Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ስታንዳርድ ባንክ በኢትዮጵያ የሾማቸው ኢትዮጵያዊት ምን ዓይተዋል?

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የደቡብ አፍሪካው ስታንዳርድ ባንክ በአፍሪካ በሀብት ደረጃ ቀዳሚ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ባንክ በአፍሪካ አገሮች ሥር የሰደደ ሲሆን፣ ከጥቂት ቀናት በፊትም በአዲስ አበባ ወኪል ጽሕፈት ቤቱን በመክፈት ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት ለሚፈልጉ ደንበኞቹ ስለኮኖሚውና ስለሚሰማሩበት መስክ ምክር ለመስጠት መምጣቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ቦሌ አካባቢ ከኤድና ሞል ወረድ ብሎ በሚገኘው ፓርክ ሌይን ታወር ሕንፃ ላይም ቢሮው ሥራውን ጀምሯል፡፡ በመሆኑም ባንኩ በኢትዮጵያ መሰማራት ለሚፈልጉና ከየትኛውም ዓለም የሚመጡ ደንበኞቹ የሚነሷቸውን ጥያቄዎች በማጥናት ከማስተናገድ ባሻገር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በኃይል፣ በመሠረተ ልማት፣ በነዳጅና በጋዝ፣ በማዕድን መስክ እንዲሁም በፍጆታ ዕቃዎች ላይ ለሚሰማሩ ደንበኞች ብድር የማቅረብ ፍላጎት እንዳለውም አስታውቋል፡፡

ይህንን ባንክ በከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንትነት የሚመሩት ወይዘሪት ጣይቱ ወንድወሰን፣ በአዲስ አበባ የተከፈተውን ወኪል ጽሕፈት ቤት እንዲመሩ መሾማቸው ይፋ ከተደረገ ቢቆይም፣ የቢሮው ሥራ መጀመር በተገለጸበት ባለፈው ሳምንት ከውጭና ከአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ጋር በሸራተን ትውውቅ አድርገዋል፡፡ ወይዘሪት ጣይቱ ስታንዳርድ ባንክን ከመቀላቀላቸው ቀድሞ በአሜሪካ የገዘፈ ስም ባላቸው ሁለት ባንኮች ውስጥ አገልግለዋል፡፡ በኒውዮርክ ፌዴራል ሪዘርቭ ባንክ የጀመረው የባንክ ሙያቸው ኋላ ላይ ወደ ጄፒ ሞርጋንም ወስዷቸዋል፡፡ የዓለም የፋይናንስ ቀውስ በተቀጣጠለበት ሰሞን፣ ከኒውዮርክ ፌደራል ሪዘርቭ ባንክ ጋር እየሠሩ እንደነበር ያጫወቱን ወይዘሪት ጣይቱ፣ ስታንዳርድ ባንክ በኢትዮጵያ ስለከፈተው ወኪል ጽሕፈት ቤት ተልዕኮዎችና ባንኩ በኢትዮጵያ ፍላጎት ስላሳየባቸው መስኮች ከብርሃኑ ፈቃደ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡– በኢትዮጵያ የአፍሪካን ትልቁን ባንክ እየወከሉ፣ እንዴት እንደታሰበ ቢገልጹልን?

/ሪት ጣይቱ፡ ይህ አባባል መስተካከል አለበት፡፡ ስታንዳርድ ባንክ ባለው ሀብት ከአፍሪካ ትልቁ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን ባንክ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ትልቁ ባንክ አይደለንም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የባንክ ሚና የለንም፡፡ ባንክ መሆንም አንችልም፡፡ እንዲሁ ወኪል ጽሕፈት ቤት ነው የምንመራው፡፡ የውጭ ተቋም በመሆናችን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ባንክ መንቀሳቀስ አንችልም፡፡ መንግሥት እንድናደርግ የሚፈልቅድልን ብቸኛው ነገር የንግድ ወኪል የሆነ ጽሕፈት ቤት እንድንከፍት ነው፡፡ ይህ ጽሕፈት ቤት ራሳችንን ለገበያው እንድናቀርብ፣ ሕዝቡ ምን እንደምንሠራና እንዴት እንደምንሠራ እንዲያውቅ ይረዳናል፡፡ ሌላኛው ትልቁ እውነታ ግን ደንበኞቻችን የሆኑ ትልልቅ ኩባንያዎችን ለመደገፍ ነው፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት ፈልገው መረጃ የሚጠይቁን ናቸው፡፡ ጽሕፈት ቤቱን ኢትዮጵያ ውስጥ እንድንከፍት ምክንያት የሆኑንም እነሱ ናቸው፡፡ ደንበኞች በየቀኑ ስለኢትዮጵያ ይጠይቃሉ፡፡ እየደወሉ ይሄ ነገር ኢትየጵያ ውስጥ እንዴት እንደሚሠራበት ታውቃላችሁ? ይሄ ነገር እንዴት ነው የሚታየው? ወዘተ. እያሉ ይጠይቁናል፡፡ ስለዚህ እኛም እዚህ የመጣነው ገበያውን ለመረዳት፣ ኢኮኖሚውን በቅጡ ለመረዳት፣ የጥናት አቅማችንን ለማዳበር፣ እያንዳንዱን ነገር ለመረዳት፣ ነገሮች እንዴት እንደሚንቀሳቀሱና እዚህ ኢንቨስት የማድርግ አቅም ያለው ደንበኛችን ሲኖርም እዚህ እንዲመጡ ለመርዳት እንዲያስችለን ነው ጽሕፈት ቤቱ የተከፈተው፡፡

ሪፖርተር፡– ስለዚህ ደንበኞቻችሁ በመላው አፍሪካ ብቻ ናቸው ወይስ ከዚያም ባሻገር ይገኛሉ?

/ሪት ጣይቱ፡ በአፍሪካ የሚሠሩ አሉ፡፡ ከአፍሪካ ባሻገርም በመላው ዓለም ደንበኞች አሉን፡፡ ወደ አፍሪካ ለሚመጡም አፍሪካ ውስጥ ላሉትም ኩባንያዎች እንደ መግቢያ በር ልንታይ እንችላለን፡፡ ዋናው ትኩረታችንና ፍላጎታችን አፍሪካን በሙሉ ማዳረስ ቢሆንም ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከእስያ፣ ከደቡብ አሜሪካና ከሌላውም አካባቢ የሚመጣውን ደንበኛ ከማገልገል አያግደንም፡፡ ደንበኞቻችን ሁሉም ቦታ አሉ፡፡

ሪፖርተር፡– እንደ ስታንዳርድ ባንክ ያለውን ትልቅ ባንክ ገጽታ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት መሥራት እንዴት ይታያል

/ሪት ጣይቱ፡ ለስታንዳርድ ባንክ መሥራት ትልቅ ነገር ነው፡፡ ባንኩ በመላው አፍሪካ እያደገ፣ እየተለወጠና በጣም በርካታ ፍላጎቶች ከመላው ዓለም እየጎረፉለት ያለ ነው፡፡ ሌሎች አካባቢዎች የማናየውን ያህል የኢኮኖሚ ዕድገት በአፍሪካ እያየን ነው፡፡ በርካታ ሰዎች እየመጡ ቢዚነስ መሥራት ይፈልጋሉ፡፡ አፍሪካን ለማሳደግ ትኩረት አድርጎ ከሚሠራ ባንክ ጋር አብሮ መሥራት ትልቅ ነገር ነው፡፡ ባንኩ በአፍሪካ የሚታየው ዕድገት ቀጣይነትን የማስጠበቅ ድርሻ አለበት፡፡ ስለዚህ ከዚህ ባንክ ጋር መሥራት ትልቅ ዕድልና መታደል ነው፡፡

ሪፖርተር፡– አመጣጥዎ ከትልልቅ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመሥራት ልምድ የታጀበ እንደመሆኑ ሌሎች እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ሳይቀር ያላቸውን ዓይነት የካፒታል ገበያ ወይም ስቶክ ገበያ ኢትዮጵያ ውስጥም እንዲኖር ቢደረግ ይመክራሉ?

/ሪት ጣይቱ፡ እዚህ የመጣነው መንግሥት ምን ማድረግ እንዳለበትና እንደሌለበት ለመንገር አይደለም፡፡ ነገር ግን ካፒታል ገበያዎች አገሮች እንዲያድጉ፣ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ አግዘዋል፡፡ እዚህ መንግሥት ምን እንደሚሠራ ያውቃል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የራሳቸው ዕቅድም ይኖራቸዋል፡፡ አገሪቱ በታሪኳ ለኢንቨስተሮች ክፍት በመሆን ትልቁን ምዕራፍ ጀምራለች፡፡ በቅርቡም የዩሮ ቦንድ ሽያጭን ለገበያ አውላለች፡፡ እዚህ የካፒታል ገበያ ላይኖራችሁ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከውጭ ያሉ ገበያዎችን እየተጠቀማችሁ ነው፡፡ ኢንቨስተሮች እንዲመጡ እያደረጋችሁ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ያልተከፈቱ የኢኮኖሚ አውታሮችን ክፍት እያደረጋችሁ በመሆኑ በጠቅላላው ለውጦች አሉ፡፡ መንግሥት ኢኮኖሚው ለግሉ ዘርፍ እየከፈተ ነው፡፡ የተወሰኑ ዘርፎችን አልከፈተም ማለትም ሊበራል ያልሆነ መንግሥት አያሰኘውም፡፡ እንደማስበው በጊዜ ሒደት በራሳቸው አካሄድ ሌሎች የኢኮኖሚ መስኮችን ክፍት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡– በርካታ ደንበኞችን ሊወክሉ መጥተዋል፡፡ ሌሎችም እንደ የህንድ ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ ያሉት፣ እንደ ኮሜርስ ባንክ ያሉትን ጨምሮ ከቻይናም ከአፍሪካም ጽሕፈት ቤታቸውን በኢትዮጵያ ከፍተዋል፡፡ ከእነዚህ ባንኮች ጽሕፈት ቤቶች ጋር ግንኙነት መሥርታችኋል?

/ሪት ጣይቱ፡ ኤኮ ባንክ ወኪል ጽሕፈት ቤት እንደከፈተ እናውቃለን፡፡ ዋና ከሚባሉት ተዋናዮች መካከል የሚመደቡ ናቸው፡፡ ኮሜርስ ባንክም እንደዚሁ ብዙዎቻችን ከመምጣታችን ቀድሞ ወኪል ጽሕፈት ቤት በመክፈት ቀዳሚው ነው፡፡ ከሌሎች ገበያዎች ጋርም እየተባበርን ነው፡፡ ግንኙነት መመሥረቱ አስፈላጊ ነው፡፡ ገና መክፈታችን ነው፡፡

ሪፖርተር፡– አንዳችሁ ከሌላችሁ ጋር የመወዳደር አዝማሚያ አይሆንም፡፡ ወኪል ጽሕፈት ቤቶች እየተበራከታችሁ እንደመሆኑ አንዳችሁ ከሌላችሁ ጋር ደንበኛውን ለማገልገል፣ጥናት ለማድረግ ወዘተውድድር እየሆነ ነው?

/ሪት ጣይቱ፡– እኛ እዚህ እንደባንክ አይደለም እየሠራን ያለነው፡፡ የባንክ ዘርፉ ክፍት ቢደረግ ነበር ውድድር ውስጥ ስለመሆናችን ልንናገር የሚቻለው፡፡ እኛ ግን ኢኮኖሚው ምን እንደሚመስል ለደንበኞቻችን ለማስረዳት፣ ሕዝቡም እንዲያውቀን ነው የመጣነው፡፡ ስለዚህ ውድድር የሚለው ገላጭ አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡– ስታንዳርድ ባንክ ንግድ ባንክ ነው፡፡ አንዳንድ ባንኮች ንግድ ላይ ያልተመሠረተ ብድር ያቀርባሉ፡፡ የዚህ ዓይነት አካሄድ ይኖራችኋል?

/ሪት ጣይቱ፡ የዓለም የኤክስፖርትና የኢምፖርት ባንኮች ይሄንን ከእኛ ይልቅ በተሻለ ያከናውኑታል፡፡ እኛ ከንግድ ብድር ውጭ አንሠራም፡፡

ሪፖርተር፡– ለኢትዮጵያ ብድር ልትሰጡባቸው የምታስቧቸው መስኮች የትኞቹ ናቸው?

/ሪት ጣይቱ፡ በኢትዮጵያ ሁሉም የኢኮኖሚ መስክ ላይ የሚታየው እንቅስቃሴ መስህብ አለው፡፡ በኃይል ዘርፍ፣ በመሠረተ ልማትና በፍጆታ ዕቃዎች ኢንዱስትሪ ላይ በርካታ ኩባንዎች ፍላጎት እንዳላቸው እያየን ነው፡፡ ከሕዝቡ ብዛት አኳያ ሁሉም ሸማች ይህንን ዜና መስማቱ የሚያስደስተው ይመስለኛል፡፡ እኛ ግን ደንበኞቻችን መሥራት በሚፈልጉባቸው መስኮች መሠረት እንከተላቸዋለን፡፡

ሪፖርተር፡– ስለዚህ ቅድሚያ የምትሰጧቸው መስኮች የትኞቹ ናቸው?

/ሪት ጣይቱ፡ ስታንዳርድ ባንክ በተለምዶ በኃይልና በመሠረተ ልማት ዘርፍ ላይ ጠንካራ ገበያ አለው፡፡ በነዳጅና በጋዝ መስክም ጠንካራ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ በማዕድን ኢንዲስትሪው መስክ ጠንካራና ትልቅ ቦታ ስላላት ባንኩም በዚያ ላይ በርካታ ፋይናንሶችን ያቀርባል፡፡ እዚህ ለባንኩ ብዙ ባይሆንም እነዚህ ላይ ትኩረት ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡– በባቡርም ሊሆን ይችላል በሌላው መስክ ፋይናንስ ለማድረግ የያዛችኋቸው ፕሮጀክቶች አሉ?

/ሪት ጣይቱ፡ ገና እያየን ነው፡፡ ፋይናንስ ስናደርጋቸው ለሕዝቡ እናሳውቃለን፡፡ አሁን ግን ፋይናንስ ለማድረግ የሚያችሉ አጋጣሚዎችን እየቃኘን ነው፡፡

ሪፖርተር፡– ስታንዳንድር ባንክ ጽሕፈት ቤቱን እንዲመሩለት በኢትዮጵያ የመደበዎት ኃላፊ ነዎት፡፡ ስለራስዎ ቢነግሩን፤

/ሪት ጣይቱ፡ ተወልጄ ያደግሁት እዚህ ነው፡፡ በአብዛኛው ዕድሜዬን ያሳለፍኩትና ትምህርቴን የተከታተልኩት በአሜሪካ ነው፡፡ አሁን ወደ አገሬ መጥቻለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ መምጣቱ ትክክልም ይመስለኛል፡፡ ኢኮኖሚው በጣም በሚያስገርም መልኩ እያደገ ነው፡፡ ሁልጊዜም በኢኮኖሚክስና በፋይናንስ ሙያዎች ላይ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ከያዝኩ በኋላ ወደ ኒውዮርክ በማቅናት ተጨማሪ ዲግሪዬን ከያዝኩ በኋላ ኒውዮርክ ፌደራል ሪዘርቭ ባንክን ተቀላቅያለሁ፡፡ ይህ ባንክ በአሜሪካ ካሉ ማዕከላዊ ባንኮች አንዱ ትልቁ ባንክ ነው፡፡ በዚያ ለተወሰኑ ዓመታት ሠርቻለሁ፡፡ ከዚያም ወደ ንግድ ባንኮች በማቅናት ጄፒ ሞርጋን የሚባለውንና ኒውዮርክ የሚገኘውን ባንክ ተቀላቅዬ ሠርቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡– መቼ? ከፋይናንስ ቀውሱ በፊት ወይስ በኋላ?

/ሪት ጣይቱ፡ እርግጥ ስሠራ የነበረው በቀውሱ ጊዜ ነው፡፡ በዚያ ወቅት ለኒውዮርክ ፌደራል ሪዘርቭ ባንክ ነበር የምሠራው፡፡ ቀውሱን የማርገብ ኃላፊነት ተሰጥቶን ነበር፡፡ አንዳንድ ባንኮችን የመታደግ (ቤል አውት) ሥራንም ያካትታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች