እነሆ መንገድ። ከመገናኛ ወደ ኮተቤ ልንጓዝ ነው። እልፍ አዕላፍ ተረቶች በህላዌ መንደር ዛሬም እየተኖሩ ይተረካሉ። እዚህ የተሳፈርንባት ታክሲ ውስጥ መካከለኛው የጥንዶች ረድፍ ላይ አባት የልጁን የፈተና ወረቀት ዘርግቶ ‘ኤክሶቹን’ ይቆጥራል። ልጅ አብዛኞቻችን የዕድሜ ልክ ደመወዛችን ቢደመር የማይሸምተው፣ ከፍሬው ቀድመን ያወቅነውን አፕል ስልክ የመጨረሻ ምርት ይዞ ‘ከረሜላ ማፍረስ’ ይጫወታል። “እንዴት ይኼን ትሳሳታለህ?” አባት በድንገት ወደ ልጁ ተቆጥቶ ዞረ። ልጅ ቀናም አላለ። “የቱን?” ከረሜላ በከረሜላ እያፏጨ፣ በለስ ከቀናው ቦምብ እያፈነዳ የቸኮሌት ‘ቦነስ’ ይለቅማል። “እስኪ አሁን ከረሚላ መሀል ቦምብ እያፈነዱ አድገው ነው ለሰው የሚመለሱት?” ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመች ደርባባ ወይዘሮ ትጠይቀኛለች። “ይኼ ‘ካንዲ ክራሽ’ የሚሉት ጌም የስንቱን ትዳር በተነው መሰለህ። ታውቃለህ የጋሼ (ማን ነበር ስማቸው?) ልጅ ከባሏ ያፋታት እኮ ይኼ ‘ጌም’ ነው፤” መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ ጓደኛማቾች ያወጋሉ።
“አንተን እኮ ነው የማናግረው! ይኼን እንዴት ‘ኤክስ’ ልትሆን ቻልክ?” አባት ብስጭቱ ጨምሯል። እግዜር ባርኮለት ምንም እንኳ በሁለተኛው ዙር ቢሆንም ልጁም ደነገጠለት። “መቼ ያሳፍራል የእሱ ስጦታ ከሆነ?” ብሎ ያጉተመተመውን ተሳፋሪ ልለየው አልቻልኩም። “እኔ ልክ ነኝ፣ አስተማሪው ነው የተሳሳተው፤” ልጅ በኩራት አባቱን ያስረዳዋል። “ጥያቄው ‘ገፀ ባህሪያት ቀርፀን ታሪክ ስንጽፍ ስንት ዓይነት የግጭት ዓይነቶችን መጠቀም እንችላለን?’ ነው የሚለው። መልሱ ‘ሰው ከሰው ጋር፣ ሰው ከራሱ ጋር፣ ሰው ከተፈጥሮ ጋርና ሰው ከመኪና ጋር’ ነው። አስተማሪው ግን ‘ሰው ከመኪና ጋር’ አልክ ብሎ ‘ኤክስ’ ሰጠኝ፤” ብሎ እንዳበቃ፣ “ተባረክ! ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ ማለት አንተ ነህ። ስንቱ በመኪና አደጋ እንዳይሆኑ ሲሆን፣ ሰንቱ የትዳር አጋሩን በመኪና አደጋ እያጣ፣ ያለ እናት ወይም ያለ አባት ልጁን እያሳደገና ቤተሰብ እየተበተነ እያየ ይኼን ‘ኤክስ’ ካደረገህ መገምገም አለበት፤” ብላ ወይዘሮዋ ደነፋች። ይኼ ዘመን ስንቱን ያሳየናል? ስንቱን ያሰማናል?
ጉዟችን ከተጀመረ ጥቂት ደቂቃዎች አምልጠዋል። ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየመ ጎልማሳ ያዙኝ ልቁኝ እያለ ነው። “ውይ! ኧረ አገር ስጡኝ ተው?! የት ሄጄ ልፈንዳ በመድኃኔዓለም?” ይወራጫል። “ኧረ ቀስ! በተረጋጋ ቀጣና ውስጥ ምንድነው እንደዚህ ማተራመስ?” ወይዘሮዋ ናት። “ምንድነው የሚለው? የት አለና ነው እንቆቅልሹ አገር ስጡኝ የሚለን?” ይኼን የምትለው ከኋላዬ ከተደረደሩት መካከል አንዲት የቀይ ዳማ ናት። “አይ! እንቆቅልሹንስ ተይው። እንዲያውስ ለእንቆቅልሾቻችን የሚበቃ አገር አለ እንዴ?” ሥጋ ባዳው አጉል ሰብቶበት፣ በከፊል ደመናማ የአየር ፀባይ ላብ የሚያጠምቀው ህያው ገፀ ባህሪ ከጎኗ ያሽሟጥጣል። “ተልባ ቢንጫጫ በአንድ ሙቀጫ’ ተብሏል። ምን እንቆቅልሾቻችን ቢበዙ በመልካም አስተዳደር ችግር ተጠቃለው ዕውቅና ተሰጥቷቸው ተቀምጠናል። ከዚህ በላይ ምን ይምጣ?” ሲል ጋቢና መሀል ላይ የተቀመጠ ወጣት ዞሮ ታክሲያችን በምትሃት ወደ ክብ ጠረጴዛነት የተቀየረች መሰለች።
“ዓይኔ ነው ጆሮዬ?” ትላለች ከጎልማሳው አጠገብ የተቀመጠችው ደግሞ ተደናግራ። “ምን የሆነው?” ጎልማሳው መወራጨቱን ቀነስ አድርጎ ሲጠይቃት፣ “በአንዴ እንቆቅልሹን በፖለቲካ ፈቶ ያሳየኝ ወይ ያሰማኝ ነዋ?” ስትለው ቀልደኛው ጎልማሳ፣ “የለም! የለም! የአላዲንና የፋኖሱ ነገር ነው። ሳናስበው ዴሞክራት፣ ስናስበው ደግሞ አውቶክራትና ታይራንት የሚያደርገን፣ የአላዲንና የፋኖሱ ጂኒ ነው፤” ይላታል። “ ‘ዳዲ’ ጂኒ ምንድነው?” ሲል ደግሞ ብላቴናው በከረሜላ ጥርሶቹን መጨረስ በሚገባው ዕድሜ ጌሙ ላይ እንዳፈጠጠ ዓይኑን ከስልኩ ባትሪ እኩል እያዳከመ ይጠይቃል። ወጋ ወጋ ጠቅ ጠቁ ጂኒ፣ ጂኒ ቁልቋል ወሬ ቢመስልም ሰውን ግን ያስተነፍሰዋል። ታክሲ ሳንባን የመተካት አቅም እንዳለው ሳይንስ ደርሶበት ይሆን?
ሾፌራችን እንደ ሰደድ እሳት ጨዋታ ተጀምሮ ሲቀጣጠል፣ “ታክሲ ውስጥ በህቡዕ መደራጃት ሳይጀመር…” እያለ ለወያላው የሬዲዮኑን ድምፅ ጨመር ያደርገዋል። አንጀት የሆነ የስፖርት ትንታኔ እናዳምጣለን። “ክርስቲያኖ ሮናልዶና ሊዮኔል ሜሲ እንደ አሜሪካና ሩሲያ ተፋጠዋል፤” ይላል ጋዜጠኛው። “አሜሪካና ሩሲያ ተፋጠዋል እንዴ? ለመሆኑ እነሱም እንደኛ የሚያፋጥጥ ጉድ ያውቃቸዋል እንዴ?” ትላለች ከኋላችን ቆንጂት። ወይዘሮዋ ቀበል አድርጋ፣ “ኧረ ዝም በይው። ይኼ ይኼ አንቺን አይመለከትም። የኮስሞቲክስና የፀጉር መሥሪያ ዋጋ የሚያሳስባችሁ አልበቃ ብሎ ጭራሽ የሩሲያና የአሜሪካ ፍጥጫ ይጨመርባችሁ?” ስትላት ተሳፋሪዎች ተደናገጡ። ወዲያው ግን፣ “በተመሳሳይ ፆታ መሀል የተነሳ ‘ክሪቲሲዝምን’ የሚዳኝ ሕግ እስኪወጣ ምን ማድረግ ይቻላል?” ብሎ ጋቢና የተቀመጠው ወጣት ቀልባችንን ወደ ሜሲና ሮናልዶ ፍጥጫ መለሰው። አፍታም አልቆየ ሜሲ ይበልጣል ሮናልዶ ክርክሩ ጦፈ።
“ደግሞ ሜሲ ጀግና ይባላል? በስንት ተጋዳይ ሰማዕታት ላብና ደም እኮ ነው እዚህ የደረሰው፤” ሲል አንዱ ሌላው ተቀብሎ፣ “ስለኳስ ተጫዋቹ ሜሲ ነው የሚያወራው ወይስ ሜሲ የሚባል ታጋይ ነበረ?” ይላል ሌላው። “ሮናልዶንማ የሚያክለው የለም አይገርማችሁም? (ኧረ ማንም አልተገረመም ወንድም) ምናልባት ራሱ ስለራሱ ችሎታ አዳንቆ ሜሲን እበልጠዋለሁ ማለቱ ቢያስተቸውም…፤” ብሎ ሌላው ንግግሩን ሳይጨርስ ደግሞ ወዲያ ገቢና ያለው ጣልቃ ገብቶ፣ “እኔ እኮ ሐበሻ ብቻ ይመስለኝ ነበር በእኔ እበልጥ በእኔ እሻል የሚዳማው። የእኔ አስተዳደር፣ የአገር ግንባታ፣ የኢኮኖሚ ልማት፣ ወዘተ ካለፈው ከሚመጣው ይለያል የሚል ሐበሻ ብቻ ይመስለኝ ነበር። ለካ ፈረንጅም ራሱን ያንቆለጳጵሳል?” ብሎ ባለታኬታውን ዘውድ ከሚጭነው ጋር ያመሳስላል። በተረፈ ልፋ ያለው ‘የሜዳን ለባለሜዳው! የዙፋንን ለባለዙፋኑ!’ ቢባል ጆሮ ዳባ ልበስ ባይ ሆኖ ይኼው እጅግ በጣም ብዙ በርካታ ዓመታትን የእንፉቅቅ እያዘገመ ነው፡፡
ቀዘዝ ያለው ወያላችን ነገረ ሥራው ሁሉ ዝግ ያለ ነው። “አቤት አንተ! እንኳንም ‘ቪዛ’ ሰጪ አልሆንክ፤” ትለዋለች እዚህ ከጀርባዬ። “እውነትም! ቆይ አንተን እንደምንም ብዬ በዘመድም ቢሆን ገቢዎች ማስቀጠር አለብኝ፤” ስትል ደግሞ ከጎልማሳው አጠገብ ያለቸው ትቀልዳለች። “እንዴ በዘመድ መቅረት አለበት አልተባለም እንዴ?” መሀል ላይ የተሰየመው ወላጅ ልሳኑ ተከፈተ። “ቢባልም አይተገበርም፣ ቢተገበርም አይዘልቅም በሚል ለምን አንይዘውም?” ልጅት ፈገግታዋ ከፊቷ ላይ ሳይከስም ጨዋታውን አደራችው። “ለምን እንይዘዋለን እንዳንቺ ዓይነቷን ነው እንጂ ማስያዝ፤” ሰውዬው የምሩን ጭሯል። ልጅት ቀልድ ያለችው መምረሩ ሲገባት ፊቷን አዙራ ድምጿን አጠፋች። ወዲያው ከጎኔ የተሰየመችው ወይዘሮ ባረጋጋው ብላ ነው መሰል “እንደሷ ያለውን ከማስያዝ አንድኛውን አገሪቷን ማስያዝ አይቀልም ብለህ ነው? ሃሃሃ ቂቂቂ . . .” የውሸት ሳቅ ናት።
“ወያላ! በልማ ‘የሚሳቀው አርቴፊሻል’ የሚለውን ዘፈን ጋብዘን፤” መጨረሻ ላይ ካሉት ጓደኛማቾች አንደኛው ‘ሙድ’ ይይዛል። ወይዘሮዋ ግን ያሰበችው ተሳክቷል። “ልክ ነሽ። እንክርዳዱና ገለባውን ማሳውን ሞልቶት፣ እሱን ከመለየት ፍሬውን ለቅሞ ሲያበቁ ማሳውን ባለበት ማቃጠል ይቀላል፤” ብሎ ሰውዬው ተንፈስ አለ። “እንዴት ነው ነገሩ ጎበዝ? ‘ እናት አባት ቢሞት በአገር ይለቀሳል፣ አገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል?’ ብለን መስሎኝ ያደግነው? አላባውስ ጎተራ ሳይኖረው ተመርጦ ቢታጨድ ምን ይረባል?” ብሎ ጎልማሳው ገባበት። “ምን እናድርግ ጠፍቶን መሰለህ እሱ?” ሲለው ሰውዬው ጎልማሳው ይመልሳል ብልን ስንጠብቅ ‘8100 A-A-A’ በጩኸት አቋርጦት ገባ። “ህዳሴያችንማ የፈለገው ቢሆን ዕውን ይሆናታል እንጂ ወደኋላ ብሎ ነገር አይታሰብም፤” እያለ ተሳፋሪው ሞባይሉን አውጥቶ ‘‘A’’ን ጠቀጠቀ። የሞት ሽረት ማለት ይኼም አይደል?
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ሾፌራችን እስኪያወርደን ከመቸኮሉ የተነሳ መንገዱ ሲዘጋጋበት እግረኛው መንገድ ላይ ተጠምዝዞ ወጥቶ ‘ቼ’ ይላል። “አይይ! ምናለበት አሁን መንገድህን ይዘህ ብትሄድ? አላልቅ አላችኋ ሰው! በዚህ እናንተ አላችሁ፣ ጉንፋንም በአቅሙ የ13 ወራት ደዌ ሆኖ ሥራ አላሠራ ብሏል አሉ። ‘በሞቴ አፈር ስሆን’ ቀርቶ ‘በኩላሊቴ ይዤሃለሁ’ ማለት እስክንጀምር ይኼው ኩላሊት ማሳጠቢያ አጥቶ ሰው ረገፈ። ልብስ ማጠቢያ ሳሙና መግዛትም አልሆነልን እንኳን ኩላሊት ልናሳጥብ፤” ወይዘሮዋ ትለዋለች። “ምን ይደረግ? የዚህ ዓለም ነገር ይኼው ነው። አንዱ ሲመጣ አንዱ ይሄዳል። ዓለም ሐዘን ሲለመድ እንባ እንደሚደርቅ አውቃ በሽታውን፣ መጥፊያ መክሰሚያውን ትለዋውጠዋለች፤” ጎልማሳው ነው ከንፈር እየመጠጠ የሚያስተክዘን። ድንገት ዘወር ስንል ‘ለሽምቅ ውጊያ ማስታጠቅ ጀምረናል’ የሚል ማስታወቂያ የተጻፈባት ያዘመመች ቤት አየንና ዓይናችንን ማመን ቢያቅተን ወያላው “ተረጋጉ! ምግብ ቤት ነው፤” ብሎ አፋችንን አስከፈተው።
“እና ስም አልቆባቸው ነው ‘ለሽምቅ ውጊያ ማስታጠቅ ጀምረናል’ የሚሉት?” ሲለው ጋቢና የተሰየመው፣ “በዚህ ጊዜ ከዚህ የበለጠ ድንቅ ስያሜ ምን አለ? ሽምቅ ውጊያ የተባለው ኑሮ ነው የሚዘጋጀው ትጥቅ ምግብ መሆኑ ነው። ሁለት ጥብስ ፍርፍር ለአራት አጥቅተህ፣ ጥግብ ብለህ . . . ሻይ ቡና አምቦ ውኃ ጠጥተህ፣ 45 ብር ከከፈልክ ምን ትፈልጋለህ?” ሲል ሰውየው ተሳፋሪዎች በጠቅላላ “ወራጅ” ብለው ከመቀመጫቸው ተነሱ። ጎልማሳው ብቻ ከመቀመጫው ንቅንቅ ሳይል፣ “ቅድም ምን ስትሉ ነበርና ነው አሁን እንዲህ የሚያደርጋችሁ?” ብሎ ተቆጣ። “ቅድም የዓለም ሴራዋ፣ በሽታዋ፣ ስቃዩዋ፣ ጦርነቷ፣ ስደቷ፣ ፍትሕ አልባነቷ፣ ወዘተ ምን ያላላችሁት ነበር። አሁን ደግሞ ዓለም አታላይ ሆዬ ‘ይውጋሽ ብላ በይማርሽ’ ሥልቷ ምግብ በነፃ በእጅ አዙር ስታቀርብ ትሻማላችሁ? የወጋ ቢረሳ የተወጋም ይረሳ?” ብሎን አረፈው። “ቆይ ግን” በመንገዱ ቂም ይዘን፣ ባለፉት ሥርዓቶች ቂም ይዘን፣ በፍትሕና በዴሞክራሲ እጦት፣ በሐሳብ አፈናው ካሁኖቹ ጋር ሳይቀር ተኮራርፈን፣ ይኼ ሁሉ አልበቃን ብሎ ደግሞ በዓለም ላይ ቂምና ኩርፊያ? ጉድ ሲንተከተክ እንዲህ ነው ይኼውላችሁ፤›› ብላ ያቺ ወይዘሮ የጉዞውን ማጠናቀቂያ ትችት ስታቀርብ ተግተልትለን ወረድን፡፡ በስንቱ ቂም ተይዞ ይቻላል? መልካም ጉዞ!