Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበመንግሥት በሞኖፖል የተያዙ የኢኮኖሚ አውታሮች ሳይረፍድባቸው እንዲከፈቱ ጥሪ ቀረበ

በመንግሥት በሞኖፖል የተያዙ የኢኮኖሚ አውታሮች ሳይረፍድባቸው እንዲከፈቱ ጥሪ ቀረበ

ቀን:

በአንድ ቀን ተኩል በተደረገው ውይይት፣ በታዋቂው ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት የኢትዮጵያ ጉባዔ ላይ መንግሥት በሞኖፖል የያዛቸውን ኢኮኖሚ አውታሮች ክፍት እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ተጠየቀ፡፡ ዘ ኢኮኖሚስት ሰሞኑን ያካሄደውን ጉባዔውን ባጠቃለለበት ወቅት ጉዳዩን አጽንኦት ሲሰጥበት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንም ዘርፎቹ ሳይረፍድባቸው ክፍት እንዲደረጉ አሳስቧል፡፡

በተለያዩ የውይይት መድረኮች ተከፋፍሎ ሲካሄድ በቆየው ጉባዔ ላይ በተለያዩ መንገዶች አጀንዳ ሆኖ ሲነሳ የቆየው፣ መንግሥት እንደ ቴሌኮምና ፋይናንስ ያሉትን መስኮች ለግሉ ዘርፍ ክፍት ያድርግ የሚለው ነጥብ ነበር፡፡ ይሁንና ጥቅምት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ሚኒስትር ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ፣ እነዚህ ዘርፎች ክፍት እንደማይደረጉ በመግለጽ የመንግሥትን አቋም ይፋ አድርገዋል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዷለም አድማሴም የቴሌኮም ዘርፍ ከመንግሥት ይዞታ ውጪ እንደማይሆን ለታዳሚዎች አረጋግጠዋል፡፡

መንግሥት ሁልጊዜም በዚህ አቋሙ እንደጸና ቢሆንም ውትወታዎቹ ግን አላባሩም፡፡ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ኢንቨስተሮች የታደሙበትና ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ያሰናዳው የኢትጵያ ጉባዔ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ካርሎስ ሎፔዝ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የዘጋቻቸው መስኮች ወቅቱ ከሚያመጣቸው ዕድሎች ጋር ከመተላለፋቸው በፊት ክፍት እንዲደረጉ አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የተቆጣጠራቸውን መስኮች በመዝጋትና በለውጥ መካከል ያለውን ሚዛን እንዳይስትም አሳስበዋል፡፡

ፕራቲባ ታከር የመካከኛው ምሥራቅና የአፍሪካ የዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ዳይሬክተር (ዋናው ኃላፊነታቸው የትንታኔ ሥራዎችን ለሚሠራው ዘ ኢኮኖሚስት ኢንተሊጀንስ ዩኒት ነው) ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ የኢትዮጵያ ጉባዔ በአገሪቱ ያሉትን የኢንቨስትመንት አጋጣሚዎችና ፈጣኝ ሁኔታዎች ኢንቨስተሮችና ፖሊሲ አውጪዎች እንዲወያዩባቸው ማድረግ ነበር፡፡ በተለይ መንግሥት እንደ ስስ ብልቱ የሚቆጥራቸውን መስኮች ክፍት እንደማያደርግ በግልጽ ማስቀመጡን የገለጹት ኢኮኖሚስቷ ታከር፣ እንደ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሒደት ላይ ቅድመ ሁኔታ ይደረጋሉ ተብሎ የሚሰጋው፣ የመስኮቹን ክፍት ማድረግ ጥያቄም ብዙ የማያስኬድ መከራከሪያ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና መንግሥት ለምንጊዜውም በሞኖፖል የያዛቸውን አውታሮች ለብቻው ይዞ እንደማይቆይ ገልጸዋል፡፡

የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ባለፉት 15 ዓመታት በነበረው ሁኔታ እንደሚቀጥል የገለጹት ታከር በትምህርት፣ በመሠረተ ልማትና በግብርና መስኮች ጫንቃ ላይ የተገኘው ለውጥ እንደሚያስደምማቸው ሳይገልጹ አላላፉም፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በአፍሪካ አኅጉር ካሉ አገሮች ይልቅ የታቀደው ዕውን የሚሆንባት አገር ናት፡፡ መቶ በመቶ እንኳን ባይፈጸም ወደዚያው የቀረበ አፈጻጸም ይታይባታል፡፡ የሰብዓዊ ልማት መመዘኛዎች ላይ መሻሻል አለ፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች ፍላጎቶችን እያሳዩ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይሁንና ኢንቨስተሮች የረጅም ጊዜ ዕቅድ ይዘው መምጣት እንዳለባቸውና በየጊዜውም ስትራቴጂያቸውን መለወጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ጉባዔው የመጪውን ዓመት ዕቅድና እየጨመረ በመጣው የቻይና ተሳትፎ ላይም ትኩረት እንዳደረገ ታከር ይናገራሉ፡፡ መንግሥት ኢንዱስትሪ ላይ በማተኮሩም አሁን  በኢኮኖሚው ውስጥ የአምስት በመቶ ድርሻ የያዘውን ዘርፍ በአምስት ዓመት ውስጥ ወደ 25 በመቶ የማድረስ ውጥኑ የሚጠቀሱ ናቸው የሚሉት ታከር ቻይና በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት መስክ ላይ ያላት ሚና፣ በፋይናንስ መስኮችም የምታደርገው አስተዋጽኦም ታይቷል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እየጎላ የመጣ ቦታ ከያዙ ሰብዕናዎች መካከል የመንግሥት ኢንዱስትሪ ጉዳዮች አማካሪ የነበሩት፣ ቀደም ሲልም የቻይናው ኋጂያን ጫማ አምራች ኩባንያ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን የመሩት ሔለን ሃይ አንዷ  ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ‹‹ሜድ ኢን አፍሪካ›› የተባለውን ኩባንያ በመመሥረት በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩት ቻይናዊቷ ሔለን ሃይ፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት መስኮች ላይ በተካሄደው ውይይት ወቅት የቢቢሲዋን ጋዜጠኛ ተጋፍጠዋል፡፡

 የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት በአብዛኛው አሉታዊ ገጽታዎችን በመምረጥ ስለአፍሪካ የሚተርካቸው የጦርነት፣ የግጭትና የድርቅ ታሪኮች ተፅዕኖ ሲያሳድሩ መቆየታቸውን በመግለጽ ጥሩውን ጎንም እንዲመለከት አሳስበዋል፡፡ በቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት የአፍሪካ አዘጋጅ የሆኑትና መድረኩን የመሩት ሜሪ ሃርፐር ቢቢሲ በአፍሪካ የሚካሄዱ መልካም ክንዋኔዎችን የመዘገብ ፍላጎቱ ደካማ መሆኑን አምነዋል፡፡ መልካም ጎኖችንም እንዲዘግብ እየተጣጣሩ እንደሚገኙም ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡

እንዲህ ያሉ አነጋጋሪ ይዘቶችን ያስተናገደው ጉባዔ በመጪው ዓመት በድጋሚ ስለመካሄዱ የተጠየቁት ታከር፣ ምንም እንኳ በሚቀጥለው ዓመት የመምጣት ፍላጎት ቢኖረንም የነገሮች መለዋወጥ ይወስነዋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...