Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለደብረ ብርሃን – አንኮበር መንገድ ግንባታ ተጫራቾች ከ799 ሚሊዮን እስከ 2.2 ቢሊዮን ብር ዋጋ ሰጡ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዋናነት ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር ለሚገነባው የአንኮበር – ደብረ ብርሃን መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ጨረታ፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ኮንትራክተሮች ከ799 ሚሊዮን ብር እስከ 2.2 ቢሊዮን ብር ዋጋ መስጠታቸው ተጠቆመ፡፡

42 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውን ይህንን መንገድ ለመገንባት ስምንት የአገር ውስጥና የውጭ ኮንትራክተሮች የተሳተፉ ሲሆን፣ ተወዳዳሪዎቹ ከፍተኛ ልዩነት ያለው ዋጋ የሰጡበት ጨረታ ሆኗል፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ ከተወዳዳሪ ኮንትራክተሮች ውስጥ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ መንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን 799 ሚሊዮን ብር በመስጠት ከተወዳዳሪ ኮንትራክተሮቹ ሁሉ ዝቅተኛ የተባለውን ዋጋ መስጠት መቻሉን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ የአማራ የገጠር መንገድ ኮንስትራክሽን ደግሞ በዚህ ጨረታ የሰጠው 2.2 ቢሊዮን ብር ከፍተኛ የመወዳደሪያ ዋጋ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ከባለሥልጣኑ ያገኘነው መረጃም እንደሚያመለክተው አሁን የተከፈተው የፋይናንሻል መወዳደሪያው ሲሆን፣ በቅርቡ የቴክኒካል ምዘናው ከተካሄደ በኋላ አሸናፊው ይፋ ይደረጋል፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ተወዳዳሪዎቹ ያቀረቡት ዋጋ ቢታወቅም፣ አሸናፊው የሚለየው ግን ተወዳዳሪዎቹ ያቀረቡት የቴክኒካል ብቃት ካቀረቡት ዋጋ ጋር ተመዝኖ በሚሰጠው ውጤት ነው ተብሏል፡፡

በዚህ ጨረታ ከተጫራቾች ሁሉ ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረበው የኢትዮጵያ መንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን አሸናፊ የሚሆን ከሆነ፣ እንደ ዓለም ባንክ ባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ፋይናንስ ባደረጉትና በዓለም አቀፍ ደረጃ በወጣ ጨረታ አሸናፊ የሚሆን አገር በቀል ተቋራጭ ይሆናል፡፡

የአንኮበር – ደብረ ብርሃን መንገድ ከዚህ ቀደም በጠጠር መንገድ ደረጃ የነበረ መንገድ ነው፡፡ አሁን በአስፓልት ኮንክሪት የመንገድ ደረጃ የሚሠራ ይሆናል፡፡

በበጀት ዓመቱ ወደ ሥራ ከሚገቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የአንኮበር – ደብረ ብርሃን መንገድ ፕሮጀክት፣ የደብረ ብርሃን – አዋሽ አርባ መንገድ ፕሮጀክት አንድ አካል ነው፡፡

የደብረ ብርሃን – አዋሽ አርባ ፕሮጀክት በሦስት ተከፋፍሎ የሚሠራ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የጨረታ ሒደቱ በመጠናቀቅ ላይ ካለው የደብረ ብርሃን – አንኮበር መንገድ ሌላ 42 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው የአንኮበር – ዱለቻ መንገድ ሥራም በተመሳሳይ በጨረታ ሒደት ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሦስተኛው የፕሮጀክቱ አካል የሆነውና ከዱለቻ – አዋሽ አርባ ያለው መንገድ ደግሞ ባለፈው ዓመት አታዮል ለተባለ የቱርክ ኮንትራክተር መሰጠቱ ይታወሳል፡፡  የቱርኩ ኮንትራክተር የተረከበው ይህ መንገድ አጠቃላይ ርዝመቱ 52 ኪሎ ሜትር ነው፡፡ ኮንትራክተሩ ከአንድ ዓመት በፊት በተካሄደ ጨረታ አሸናፊ ሆኖ ሥራውን የተረከበበት ዋጋ ደግሞ 595 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡

ሦስቱም ፕሮጀክቶች በዓለም ባንክ በተገኘ ብድር የሚገነቡ ሲሆን፣ ከጠቅላላ የፕሮጀክቶቹ ወጪ የኢትዮጵያ መንግሥት ከ25 እስከ 30 በመቶውን ሊሸፍን እንደሚችል ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ የደብረ ብርሃን – አንኮበር መንገድና ቀሪዎቹ ሁለት የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ይካሄዳል ተብሎ ከታቀደበት ጊዜ ዘግይተው ወደ ሥራ የገቡ ናቸው፡፡ ለፕሮጀክቶቹ መዘግየት ምክንያት የሆነው ደግሞ ለግንባታው የሚያስፈልገውን ገንዘብ የዓለም ባንክ በቶሎ ባለመልቀቁ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች