Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል የፊልሞች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ላይ እንደሚያተኩር ተገለጸ

የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል የፊልሞች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ላይ እንደሚያተኩር ተገለጸ

ቀን:

ዘንድሮ አሥረኛ ዓመቱን የያዘው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ‹‹የፈጠራ ውጤቶች የመጪው ተስፋ›› (ዘ ፕሮሚሲንግ ኦፍ ክሪኤቲቭ ኢኮኖሚ) በሚል መሪ ቃል በቀጣዩ ሳምንት ይካሄዳል፡፡

 የአገር ውስጥና የውጪ ፊልሞችን ለዕይታ በማቅረብ እንዲሁም ምርጥ ፊልሞችን በመሸለም ለዓመታት የዘለቀው ፌስቲቫሉ፣ የዚህ ዓመት ትኩረቱን ያደረገው ፊልሞች ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ ማሳደግ ላይ እንደሆነ የፌስቲቫሉ ዳይሬክተር አቶ ይርጋሸዋ ተሾመ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

በሌሎች አገሮች የፊልም ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ በማስገኘትና ለኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋፅኦ በማድረግ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚወስድ የጠቀሰው ዳይሬክተሩ፣ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ  አወንታዊ ተፅዕኖ እንዲታይ ዘርፉ ሊተኮርበት እንደሚገባ ተናግሯል፡፡

 ‹‹ፊልም ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ግብዓት ነው፤ በኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ጅማሮዎች ስላሉ ዘርፉ ትኩረት ሊቸረው ይገባል፤›› ብሏል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጡት ፊልሞች በጥራት፣ በዓለም አቀፍ ተቀባይነትና  በተመልካች ቁጥርም እየተሻሻሉ እንደመጡ የሚያምነው ዳይሬክተሩ፣ ዘርፉ ያለው አቅም ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ እንዲውልም አሳስቧል፡፡

በፌስቲቫሉ ላይ የሚካሄዱ ውይይቶች በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ ሲሆን፣ በተጨማሪ ‹‹ዘ ሜኪንግ ኦፍ ሎው በጀት ፊልም›› (በዝቅተኛ ወጪ የሚሠሩ ፊልሞችን የሚመለከት) ጥናት በእስራኤላዊው ፊልም ሠሪ ዳን ዋልማን ይቀርባል፡፡ ኢትዮጵያውያንና ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ፊልም ሠሪዎች ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክም ይኖራል፡፡

በውይይቱ ከአሜሪካው የፊልም ኢንዱስትሪ (ሆሊውድ) የሚመጡ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ፡፡ የኢትዮጵያን ፊልም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ፣ የፊልሙ ዘርፍ ተግዳሮቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ሲኒማ የወደፊት ተስፋ በውይይት ከሚዳሰሱ ነጥቦች ጥቂቱ ናቸው፡፡

በዘንድሮው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ላይ 19 ፊልሞች ይወዳደራሉ፡፡ ከመወዳደሪያ ዘርፎች ውስጥ ሲኒማቶግራፊ፣ የፊልም ዝግጅት፣ የፊልም ጽሑፍና ትወና ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ከአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያና አሜሪካ የተወጣጡ ወደ 45 የሚሆኑ ፊልሞች ይታያሉ፡፡

ለዕይታ ከሚበቁ ፊልሞች መካከል ሁለት በአማርኛ ትርጉም የሚቀርቡ የህንድ ፊልሞች ይኖራሉ፡፡ ከህንድ ፊልም ኢንዱስትሪ (ቦሊውድ) የተውጣጡ ባለሙያዎች በፌስቲቫሉ ተገኝተው ልምዳቸውን ያካፍላሉ፡፡

ይርጋሸዋ እንደሚለው፣ የፌስቲቫሉን ቀደምት ተሞክሮዎች በመመርኮዝ በዚህ ዓመት የተሻለ ዝግጅት ይቀርባል፡፡ በተደጋጋሚ በተመልካቾች የሚተቹ በፌስቲቫሉ መክፈቻና መዝጊያ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ የሚስተዋሉ የቴክኒክ ችግሮች እንዳይከሰቱ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ተናግሯል፡፡

ለውድድር የቀረቡ ፊልሞችን የሚዳኙ ባለሙያዎች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተውጣጡ ሲሆን፣ ገለልተኛነታቸውን ለማረጋገጥ የፌስቲቫሉ አዘጋጆች ማንነታቸውን፣ ዳኞቹም የሚገመግሙትን ፊልም አስቀድመው እንዳያውቁ መደረጉን ገልጿል፡፡ ካለፉት ዓመታት በበለጠ በርካታ ተመልካቾች በፌስቲቫሉ የሚቀርቡ ፊልሞችን እንዲመለከቱ፣ በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን ሰፊ ማስተዋወቂያ መሠራቱንም አክሏል፡፡ የፌስቲቫሉን የአሥር ዓመት ቆይታ የሚያሳይና ፊልም ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን የያዘ ካታሎግም ተዘጋጅቷል፡፡

ፌስቲቫሉ በፊልሙ ዘርፍ የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ እንዳለ፤ በሽልማቶች ፊልም ሠሪዎችን ከማበረታት ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ፊልሞች በዓለም አቀፍ ፌስቲቫሎች እንዲሳተፉ መንገድ ከፍቷል ብሎ ያምናል ዳይሬክተሩ፡፡ የፊልም ፌስቲቫሎች ያለማቋረጥ ሊካሄዱ እንደሚችሉ ካመላከቱ ፌስቲቫሎች አንዱ መሆኑ የሚጠቅሰው  ሌላ ነጥብ ነው፡፡

ፌስቲቫሉ ጥቅምት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ ባህል ማዕከል ‹‹ላምብ›› የተሰኘውን የያሬድ ዘለቀ ፊልም በማሳየት ይከፈታል፡፡ እስከ ኅዳር 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በማዕከሉ፣ በፑሽኪንና አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ  ሌሎች ፊልሞች ይቀርባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...