Sunday, October 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከእጥፍ በላይ የዋጋ ቅናሽ የታየበት በርበሬና የሚጠበቀው የዋጋ ለውጥ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለፈው ዓመት በከፍተኛ ደረጃ የዋጋ ጭማሪ የታየበት የዛላ በርበሬ ዋጋ እየወረደ መጥቶ ከዕጥፍ በላይ የዋጋ ቅናሽ ለውጥ አሳየ፡፡ ከመስከረም 2008 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ በተወሰነ ደረጃ የዋጋ ለውጥ የታየበት ዛላ በርበሬ፣ በአሁኑ ወቅት በኪሎ ከ75 እስከ 85 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የዋጋ ለውጥ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ከእጥፍ በላይ ቅናሽ የታየበት ነው፡፡

ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ባልተለመደ ሁኔታ የዛላ በርበሬ የመሸጫ ዋጋ እየጨመረ በመምጣት ሐምሌ 2007 ዓ.ም. የአንድ ኪሎ ዛላ በርበሬ ዋጋ እስከ 200 ብር ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ገበያ ላይ ግን ለተከታታይ ሦስት ወራት ከ170 እስከ 180 ብር ሲሸጥ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ኅዳር 2007 ዓ.ም. ላይ የአንድ ኪሎ ዛላ በርበሬ ዋጋ 30 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ ከታህሳስ በኋላ ግን ባሉት በተከታታይ ወሮች የታየው ጭማሪ ግን የበርበሬ ዋጋ መረጋጋት እንዳይታይበት አድርጎት ቆይቷል፡፡

ለተከታታይ ዘጠኝ ወራት ዋጋው እያደገ የመጣው የዛላ በርበሬ፣ በተለይ ካለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት ወዲህ ግን በአዲስ አበባ ገበያዎች ኪሎው በአማካይ 80 ብር ድረስ ለመሸጥ በቅቷል፡፡

ከአዲስ ምርት መግባት ጋር ተያይዞ እየቀነሰ ያለው የዛላ በርበሬ ዋጋ ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ግን የተጠበቀውን ያህል ያለመቀነሱን ሸማቾችና ነጋዴዎች ይገልጻሉ፡፡

በሾላ ገበያ ያገኘናቸው የቅመማ ቅመምና የበርበሬ ነጋዴ እንደገለጹት ‹‹የበርበሬ ዋጋ እየቀነሰ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ጥቅምትና ኅዳር ወር ላይ ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ግን አሁን እየተሸጠበት ያለው ዋጋ ብልጫ አለው፤›› ይላሉ፡፡ አምና በዚህ ወቅት አንዱን ኪሎ ዛላ በርበሬ ከ30 እስከ 35 ብር ይሸጡ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በተለይ በሚቀጥለው ወር ግን ዋጋው ይቀንሳል ብለው እንደሚጠብቁ ጠቁመዋል፡፡ እንደ ነጋዴዋ ገለጻ ግን የበርበሬ ዋጋ እንደዓምና በከፍተኛ ደረጃ የተሸጠበትን ወቅት የለም፡፡

ባለፈው ዓመት ለበርበሬ ዋጋ መጨመር ዋና ምክንያት የምርት እጥረት እንደነበር ሲገለጽ የነበረ ሲሆን፣ ሰው ሠራሽ ድርጊቶችም ለዋጋው መጋጋል ሌላው መንስዔ እንደነበር መገለጹ ይታወሳል፡፡

ከዚህ ቀደም የተከሰተው የዋጋ ንረት ተፈጭቶ ለገበያ ይቀርብ የነበረው በርበሬ ላይም ተፅዕኖ ማሳደሩ አይዘነጋም፡፡ በዚህም ምክንያት ተፈጭቶ የተዘጋጀ አንድ ኪሎ በርበሬ ከ250 ብር በላይ ዋጋ እንዲያወጣ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ከ140 እስከ 170 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ከበርበሬ ሌላ ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ዋጋው የተሰቀለው የሚጥሚጣ ዋጋ ግን አሁንም የዋጋ ለውጥ ሳያሳይ ቀጥሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት አንድ ኪሎ ዛላ ሚጥሚጣ ዋጋው ከ230 እስከ 250 ብር ይደርሳል፡፡ ያነጋገርናቸው የሾላ ነጋዴዎች ካለፈው ዓመት አጋማሽ በፊት ተወደደ ተብሎ ይሸጥበት የነበረው ዋጋ 50 ብር እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ እንደ በርበሬው ሁሉ በሚጥሚጣ ምርት ላይም ተመሳሳይ የምርት እጥረት ነበር የተባለ ሲሆን፣ የበርበሬ ዋጋ እየወረደ ቢመጣም ይህ ለውጥ በሚጥሚጣው ላይ አልታየም፡፡ እንደ ነጋዴዎቹ ገለጻ የሚጥሚጣ ምርት የሚደርሰው በጥር አካባቢ በመሆኑ፣ የምርት ወቅቱ ሲደርስ ይቀንሳል ብለው እየጠበቁ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በበርበሬ ምርት ከዓለም በአምስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ነች፡፡ በቅርቡ የአገሪቱን የቅመማ ቅመም ምርቶች በተመለከተ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት ላይ በቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ፣ በአፍሪካ ደረጃም ኢትዮጵያ ቀዳሚ የበርበሬ አምራች አገር መሆኗን ያመለክታል፡፡ በየዓመቱም የበርበሬ ፍላጎቱ እየጨመረ መምጣቱንም ይጠቅሳል፡፡

በወቅቱ በአቶ አዲሱ ዓለማየሁ የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍም፣ በኢትዮጵያ እየተመረተ ያለው የበርበሬ መጠን በየዓመቱ እያደገ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በበርበሬ አምራችነታቸው ከሚታወቁት ውስጥ ህንድ በመጀመርያው ረድፍ ላይ የተቀመጠች መሆኗን ጥናቱ ያሳያል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች