የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁለተኛው ጂቲፒ የፍሳሽ መሠረተ ልማት ሽፋንን ከአሥር ወደ 76 በመቶ ለማሳደግ አቅዷል፡፡ የከተማውን የፍሳሽ ማስወገጃ መሠረተ ልማት ሽፋንን ማስፋት ብቻም ሳይሆን ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር መዘርጋትም የቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ተግባር እንደሆነ በከተማ አስተዳደሩ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ረቂቅ ሰነድ ተገልጿል፡፡
ተጨማሪ የፍሳሽ ማንሻ ተሽከርካሪዎች ግዥ መፈጸም፣ የአሠራር ሥርዓትን ማሻሻል በመስመር የፍሳሽ አገልግሎት ለማያገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች የ24 ሰዓት በተሽከርካሪ ፍሳሽ ማንሳት አገልግሎት መስጠትና እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶችን በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች መገንባት ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች ይሆናሉ፡፡
በሌላ በኩል በተለያየ መንገድ የሚባክነውን ውኃ ከ37 በመቶ ወደ 22 በመቶ በመቀነስ ዕለት በዕለት ሊባንክ የሚችለውን ውኃ ወደ ሥርጭት በማስገባት የተከማው የውኃ አቅርቦት እንዲጨምር የሚያስችሉ ሰፊ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንደሚደረጉም በሰነዱ ተመልክቷል፡፡
የእነዚህ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ መሆን ለከተማዋ ነዋሪዎች ንፁህ የመጠጥ ውኃ በአስተማማኝ መልኩ ለማቅረብ፣ የመጠጥ ውኃ ሥርጭቱ ፍትሐዊ እንዲሆን ማለትም 90 በመቶ የሚሆነው የከተማው አካባቢ 24 ሰዓት ውኃ እንዲደርሰው፣ የፍሳሽ ቆሻሻ የማንሳትና የማጣራት አሠራር አቅምም እንዲጎለብት እንደሚያደርግ ታምኗል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የከተማው ነዋሪ የረዥም ጊዜ ራስ ምታት ሆኖ የቆየውን የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር መፍታት ያስችሉኛል ያላቸውንና በቀን ከ780 ሺሕ ሜትር ኩብ በላይ ውኃ መስጠት የሚያስችሉ የከርሰ ምድርና ገፀ ምድር ውኃ መገኛ ጥናቶችን አጠናቆ ወደ ተግባር የመግባት ዕቅድም አለው፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን በሚመለከት ተግባራዊ በሚያደርጋቸው ፕሮጀክቶች የመጠጥ ውኃ አቅርቦት በአሁኑ ወቅት ካለበት ወደ ሙሉ በሙሉ ሽፋን እንደሚያሻግረው አመልክቷል፡፡