Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትምሕረት የመስጠት የመንግሥት ሥልጣን የማን ነው?

ምሕረት የመስጠት የመንግሥት ሥልጣን የማን ነው?

ቀን:

   በበሪሁን ተሻለ

‹‹የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በሚገዛው አገር ላይ ያለው ሥልጣን በጣም የተስፋፋ፣ ወሰን የሌለው ነው፡፡ በሥጋዊም በመንፈሳዊም ሥራ ሁሉ ይገባል፡፡ ከፍ ባለው ሥልጣኑም ይሾማል፣ ይሽራል፣ ይሰጣል፣ ይነሳል፣ ያስራል፣ ይፈታል፣ ይቆርጣል፣ ይገድላል፣ ይምራል፣ ይህንንም የመሳሰለውን ሁሉ ይፈጽማል፡፡

‹‹ሕዝቡም ከትልቅ እስከ ትንሽ ንጉሥ የእግዚአብሔር እንደራሴ ነው በማለት ያለቅሬታ ትዕዛዙን ሁሉ በደስታ ይቀበላል፡፡ በማንም አገር ቢሆን ንጉሥ እንደ ኢትዮጵያ የሚከበርበትና የሚወደድበት ያለ አይመስለኝም፡፡ ስሙ እንኳ ያንቀጠቅጣል፡፡ ምንም ጌታ ወይም ጐበዝ ቢሆን በንጉሡ ቁም ሲሉት የሚሄድ ንጉሥ ይሙት ብሎ በተፈጠመበት ቀን የሚቀር፣ በተዋዋለበት የማይፀና ይገኝ አይመስለኝም፡፡

- Advertisement -

‹‹ክቡር በሆነውም በጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የቃል ኪዳኑ ዋናው ማሰሪያ ንጉሥ ይሙት ነው፡፡ በአገራችን በኢትዮጵያ የንጉሥ ቃል በጣም ከመፈራቱ የተነሳ ሕዝቡ በንጉሡ ቁም ሲባል እንኳን ሰው ፈሳሽ ውኃ ይቆማል እያለ ምሳሌ ይሰጣል፡፡››

ይህ በብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል የታሪክ ማስታወሻ (ዝክረ ነገር) መሠረት የኢትዮጵያ ንጉሥ ‹‹ሥልጣን›› ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ንጉሠ ነገሥቱን ወይም መንግሥቱን ከበላይ ሆኖ የሚያዝና የሚመራ›› የተጻፈ ሕገ መንግሥት ከመውጣቱ በፊት፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ለመቼውም የንጉሠ ነገሥት መንግሥት ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ባለሙሉ ሥልጣን ነው፡፡ ገዥነቱም በሕግ አወሳሰን ነው፤›› ሳይባል አስቀድሞ፣ ‹‹ንጉሡ ባለሙሉ ሥልጣን ሆኖ በአገሩ ምንም የተለየ ልማድ ወይም ደንብ ሳይኖርበት እብሪቱ ብቻ በየቀኑ የመራውን ሐሳብ እንደፈቀደ እንደ ባህርይው ድንገተኛ መለዋወጥ እየለዋወጠ ያደርጋል፣ ያለፍርድ ይቀጣል፣ ይገድላል ይሰቅላል፤›› የሚባልለት ዓይነት ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ንጉሥ ከዚህ ሻል ያለና የተለየ ነው ቢባል ግፋ ቢል፣ ‹‹ንጉሡ ባለሙሉ ሥልጣን ሆኖ በትክክል ተለይቶ የተጻፈ ሕግ ሳይኖረው ከትውልድ እየተሸጋገረ በቆየው ልማድ ይሠራል፡፡ ቅጣትም ምሕረትም ለማድረግ፣ ለመሾም ለመሻርም፣ በአደባባይ በጉባዔ እያስፈረደ፣ በክብር እየሸለመ፣ በገሀድ እያሳወጀ ነው፡፡ ድንገት በደል ነገር ቢሠራ ማገጃ አልተደረገለትም፤›› ብለው (የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የተጻፈ ሕገ መንግሥት መሐንዲስ የሆኑት በጅሮንድ ተከለ ሐዋርያት) የገለጹት ዓይነት ነው፡፡

ከ1923 ዓ.ም. ወዲህ ንጉሠ ነገሥቱንም፣ መንግሥቱንም ጭምር ‹‹ከበላይ ሆኖ የሚያዝና የሚመራ›› ሕገ መንግሥት ‹‹ተሰጠ››፡፡ በዚህ መሠረት ‹‹ሕግ የማይተላለፉት ወሰን ነው፤›› ተባልን፡፡ ሕግ የሚፈርሰው ወይም የሚታደሰው በሌላ ሕግ መሆኑን፣ ሕግ የሚወሰነው በጽሕፈት እንደሆነ፣ ከዚህም በላይ ሕግ ‹‹ደምሳሹ ኃይል ነውና ከወሰን እስከ ወሰን ከጠረፍ እስከ ጠረፍ ድረስ የአንዱን መንግሥት አገርና ሕዝብ›› እንደሚያዝ ተሰበከ፡፡

ከ25 ዓመት በኋላ ደግሞ (በ1948 ዓ.ም.) ከሌሎች መካከል ‹‹ከብዙ ዘመን ጀምሮ ተመሥርተው የቆዩት ሦስቱን ክፍል የመንግሥት ዘርፎች ማደራጀትና ማጠንከር ይገባል፡፡ እነዚህም የሕግ አውጪና የፈራጅ ያስፈጻሚ የሚባሉት ክፍሎች ናቸው፤›› ተብሎ የተሻሸለው የ1948 ሕገ መንግሥቱ ታወጀ፡፡

ከዚህ ቀደም ሲል ተደጋግሞ እንደተጠቀሰው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተለይም ከኤርትራ መመለስ ወዲህ (መስከረም 1 ቀን 1945 ዓ.ም.) የፀደቁት ሕገ መንግሥቶች መብቶችን በመደርደርና ሕጋዊ ሥርዓቶችን በወረቀቱ ላይ በማስፈር አንፃር ብዙ የሚነቀፍ ነገር የነበራቸው አይደሉም፡፡ የ1948ቱን ሕገ መንግሥት ያገደውን የደርግን የአድኅሮት ኃይል የወለደውን የየካቲቱን 1966 አብዮት የደገሰውም ሕገ መንግሥቱ በተግባር አለመዋሉ ነው፡፡ የንጉሠ ነገሥቱን ሥልጣን ከመገደብ አኳያ ደግሞ አሁንም በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ታሪክ ውስጥና በወረቀት ደረጃ የእንዳልካቸው መኰንን የሕገ መንግሥት ኮሚሽን ያዘጋጀውን ረቂቅ ሕገ መንግሥት የሚስተካከል የነጠረ ሥራ አልነበረም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በወረቀት እንኳን ተቀባይነት አግኝቶ ሳይፀድቅ ቀረ፡፡

ለማንኛውም ግን ዛሬ በሚገዛው አገር ላይ ያለው ሥልጣን በጣም የተስፋፋና ወሰን የሌለው በሥጋዊውም በመንፈሳዊውም ሥራ ሁሉ የሚገባ፣ ከፍ ባለው ሥልጣኑም የሚሾም የሚሽር፣ የሚሰጥ የሚነሳ፣ የሚያስር የሚፈታ፣ የሚቆርጥ የሚገድል፣ እንዲሁም የሚምር ንጉሥ ቢያንስ ቢያንስ በሕግ የለንም፡፡ ወግና ባህላችን የሴት ልጅ ውበትን ለማድነቅ ‹‹… እንደ ባለሥልጣን ፈላጩ ቆራጩ›› ማለቱን ቢቀጥልም ዛሬ በሕግ ይህንን አደርጋለሁ የሚል የለም፡፡ በሕግ፡፡ በተግባር ግን የተለየ ሊሆን ይችላል፡፡ በሕግ የተከለከለ ፈላጭ ቆራጭነት በተግባር ሲታይ ደግሞ ሕገወጥ ድርጊት ይባላል፡፡ ያስጠይቃል፤ ሳይጠየቁ መቅረት ልማድ ቢሆንም እንኳን ሳይጠየቁ መቅረት የነገሠበት አገር ማለት ራሱ አንድ ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ ታልማለች፣ ከዚህ በላይም ይገባታል፡፡

ሰሞኑን በተነገረ ዜና መሠረት የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ምሕረት ሰጡ ሲባል ሰምተናል፡፡ ምሕረት የተሰጠበትን (የተደረገበትን) የምሕረቱን ኦሪጅናል ሰነድ በእኔ በኩል አላየሁም፡፡ ስለመኖሩም አላውቅም፡፡ ምሕረት መደረጉን በሰማንበት በመንግሥቱ የቴሌቪዥን ዜና መሠረት ግን፣

  • ፕሬዚዳንቱ ጳጉሜን 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ለገቡት ለዴምሕት (የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ወይም ትሕዴን) አባላት ምሕረት ማድረጋቸውን፣
  • ለቡድኑ አባላት ምሕረት የተሰጠው ቡድኑ የኤርትራ መንግሥት የያዘውን ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂ ሴራ በመቃወም ወደ አገሩ በመመለሱ መሆኑን፣ እንዲሁም የቡድኑ አባላት በድርጊታቸው በመፀፀትና ከአንድ ዓመት በላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት በመፍጠር የኤርትራ መንግሥት የሚያደራጃቸው የጥፋት ኃይሎች ኢትዮጵያ ላይ የሚጠነስሱትን የሽብር ተግባራት ሴራ በማጋለጥ፣ ለአገራቸው ሰላምና ደኅንነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከታቸው፣ በዚህ ሒደት ውስጥ የቡድኑ አባላት የኤርትራን መንግሥት ምሽግ በማፈራረስና በመጣስ ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈላቸውና የኤርትራ መንግሥት የሚያደራጃቸውን የጥፋት ኃይሎች ተስፋ የሚያስቆርጥ ተግባር በመፈጸማቸው ጭምር መሆኑን፣
  • የቡድኑ አባላት ካለፈ ድርጊታቸው በመፀፀት የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተቀብለው አገሪቱ በምትካሂደው የልማትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት በመወሰናቸውና በፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ውስጥ በነበሩበት ጊዜያት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28/1/ ሥር በሰው ልጅ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው በተለዩት ወንጀሎች አለመሳተፋቸው በመረጋገጡ መሆኑን፣
  • የቡድኑ አባላት በፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ውስጥ በነበሩባቸው ጊዜያት በፈጸሟቸው ሁሉም ወንጀሎች ሁሉ ያለምንም ገደብ ጠቅላላ ምሕረት የተደረገላቸው መሆኑንና የምሕረቱ ተጠቃሚዎችና ተፈጻሚነቱም ጳጉሜን 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ አገራቸው ለተመለሱት ለዴምሕት አባላት ብቻ መሆኑን፣
  • በምሕረቱ ተጠቃሚዎች ላይ ምሕረት ከተሰጠበት ድርጊት ጋር በተገናኘ ከዚህ በፊት የተጀመረ የወንጀል ምርመራና ክስ ቢኖር የሚቋረጥ፣ ወደ ፊትም ምሕረት በተሰጠበት ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት የወንጀል ምርመራና ክስ የማይቀርብ፣ ምሕረት ከመሰጠቱ በፊት ምሕረት ከተሰጠበት ጉዳይ ጋር በተገናኘ በቡድኑ አባላት ላይ የተጣለ ቅጣት ወይም የጥፋተኝነት ውሳኔ ቢኖር እንዳልነበር እንደሚቆጠር፣
  • ምሕረቱ ለተሰጣቸው ለእያንዳንዱ የቡድኑ አባላትም በአገሪቱ ፕሬዚዳንት የተፈረመ የምሕረት ሰርቲፊኬት እንደሚሰጥ፣ የምሕረቱን ተፈጻሚነት እንዲከታተልና እንዲያስፈጽም ለፍትሕ ሚኒስቴር ኃላፊነቱን መሰጠቱን፣ ምሕረቱም በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ከተፈረመበትና ከፀደቀበት ከጥቅምት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የፀና መሆኑን በዜናው ሰምተናል፡፡

ኢትዮጵያ በነፃነቷ ኮርታ፣ ታፍራና ተከብራ የኖረች ሉዓላዊት አገር ናት፡፡ በዚህ ሉዓላዊ ሥልጣን ውስጥ አገሪቷን የሚገዛ (ከሌሎች አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ጭምር የሚወስን) ሕግ የማውጣት፣ ጦርነት የማወጅ፣ የገዛ ራሷን መንግሥት የመሰየም፣ የመለወጥ፣ የመሻር፣ የመሾም፣ የመቅጣት፣ የመማር ሥልጣን አላት፡፡ መስጠት መንሳትም፣ ማሰር መፍታትም የሚወድቀው በዚሁ ሰፊ ሉዓላዊ የአገር ሥልጣን ውስጥ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነውም በሕግ ነው፡፡ የተለየ ደንብ ሳይኖርበት ወይም የሌለበት እብሪቱ ብቻ በየቀኑና በየሰዓቱ የመራውን ሐሳብ እንዳፈቀደውና እንደ ባህርይው ድንገተኛ መለዋወጥ እየለዋወጠ አድራጊ ፈጣሪ፣ ሰጭ ነሽ፣ መሆን የሚባል ነገር ግን በጭራሽ የለም፡፡ መቁረጥ መፍለጥማ ጨርሶ የለም፡፡ ፍፁም ክልክል ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ መግደል እንኳን (የሞት ፍርድ በሕግ በቀረባቸው አገሮች) ፍፁም ክልክል ነው፡፡ የሞት ፍርድ በኢትዮጵያ ውስጥ ገና በሕግ አልቀረም እንጂ መደበኛው የወንጀል የፍትሕ ሥርዓቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ (በደርግ ጊዜ ጭምር) እየተፀየፈው የመጣ የቅጣት ዓይነት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ሾመች ሻረች፣ ሸለመች ቀጣች፣ ምሕረት ሰጠች፣ ይቅርታ አደረገች፣ ሲባል ኢትዮጵያ እንዴት አድርጋ ብሎ ነገር የለም፡፡ ይህን የማድረግ ትክል ሥልጣን አላት፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ይህን ልዩነት ያለውን የመንግሥቱን ሥልጣን አሁንም ቢያንስ ቢያንስ በተጻፈ ሕግ ደረጃ ከጥንት ጀምሮ ለተለያዩ የመንግሥት ሥልጣን አካላት አከፋፍላለች፣ አደላድላለች፡፡

በዚህ ረገድ መጀመሪያ የሚነሳው ጥያቄ ምሕረት የመስጠት የመንግሥት ሥልጣን የማን ነው? የሚለው ነው፡፡ ጥያቄው ይበልጥ ግልጽ እንዲሆን ከታወቀ ወይም የታወቀ ነው ከሚባል ጉዳይ እንነሳ፡፡ የዳኝነት ሥልጣን የመንግሥት ነው፡፡ ጥያቄው ግን የመንግሥት የዳኝነት ሥልጣን የማን ነው የሚለው ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79 እንደተደነገገው ‹‹በፌዴራልም ሆነ በክልል የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው፡፡›› ምሕረት የመስጠት የመንግሥት ሥልጣንስ የማን ነው? መጀመሪያ  ነገር የፍርድ ቤቶች አይደለም፡፡ ፍርድ ቤት ዳኝነት ያያል፡፡ የተከሰሰው ሰው የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን አረጋግጦ ጥፋተኛ ይላል፡፡ ቅጣት ይወስናል፡፡ አለዚያም ነፃ የለቀዋል እንጂ ይቅርታና ምሕረት የሚባል ሥልጣን የፍርድ ቤት አይደለም፡፡ ይቅርታና ምሕረት ደግሞ በትርጉማቸው በሚሸፍኑት ጉዳይ መጠንና በውጤታቸው ብቻ ሳይሆን፣ በባለ መብቱ (በሰጪው) የሥልጣን አካል ጭምር የተለያዩ ናቸው፡፡

ለምሳሌ ይቅርታ የማድረግ ሥልጣን በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት (አንቀጽ 71/7) የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ነው፡፡ በሕግ መሠረት ይቅርታ ያደርጋል ይላል፡፡ ስለዚህም የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ይቅርታ የማድረግ ሥልጣኑን ተግባራዊ የሚያደርግበትና የይቅርታ ዓላማም ተፈጻሚነት የሚያገኝበት ተብሎ የተወካዮች ምክር ቤት የይቅርታ ሕግ አውጥቷል፡፡ የአገራችን ሚዲያ እንደሚምታታበትና ግራ እንደሚገባው ምሕረትና ይቅርታ የአንድ ነገር የተለያዩ ስያሜዎች አይደሉም፡፡

የምሕረትና የይቅርታ ልዩነት ቢያንስ ቢያንስ ከ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ጀምሮ በሕግ ተለያይቶ ተወስኗል፡፡ የወንጀሉ መቅጫ ሕጉ በእንግሊዝኛው (Pardon) የሚባለውን እኛ አሁን ይቅርታ ብለን የምንጠራውን ‹‹ምሕረት›› ይለዋል፡፡ በእንግሊዝኛው የሕጉ ቅጅ እንዲሁም በአማርኛውም ጭምር በትምርተ ጥቅስ አድርጐ ‹አምነስቲ› የሚባለውን ደግሞ የአዋጅ ምሕረት ብሎ ይጠራዋል፡፡ ሁለቱም ምሕረት ናቸው፡፡ አንዱ ተራ ምሕረት ሌላው የአዋጅ ምሕረት ማለት ነው፡፡ የሁለቱም ልዩነትና የባለመብቱ የሥልጣን አካልም እዚያ በደንብ ተወስኗል፡፡ ከሕገ መንግሥቱ በኋላ የወጣውና የ1949ኙን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የተካው የ1996 ዓ.ም. የወንጀል ሕግ ምሕረትን (ፓርደንን) ይቅርታ፣ የአዋጅ ምሕረትን ‹አምነስቲ› ብሎ ስያሜው ላይ ‹‹ማስተካከያ›› ቢያደርግም፣ ይቅርታና ምሕረት ዛሬም ማምታታቻቸው ገና አልቀረም፡፡

በፍርድ የተወሰነ ቅጣት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲቀር ሲደረግ ወይም የቅጣቱ አፈጻጸምና ዓይነት በቀላል/አነስተኛ ሁኔታ እንዲፈጸም ሲደረግ ይቅርታ ይባላል፡፡ ይቅርታ በተቀጣው ሰው ላይ የተወሰነውን የጥፋተኛነት ፍርድ አይፍቀውም፡፡ በወንጀል ፍርድ መዝገብ ላይ ተመዝግቦ ይኖራል፡፡

ምሕረት እንደ ይቅርታ የመጨረሻ ፍርድ ባገኘና ቅጣት በተወሰነበት ሰው ላይ የሚደረግ ‹‹ይቅር ባይነት›› አይደለም፡፡ የተፈጸመ ወንጀል ክስ ካልተመሠረተበት ክስ እንዳይመሠረትበት፣ ክስ ተመሥርቶበት ከሆነም እንዲቆም፣ የፍርድ ውሳኔ የተሰጠበት ከሆነም እንዳይፈጸም ያደርጋል፡፡ ከዚያም በላይ ሄዶ የፍርድ ውሳኔውን ከመሰረዝ አልፎ ወንጀሉ ከሥር ከመሠረቱ እንዳልተፈጸመ ያደርጋል፡፡ የወንጀሉን ክስና ቅጣት ምሕረቱ ይደመስሰዋል፡፡ የተሰጠው ፍርድ እንዳልነበረ ተቆጥሮ ከወንጀል የፍርድ መዝገቡ ይሰረዛል፡፡

በይቅርታና በምሕረት መካከል ያለው ልዩነት ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ይቅርታና ምሕረት የመስጠት ሥልጣን የተሰጠው አካል አንድ አይደለም፡፡

የ1948ቱ ሕገ መንግሥት ‹‹ይቅርታና (አምነስቲ) ምሕረት ለማድረግ ቅጣቶችንም ለማሻሻል መብቱ ነው፤›› ብሎ ሥልጣኑን የሰጠው ለንጉሠ ነገሥቱ ነው፡፡ ከሚያዝያ 1950 ዓ.ም. ጀምሮ በፀናው የ1949 የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ፣ በፍርድ የተሰጠ ቅጣት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ቀሪ የሚደረገው በንጉሠ ነገሥቱ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ምሕረት ደግሞ በአዋጅ ጠቅላላ ምሕረት ለመስጠት በሕገ መንግሥቱ መብት በተሰጠው ባለሥልጣን ሊፈቀድ ይችላል ይላል፡፡ የወንጀልን ክስ ቅጣት ጭምር የሚደመስሰው፣ በክስ የመከታተልን ጉዳይ የሚሰርዘውና የሚያቋርጠውን ምሕረትን የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ከነስያሜው የአዋጅ ምሕረት ይለዋል፡፡ በ1948ቱ ሕገ መንግሥትና በ1949ኙ የወንጀል ሕግ የተፈጻሚነት ዘመን የነበረው አሠራር ምሕረት የመስጠት ሥልጣንን ለሕግ አውጪው አካል አድርጐ የመረቀና ያፀደቀ ነው፡፡

የ1980 የኢሕዲሪ ሕገ መንግሥትም ምሕረት የማድረግን ሥልጣን የብሔራዊው ሸንጐ ቋሚ አካል ሆነ ለተቋቋመው ለመንግሥት ምክር ቤት ሲሰጥ፣ ይቅርታ የማድረግ ሥልጣንን ደግሞ ለሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ሰጥቶታል፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ይቅርታ የማድረግ ሥልጣንን ለሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ቢሰጥም፣ ምሕረት የማድረግ ሥልጣን ግን የየትኛውም የሥልጣን አካል ነው አላለም፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት ስለይቅርታና ስለምሕረት የሚያነሳበት ብቸኛ ቦታ በመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ምዕራፍ ውስጥ በአንቀጽ 28/1/ ውስጥ ነው፡፡ የምሕረትና የይቅርታ ጉዳይ እዚህ የሰብዓዊ መብት ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሰበት ምክንያት ሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚፈጸም በተለይም የሰብዕና ወንጀል ምሕረት የለሽ፣ ይቅርታም ምሕረትም የማይደረግለት መሆኑን አስረግጦ ለመደንገግ ነው፡፡ ስለዚህም እነዚህን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28/1 እና በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 269 ጀምሮ የተዘረዘሩትን ወንጀሎች ‹‹በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም፣ በሕግ አውጪው ክፍልም ሆነ በማናቸውም የመንግሥት አካል ውሳኔዎች በምሕረት ወይም በይቅርታ አይታለፍም፤›› ተባለ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይህን ሲደነግግ ይቅርታ የማድረግም ሆነ ምሕረት የመስጠት ጉዳይ ‹‹በማናቸውም የመንግሥት አካል›› ውሳኔዎች ሊፈጸም ይችላል ማለት አይደለም፡፡

የአገር ይቅርታም ሆነ ምሕረት የማድረግ ሥልጣኗ የሉዓላዊነቷ ትክል (Inherent) ባህርይ ነው፡፡ ምሕረት የማድረግ የመንግሥት ሥልጣን ደግሞ በሕግ ተለይቶ ለሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት አልተሰጠም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ምሕረት የመስጠት የመንግሥት ሥልጣንን ለሚገባው የመንግሥት የሥልጣን አካል ሳይደለድል የቀረበትን አሠራር ዝም ማለትና ማለፍ ይቻላል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ነው ሲባልና ሲሆን ማየት ግን ዝም የሚባል ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡

በ1996 ዓ.ም. የወጣው የወንጀል ሕግ በቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ውስጥ ያለውን የስያሜ ህፀፅ አፀዳሁ ቢልም፣ ይቅርታ የአስፈጻሚው የመንግሥት መሆኑን በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚደነግገውን የቀድሞውን የምሕረትና የአዋጅ ምሕረት ድንጋጌዎች ጭምር አስወግዷቸዋል፡፡ በዚህ ሕግ የታሰበውና ይወጣል የተባለው ሕግም (ከይቅርታ ሕግ በስተቀር) እስካሁን አልወጣም፡፡

የወንጀሉ ሕግ ይቅርታም ምሕረትም ‹‹ሥልጣን በተሰጠው አካል›› ሊሰጥ ይችላል ቢልም፣ ምሕረት የመስጠት ሥልጣንን አገናዝቦ፣ ሕገ መንግሥታዊውን የሥልጣን ድልድል ባህርይ ከቁጥር አስገብቶ የዚህ አካል ሥልጣን ነው ያለ ሕግ የለንም፡፡ የዚህ ሕግ አለመኖር የኢትዮጵያን መንግሥት ምሕረት የማድረግ ሥልጣን ፉርሽ ባያደርገውም፣ እነሆ የምናየውን ‹‹ሠርገኛ መጣ በረበሬ ቀንጥሱ›› የባሰ ዓይነት ችግር ግን ማስከተሉ አልቀረም፡፡ ሕገ መንግሥታዊና ታሪካዊ አረማመዳችንን ያጤነ አሠራር ምሕረት የመስጠት ዕርምጃውን ባለቤት በጭራሽ ከተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣን ባልወጣም ነበር፡፡

ይቅርታና ምሕረት ከሚለያዩበት ጉዳዮች መካከል ሌላው ይቅርታ የሚደረገው ወንጀል ለፈጸሙ ግለሰቦች ሲሆን፣ ምሕረቱ የሚመለከተው ግን ለተፈጸመው ወንጀል መሆኑ ነው፡፡ ለተፈጸመው ወንጀል ምሕረት ተደረገ ማለት የተባለውን ወንጀል ፈጽመው ያልታወቁ ያልተደረሰባቸው ሰዎች ጭምር አሉ ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ምሕረት የተደረገበት የወንጀል ጉዳይ ምሕረቱ የሚሸፍናቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር አሟጦ ሊያውቅ አይችልም፡፡ በዚህ ምክንያት ‹‹የምሕረቱ ተጠቃሚዎችና ተፈጻሚነቱም ጳጉሜን 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ አገራቸው ለተመለሱት ለዴምሕት አባላት ብቻ ነው፤›› የሚለው የመንግሥት መግለጫ የተወሰደውን ዕርምጃ ምንነትና ባህርይ የተምታታ ያደርገዋል፡፡ ይቅርታ ነው እንዳይባል እንኳን የመጨረሻ ፍርድ ስለመስጠቱ፣ ክስ ስለመመሥረቱ ወይም ይፈለጉ የነበሩ ሰዎች ስለመሆናቸው አናውቅም፡፡ ምሕረት ነው እንዳንል ደግሞ የምሕረቱ ተጠቃሚዎች የተመለሱት አባላት ብቻ ናቸው ተባለ፡፡

ምሕረትን ከይቅርታ የሚለየው አንደኛው ይኸኛውና በጣም ከባድነቱ ነው፡፡ የተፈረደባቸውን ሰዎች ይቅር ከማለት በጣም የተለየ ነው፡፡ ለዚህም ነው ምሕረት የሚሰጠው ‹‹የጊዜው ሁኔታ አስፈላጊነቱን የሚገልጽ ሲሆን›› (በቀድሞው) ‹‹ሁኔታዎች ሲገመገሙ የዕርምጃውን አስፈላጊነት ጠቃሚ መሆኑን በሚያመለክቱበት ጊዜ ለአንዳንድ ዓይነት ወንጀሎች፣ ለአንዳንድ ክፍል ወንጀለኞች … ምሕረት ሊፈቀድ ይችላል፤›› የተባለው፡፡

ምሕረት የተደረገበት ጉዳይና ምሕረት የተደረገላቸው ሰዎች የመጀመርያ ወሬ የተሰማበት ሁኔታና አገር ውስጥ ገቡ ሲባል ኋላም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ሲዘዋወሩ፣ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ የተደረገላቸው መስተንግዶና የተሰጣቸው ትኩረት እንዲህ ያለ የ‹‹ምሕረት›› ወይም የሌላ ነገር ጣጣ የሚጠብቃቸው መሆኑን በጭራሽ የሚያመላክት አልነበረም፡፡ ምሕረት የተደረገበትን የዘገባው ዜናና መግለጫም ካለፈ ድርጊታቸው ስለመፀፀታቸው በፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ውስጥ በነበሩባቸው ጊዜያት ከማለቱ በስተቀር፣ የመንግሥትን የሹመትና ሽልማት ጉዳይ እንጂ የምሕረት ነገር የሚያወራ በጭራሽ አይመስልም፡፡

እነዚህ ሰዎች ካለፈው ድርጊታቸው የተፀፀቱበት ጉዳይ ውስጡ የነበሩበት የፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ልክና መልኩ፣ ጥልቀቱና ስፋቱ ቢያንስ ቢያንስ ከግል ተበዳዮች አንፃር መታወቅ የለበትም ወይ?

የጀግና አቀባበል ወይም አከል መስተንግዶ የተደረገላቸውን ሰዎች የምሕረት ዜና ስንሰማ፣ ከዚህም ጋር የመንግሥት ምሕረት የማድረግ ሥልጣን የፕሬዚዳንቱ ነው መባሉን ስንረዳ፣ ዜናው ዋናው ርዕሰ ጉዳይ ካደረገው የምሕረት (የይቅርታ) ጉዳይ ይልቅ፣ የመንግሥታችን የአደጋ ጊዜ፣ ያልተለመደ ጉዳይ በመጣ ጊዜ ዝግጁነትና መሰናዶ ይበልጥ ያሳስበናል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ለሁሉም ነገር ዝግጁና ስንዱ ሆነን እንድንጠብቅ ያስገድደናል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ለሁልጊዜ ዓላማችን፣ ለክፉም ለደግም ጊዜ፣ ለጨለማም ለብርሃን፣ ለክረምትም ለበጋም ወቅት ያገለግል ዘንድ የተበጀ መሣሪያ ነው፡፡ ልዩ ልዩ ሁኔታዎች ሲፈራረቁ ማርሽ ይቀየራል እንጂ ሞተር አያወርዱም፣ አወርዳለሁ አይሉም፡፡

ምሕረት የመስጠት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ በግልጽ አለመደንገጉ፣ እንደ ይቅርታ ሕግ አገር የምሕረት አሰጣጥ ሕግ አለማውጣቱ ሁሉ፣ በተወሰደው ዕርምጃ ሕጋዊነትና ምናልባትም ግብታዊነት ላይ ለሚሰነዘረው ትችት ማመካኛ ሊሆን አይችልም፡፡ እሱ ራሱ ሌላ ጉድለታችንና ጥፋታችን ነው፡፡

ትናንት ተሳስቼ ነበር ማለት ደግሞ ዛሬ የተሻልኩ ነው ማለት ነውና ስህተቶቻችንን ለማረም ከማንም በፊት እንፍጠን፡፡ ሕዝብ በዓይንና በጆሮው፣ በአንደበትና በብዕሩ ጥፋቶችን እየለቀመና እያሳደደ መድረሻ የሚያሳጣበት እንቅስቃሴ ካልተበረታታ በቀር ከዚህ የከፋ ጥፋትና ጉዳት አይመጣም አይባልም፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...