ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የሚውል አርማታ ብረት ግዥ ለመፈጸም፣ መንግሥት በሕግ አካሄዶች ላይ ውሳኔ ተጠይቆ ምላሽ እየተጠበቀ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በቃል ትዕዛዝ ብቻ ሲፈጸም የቆየውን ግዥ በመግታት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በጽሑፍ ሰርኩላር እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩልም የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ቀደም ሲል የአርማታ ብረት ግዥ ለመፈጸም በወጣው ጨረታ ላይ የአካሄድ ለውጥ ማድረግ በመፈለጉ፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ፈቃድ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እስኪሰጠው እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በቃል ትዕዛዝ ወይም በቦርድ በሚያዝ ቃለ ጉባዔ ብቻ፣ ሕግን በመተላለፍ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ በማድረግ የአርማታ ብረት ግዥ ሲፈጽም ቆይቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝን በመጥቀስ ሰሞኑን እንደተዘገበው፣ የበላይ አመራሮች በሚሰጡት ትዕዛዝ ብቻ ከሕግ ውጪ ግዥ እየተፈጸመ ነው፡፡ አቶ ይድነቃቸው በአዲስ አበባ በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ ‹‹የሕግ ማዕቀፍ እንዲስተካከል ወይም ሰርኩላር እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ጠይቀናል፤›› ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ከሕግ ውጪ ግዥ መፈጸሙ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ትኩረት የሳበ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ በፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ላይ ምርመራ መጀመሩም ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት ይህንን በቃል ትዕዛዝ ብቻ ሲፈጸም የቆየውን ግዥ በማቆም፣ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በቦርድ አመራሩ አማካይነት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በጽሑፍ ሰርኩላር እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ምንጮች እንደሚገልጹት፣ ይህ ሰርኩላር እስካልወረደ ድረስ፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ግዥ ከመፈጸም ለመቆጠብ ወስኗል፡፡
በሌላ በኩል የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ከአራት ወራት በፊት 44 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የአርማታ ብረት ግዥ ለመፈጸም ጨረታ አውጥቶ ነበር፡፡ በዚህ ጨረታ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ተወዳድረዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ጨረታው ለአሸናፊ ኩባንያዎች ሳይሰጥ የቆየ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በዓለም አቀፍ ገበያ የብረት ዋጋ በአንድ ቶን የ30 ዶላር ቅናሽ በማሳየቱ፣ ተጫራቾቹ ቀደም ሲል ያቀረቡትን ዋጋ በድጋሚ ከልሰው እንዲያቀርቡ ለማድረግ ግዥውን የሚያከናውነው መሥሪያ ቤት ፍላጐት አሳይቷል፡፡
የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ የብረት ዋጋ ቀንሷል፡፡ ይህ እየታየ ከአራት ወራት በፊት በተሰጠ ዋጋ ግዥ ለመፈጸም አለመፈለጋቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹ይህ ሁኔታ ደግሞ ከሕግ ውጪ በመሆኑና የግድ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ፈቃድ መስጠት ስላለበት ለኤጀንሲው ጥያቄ አቅርበናል፤›› በማለት አቶ ይገዙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አቶ ይገዙ ጨምረው እንደገለጹት፣ ኤጀንሲው በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የኤጀንሲው ምላሽ አዎንታዊ ከሆነ ተጫራች ኩባንያዎች በድጋሚ ዋጋቸውን ከልሰው እንዲያቀርቡ ይደረጋል፡፡
የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱም፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎትም ግዥ ይፈጽማሉ፡፡ አቶ ይገዙ እንዳሉት፣ አነስተኛ ግዥ ከሆነ የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ይፈጽማል፡፡ ከፍተኛ ግዥ ከሆነ ግን ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ይፈጽማል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2007 ዓ.ም. በ6.3 ቢሊዮን ብር ለኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ የሚሆኑ ግብዓቶች ግዥ ፈጽሟል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት ከዚህ ገንዘብ የበለጠ ለግብዓቶች ግዥ እንደሚያውል ተጠቅሷል፡፡