ስቡህ ኃይለልዑል፣ በምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ የማይክሮሶፍት ጀነራል ማናጀር
44 ዓመታቸው ነው፡፡ የተወለዱት አዲስ አበባ ነው፡፡ በሴንት ጆሴፍ ትምህርት ቤት እስከ ዘጠነኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በኬንያና በታንዛኒያ ነው፡፡ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታውን በአሜሪካ የተከታተሉ ሲሆን፣ በአግሪካልቸር ሳይንስም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡
ለኮምፒዩተር ሳይንስ የነበራቸው ፍቅርም ሁለተኛ ዲግሪአቸውን በኮምፒዩተር ሳይንስ እንዲሠሩ አስገደዳቸው፡፡ ከዚያም በሶፍትዌር ኩባንያ ተቀጠሩ፡፡ በአሜሪካ ጥቂት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ አካባቢ በሚገኙ ስምንት አገሮች የማይክሮሶፍት ጀነራል ማናጀር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ የ ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ አጠቃላይ ሁኔታን በተመለከተ ከአቶ ስቡህ ኃይለ ልዑል ጋር ሻይዳ ሁሴን አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡
ሪፖርተር፡‑ ሴክተሩ በኢትዮጵያ ምን ዓይነት ገጽታ አለው?
አቶ ስቡህ፡‑ እንደየ አገሩ ይለያያል፡፡ ለምሳሌ ኬንያን ብናይ ማይክሮሶፍት በኬንያ መሥራት ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ስለዚህም የማይክሮ ሶፍትና ተያያዥ ቴክኖሎጂ ዕድገት በኬንያ የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያም በፍጥነት በማደግ ላይ ያለች አገር እንደመሆኗ ማይክሮሶፍት በአገሪቱ ባለው ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ላይ ለውጥ ማምጣት ዓላማው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ ከባለቤትነት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችም ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ኦርጅናል ሥራዎችን ከመጠቀም ይልቅ ኮፒ ማድረግ ተለምዷል፡፡ ለዚህም አገሪቱ ውስጥ ጠንካራ የፈጠራ ሥራ ጥበቃ ሊደረግ ይገባል፡፡ ካልሆነ ባለው ሁኔታ ውስጥ ለመሥራት አስቸጋሪ ነው፡፡ ባለሙያው ኮፒ የሚደረግበት ከሆነ ለምን እለፋለሁ ብሎ መሥራት ያቆማል፡፡ ይህም ሙያውን ይገድለዋል፡፡
ሁኔታው በኢንዱስትሪው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡ ፎር አፍሪካ በተሰኘው ፕሮጀክታችንም አይፒ ሀብ የተሰኘ የፈጠራ ሥራ ጥበቃ ላይ ያተኮረ ፕሮግራም አካተናል፡፡ ዋና ተግባሩም መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች ሴክተሩን የሚደግፉ እንዲሆኑ ተፅዕኖ ማድረግ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ሥራ ከጀመረ ሁለት ዓመት አልፎታል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም ከአንዳንድ አገሮች ጋር መሥራት ችለናል፡፡ አይፒ ሀብ ከመቋቋሙ አስቀድሞም በኢትዮጵያ ከአእምሮአዊ ንብረት ጥበቃ ቢሮ ጋር በመሆን ልዩ ልዩ ሥልጠናዎች ሰጥተናል፡፡ ይሁን እንጂ ከሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች በተለየ በኢትዮጵያ ገና ብዙ ሥራዎች ይጠበቃሉ፡፡ ይህ በአንድ ቢሮ ብቻ የሚከወን አይደለም፡፡ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሊተባበሩ ይገባል፡፡ እኛም በራሳችን የበኩላችንን ልናደርግ ዝግጁ ነን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ብቁ ባለሙያ ከማፍራት ጋር በተያያዘ ችግሮች ይታያሉ፡፡ ይህም የተለያዩ መርጃ መሣሪያዎችና ቴክኖሎጂን በማቅረብ የሚስተካከል ነው፡፡ በዚህ ረገድ እኛ የበኩላችንን እያደረግን እንገኛለን፡፡ መንግሥትም በፖሊሲዎችና በሌሎችም ሴክተሩን ሊደግፍ ይገባል፡፡ እንዲሁም ሴክተሩን ከማሳደግ አንፃር መንግሥት ሊያስተዋውቀውና ለፈጠራ ሥራዎች ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል፡፡
ሪፖርተር፡‑ በአገሪቱ የኮፒ ራይት ሶሳይቲ አለመቋቋም ለዘርፉ ምን ያህል ችግር ሆኗል?
አቶ ስቡህ፡‑ ሁሉም አገሮች ኮፒ ራይት ሶሳይቲ አላቸው ማለት ይከብዳል፡፡ ቴክኖሎጂ በራሱ በማኅበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ኖሮት በስፋት አገልግሎት ላይ መዋል የጀመረው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ድንገት ተነስቶ ኮፒ ራይት ሶሳይቲና ሌሎችም መኖር አለባቸው ማለት ለእኔ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች በኢኮኖሚ ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት ገና አሁን ነው፡፡ ነገሮች በአንዴ ተነስተው እንከን አልባ መሆን አይችሉም፡፡ ያሉትን ችግሮች ቴክኒካል ድጋፍ በማድረግ፣ የሕዝቡን ግንዛቤ በማሳደግና የተለያዩ ቴክኒካል ሥልጠናዎች በመስጠት ቀስ በቀስ መቅረፍ ይቻላል፡፡ ያደጉት አገሮችም ቢሆኑ በእነዚህ ችግሮች አልፈዋል፡፡ ሴክተሩ እያደገ ሲመጣ ኮፒ ራይት ስርቆትና ሌሎችም በዘርፉ የሚታዩት ችግሮች በራሳቸው እየጠፉ ይሄዳሉ፡፡
ሪፖርተር፡‑ ቴክኖሎጂው በአገሪቱ ምን ያህል ተደራሽ ነው?
አቶ ስቡህ፡‑ ቴክኖሎጂ በመላው አገሪቱ በበቂ አይዳረስም፡፡ ይህም ካለው የኔትወርክ ችግር አንፃር ነው፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በሁሉም ቦታ ለማድረስ አስቸጋሪ ነው፡፡ ማይክሮሶፍት ቲቪዋይት ችግሩን መቅረፍ የሚችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ይህ በሴክተሩ ትልቅ ለውጥ ማምጣት የቻለ ነው፡፡ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ እስከ ናዝሬት ኔትወርክ ቢኖር ቀጥሎ ያለው ገጠራማ ቦታ ላይ ይቋረጣል፡፡ ቴክኖሎጂው በየቦታው የሚፈጠረውን ክፍተት ይሞላል፡፡ ይህ በቦትስዋና፣ በናሚቢያና በኬንያ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ይህንን በኢትዮጵያ እውን በማድረግ ያለውን የተደራሽነት ጥያቄ መመለስ እንፈልጋለን፡፡ ከሚመለከተው አካል ጋር ቀርበን እየተነጋገርንም ነው፡፡
ሪፖርተር፡‑ በአገሪቱ የሚገኙ የፈጠራ ሥራዎች ምን ያህል በተግባር ላይ ይውላሉ?
አቶ ስቡህ፡‑ የተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውሬ ተመልክቻለሁ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ድርጀቶች የአገር ውስጥ ፈጠራ የሆኑ ሶፍትዌሮችን ሲጠቀሙ ተመልክቻለሁ፡፡ በተለይም የጤና ተቋማት የአገር ውስጥ ፈጠራዎችን ያዘወትራሉ፡፡ ነገር ግን የተሠሩ የፈጠራ ሥራዎች ሁሉ ተግባራዊ ይሆናሉ ማለት አይቻልም፡፡ አንድ ፈጠራ ከመተግበሩ አስቀድሞ ሊያልፍባቸው የሚገባ ሒደቶች አሉ፡፡ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ማኅበራዊ ችግር የሚቀርፍ መሆን አለበት፡፡ እንዲሁም የላብራቶሪ ፍተሻ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ይህንን ለማድረግ ቀደም ባሉት ጊዜያት ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩ፡፡ ራሱን የቻለ ላብራቶሪ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ላይ ሒደቱ ቀለል ብሏል፡፡ እንዴት እንደሚሠራ በኮምፒዩተር ላይ ፕሮግራሙን ማሳየት በቂ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዘርፉ ያለው ግንዛቤ አናሳ ከመሆኑ አንፃር ሳይተገበሩ የሚቀሩ የፈጠራ ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ በዚህ ረገድ የሕዝቡን ንቃተ ህሊና የሚጨምሩ ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡
ሪፖርተር፡‑ ከውጭ የሚመጡ የፈጠራ ሥራዎች የአገር ውስጥ ፈጣሪዎች ላይ ጫና ያሳድራሉ ይባላል፡፡ በዚህ ረገድ ምን አስተያየት አለዎት?
አቶ ስቡህ፡‑ ዓለም አንድ መንደር እየሆነች በመጣችበት ወቅት የቴክኖሎጂ ሽግግር ይኖራል፡፡ ይህ በዚህ ሴክተር የሚፈጥረው ችግር አለ ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ምክንያቱም ከውጭ የሚመጡ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ጋር ፉክክር ሊኖርና ይበልጥ ሊሠሩ ይገባል፡፡ ከዚያ ውጪም የፈጠራ ሥራዎች በማኅበረሰብ ውስጥ ያለውን ችግር የሚፈቱ ናቸው፡፡ ይህም የአገር ውስጥ ባለሙያዎች በቅርበት የሚያውቁት ችግር ላይ እንዲሠሩ ፉክክር እንዳይኖርባቸው ይረዳል፡፡
ሪፖርተር፡‑ ማይክሮሶፍት በኢትዮጵያ ምን ምን ተግባራትን ይከውናል?
አቶ ስቡህ፡‑ የወጣቶችን ሙያ በማሳደግ ዙሪያ ብዙ እየሠራ ይገኛል፡፡ በቅርቡም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በተለይም ከኢትዮጵያ ትምህርት ጥናት ኔትወርክ ጋር ‹‹ድሪም ፓርክ›› የተሰኘ ፕሮግራም ላውንች አድርገናል፡፡ ቀዳሚ ተግባሩም ተማሪዎች የተለያዩ የማይክሮሶፍት ሶፍትዌሮች በነፃ እንዲያገኙ ለማስቻል ነው፡፡ ይህንንም በኢትዮጵያ ለሚገኙ 36 ዩኒቨርሲቲዎች ሰጥተናል፡፡ በገንዘብ ይህንን ያህል ነው ብሎ ለማስቀመጥ የድርጅቱ አሠራር አይፈቅድም፡፡ ነገር ግን ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ዓላማ ተማሪዎችን ከቴክኖሎጂዎች ጋር ማቀራረብ ነው፡፡ ይህም ተማሪዎቹ ከኮሌጅ እንደወጡ በሚሰማሩበት ሥራ ብቁ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡
በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት ኢማጅን ካፕ የሚል ሌላ ፕሮግራም ላውንች አድርገናል፡፡ ፕሮጀክቱ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ተማሪዎች የተለያዩ ሶፍትዌሮችን ሠርተው ለውድድር የሚቀርቡበት ነው፡፡ ፕሮግራሙን የሚያዘጋጀውም ማይክሮሶፍት ነው፡፡ በውድድሩ ያሸነፈም የ50,000 ዶላር ሽልማት ያገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ብዙ ተማሪዎች እንዲሳተፉ እንፈልጋለን እየሠራንም እንገኛለን፡፡ በአካባቢያቸው የሚገኝን ችግር በቴክኖሎጂ እንዴት መቅረፍ እንደሚቻል በሥራቸው ማሳየት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የጀመርናቸው ሌሎችም ሥራዎች አሉ፡፡ ከዩኤንዲፒ ጋር በመተባበር 200,000 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሥራ ፈጣሪዎችን ለማብቃት እየሠራን እንገኛለን፡፡ ኃላፊነቴ ከመንግሥትና ከግል ድርጅቶች ጋር በመተባበር ቴክኖሎጂዎቻችንን ተደራሽ ማድረግ፣ ባለሙያዎችን ለማብቃት መሥራት ነው፡፡
ሪፖርተር፡‑ ማይክሮ ሶፍት ኩባንያ በአፍሪካ የሚያከናውናቸው አበይት ነገሮች ምንድን ናቸው?
አቶ ስቡህ፡‑ እንደሚታወቀው ማይክሮ ሶፍትና ሌሎችም ቴክኖሎጂዎች በአፍሪካ ገና አላደጉም፡፡ በመሆኑም የእኔ ኃላፊነት የነበረው ከሰሃራ በበታች ለሚገኙት የማይክሮሶፍት ባለሙያዎች ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ ማንኛውም የማይክሮ ሶፍት ደንበኛ መንግሥትም ይሁን የግሉ ተቋም ማይክሮሶፍትዌር መጠቀም ሲጀምር የቴክኒካል ባለሙያዎች እገዛ ይደረግለታል፡፡