ከሚያጡ አዎን ብለው አጨብጭበው መቀበሉን ይመርጣሉ፡፡ ማን ለማን መስዋዕት ይሆናል?

አገሮችም አንዱ የሌላውን መረጃ ለማጣጣልና ላለመቀበል ወኔው የላቸውም፡፡ ከሶቭየት ኅብረት መውደቅና ከቀዝቃዛው ጦርነት ፍፃሜ በኋላ የመጣ ተቻችሎና ተግባብቶ የመኖር የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የመንግሥታት ዘይቤ ነው፡፡

ይህ የድርጅቶችና የመንግሥታት መቻቻል ሕዝቦች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ድህነት ይብቃን የሚያጠግቡን ይምሩን እንዳይሉ አደረጋቸው፡፡ ድምፃቸው የወሬ ቋቶች መገናኛ ብዙኃን በእጃቸው በሆኑ የአገሮች ባለሥልጣናትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሹማምንት ተቀማ፡፡

ሰሞኑን የቻይናው ፕሬዚዳንት እንግሊዝን ሊጎበኙ ከእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በቢቢሲ ጋዜጠኛ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዴት ዴሞክራሲያዊ ካልሆነችና ሰብዓዊ መብት ከማታከብር አገር ጋር እንግሊዝ ተባብራ ለመሥራት ወሰነች ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ፣ የኢኮኖሚ ትብብሩ ቻይናን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግም ይረዳል ነበር ያሉት፡፡ ተኮራርፎና ተበጣብጦ አብሮ መኖር የአገርን ጥቅም ለማስጠበቅ አይጠቅምም ማለታቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያ በራሷ እምነትና መንገድ ኢኮኖሚዋን በዚህን ያህል መጠን አሳድጌአለሁ ብትል፣ ይህ አለካክ ትክክል አይደለም የሚልና የሚያጣጥለው የትኛው የሕዝብን ጉዳይ ከራሱ ጥቅም የሚያስቀድም ዓለም አቀፍ ድርጅት ወይም አገር ነው?

በጥቂቱም ቢሆን ወኔው ያላቸውና መጻፍ ካስፈለጋቸው የሚጽፉትና በሳይንሳዊ መንገድ የሚተነትኑት አንዳንድ ታዋቂ የኢኮኖሚክስ ጥናት ተመራማሪ ዩኒቨርሲቲዎችና የአንድ አገር የኢኮኖሚ ተመራማሪ ግለሰቦች ናቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፡፡ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

  

       

  

  

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...