Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአይኤምኤፍ ለመንግሥት ያቀረባቸውን የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ይፋ አደረገ

አይኤምኤፍ ለመንግሥት ያቀረባቸውን የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ይፋ አደረገ

ቀን:

  • በግል ባንኮች ላይ የተጣለው የቦንድ ግዥ እንዲነሳ ጠይቋል
  • የታክስ ነፃ መብቶች እንዳይሰጡ ብሏል
  • የብር የመግዛት አቅም መቀነስ አለበት ብሏል

የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ከገመገመ በኋላ፣ ለመንግሥት ያቀረባቸውን የፖሊሲ ማሻሻያ ምክረ ሐሳቦች ይፋ አደረገ፡፡

በሚስ አንድሪያ ሪቸር ሁም የተመራው ስድስት አባላት ያሉት የአይኤምኤፍ ቡድን በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በመገኘት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ከቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሱፊያን አህመድ፣ ከብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ነዋይ ገብረ አብ ጋር በአገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎችና መወሰድ ስላለባቸው የጥንቃቄ ፖሊሲ ዕርምጃዎች መወያየታቸውን፣ ባለፈው ዓርብ ጥቅምት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው የውይይቱ አጠቃላይ ይዘት መግለጫው ይፋ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያ በተለይ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ እንደምትገኝና በእነዚህም ጊዜያት ውስጥ የአገሪቱ የነፍስ ወከፍ ገቢ እያደገ መምጣቱን፣ የአገሪቱ የድህነት ደረጃም በ2002 ዓ.ም. ወደ 29.6 በመቶ መውረዱን ይገልጻል፡፡ ነገር ግን ከዚያ በኋላ ያለውን የድህነት መጠን ሪፖርት አላመለከተም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በ2007 ዓ.ም. የአገሪቱ ዕድገት ካለፉት ዓመታት ቀዝቀዝ ቢልም 8.7 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይገልጻል፡፡ የአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ የተረጋጋ እንደሆነ የሚገልጸው የአይኤምኤፍ ዝርዝር መግለጫ፣ ይህንን መረጋጋት የሚረብሹ ግፊቶች እያንዣበቡ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ከእነዚህም መካከል ወደ ባለሁለት አኃዝ የተሸጋገረው የዋጋ ግሽበት፣ የብር የመግዛት አቅም አሁንም ከፍተኛ በመሆኑ መዋቅራዊ ሽግግሩን ለማምጣት አስቸጋሪ መሆኑ፣ የመንግሥት ከፍተኛ ኢንቨስትመንትና የውጭ ብድር ጫና እየገዘፉ መምጣታቸውን ይገልጻል፡፡

የአይኤምኤፍ ቡድን ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በአራት መሠረታዊ ነጥቦች ላይ ተወያይቶ ምክረ ሐሳቡን መለገሱን፣ ዝርዝር የውይይቱ መግለጫው ያስረዳል፡፡

የመጀመሪያው የመወያያ ነጥብ የተረጋጋውን ማክሮ ኢኮኖሚ መጠበቅ ሲሆን፣ እያሻቀበ የሚገኘው የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ዕዳ ክምችት፣ የመንግሥት ከፍተኛ ኢንቨስትመንትና የብር ምንዛሪ ማነስ ማክሮ ኢኮኖሚውን ሊያዛቡት ይችላሉ ብሏል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ኢንቨስትመንቱን የተመጠነ እንዲያደርግ፣ የዋጋ ንረቱን ለመከላከል ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት በጀት ጉድለት መሙያ የሚያበድረውን እንዲያቆም ሲል አሳስቧል፡፡

ሁለተኛው የመወያያ ነጥብ ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭን መፍጠር መሆኑን የሚገልጸው መረጃው፣ የአገር ውስጥ ቁጠባ እያደገ ቢመጣም መንግሥት እንዳቀደው ቁጠባውን የአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርቱን (GDP) 40 በመቶ ለማዳረስ ቢሆንም፣ ገና በዚህ ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡

በመሆኑም መንግሥት የታክስ መሠረቱን እንዲያሰፋና የፋይናንስ ተቋማት የረዥም ጊዜ ብድር ላይ እንዲያተኩሩ ጠይቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ለኢንቨስተሮች የሚሰጠውን የታክስ ነፃ ዕድል በማስቀረት የኢንዱስትሪ ዞን መሠረተ ልማቶችን እንዲያስፋፋ ምክረ ሐሳቡን ለግሷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መንግሥት በታክስ ነፃ ማበረታቻ በየዓመቱ የአገሪቱን አጠቃላይ ምርት ሦስት በመቶ እያጣ በመሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም በአገሪቱ የግል ንግድ ባንኮች ላይ የተጣለው የ27 በመቶ ቦንድ ግዥ ግዴታ እንዲነሳ፣ ባንኮችም ይህንን ገንዘብ ለብድር እንዲያውሉት ቢደረግ የሚል ሐሳቡን አቅርቧል፡፡

ሦስተኛው የመወያያ ነጥብ የነበረው የውጭ ገበያ ውድድርን ማሳደግና የውጭ ተፅዕኖን መቀነስ ናቸው፡፡ በዚህ ነጥብ ሥርም ኤክስፖርት ላይ ያተኮረ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ለመጀመር የሚፈጀውን የጊዜና የወጪ ፍጆታ መቀነስ፣ የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድርን መጨረስና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት መያዝ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

በአራተኛው የውይይት ነጥብ ዕድገቱ የተመጣጠነ እንዲሆንና በሁሉም ማኅበረሰብ ዘንድ ውጤቱ የሚታይ ዕድገት መፍጠር አስፈላጊነትን፣ አይኤምኤፍ በውይይቱ ወቅት ማንሳቱን አስታውቋል፡፡

መንግሥት በበኩሉ ጥብቅ የሆነ የገንዘብ ፖሊሲ በመከተል ማክሮ ኢኮኖሚው እንደተረጋጋ እንዲቆይ እንደሚያደርግ፣ መሠረታዊ የፍጆታ ምግቦችን በማቅረብ የዋጋ ግሽበት አደጋን መቅረፍ እንደሚቻል፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት በጀት ጉድለት የሚሰጠው ብድር እንዲቀንስ እንደሚደረግ መግለጹ ተመልክቷል፡፡

ከዚህ ውጭ የቀረበው ሥጋት ማለትም የውጭ ዕዳ ጫና የሚለው የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚያሠጋ አለመሆኑን መንግሥት ማስታወቁን፣ ለዚህ የሚሰጠው ምክንያት ደግሞ የሚወስደው የውጭ ብድር የሚውለው መልሶ መክፈል ለሚያስችሉ ፕሮጀክቶች መሆኑን በመግለጽ መቃወሙን የውይይቱ ዝርዝር መግለጫ ያስረዳል፡፡ የብር የመግዛት አቅም ከፍተኛ መሆን የሚፈጥረው ችግር መኖሩን መንግሥት እንደሚረዳ፣ ነገር ግን የመግዛት አቅሙን ማሳነስ የመንግሥት የውጭ ብድርን ከፍ እንደሚያደርገው በመግለጽ በተጠና ሁኔታ የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ እንደሚደረግ መግለጹም ተወስቷል፡፡

ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭ መፍጠርን አስመልክቶ የአይኤምኤፍ ቡድን ያቀረበውን የታክስ መሠረት ማስፋት መንግሥት እንደሚቀበለው፣ ነገር ግን በባንኮች ላይ የተጣለውን የ27 በመቶ ቦንድ ግዥ ለማንሳት እንደማይፈልግ ገልጿል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ይህንን ግዴታ ከባንኮች ላይ ቢነሳም፣ ባንኮቹ ይህንን የገንዘብ መጠን ለብድር ያውሉታል የሚል እምነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡ ለኢንቨስተሮች የሚሰጠው የታክስ ነፃ ማበረታቻንም እንደማያነሳ፣ ነገር ግን ቁጥጥር እንደሚያደርግ መግለጹ ታትቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...