በራሳቸው አቅም ኤሌክትሪክ አመንጭተው ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማቅረብ ፍላጐት ያሳዩ የውጭ ኩባንያዎች፣ የታሪፍ ማሻሻያ እንደሚደረግ መተማመኛ በማግኘታቸው በይፋ ጥያቄ ለማቅረብ መዘጋጀታቸው ታወቀ፡፡
ከአሜሪካ፣ ከቱርክ፣ ከቻይናና ከህንድ የመጡ 14 ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጭተው ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማቅረብ ፍላጐት ማሳየታቸው ታውቋል፡፡
መንግሥት ኢነርጂን በሚመለከት ባወጣው የፖሊሲ አቅጣጫ መሠረት ብቻውን ኤሌክትሪክ ማመንጨት ስለማይችል የግሉ ዘርፍ እንዲገባ በ2006 ዓ.ም. በወጣው የኢነርጂ አዋጅ 810/2006 ተደንግጓል፡፡
ነገር ግን እነዚህ ኩባንያዎች ኢንቨስትመንት ውስጥ ለመግባት ሥጋት ከሆኑባቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ታሪፍ አነስተኛ በመሆኑ አዋጭ አለመሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ፣ ሰሞኑን ዘ ኢኮኖሚስት በአዲስ አበባ ባዘጋጀው ጉባዔ ላይ አንድ ኪሎ ዋት ኢነርጂ ለማመንጨት ዘጠኝ የአሜሪካ ሳንቲም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በዚህ ገንዘብ የተመረተው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጠው ግን ስድስት የአሜሪከ ሳንቲም ነው በማለት ገልጸው፣ የታሰበው የታሪፍ ማሻሻያ ይህንን ክፍተት ይደፍናል ብለዋል፡፡ ምክንያቱ ደግመ የታሪፍ ማስተካከያ ካልተደረገ የውጭ ኩባንያዎችን የማይስብ በመሆኑ፣ ለኢንቨስትመንት ያወጡትን ገንዘብ ለማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል የሚል ነው፡፡
የቀድሞ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትርና በአሁኑ ወቅት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢንቨስትመንት ለመግባት እውነተኛ ፍላጐት ካላቸው፣ ማጠንጠኛው የኃይል ሽያጭ ስምምነት ነው ይላሉ፡፡
አቶ ዓለማየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የግል ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ የሚገቡ ከሆነ የኃይል ሽያጭ ስምምነት በቅድሚያ ይካሄዳል፡፡ በዚህ ስምምነት ባለሀብቶች የሚያመነጩትን ኃይል በጥቅሉ፣ በስምምነቱ ላይ በተገለጸ ዋጋ ለብሔራዊ የኃይል ቋት ይሸጣሉ፡፡
‹‹የግል ባለሀብቶች ኃይል የማከፋፈል ሥራ ውስጥ ስለማይገቡ የታሪፍ ጉዳይ ሊያሳስባቸው አይገባም፤›› በማለት አቶ ዓለማየሁ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹ከዚህ ቀደም የኃይል ሽያጭ ስምምነት ድርድር ለማካሄድ አቅም አልነበረንም፤›› የሚሉት አቶ ዓለማየሁ፣ በአሁኑ ወቅት ግን ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ ጋር በመሆን በዘርፉ የሰው ኃይል አቅም ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
እንደ አብነትም ሻሸመኔ አካባቢ ከጂኦተርማል አንድ ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በአራት ቢሊዮን ዶላር ለማመንጨት፣ ኢትዮጵያ ከገባው ሬይክቪክ ጂኦተርማል ጋር የተደረገውን ድርድር አውስተዋል፡፡
አቶ ዓለማየሁ እንደሚሉት፣ ይህ ኩባንያ የሳይት ሥራ በማከናወን ላይ ነው፡፡ ጐን ለጐን ሲያካሂድ የቆየው የኃይል ሽያጭ ስምምነት ድርድር ወደ መጠናቀቁ ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡
‹‹የታሪፍ ጉዳይ ወደኋላ የሚመጣና በጥናት የሚተገበር ነው፡፡ በአንዴ አምጥተን ሕዝባችን ላይ የምንጥለው አይደለም፡፡ ይህን በፍፁም አንፈቅድም፤›› በማለት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ አስረድተዋል፡፡
ፍላጐት ያሳየ የግል ኩባንያ ሁሉ ኢንቨስት ያደርጋል ተብሎ እንደማይታሰብ፣ በትክክል ፍላጐት ያለው ኩባንያ ግን በኃይል ሽያጭ ስምምነቱ መሠረት ኢንቨስት ለማድረግ ይገባል ተብሎ እንደሚታመን አቶ ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡
‹‹ፓወሪንግ አፍሪካ›› በሚል ርዕስ በኅዳር 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ጉባዔ፣ በርካታ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በኃይል ዘርፍ ለሚሰማሩ ኩባንያዎች ፋይናንስ እንደሚያቀርቡ በግልጽ መናገራቸው ይታወሳል፡፡