– ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ሁነኛ ተሿሚ አልተገኘም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፌዴራል መንግሥት ቅርጽ በአራት ክላስተሮች እንዲደራጅ ተወሰነ፡፡ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ክላስተር፣ የፋይናንስና አኪኮኖሚ ክላስተር፣ የማኅበራዊ አገልግሎቶች ክላስተርና የሲቪል ሰርቪስና የአቅም ግንባታ ክላስተር ናቸው የሚደራጁት፡፡
የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ክላስተር በሥሩ ቤቶች፣ ኮንስትራክሽን፣ መንገድና ትራንስፖርት ዘርፎችን ያቅፋል፡፡ ይኼንን ክላስተር የከተማው ምክትል ክንቲባ አቶ አባተ ስጦታ እንዲያስተባብሩ መወሰኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የተቀሩትን ሦስት ክላስተሮች በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሚሾሙ አመራሮች ያስተባብራሉ ተብሏል፡፡
የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይሌ ከቦታው ተነስተዋል፡፡ አቶ ሰለሞን የከተማው ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ሆነው መሾማቸውም ታውቋል፡፡ በዚህ ኃላፊነት ላይ የነበሩት አቶ ዮሐንስ በቀለ ወደ ፌዴራል መንግሥት ተዛውረዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ የፓርላማ አባል በመሆን ማገልገል ጀምረዋል፡፡
የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮን የሚመራ ሁነኛ ተሿሚ እስካሁን አለመገኘቱን ምንጮች አስረድተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ አቶ አወቀ ኃይለ ማርያም እንዲሾሙ ሐሳብ አቅርበው ነበር፡፡
አቶ አወቀ ቀደም ሲል በአቶ ኩማ ደመቅሳ ከንቲባነት ጊዜ የአዲስ አበባ ከተማ ምክልት ሥራ አስኪያጅ ሆነው የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ዘርፍን በዋነኛነት ይመሩ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ በርካታ ውሳኔዎችን ማሳለፋቸው ይታወቃል፡፡ አቶ አወቀ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ከአቶ ድሪባ ምክረ ሐሳብ የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ አቶ አወቀ ከውኃ ዘርፍ እንዲነሱ ፍላጎት ባለማሳየታቸው የአቶ ድሪባ ሐሳብ ተቀባይነት አለማግኝቱ ተገልጿል፡፡
ምንጮ እንደሚናገሩት የአዲስ አበባን የውኃ ፕሮጀክቶች በቅርብ የሚከታተሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአዲስ አበባ የውኃ ፕሮጀክቶች በአቶ አወቀ አመራር ውጤታማ በመሆናቸው በዘርፉ የታየው መሻሻል ወደ ኋላ እንዳይመለስ በቦታው እንዲቆዩ ወስነዋል ይላሉ፡፡
በዚህ ምክንያት በርካታ የሕዝብ ቅሬታ የሚነሳበትና የሁሉም የትኩረት አቅጣጫ የሆነው የመሬት ዘርፍ እስካሁን ሁነኛ ተሿሚ አለማግኘቱ ታውቋል፡፡
የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር በሥሩ ንግድ፣ ጥቃቅንና አነስተኛና ኢንዱስትሪን ያቀፈ ነው፡፡ የፋይናንስና ኢንዱስትሪ ክላስተርን የሚመራ ተሿሚ ከደቡብ ክልል መንግሥት የተገኘ ቢሆንም፣ የተሿሚውን ማንነት ማወቅ አልተቻለም፡፡
የማኅበራዊ አገልግሎቶች ክላስተር በዋናነት ትምህርትና ጤናን የሚይዝ ሲሆን፣ የሲቪል ሰርቪ ክላስተር ደግሞ የመልካም አስተዳደርና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ያከናውናል ተብሎ ታስቧል፡፡ ክላስተሩን በአሁኑ ወቅት የአቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ይስሃቅ ግርማይ ይመሩታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤትና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ አዲስ አበባ ከተማን የሚያስተዳድሩ አመራሮችን በጋራ መርጠው ለኢሕአዴግ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በሰነዱ ላይ በተካሄደው ውይይት መነሳት የነበረባቸው አመራሮች እንዳሉ ቢታመንም ብቃት ያላቸው አመራር ሊገኝ ባለመቻሉ፣ ከተወሰኑት በስተቀር አብዛኞቹ የቢሮ ኃላፊዎች እንዲቀጥሉ መወሰኑን ምንጮ አብራርተዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት የተወሰኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናትን ወስዷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኃይለ ማርያም፣ የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ በቀለ፣ የአዲስ አበባ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃለፊ ወ/ሮ ፍሬህይወት አያሌው፣ የአዲስ አበባ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ብዙነሽ መሠረት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪም የፌዴራል መንግሥት የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸውን የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ኃይለ ማርያምን ለመውሰድ ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ከንቲባ ድሪባ እነዚህን ባለሥልጣናት በፍፁም አልሰጥም በማለታቸው፣ ባለሥልጣናቱ ባሉበት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ተወስኗል፡፡
ከአዲስ አበባ ወደ ፌዴራል ከሄዱት አቶ ጌታቸው ኃይለ ማርያም የከተማ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ተሾመዋል፡፡ የአቶ ጌታቸውን ቦታ የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ እንዲተኩ ውሳኔ ላይ መደረሱን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ከክላስተር አደረጃጀት በተጨማሪ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ቢሮ ሆኖ እንዲደራጅ መወሰኑ ታውቋል፡፡ ባለሥልጣኑ ቢሮ ሆኖ ከተደራጀ የካቢኔ አባል ሆኖ የሚደራጅ ሲሆን፣ የካቢኔ አባል ቢሮዎችን ቁጥር 17 ያደርሰዋል ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከማዕከል በተጨማሪም በክፍላተ ከተሞች መዋቅር ላይም ዕርምጃ መወሰዱ ተገልጿል፡፡ የአምስት ክፍላተ ከተሞች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች እንዲነሱ ሲወሰን፣ የአምስቱ ክፍላተ ከተሞች ሥራ አስፈጻሚዎች ደግሞ በሥራ ላይ እንዲቆዩ መወሰኑ ታውቋል፡፡ እንዲነሱ ውሳኔ ከተሰጠባቸው ውስጥ ንፋስ ሥልክ ላፍቶ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ አዲስ ከተማና አራዳ ክፍላተ ከተሞች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
አስተዳደሩ ከዚህ ዕርምጃ በተጨማሪ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ የመሬት ልማትና ማኔጅመነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች የቦታ ቅይይር እንዲያደርጉ ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል፡፡