ፎቶ በታምራት ጌታቸው
* * *
የታዋቂው ውሻ ሞት የ20 ሚሊዮን ተመልካቾች ትኩረት ሳበ
ውሻ ከቤት እንስሳት ሁሉ ቀድሞ ከሰው መላመዱ ይነገራል፡፡ ከየትኛውም የቤት እንስሳት በተለየ ከሰው ልጆች ጋር ቁርኝትም አለው፡፡ ታማኝ ከመሆኑ አንፃርም ቤት ንብረት ይጠብቃል፡፡ ተጨማሪ ሥልጠናዎች በማከል የፖሊሶችን ሥራ ደርቦ ሲሠራ ይታወቃል፡፡
የእንግሊዙ ቲል ማን የተሰኘው ውሻ ግን ከሌሎቹ ለየት ባለ ተግባር ይታወቃል፡፡ በምዕራቡ ዓለም በሚዘወተረው ስኬቲንግ (በባለጐማ ጣውላ ላይ መንሸራተት) ይታወቃል፡፡ መሰል ዝንባሌ ካላቸው ውሾች ጋር ተወዳድሮ ብዙ ክብረ ወሰን በስሙ አስመዝግቧል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2007 ዓ.ም. በተደረገ የ100 ሜትር ስኬቲንግ ውድድር በ20 ሰከንድ በማጠናቀቅ በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ መመዝገብ ችሏል፡፡ ከስኬቲንግ ባሻገርም በውኃና በበረዶ ላይ በመንሸራተት እውቅናን አትርፏል፡፡
ባለፈው ሐሙስ ይህንን ዓለም በሞት የተለየው ውሻው ዕረፍቱ አድናቂዎቹን አሳዝኗል፡፡ የውሻው ባለቤት የንዴቪስ በፌስበቡክ ገፁ የውሻውን ዕረፍት ባሳወቀበት ጊዜ ከ100,000 የሚበልጡ ደጋፊዎቹ ሐዘናቸውን በጽሑፍ ገልጸዋል፡፡ ዕረፍቱ ከተሰማ በኋላ ዩቲዩብ ላይ የተጫነው ውሻው ሲወዳደር የሚያሳየው ቪዲዮ 20 ሚሊዮን ተመልካቾችን አግኝቷል፡፡ በውሻው ሞት ልቡ እንደተሰበረ በፌስቡክ ገፁ ያስነበበው ባለቤቱ፣ ውሻው የተፈጥሮ ሞት እንደሞተ ገልጿል፡፡
* * *
የፈረንሣይ በጀት ሚኒስትር ‹‹የታክስ አትክፈሉ›› ቅስቀሳ ጀመሩ
የፈረንሣይ የበጀት ሚኒስትር ክርስቲያን ኢክሪት 300,000 የሚደርሱ የፈረንሣይ ጡረተኞች የታክስ መክፈያ ደረሰኛቸውን ወደ ቅርጫት እንዲጥሉ ጥሪ አቀረቡ፡፡ የ2015 በጀት ዓመት ታክስ የከፈሉ ደግሞ ገንዘባቸው እንደሚመለስ አስታወቁ፡፡
በፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ አላንዴ ካቢኔት ሚኒስትር የሆኑት ኢክሪት፣ ቅስቀሳውን የጀመሩት አገሪቷ በቅርቡ ከምታካሂደው አካባቢያዊ ምርጫ አስቀድሞ መሆኑ ለትችት ዳርጓቸዋል፡፡ ሆኖም የኦላንዴ መንግሥት ሲመሠረት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩና ዝቀተኛ ገቢ ላላቸው ጡረተኞች ከወጪ ጋር ያለባቸውን ጫና ለመቀነስ የታክስ ቅነሳ እንደሚደረግ ቃል ተገብቶላቸው ነበር፡፡
የበጀት ሚኒስትሩ ‹‹ታክስ መክፈያ ደረሰኛችሁን ወደ ቅርጫት ጣሉ›› ሲሉ ለጡረተኞች ያስተላለፉት ቅስቀሳ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ዘ ቴሌግራፍ እንደዘገበው ጡረተኞች ታክስ እንዲከፍሉ ደረሰኝ የተላከላቸው ሲሆን፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ ደግሞ ወደ ቅርጫት ጣሉት ተብለዋል፡፡ ምርጫው ሊካሄድ ሳምንት ሲቀረው ‹‹የታክስ አትክፈሉ›› ቅስቀሳው መጀመሩ ጥርጣሬንም አጭሯል፡፡
* * *
ፍኖተ ሕይወት
እንጨት ቢጤ ተክለን
በልጆች ታጅበን ‑ ልጅ ሙሽሮች ሆነን
* * *
አንች እኔን አቅፈሽኝ ‑ እኔ አንችን አዝዬ
‹‹ኦሆ በል፣ ጃሎ በል›› ‑ ሲባል ሙሽራዬ
ባለ ወግ ማዕረግ ‑ ባለባህል እኛ
አሉን የብር አምባር ‑ ተቃቅፈን ብንተኛ፡፡
* * *
(ከዚያማ ምናለ)
ልጅ እናቶች ሆነን ‑ ልጅ አባቶች ሆነን
ልጆች ወልደን ወልደን
ሳናድግ አርጅተን ‑ በልጅ ተጠውረን
በጭቃ ብረት ድስት
በጭቃ ምጎጎ
በጭቃ ጉልቻ
ተጫውተን፣ ተጫውተን ‑ ተጫውተን ዕቃቃ
ሳናውቀው መሸና ‑ ሳናውቀው አበቃ፡፡
በአካል ንጉሤ፣ ፍላሎት፣ 2006 ዓ.ም.
* * *
የአፍንጫ ፕላስቲክ ቀዶ ህክምና በኢራን
ብዙዎች ኢራናውያን በተፈጥሮ ቆንጆዎች እንደሆኑ ቢያምኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በርካታ ኢራናውያን ሴቶች የአፍንጫ ፕላስቲክ ቀዶ ህክምና እያደረጉ እንደሆነ የዘ ኢኮኖሚስት ዘገባ ያመለክታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢራን መዲና ቴህራን ጐዳናዎች ላይ አፍንጫቸው ላይ ፕላስቲክ የለጠፉ ወጣት ሴቶችን መመልከት የተለመደ መሆኑን ዘገባው ያመለክታል፡፡ እነዚህ ሴቶች የአፍንጫ ፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ያደረጉ ኢራናውያን ናቸው፡፡
እንደዘገባው፣ የአፍንጫ ፕላስቲክ ቀዶ ህክምናን የሚያደርጉት በብዛት ሴቶች ይሁኑ እንጂ ወንዶችም ከነገሩ ውጭ አይደሉም፡፡ አሜሪካ፣ ብራዚልና ደቡብ ኮሪያ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና መዲና እንደሆኑ ቢነገርም ክስተቱ ወግ አጥባቂ በምትባለው ኢራን መታየቱ ግርምት ይፈጥራል፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት ደግሞ ከፊት ገጽታቸው ውጭ ሁለመናቸውን ለሚሸፍኑት ኢራናውያን የሚታየውን ብቸኛውን ፊታቸውን ለማስዋብ የሚያደርጉት እርምጃ አስገራሚ አይደለም ይላሉ፡፡
* * *
መኖር በ‹‹ስፖንሰር››
ዓውደ ዓመት በተለይ ሃይማኖታዊ በዓል በመጣ ቁጥር አዘውትሮ ድንቅ የሚለኝ ነገር እርግጠኛ መሆን ባልችልም ቤተ አምልኮዎች ጭር ብለው ጭፈራ ቤቶች ደግሞ ጢም ማለታቸው ነው፡፡ ይኸውና ወዳጄ አደፍርስም ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ ያለውን የገበያ ግርግርና ከበዓል በኋላም የቀጠለውን የኪስ መራቆት ታዝቦ በጣም አዝኗል፡፡ ‹‹እኔ የምለው ሰው ዓውደ ዓመት የሚለውን የሚረዳው ‹‹አውድም›› ዓመት በሚል ነው እንዴ? ታዲያ ይኼን ሁሉ ወጪ ከየት አገኘው ብሎ ነው የሚያወጣው? ለምንድነው ነገን አስቦ የማይቆጥበው? ኑሮ ናረ፣ ዶላር ጨመረ ምናምን ብሎ ብቻ ማማረር ተገቢ አይደለም፡፡ ራስንም መመርመር ያስፈልጋል›› ሲል ምክር ነገር ጣል አድርጓል፡፡
እውነቱን ለመናገር አንዳንዶች የሚያወጡት ወጪ ስፖንሰሮች የበዙበት የቲቪ ድራማ ይመስል የተጨናነቀ ነው፡፡ እኔና ወዳጄም እንዳማረን ቀረ እንጂ ‹‹ስፖንሰር›› ብናገኝ አውደ ዓመትን አንድ ዕለት ብቻ ሳይሆን አንድ ዓመት ብናከብረው ደስ ይለናል፡፡ ማን ነበር የሐበሻ ቀልድ ቀንድ አለው ያለው? የታክሲ ላይ ጽሑፍ ናት፡፡ እውነቱን ለመናገር ሐበሻ ዘንድ ተረትና ወረት ለጉድ ነው፡፡ ያኔ ሚሊኒየም የምለውን ዘመን እንዲሁ ስንቋምጥለት፣ ብዙ አስተዛዝቦን ኩም አድርጐን እብስ አለ፡፡ እነሆ በምርጫና በቁልምጫ፣ በድብታና በዕልልታ ያጠመቀን 2002 ዓ.ም. እንዲህም ነው፤ እንዲያም ነው ሳይለን እብስ አለ፡፡
አደፍርስ እንዳለው መብራት ከማብራት ግድብ መሥራት የሚቀልበት አገር ላይ በመኖራችን በዓላትን ሁሉ ድሆችን ስፖንሰር የሚያደርግ ድርጅት ይመሥረትልን፡፡ በዓሉን በአያቴ ምርቃትና በወዳጄ ችግርን በሳቅ የማሳለፍ ብቃት መካከል ሆኜ አሳለፍኩ፡፡ ሳምንት ሙሉ ጠፍቶ ያገኘሁት ገር ወዳጄን ምነው ጠፋህ ጃል? ብዬ ብጠይቀው፣ ‹‹የመብራቱ ተራ ወደኔ ‹ዳይቨርት› ተደርጐ ነው›› ብሎ ወዝ ባለው ነገር ጀመረልኛ፡፡ እውነቱን ነው፤ በዓል የሚባለው ነገር እኮ ኪሳችን ውስጥ ባለው ገንዘብ ልክ ብልጭ ድርግም የሚል ሆኗል፡፡
ለማንኛውም በዓሉን በ‹‹ስፖንሰር››ም ሆነ ራስን በማክሰር ላሳለፋችሁ ወገኖች ሁሉ የጀመርነው አዲስ ዓመት የጥረትና የውጤት እንጂ የምኞት ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ጠንቀቅ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በሬዲዮ የሚሰጠው የስፖንሰሮች በግ ምን ምን ይላል በናታችሁ? ዘንድሮ ኑሯችን በስፖንሰሮች እጅ ላይ የወደቀ ሆኗል፡፡ ይኸውና የሕይወቴ አጋር፣ የቤቴ ማገር ያልኳት ልጅም ከኔ የተሻለ ‹‹ስፖንሰር›› አግኝታ ነው መሰል አውላላ መስከረም ላይ ጥላኝ እብስ አለች፡፡ እውነት በ‹‹ስፖንሰር›› ዘመን ወይ በ‹‹ሰፖንሰር›› ወይ በፍቅር ካልተሻገርነው በቀር ወዮልን፡፡
አሸናፊ ደምሴ፣ የኢሕአዴግ የማርያም መንገድ፣ 2007 ዓ.ም.