ቀደም ሲል የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ፣ በኋላም የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማኅበር የአስተዳደርና ፋይናንስ ምክትል ኃላፊና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ወንድሙ ቢራቱ በሥልጣን በመነገድ፣ ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብና ንብረት በመያዝ፣ በከባድ አታላይነትና በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብና ንብረት ሕጋዊ በማስመሰል የሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው፣ ጥቅምት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
በአቶ ወንድሙ ላይ ክስ የመሠረተው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ፣ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩትን አቶ ባህሩ ቢረዳንና ወንድማቸውን አቶ ሸዋረጋ ቢረዳን፣ እንዲሁም ወ/ሮ እልፍነሽ ቢራቱንና የአቶ ወንድሙ ባለቤት መሆናቸው የተጠቀሱትን ወ/ሮ አሰገደች መንግሥቱን በክሱ አካቷል፡፡
የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 18ኛ ወንጀል ችሎት ባቀረበው ክስ፣ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ቻይናውያንና አቶ ባህሩ ቢረዳ ጠጠር እየፈጩ የጅምላ የንግድ ሥራ ያከናውኑ ነበር ብሏል፡፡ ከ2000 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ውስጥ ለመንግሥት ገቢ ማድረግ የነበረባቸውን የንግድ ትርፍ ግብርና ተጨማሪ እሴት ታክስ በወቅቱ አሳውቀው አለመክፈላቸውንም አስረድቷል፡፡ ወለዱን ጨምሮ 5,763,516 ብር በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸው በኦዲት ተረጋግጦ፣ የወንጀል ክስ እንዲመሠረትባቸው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ማዘዙን ክሱ ያብራራል፡፡ ጠጠር እየፈጨ በጅምላ የሚሸጠውን ድርጅት የማስተዳደር ሥራን የሚሠሩት የቻይና ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች እንደነበሩ የሚገልጸው ክሱ፣ የባለሥልጣኑ ዓቃቤ ሕግ መመርያ በቻይናዎቹ ላይ ምርመራ ተጣርቶ በወቅቱ የወንጀል ነክ ጉዳዮች ክትትል ቡድን አስተባባሪ ለነበሩት አቶ መርክነህ ዓለማየሁ (አሁን በእስር ላይ ናቸው) እንዲተላለፍ ትዕዛዝ ተሰጥቶ እንደነበር ተገልጿል፡፡
በአቶ ባህሩ ቢረዳ ላይ የተመሠረተውን ክስ ለማሰረዝና ለማዘጋት አቶ ወንድሙ አቶ መርክነህን፣ ‹‹ክሱን ዝጋልን ገንዘብ እንከፍልሃለን፡፡ የቻይና ዜግነት ባላቸው ግለሰቦች ላይ ክስ ቢቀርብባቸው ተደናግጠው ከአገር ስለሚወጡ፣ በጠጠር ማምረቻው ድርጅት ላይ ያላቸውን ድርሻ ስንረከብ የበለጠ እንከፍልሃለን፡፡ አይሆንም የምትል ከሆነ እኔ (አቶ ወንድሙ) የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ስለነበርኩ አካሄዱን አውቅበታለሁ፡፡ ጉቦ ጠይቆን እምቢ በማለታችን በደል እያደረሰብን ነው ብለን በማመልከት እንከስሃለን፤›› በማለት በማስፈራራትና በማግባባት አቶ መርክነህ እሺ እንዲሉ ማድረጋቸውን ክሱ ያብራራል፡፡
ለአቶ መርክነህ 50 ሺሕ ብር ጉቦ በመስጠት ቻይናዎቹ ከአገር እንዲወጡ መደረጉም በክሱ ተገልጿል፡፡ ለዚሁ ሥራ ማስፈጸሚያ በማለት 109 ሺሕ ብር አቶ ወንድሙ በመውሰድ ክሱ እንዲቋረጥ ማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ ጠቁሟል፡፡ አቶ ሸዋረጋ (የአቶ ባህሩ ወንድም) ለአቶ መርክነህ 60 ሺሕ ብር በመጨመር የክስ መዝገቡ እንዲቋረጥ በመተባበራቸው፣ ሦስቱም ተከሳሾች ተመሳጥረው ባደረጉት ጥረት አቶ ባህሩ የቻይናውያኑ ከፍተኛ ድርሻ የነበረበትን ጠጠር ማምረቻ ድርጅት ጠቅልለው እንዲይዙ ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡
አቶ ወንድሙ አቶ መርክነህን በማግባባትና በማስፈራራት በአቶ ባህሩ ላይ የተመሠረተውን ክስ እንዲቋረጥ ካደረጉ በኋላ፣ የባለሥልጣኑን ኃላፊዎች በማነጋገር ጠጠር ማምረቻውን ያለምንም ችግር ጠቅልለው እንዲይዙ እንደሚያደርጉ ለአቶ ባህሩና ወንድማቸው በመንገር፣ ለዚሁ ሥራ ማስፈጸሚያ አምስት ሚሊዮን ብር እንዲሰጧቸው መጠየቃቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ አቶ ባህሩም በተለያዩ ጊዜያት የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ በድምሩ 3,310,000 ብር መስጠታቸውንም ክሱ ይገልጻል፡፡
አቶ ወንድሙ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ተቋማት ተቀጥረውና ተሹመው በሠሩባቸው ከሐምሌ 1 ቀን 1989 ዓ.ም. እስከ የካቲት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. 889,976 ብር፣ ወ/ሮ እልፍነሽ ቢራቱ ደግሞ ከመስከረም 5 ቀን 2002 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ 242,150 ብር ያልተጣራ ደመወዝ እንደተከፈላቸው ክሱ ይገልጻል፡፡ ነገር ግን አቶ ወንድሙ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የግልና የመንግሥት ንግድ ባንኮች በድምሩ ከ36.5 ሚሊዮን ብር በላይ፣ እንዲሁም በነቀምት ከተማ በእናታቸው ስም 500 ካሬ ሜትር ቦታ፣ በሱሉልታ ከተማ 200 ካሬ ሜትር፣ በአዳማ ከተማ 403 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተሠራ ቤት ይዘው እንደሚገኙ ክሱ ያብራራል፡፡
ወ/ሮ እልፍነሽ ነዋሪነታቸው ነቀምት ቢሆንም በለገጣፎ-ለገዳዲ 140 ካሬ ሜትር ቦታ ይዘው መገኘታቸውን፣ የአቶ ወንድሙ ባለቤት ወ/ሮ አሰገደች አዳማ ከተማ ውስጥ 200 ካሬ ሜትር ቦታ እንዳላቸው፣ በዚያው ከተማ በ140 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ መኖሪያ ቤት፣ በዓባይ ባንክ የ500,000 ብር የባለቤትነት ድርሻ፣ በአዳማ ከተማ በግል የቁጠባ ሒሳባቸው 577,000 ብር እንደሚያንቀሳቅሱ በክሱ ተገልጿል፡፡
አቶ ወንድሙ በራሳቸውና በውክልና ስም ያገኙትን ገንዘብና ንብረት ሕጋዊ ማስመሰላቸውን፣ በእናታቸው ስም እሳቸው ሳያውቁበት በሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ቦታና ተሽከርካሪዎችን በመግዛት፣ በአጠቃላይ ያላቸውን ቤተሰባዊ ግንኙነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ገንዘብ በማስገባትና በማስወጣት፣ ንብረት በመግዛትና በመያዝ መጠርጠራቸውን ክሱ ያብራራል፡፡ በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ ጉቦ በመስጠት ከባድ የሙስና ወንጀል፣ በሥልጣን መነገድ የሙስና ወንጀል፣ ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብና ንብረት በመያዝ የሙስና ወንጀል፣ በሙስና ድርጊት የተገኘን ገንዘብና ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና በወንጀል መርዳት የሙስና ወንጀልና በከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል ክስ መመሥረቱን፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የክስ ሰነድ ያብራራል፡፡ ፍርድ ቤቱ በችሎት የቀረቡት አቶ ወንድሙ ክሱን የሚቃወሙ ከሆነ የክስ መቃወሚያ ለመቀበልና ያልቀረቡ ተከሳሾች እንዲቀርቡ በማዘዝ ለጥቅምት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡