Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ለቆዳው ዘርፍ የሚያገልግል የምርት ገበያ መፈጠር አለበት››

አቶ ብርሃኑ አባተ፣ የኢትዮጵያ ጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት

ከሰላሳ ዓመታት በላይ በቆዳ ዘርፍ የካበተ ልምድ አላቸው፡፡ ከቴክኒሻንነት አንስቶ እስከ ከፍተኛ ኤክስፐርትነት ደረጃ በዘርፉ አገልግለዋል፡፡ በጥሬ ቆዳ ንግድ መስክ ስለሚታዩ ችግሮች መፍትሔ ለማፈላለግና የነጋዴውን ጥቅም ለማስጠበቅ በማለት በ2005 ዓ.ም. የተቋቋመውን የቆዳ ነጋዴዎች ማኅበር በፕሬዚዳንትነት ይመራሉ፡፡ አቶ ብርሃኑ አባተ በቆዳ ዘርፍ ላይ የሚታዩትን ችግሮች ለመቅረፍ መንግሥት በ2006 ዓ.ም. አዋጅ ሲያወጣ ጀማሪው ማኅበርና አባላቱ ተሳትፈው እንደነበር፣ አብዛኞቹ በማኅበሩ የተነሱ አንኳር ጉዳዮችም በአዋጁ መስተናገዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁንና በቆዳ ነጋዴዎችና በቆዳ አቀነባባሪ ኢንዱስትሪዎች መካከል አለግባባቶች ሰፍነው እንደቆዩ ሲናገሩም፣ የቆዳ ነጋዴዎችን እየተጎዱበት ስለሚገኘው አዝማሚያ አበክረው አሳስበዋል፡፡ የቆዳ ዋጋና የአገር ውስጥ አምራች ፋብሪካዎች በጥራት እያሳሰቡ አንገዛም ማለታቸውን አንዱ ነጋዴዎቹን የሚጎዳ ችግር ነው፡፡ ከገዙ በኋላም ቀድሞ የተስማሙበትን ዋጋ እየቀነሱ የሚሰጡ፣ በዱቤ ካልሆነ አንገዛም የሚሉ ፋብሪካዎች  መብዛታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህም ሳያንስ በአገሪቱ ያሉት 32 የቆዳ ፋብሪካዎች በዓመት 40 ሚሊዮን ቆዳ የማቀነባበር አቅም እያላቸው፣ ከአገር ውስጥ ገበያ ማግኘት የሚችሉት ግን ግማሹን ብቻ ቢሆንም ይህንንም ሳይጠቀሙበት ከውጭ እናስመጣለን ማለታቸውን አጣጥለዋል፡፡ በአገሪቱ የጥሬ ቆዳ ግብይት ላይ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ልክ ቡናና ሌሎችንም የግብርና ምርቶችን የሚያስተናግደው ማዕከላዊ ገበያ ወይም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዓይነት ለቆዳ ዘርፍም መቋቋም እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ የአገሪቱ የቆዳ የተፈጥሮ ጥራት ተፈላጊነት በዓለም የታወቀ በመሆኑ፣ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት የሚሳተፉበት ተቋም ተመሥርቶ ለቆዳው ዘርፍ መፍትሔ እንዲበጅለት የሚያሳስቡትን አቶ ብርሃኑን አሥራት ሥዩም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበሩ ዋና ዓላማ ምንድነው? ምንን መሠረት አድርጎ ነው የተመሠረተው?

አቶ ብርሃኑ፡- የኢትዮጵያ ጥሬ ቆዳ አቅራቢዎች ማኅበር የተመሠረተው በ2005 ዓ.ም. ነው፡፡ ዋና ዓላማውም የቆዳና ሌጦ ዘርፍ ወደ ዘመናዊነት ለመቀየር ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሥራት ኋላቀሩን ወደ ዘመናዊ አሠራር ለመቀየር በማሰብ፣ ያለውን የገበያ ክፍተትና የመሳሰሉትን ለመፍታት ነጋዴውም ቆዳ በአፋጣኝ እንዲደርሰው፣ ገበያውም ከዓለም አቀፍ የገበያ ሁኔታ ጋር አብሮ እንዲሄድ፣ የውጭ ገበያው ሁኔታም ለነጋዴው እንዲደርሰው ለማድረግ የተመሠረተ ነው፡፡ የቆዳ ሥራ በአብዛኛው ከዘር ወደ ዘር እየተላለፈ የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ ይህንን ሥራ ማንኛውም ሰው የሚሠራው አይደለም፡፡ ለሥራው ፍቅር ያላቸውን ሰዎች ይፈልጋል፡፡ የቆዳ ሥራ ከገባህበት በኋላ ለመውጣት አዳጋች ነው፡፡ አድካሚና ገንዘብ የሚፈልግ፣ ገንዘብ የሚበላም ጭምር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አባላቶቻችሁ ምን ያህል ናቸው?

አቶ ብርሃኑ፡- አርባ ያህል አሉን፡፡ ዋናው ዓላማችን በኢትዮጵያ ያሉ የቆዳ ነጋዴዎችን ማሰባሰብ ነው፡፡ ነገር ግን ማኅበሩ እንደተመሠረተ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ላይ የወጣው አዲስ አዋጅ ቀደም ሲል የነበረውን ለመቀየር ይደረግ የነበረው ዝግጅት ላይ በመሳተፍ ነው ብዙውን ጊዜ ያሳለፍነው፡፡ ይህ ሲሆን እግረ መንገዳችንን በየክልሉ ያለውን ሥራም እየሠራን ነው፡፡ አዋጁ ላይ ብዙ ተወያየተናል፡፡ ተናጋርግረናል፡፡ ፓርላማ ቀርበንም ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ አዋጅ ቁጥር 814/2006 ዓ.ም. ወጥቷል፡፡ ማስፈጸሚያ ደንቦችና መመርያዎችም ወጥተዋል፡፡ አዋጁ ሲወጣ ካቀረብናቸው ሐሳቦች ውስጥ አብዛኞቹ ተካተውልናል፡፡ የተወሰኑ ያልካተቱ ግን አሉ፡፡ መንግሥትም ለዚህ ጉዳይ ትኩረት በመስጠቱ ከጥያቄዎቻችን ውስጥ ብዙዎቹ ተመልሰዋል፡፡ ነገር ግን እኛ ስንል የነበረው መሀል ላይ ያለው ሰንሰለት በዝቷል፡፡ ቅብብሎሹ ይቀንስና ነጋዴው በቀጥታ ለፋብሪካ ቆዳ መሸጥ እንዲችል፣ ነጋዴ ለነጋዴ እንዳይገበያይ ወይም የጎንዮሽ ግብይት እንዳይኖር አዋጁ አስፍሯል፡፡ እኛ ያልነው ግን ከ80 እስከ 90 ከመቶው የአገሪቱ ዕርድ የጓሮ ዕርድ በመሆኑ ይህ አሠራር በዚህ አዋጅ ሊመለስ አይችልም፡፡ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ቆዳ እንደ ቡና ወይም እንደ ሰሊጥ ዓይነት ምርት አይደለም፡፡ ከየግለሰቦች በየቤቱ እየተመረተ የሚሰበሰብ በመሆኑ፣ የሚሰበስበው አካል ሰብስቦ ካላመጣው የሚያሳውሰውም የለም፡፡ የበቃ ቆዳ ያለሽ እየተባለ በመዞር ነው የሚሰበሰበው፡፡ ይህንን ለማስቀረት አዋጁ አስፈላጊ ቢሆንም አሁን ባለንበት ሁኔታ አያስኬድም፡፡ ይህንን አሠራር ሊፈታው የሚችለው ሥልጣኔ ነው፡፡ በርካታ ቄራዎች ሲሠሩ ብዙ ቆዳ ይገኛል፣ የንፅህና አጠባበቅም የተሻለ ይሆናል፡፡ ይህ መሆን ካልቻለ ግን ችግር ስለሚኖር ቢታይ ብለን ነበር፡፡ ብዙ ውይይት ከተደረገ በኋላ አዋጁ ወጣ፡፡

ይሁንና አዋጁ መሬት እንዲነካ፣ እንዲተገበር እንፈልጋለን፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ፣ የሁለተኛ ደረጃ ገበያ የሚባሉት ሁሉ በርካታ የመገበያያ ቦታዎች እንዲኖራቸው አስቀምጧል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በቆዳና ሌጦ ዘርፍ የተሠማሩ በርካታ ነጋዴዎች አሉ፡፡ ከኢንዱስትሪ ባለቤቶች የበለጠ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ነጋዴዎች በአዲስ አበባ ቆዳ ይሰበስቡ የነበሩ አሉ፡፡ ለእነሱ የሚያቀብሉ ትንንሽ ነጋዴዎችም አሉ፡፡ የድሮው ሕግ ቆዳ ነጋዴ ለፋብሪካ አይሽጥ አይልም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ቶሎ ገንዘቡን አግኝቶ መሄድ ስለሚፈልግና ሌሎችም ነገሮች ስለነበሩ ነው በመሀል ላይ ያለው ቅብብሎች የተበራከተው፡፡ ይህ ዘርፍ በጣም ውስብስብ ችግሮች የነበሩበት ስለሆነ አዲሱ አዋጅ ወጣ፡፡ እኛም አባሎቻችንን በሚገባ አስተምረን አዋጁ እንዲተገበር እያገዝን ነው፡፡ ነገር ግን ለመተግበር ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ገበያው ላይ የሚታዩ ችግሮች አሉ ይባላል፡፡ የጥራትና የመሳሰሉት ችግሮች ይነሳሉ፡፡ በእነዚህ የተነሳ በተገቢው መንገድ እየተተገበረ አይደለም፡፡ 30 እና 40 ነጋዴ ይቀበል የነበረውን ፋብሪካ አሁን በሺዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎች ወደ እሱ ሲመጡ ማስተዳደሩ ላይ ችግር አለ፡፡ ነጋዴው ገንዘቡን ይፈልጋል፡፡ በዱቤ ሸጦ መሄድ አይፈልግም፡፡ እንዲህ ያሉ ክፍተቶች በመኖራቸው ነጋዴው ዕቃውን መሸጥ አልቻለም፡፡ በየገጠሩ ቆዳ አለ፡፡ ስለዚህ ይኼንን ችግር እኛም፣ ንግድ ሚኒስቴርና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም በጋራ በመሥራት ችግሩን ለመፍታት እየተሠራ ነው፡፡ ሚኒስትሮቹ ራሳቸው ጉዳዩን ይዘው እያዩ ነው፡፡ ተረድተውታል፡፡ ችግሩ አዋጁ ሳይሆን የምንገኝበት ሁኔታ ነው፡፡ የፋብሪካዎች አቅም አንዱ ነው፡፡ ጥሬ ዕቃው ሲመጣ የመቀበልና የመክፈል አቅም ችግር አለ፡፡ ጥሬ ዕቃው ከተለያየ ክልል ይመጣል፡፡ ፋብሪካዎች ግን የሚፈልጉት የተለየ ክልል ይኖራል፡፡ ለምሳሌ ወሎ፣ ትግራይ፣ በበረሃው አካባቢ የሚገኙ የአርብቶ አደሩ ቆዳዎች ተፈላጊ አይደሉም ይሉሃል፡፡ ጥራት የላቸውም የሚል ምላሽ ይሰጣል፡፡ ስለዚህ የቆዳው ምንጭ እንዲሆኑ ከሚፈልጉት መካከል ጎጃም ይጠቀሳል፡፡ ጥሩ ጥሩውን የሚባለውን ገዝቶ ሌላውን የማግሸሽ ነገር ይታያል፡፡ የቆዳ መጥፎ ግን የለውም፡፡ በእርግጥ ደረጃ አሰጣጥ ላይ ሊለያይ ቢችልም፡፡ ይህ የእኛ ችግር አይደለም፡፡ ግብርና ሚኒስቴር በዚህ ላይ እየሠራ ነው፡፡

ከጥራት አኳያ ፋብሪካዎች የቆዳ ጥራት ወድቋል እያሉ ነው፡፡ እዚያ ላይ መሠራት አለበት፡፡ በዚህና በሌላውም ምክንያት የአዋጁ አተገባበር ላይ ችግር እየታየ ነው፡፡ በፊት በዱቤ ይቀርብ ነበር፡፡ አሁን ግን ዕቃውን ስትሰጥ እጅህ ላይ ቆዳው ከቆየ ይበላሻል፡፡ ምንም ዋስትና የለህም፡፡ ወደ ውጭ መላክ ተከልክሏል፡፡ 150 በመቶ ታክስ ስለተጣለበት መላኩ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ነግር ግን ‹ዌት ብሉ› የሚባለውን ጥሬውን ቆዳ ‹ፒክል›  ወደሚባለውና በከፈል ወደ ለፋ ቆዳ በፋብሪካ በመቀየር ማስቀመጥ ከተቻለ የተሻለ፣ የማቆያ ዘዴ ስለሚሆን ሳይበላሽ ወዳለቀለት ቆዳ ለማቆየት ያስችላል፡፡ ፋብሪካዎች አሁን ያለው የዓለም የቆዳ ዋጋ ጥሩ አይደለም እያሉ ነው፡፡ የሚያከስራቸውን ነገር ግዙ ብለህ ልታስገድድ የማትችልበት ሁኔታ ቢኖር እንኳ ቆዳው ግን መዳን አለበት፡፡ ነጋዴው እጅ ላይ እያለ ከበሰበሰ ጉዳቱ ለነጋዴውም ለአገርም ነው፡፡ አሁን በስተመጨረሻ ግን ተቀባይ ካጣ በላተኛው እጅ ላይ እየወደቀ ነው፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ከሁለት ወር አሊያም ከስድስት ወር በኋላም ቢሆን የዓለም ገበያ እንደገና ወደ ላይ ሊወጣ ይችላል፡፡ በዚህ ወቅት ግን ቆዳ ላታገኝ ትችላለህ፡፡ ምክንያቱም ቆዳ የሚሰበሰበው በባህል፣ በበዓላት ወቅት ነው፡፡ ብዙ ዕርድ ስለሚኖር፡፡ ስለዚህ ይህንን ገበያው ሲቀር ላግኘው ብትል አታገኘውም፡፡ ነገር ግን ጥሬውን ቆዳ በማቆያ ዘዴ ተጠቅመህ በከፊል በማቀነባበር አልፍቶ ማስቀመጥ ሊሠራበት የሚገባ ነው፡፡ በዚህ አኳኋን ቢሠራበት የሚል ሐሳብ እያቀረብን ነው፡፡ መንግሥትም አብሮን እየሠራ ነው፡፡ በሒደት የመንግሥት ጣልቃ መግባት ያስፈልገው ይሆናል፡፡ የካፒታልና የተለያዩ ችግሮች የት አካባቢ እንዳሉ በጋራ እየታየ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አዋጁ የመጀመሪያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ግብይት ብሎ አስምጧል፡፡ በሁለቱም ሒደት እናንተ ናችሁ ተሳታፊዎቹ፡፡ ከየሰው ትሰበስባላችሁ፣ ከነጋዴውም ትሰብስቡና ለፋብሪካዎች ታስረክባላችሁ፡፡ ሁለቱም ላይ አላችሁበት፡፡ ይህ ከሆነ በደረጃ የተቀመጡ ገበያዎች አሉ ማለት ይቻላል? ሥራ እየሠሩ ገበያው ላይ ወይስ ገና በወረቀት ላይ ያለ አሠራር ነው?

አቶ ብርሃኑ፡- በመሠረቱ አዋጁ ጠቃሚ ነው፡፡ ቆዳ ነጋዴው እስከዛሬ ቆዳ ሲሸጥ ያለ ውል በአመኔታ ላይ ተመሥርቶ ነበር፡፡ በአዋጁ ግን ፋብሪካውና ቆዳ ነጋዴው ሲገበያዩ በውል መሠረት ይገበያዩ ይላል፡፡ ይህን ያህል አቀርብልሃለሁ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ልትከፍለኝ ትችላለህ ተባብለህ ልክ የባንክ ኤልሲ (መተማመኛ ሰነድ) እንደምትከፍተው፣ በዚያ መሠረት ተዋውለህ ሥራ ነው የሚለው፡፡ ጠቃሚ ቢሆንም ይህንን የሚተገብርልህ የለም፡፡ ፋብሪካው በውል መቀበል ላይፈልግ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ውል ከሆነ አልከፍልህም ቢል ትይዘዋለህ፡፡ ወደ ሕግ ትሄዳለህ፡፡ ከዚህ አንፃር ብዙዎቹ ናቸው በዚህ መሥራት የማይፈልጉት፡፡ አልፎ አልፎ በውል የሚሠሩ አሉ፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ሰው እንደፈለገ መጥቶ ቆዳውን የሚሸጥበት ሁኔታ የለም፡፡ ፋብሪካው አይገደድም፡፡ ቆዳ ይዤ ሄጄ ግዛኝ እንዋዋል ብዬው እምቢ ብል ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ ያሉት ፋብሪካዎች 32 ገደማ ናቸው፡፡ የሚሠሩት ምን ያህሉ ናቸው? በዚህ አሠራር የሚገበያዩት ምን ያህል ናቸው? ነጋዴውስ ምን ያህል ነው? ብለህ ስታስብ በአገሪቱ በርካታ ቆዳ ነጋዴ ስላለ ክፍተቱ ብዙ ነው፡፡ ችግሮች አሉ፡፡ ሌላው ጉዳይ የመጀመሪያ ደረጃ ገበያ ማለት በላተኛው፣ አምራቹ አምጥቶ ለቆዳ ነጋዴው የሚሸጥበት ቦታ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ገበያዎች መደራጀት አለባቸው፡፡ እዚያ ገበያ አንድ ነጋዴ ከአንድ በላይ ወኪል ማቆም አይችልም፡፡ እነዚህ ግን ገና አልተደራጁም፡፡ እንደገና ትንንሽ ነጋዴው 500 ወይም 1,000 ቆዳ ለፋብሪካ ለማቅረብ ቅድም ያነሳናቸው ችግሮች አሉ፡፡ የመሠረተ ልማት ችግሮችም አሉ፡፡ አዋጁ ተግባራዊ ለመሆን ገና ነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ብዙ ችግር አለ፡፡

ገበያው ራሱ በዱቤ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ በፊትም በዱቤ አሁንም ያው በዱቤ ነው፡፡ ያልተከፈሉ ሐሳቦች ብዙ አሉ፡፡ በዱቤው ወስደህ ሥራ እያልከውም አልቀበልም የሚል ፋብሪካ ብዙ ነው፡፡ በበዓል ወቅት የተገዙና ነጋዴዎች እጅ ያሉ ጥሬ ቆዳዎች አሉ፡፡ መንግሥት ትልቅ እንቅስቃሴ በማድረግ እኛም የምንሳተፍበት ኮሚቴ አዋቅሮ እየሠራ ነው፡፡ ፍጥነት ግን ያስፈልገዋል፡፡ በቶሎ ካልተደረሰበት ዕቃው ሊበላሽ ይችላል፡፡ እንደ ነጋዴ የምንፈልገው ግን እንደ ቡናና ሰሊጥ የጥሬ ቆዳ ገበያ ያለሥጋት የምንሠራበት በከፊል በፋብሪካ የለፋ ቆዳ የምንሸጥበት ገበያ እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ ቆዳ ስንገዛ ፋብሪካውን አምነን ነው፡፡ ከዚያ ባይገዛኝ ግን ቆዳው እጄ ላይ ይበላሽብኛል ማለት አይኖርብኝም፡፡ ወደ ውጭ መሸጥ ከተከለከልን፣ ቆዳውን ወስዶ ልጦ፣ በከፊል ወደ ተዘጋጀ ደረጃ ደርሶ የሚሸጥበት ገበያ መመቻቸት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ነጋዴው በልበ ሙሉነት ይሠራል፡፡ የቡና የውጭ ገበያ ቢወድቅ አገር ውስጥ ይሸጣል፡ ቆዳንም በጥሬው የምትሸጥ ከሆነ በልበ ሙሉነት ትሠራለህ፡፡ በፊት ስትገዛው 100 ከነበረ አሁን በ50 ብር ልትገዛው ትችላለህ፡፡  በወቅቱ ገበያ ሸጠህ ያለሥጋት መልሰህ ትገዛለህ፡፡

ሪፖርተር፡- በጥሬ ቆዳና በከፊል በለፋ ደረጃ አቀነባብረን፣ አከማችተን፣ ከዚያ በኋላ ለፋብሪካዎች የመሸጥ ዕድል ይኑረን እያላችሁ ነው ማለት ነው?

አቶ ብርሃኑ፡- አዎን፡፡ አሁን ይህንን ማድረግ አንችልም፡፡ እኛም ባንሆን ይህንን የሚሠራ አካል መፈጠር አለበት፡፡ አለበዚያ ነጋዴው ሁሌም በሥጋት ይኖራል ማለት ነው፡፡ እንዳቅምህ በሺዎችም በሚሊዮኖችም ልትገዛ ትችላለህ፡፡ ይኼንን የሚቀበልህ ካጣህ ግን ገንዘቡን እጅህ ላይ ተበላሸ፣ አጣኸው ማለት ነው፡፡ ሚሊዮን አውጥተህ የገዛኸው ነገር እጅህ ላይ ከሞተ ከሰርክ ማለት ነው፡፡ ይህ ሲደረግ ሰው በሕይወቱ ላይ ተፈረደበት ማለት ነው፡፡ ቤተሰቡ ይበተናል፣ የተለያየ ችግር ውስጥ ይወድቃል፡፡ ይህንን አደጋ የሚቀንስ አካል ስለሌለ ይኼ መፈታት አለበት ብለን በተለያዩ ጊዜያት ለመንግሥት እያቀረብን ነው፡፡ ለቆዳው ዘርፍም የሚያገልግል የምርት ገበያ መፈጠር አለበት፡፡ ቆዳው ሲመጣ የሚገዛው አካል መኖር አለበት፡፡ በሁለትዮሽ ግብይት የሚያመርት ይኖራል፡፡ ፋብሪካዎች መግዛት ባልፈለጉ ጊዜ ታስመርታለህ፡፡ የወሎ፣ የጎጃም፣ የትግራይ፣ ወዘተ. ተብሎ  ሲመጣ ጥሬውም ሆነ በከፊል የለፋው በጨረታ እንዲሸጥ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በጥቅሉ ለቆዳ ግብይት ተቋም ይፈጠር ነው ጥያቄው?

አቶ ብርሃኑ፡- አዎ፡፡ ተቋም መኖር አለበት፡፡ ከሥጋት የሚያድን ተቋም መፈጠር አለበት፡፡ ወደ ዘመናዊነት ለመምጣትም ያግዛል፡፡ ትልልቅ ቄራዎች አሉ፡፡ ገበያ የለም ከተባሉ እኮ ቆዳውን ሊጥሉት ነው ማለት ነው፡፡ የበሬውም ይሁን የበጉና የፍየሉ ቆዳ፣ የደጋማው አካባቢ የበግ ሌጦ፣ የባቲ ምርጥ ቆዳ በዓለም ላይ ትልቅ ደረጃ ያለው ነው፡፡ የእኛ ቆዳ ከነችግሩ በዓለም ላይ ተፈላጊ ነው፡፡ እንግሊዞች፣ ጣልያኖች፣ አውሮፓ ገበያ ላይ ማንኛውም አምራች ይፈልገዋል፡፡ ለምንድነው ቢባል ድርና ማጉ በጣም ቆንጆ ነው፡፡ ከበግ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የፍየልና የበሬ ቆዳ ሳይቀር በጣም ተፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሌላው ምርት ሁሉ በቆዳ ሮጣ መቅደም ትችላለች፡፡ በወተት፣ በሥጋ ምርት ወይም በሌላው ላይ ገበያ ለማግኘት ብዙ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሌሎች አገሮች ርቀውን ሄደዋል፡፡ ቆዳ ላይ ግን ትንሽ ሥራ ብንጨምር እናሸንፋለን፡፡ ተፈጥሮ የሰጠን ነው፡፡ ከእንግሊዞች ፒታርድስ ለምን መጣ? ቻይኖች ወደዚህ ለምን መጡ? ይኼንኑ ቆዳ ፍለጋ ነው፡፡ ዓለም ያወቀዋል፡፡ ባቲ ጄኒዩን፣ ሰላሌ የበግ ቆዳ፣ አዲስ አበባ የበግ ቆዳ ለጓንት ምርትና ለተለያዩ ውጤቶች በጣም ይፈለጋል፡፡ ባቲ ጄኒዩን ኮምቦልቻ አከባቢ ብቻ ለገበያ ሲሸጥ በደርዘን ከ12 እስከ 15 ዶላር ድረስ ተጨማሪ ዋጋ ያወጣ ነበር፡፡ ይሄ ለምንድነው ጄኒዩን ወይም የተፈጥሮ ንፁህና ከፍተኛ ጥራት ያለው ቆዳ መሆኑ ስለሚታሰብ ነው፡፡ ይኼንን ማጣት የለብንም፡፡ ይኼንን ትልቅ ሀብት በኮንትሮባንድ ማጣት የለብንም፡፡ ቡናችን ቆንጆ ስለሆነ ተፈላጊ የሆነውን ያህል ቆዳም እንደዚሁ ተፈላጊ በመሆኑ ከሠራንበት፣ መሥራትም አለብን፡፡ ነገር ግን ደረጃው የወረደ ሆኖ ይገኛል፡፡

እንስሳው በሕወይት እያለ፣ በዕርድ ወቅት፣ ከዕርድ በኋላ መሠራት ያለበት ሥራ አለ፡፡ በሕይወት እያለ ቆዳው ላይ በሚወጣበት በሽታ ምክንያት በእሳት ይተኮሳል፡፡ በዕርድ ወቅትም ጥሩ ገፋፊ ካላገኘና የቢላዎቹ ሥለት በአግባቡ ካልተሰናዳ ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ ከዕርድ በኋላ ደግሞ ነጋዴውን ቆዳውን በደንብ ያዘጋጀው፡፡ ጨው በደንብ መስጠት፣ መጋዘኑ ጥሩ መሆን አለበት፡፡ በቶሎ ለፋብሪካ ለማቅረብ ማጓጓዣው የተሟላ መሆን አለበት፡፡ በየመጋዘኑ ቢኬድ ቆዳው በየሥርቻው ነው የሚከማቸው፡፡ ታስቦበት ቦታ የተሰጣቸው የሉም፡፡ በየጊዜው ሽጦ መጣ እየተባለ በአከባቢ ነዋሪዎች መከሰስ አለ፡፡ ለአገር ደግሞ ጠቃሚ ነው፡፡ ጥራት ያለው ምርት ለማምረት እንዲቻል እንዲህ ያሉ ችግሮች ሁሉ ከሥር መሠረቱ በጋራ ሊፈቱ ይገባል፡፡ ፋብሪካውስ ጥሬ ዕቃውን እንዴት ነው የሚይዘው ስንል በአግባቡ ኬሚካል አዘጋጅቶ፣ ባለሙያ አሟልቶና ተገቢውን ማሽን አዘጋጅቶ ነው ወይ የሚሉት በሙሉ መታየት አለባቸው፡፡ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የተሻለ ነገር እንሠራለን ካልን፣ ጥራት እናመጣለን ካልን አንድ ቦታ ላይ ብቻ አይደለም መወሰን ያለብን፡፡ መንግሥት የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ሚኒስቴር አቋቁሟል፡፡ ይኼንን እንደ ትልቅ ዕርምጃ እናየዋለን፡፡ ግን ለቆዳ ዘርፉ ትኩረት መሰጠት አለበት እንላለን፡፡

ሪፖርተር፡- የጥሬ ቆዳ ማከማቻ ላይ ከፍተኛ የቆይታ ጊዜው ምን ያህል ነው? በጨው ታሽቶ ነው የሚቆየው?

አቶ ብርሃኑ፡- ቆዳ ከእንስሳ አካል ላይ ከተገፈፈ በኋላ እስከ አራት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ መደራጀትና መዘጋጀት አለበት ይላል፡፡ አራት ሰዓትም ሳይሆን እንደተገፈፈ ወዲያውኑ ባክቴሪያ ሳያገኘው በፊት ይዘጋጅ ነው የሚባለው፡፡ በጥሩ መጋዘን ብትይዘው ሦስት ወራት ድረስ ሊቆይ ይችላል፡፡ ይኼ ግን ደጋማ አካባቢ ነው፡፡ ነገር ግን ባቆየኸው ቁጥር በየቀኑ ደረጃው እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ አንዳንዶች ስድስት ወራት ድረስ መቆየት ይችላል ይላሉ፡፡ እኔ ግን በዚህ አልስማማም፡፡ ቆላማ አካባቢ ከሆነማ ብዙ ጊዜ አይሰጥም፡፡ ቶሎ የመበላሸት ዕድል አለው፡፡ አያያዝና እንክብካቤ ይፈልጋል፡፡ እያገላበጥክ መንከባከብ አለብህ፡፡

ሪፖርተር፡- የቆዳ የጥራት ጉዳይን እንመልከት፡፡ በቆዳ አቅራቢዎችና በፋብሪካዎች መካከል ያለው ድርድር ይነሳል፡፡ ገለልተኛ በሆነ መንገድ የቆዳው ጥራት ይኼን ያህል ነው የሚለውን የሚመዝን ሥርዓት አለ? ወይስ እንዲሁ በዓይን በማየት ነው የጥራት ደረጃ የሚወጣለት? ያየኋቸው ሰነዶች የሚገልጹት የጥራት መመዘኛ መሥፈርት ባለመኖሩ በቆዳ አቅራቢና በፋብሪካዎች መካከል አለመግባባት እንዳለ ነው፡፡ ይኼ ችግር እንዴት ይታያል?

አቶ ብርሃኑ፡- በኢትዮጵያ የቆዳ ጥራት መመዘኛ ደረጃ አለ፡፡ ቀደም ሲል በንጉሡ ጊዜም ሆነ በደርግ፣ በአሁኑ ሥርዓትም ቢሆም ቆዳ አስገዳጅ ደረጃ አለው፡፡ ጥሬ ቆዳ የሚሸጠው በአስገዳጅ ደረጃ ነው፡፡ ደረጃ አንድ፣ ደረጃ ሁለት፣ ወዘተ. እየተባለ እንዲሸጥ ደረጃ ወጥቶለታል፡፡ አሁን ግን የሚሠራበት አካሄድ ተፈላጊነት የሌለው የሚባለው  ነው፡፡ በጨው የታሸ ነው እየተባለ ውድቅ የሚደረግበት አሠራር አለ፡፡ ቆዳ በደረጃ መሥፈርት እየተሸጠና እየተለወጠ አይደለም፡፡ ሌላው ደግሞ ፋብሪካዎች ትልልቅ ነው የምንፈልገው ይሉሃል፡፡ አንተ ስትገዛ ትንሹንም፣ መካከለኛውንም አቀላቅለህ ነው፡፡ ሕጉ ላይ በጣም ትልቅ፣ ትልቅ፣ መካከለኛና አነስተኛ የሚባለው ቆዳ ስንት እንደሚሸጥ አስቀምጧል፡፡ በመቶኛ የአነስተኛው፣ የመካከለኛውና የትልቁ ድርሻ ምን ያህል መሆን እንዳለበት ሕጉ አስቀምጧል፡፡ ጥሬ ቆዳ ስትገዛ ሊታይ የሚችልውን ዓይተህ ነው ደረጃ የምታወጣው፡፡ ሕጉም የሚለው ይህንኑ ነው፡፡ አዋጁ በደረጃ መሠረት ግብይት እንዲፈጸም ደንግጓል፡፡ ደንብም አለ፡፡ መሻሻል ያስፈልገዋል ከተባለም ማሻሻል ነው፡፡ ቆዳ አስገዳጅ ደረጃ  ቢኖረውም እየተተገበረ ግን አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- አስገዳጅ ደረጃ ያለው ከሆነ ለምንድነው የማይተገበረው? ለምንስ ነው ቆዳው ውድቅ የሚደረገው?

አቶ ብርሃኑ፡- በሁለታችሁ መሀል ጠብ ሲነሳና ውድቅ ሲያደርግብህ ይኼ ፍትሐዊ አይደለም ነው እያለ የሚዳኝ አካል መኖር አለበት፡፡ ዱሮ ግብርና ሚኒስቴር እንደ ዳኛ መጨረሻ ላይ ይገባ ነበር፡፡ ዛሬ በዚህ አኳኋን የተዳኘኸው ሰው ነገ ላይገዛህ ይችላል፡፡ ገንዘቤን ስጠኝ ስትለው ያኮርፋል፡፡ አማራጭ ገበያ የለህም፡፡ ይህ ባለመኖሩ ችግር አለ፡፡ ወዴት ትሄዳለህ? በግድ የምታደርገው ነገር የለም፡፡ መሻሻል ያለበት ነገር ካለም መሻሻል አለበት እንጂ ደረጃው ግን አለ፡፡ የወሎ፣ የትግራይ፣ ወዘተ. አካባቢ ቆዳ ውድቅ ይደረጋል፡፡ ፋብሪካው ገዝቶ ከወሰደ በኋላ በጥሬው ወይም በከፊል የተዘጋጀ በማድረግ ቆዳውን ያለፋዋል፡፡ ካንተ ጋር በ60 ወይም በ79 ብር ተናጋግሮ የወሰደውን ቆዳ ከላጠው በኋላ ወይም በከፊል ካዘጋጀው በኋላ የለም ያንተ ቆዳ ጥሩ አይደለም ስለዚህ በሽያጩ ወቅት ገንዘብ ስላልከፈለህ እቀንሳለሁ ይልሃል፡፡ አንተ ስለጉዳዩ የምታወቀው ነገር የለም፡፡ የፋብሪካው ኬሚስት ሊያበላሸው ይችላል፡፡ በሌላ ምክንያትም ሊበላሽ ይችላል፡፡ መብቱ ባልሆነ መንገድ ገንዘብ ይቀንስብሃል፡፡ ዓይተው ከገዙ በኋላ ገንዘብህን ቆርጠው የሚሰጡ ፋብሪካዎች አሉ፡፡ ወዴት ትሄዳለህ? ለምን ካልክ ቆዳው ውድቅ  ነው፡፡ 75 በመቶው የሚጣል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጥራት ደረጃ አምስት በመቶ ነው፣ ወዘተ. ይሉሃል፡፡ ነገር ግን ማረጋገጫውን የሚሰጠው ማን ነው? ነጋዴ ያለውን ቆዳ ያቀርባል እንጂ ከብት አርቢ አይደለም፡፡ የከብት እከክ አለ ከተባለ፣ በሽታ አለ ከተባለ፣ የነጋዴው ችግር አይደለም፡፡ ነጋዴ መጠየቅ ያለበት ቆዳውን በሚያቆይበት ጊዜ ለሚፈጠር ችግር ነው፡፡ ቆዳውን ከፀጉሩ ልጠን እንስጣችሁ፣ ገፈቱን እኛ እንሸከመው እያልን ነው፡፡ ጥሬውን ከመሸጥ ይልቅ በጥቂቱም ቢሆን ቆዳው ሳይበላሽ ለማቆየት በከፊል በማልፋት ብንሰጥ እንግባባለን፡፡ መንግሥትም ያውቀዋል፡፡ እኛም የማያዋጣን ከሆነ ኡኡ ማለታችን አይቀርም፡፡ ገንዘብ አውጥተን የገዛነው ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ጥሩ ላመጣው ጥሩ ዋጋ፣ መጥፎ ላመጣውም እንደ ደረጃው ሊከፈለው ይገባል፡፡ የመንግሥት ዓላማም ይኼው ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ዋጋን እንይ፡፡ የዋጋ አወሳሰን የዓለም አቀፍ ገበያን በማየት ነው ወይስ እንደሚባለው ፋብሪካዎች ናቸው የቆዳ ዋጋን የመወሰን ኃይል ያላቸው? አቅራቢው ምን አስተዋጽኦ አለው?

አቶ ብርሃኑ፡- የዓለም አቀፍ ገበያን ያገናዘበ ዋጋ መወሰን አለበት፡፡ የዓለም ገበያ ዋጋ ምን ያህል ነው? እዚህስ ምን ያህል መሆን አለበት? ብለህ ከሠራህ ኮንትሮባንድንም ታስቆማለህ፡፡ አለበለዚያ ግን የዓለም ገበያ ዋጋ ከፍ እያለ ከሄደና እዚህ ዋጋው ቢሞት፣ ቆዳው በኮንትሮባንድ መውጣቱ አይቀርም፡፡ ለፋብሪካዎች ይኼ ጥሩ አይደለም፡፡ በፊት ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ እየናረ ነው፣ ነጋዴው እያናረው ነው ይባል ነበር፡፡ ነጋዴው ዋጋ የማናር አቅም የለውም፡፡ ባለፋብሪካው ግዛልኝ ስለሚለው ነው እንጂ ነጋዴው ቆዳውን አይበላው፣ ወደ ውጭ ማውጣት አይችል፡፡ ነገር ግን ፋብሪካዎቹ እርስ በራሳቸው ሲፎካከሩ ዋጋ ይንራል፡፡ ወይም ደግሞ ገበያ ማሟላት ያለበት የጎደለው ቆዳ ሊኖርም ይችላል፡፡ ፋብሪካው እንዲህ ያለውን ዓይነት ቆዳ ገዝተህ አምጣልኝ በማለት ነጋዴውን ያዘዋል፡፡ ነጋዴው ጥቅም ማግኘት ስለሚፈልግ በዚህ ወቅት የተወሰነ ዋጋ ሲጨምር የሚፈጠሩ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ መነሻቸው ከፋብሪካዎቹ ነው፡፡ 150 ፐርሰንት ቀረጥ ተጥሎበት ወደ ውጭ እንዳይወጣ የተደረገ በመሆኑ ይህንን የመወሰን ሥልጣን የእነሱ ነው፡፡ ማኅበርም አላቸው፡፡ የእኛ ማኅበር ከተቋቋመ በኋላ ግን መመካከር ተጀምሮ ነበር፡፡ ዋጋው እንዲህ ባይሆን እየተባለ በመደራደር እንዲሸጥ ተሞከረ፡፡ መሀል ከፍተቶች ስለሚኖሩ መቶ በመቶ አትቆጣጠረውም፡፡ በመሆኑም ምክክሩ አሁን ላይ የለም፡፡ ሲፈልጉ ዋጋውን ያወርዳሉ፡፡ ነገር ግን አብሮ መሠራት ያለበት ነገር ነበር፡፡ አንድ ተቋም ቢኖር ኑሮ ግን የውጭውንም እያየ፣ አገር ውስጥ መሆን ያለበትን እያጠና መፍትሔ ያመጣ ነበር፡፡ አለበለዚያ ወሳኞቹ ፋብሪካዎች ብቻ ከሆኑ ያስቸግራል፡፡

ሪፖርተር፡- የቆዳ ፋብሪካዎች የአገር ውስጥ የቆዳ አቅርቦት አልበቃንም ብለው ከውጭ ያለቀረጥ እንዲያስገቡ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ አቅራቢው በሌላ ወገን የማቀርበውን ቆዳ 75 በመቶ የሚጣል ውድቅ ነው እያሉ አይወስዱትም ካለ ይኼ ክፍተት እንዴት ነው የሚሞላው?

አቶ ብርሃኑ፡- 32 ፋብሪካዎች አሉ፡፡ የፋብሪካዎቹ አቅም በዓመት 40 ሚሊዮን ጥሬ ቆዳ ይፈልጋል፡፡ የአገሪቱ የእንስሳት ዕርድ ትልቁ ብዛት 20 ሚሊዮን ነው፡፡ የ20 ሚሊዮን ክፍተት አለ፡፡ ስለዚህ 20 ሚሊዮኑን ከውጭ ማስገባት አለብን እያሉ እኛ የምንለው ግን አቅማቸው ተብሎ የተገለጸው ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ስንቱ ፋብሪካ ነው በትክክኛው አቅሙ እያመረተ የሚገኘው ነው፡፡ ከውጭ አያምጡ ሳይሆን እዚህ ቆዳው እየወደቀ ለምን ከውጭ ይመጣል የሚለው ግን መታየት አለበት፡፡ እዚህ ያለው ቆዳ የጥራት ችግር ካለበትና ካልተፈለገ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ገንዘብ መሆን ግን ይችላል፡፡ በመሠረቱ ቆዳ አይጣልም፡፡ ብዙ ሥራ አለው፡፡ ያውም የኢትዮጵያ ቆዳ፡፡ እኛ እየጠየቅን ያለው እዚህ ያለውን ቆዳ ሳይወስዱ እንዴት እንዲመጣ ይደረጋል ነው፡፡ የተወሰኑ ፋብሪካዎች ናቸው ከአቅማቸው 80 በመቶና ከዚያ በላይ እየሠሩ ያሉት፡፡ ሌላው ያለበት ደረጃ እየታየ፣ ቆዳው እዚህ እያለ፣ ትክክለኛውን ቆዳው ውድቅ ሲባልም ትክክለኛና አሳማኝ ምክንያት ሳይቀርብ ከውጭ ለማምጣት መጣደፍ ተገቢ አይሆንም፡፡ የእኛን አገር ቆዳ ከውጭ መልሶ መግዛት እንዳይሆንም ያሰጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ብክነት ነው ማለት ነው? ያለውንም አልገዙትም፣ ያልተገዛውም ቆዳ ገበያ ላይ የሚዳኝበት ነገር ከሌለ ቆዳው ይባክናል፡፡ ወይም በሕገወጥ መንገድ እየወጣ ዞረን እሱኑ እንገዛለን እያሉ ነው?

አቶ ብርሃኑ፡- እሱ ብቻም ሳይሆን ወደ ኬንያ ወደ ሌላ ይሸጥ የነበረውን ከልክለን፣ እሺ ይኸው ግዙ ሲባል ደግሞ እምቢ ይባላል፡፡ በኮንትሮባንድ የወጣውን በዶላር መግዛት የሚፈጥረው ከፍተት የማይታረቅ ነው፡፡ ይኼን ለማስተካከል የጋራ ሥራ ይፈልጋል፡፡ የዓለም ገበያ ውስጥ ያለቀለት ቆዳ ይዘህ ነው የምትገባው፡፡ ይኼንን ስታይ ፋብሪካው በዚህ ደረጃ እንዴት እየሠራ እንዳለ፣ የቴክኒክ አቅሙ፣ የማኔጅመንቱ ጉዳይም  ይታያል፡፡ ጥሬ ዕቃው ብቻ አይደለም፡፡ በዓለም ገበያ ከዚህ በፊት የለፋ ቆዳ፣ በከፊል የተላጠና የተዘጋጀ ቆዳ ሲሸጥ የነበረ ፋብሪካ አሁን ቆሞ ባለቀለት ደረጃ እንዲያወጣ፣ ይህንን ካላደረገና ጥሬውን መላክ ከፈለገ 150 በመቶ ቀረጥ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ እዚህ ያሉ የጫማ ፋብሪካዎች፣ የጃኬትና ሌላም የሚያመርቱ ፋብሪካዎችም ጥሬ ዕቃ አቀባዮች ናቸው፡፡ የዓለም ገበያ ቢወድቅ እንኳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ነው፡፡ ጫማ ይፈልጋል፡፡ ጃኬትና ቦርሳ ይፈልጋል፡፡ እዚህ ሠርተህ ለአገር ውስጥ ገበያ ብታወጣው ስንት ጥቅም አለው፡፡ የዓለም ገበያ ወድቋል በማለት ጭፍንና ድፍን ያለ አመለካከት ውስጥ መግባት የለብንም፡፡ ለእኛ ራስ ምታት ሊሆንብን አይገባም፡፡ ዱሮ በግድግዳ ላይ ወጥረን ጥሬውን ቆዳ ለውጭ ስንሸጥ በነበረበት ጊዜ እንኳ ቆዳ አልወደቀም፡፡ ከቡና ቀጥሎ ኢኮኖሚውን ቀጥ አድርጎ የያዘ ነው፡፡ ፋብሪካዎች እየበዙ ሲመጡ፣ እሴት ጨምሮ እንዲወጣ ታስቦ ነው ጥሬ ቆዳ ወደ ውጭ መላክ የቀረው፡፡ ነገር ግን አሁን ማባከን በዝቷል፡፡

ዱሮ ቆዳ ላይ የነበረውን ልማዳዊ ነገር ለመቀየር ብዙ ተለፍቷል፡፡ በአፈር ይታሽ ነበር፡፡ ይኼንን ለመቀየር በዘመቻ መልክ ብዙ ተሠርቷል፡፡ ከ80 እስከ 90 በመቶ ሲመጣ የነበረው ቆዳ ከደረጃ አንድ እስከ ሦስት ይይዝ ነበር፡፡ አሁንም ብንሠራ ወደዚህ ደረጃ ማምጣት እንችላለን፡፡ መንግሥት ብቻውን ሳይሆን ለዚህ ንዑስ ክፍል የሚሆን ጠንካራ ተቋም መፈጠር አለበት፡፡ አሁን ግብርና ሚኒስቴር፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ንግድ ሚኒስቴርና ሌላውም ያገባኛል ይላል፡፡ ባለቤቱ ማን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ነጋዴው ከገበያ እየወጣና እየሞተ ስለሆነ እንደ ሕዝብም እንደ አገርም ሊታሰብበት ይገባል፡፡ እኔ እየተናገርኩ ያለሁት እንደ ንግድ ሰው አይደለም፡፡ እንደ አገር ወዳድ፣ እንደ ባለሙያ፣ እንደ ግለሰብ ነው፡፡ ከሰላሳ ዓመታት በላይ የሠራሁበት መስክ ነው፡፡ ከቴክኒሻንነት እስከ ከፍተኛ ኤክስፐርትነት ስለሠራሁበት ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡ ነጋዴው አልሆን ሲለው ከገበያው ይወጣል፡፡ ፋብሪካው ግን ምንድነው የሚሆነው? ትልቅ ተቋም ነው፣ የሰው ኃይሉ ብዙ ነው፡፡ እንዲህ በቀላሉ ትቶ መውጣት ለፋብሪካው የሚታሰብ አይሆንም፡፡ ቆዳ ነጋዴው ብዙ ነገር ችሎ የሚሠራው ሥራ ነው፡፡ መጋዘንና መኪና ውስጥ የቆዳው ሽታ ይከተልሃል፡፡ ታክሲ ስትሳፈር ተሳቀህ ነው፡፡ ቆዳውን ተንከባክቦ ነው ለፋብሪካ የሚያደርሰው፡፡ በበዓል ቀን ሁለትና ሦስት ቀናት እየታደረ፣ ቆሞ በማሠራት ለቆዳው ይጠነቀቃል፡፡ ቆዳውን በአግባቡ ጠብቆና አጓዘጉዞ እያመጣ እሴት አይጭምርም ነጋዴው ይባላል፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው የሚሠራው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...