Sunday, June 4, 2023

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወሳኝነታቸውን ያሳዩበት መድረክ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለፉት 24 ዓመታት ፍፁም የበላይነት የያዘው ኢሕአዴግ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ወደ አመራር ከመጡ በኋላ ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች ቅድሚያ የያዘው መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚደረገው ጥረት ነው፡፡ የዚህ ጥረት መገለጫ ተደርገው የሚወሰዱ በርካታ አስተዳደራዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት የተወሰዱ ሲሆን፣ መሠረታዊ ለውጥ ባለመምጣቱ የገዢው ፓርቲ ቁርጠኝነት ላይ ጥርጣሬዎች መሰማታቸውና ‹ዕርምጃዎቹም› አፍአዊ ብቻ ናቸው ሲባል መስማት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡

በቅርቡ ግን ይህን አዝማሚያ የቀየረና ቁርጠኛነቱን አንድ እርከን ያሳደገ ክስተት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ቢሮ ተሰምቷል፡፡ የአገሪቱን ቁልፍ ሥልጣን የጨበጡት አቶ ኃይለ ማርያም ቢሮ የተካሄደው ውይይት በከፍተኛ ባለሥልጣናት ተሳትፎ የታጀበ ነበር፡፡ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱን አሳልፎ ለሕዝባዊ ተጠያቂነት አይሰጥም ተብሎ የሚታማው ኢሕአዴግ፣ በግንቦቱ ጠቅላላ ምርጫ መቶ በመቶ ማሸነፉ ይህን ተጠያቂነትን የመሸሽ አዝማሚያ ያጠናክራል ተብሎ የተሠጋ ቢሆንም፣ ውይይቱ ኢሕአዴግ ይህን የመለወጥ ዕቅድ እንዳለው ፍንጭ የሰጠ ነበር፡፡

የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ለመቅረፍ የተለያዩ መድረኮችን መፍጠር አዲስ ነገር ባይሆንም፣ ይኸኛው መድረክ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ከፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃይል ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተሠራው ጥናት መነሻነት መካሄዱ ለየት የደርገዋል፡፡ ጥናቱ የፖለቲካ አመራሩን ቁርጠኝነት፣ የአገልጋይነት መንፈስ፣ ተጠያቂነትና ብቃት፣ የመንግሥት ሠራተኛውን የአገልጋይነት መንፈስ፣ ቁርጠኝነት፣ ብቃትና የሚገጥሙት ማነቆዎች፣ የሕዝቡ ተሳትፎ ጉዳይ፣ ሕዝቡ ቅሬታ የሚያቀርብባቸው ምክንያቶች፣ ለውጥ የሚያመጣ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ሕዝቡን ምን እንደያዘውና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ እንዳተኮረ፣ በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ፍስሐ ሀፍተ ጽዮን ገልጸዋል፡፡ አቶ ፍስሐ እነዚህን ጉዳዮች ለመገምገም የጥናት ቡድኑ ቃለ መጠይቅ በማድረግ፣ የአትኩሮት የቡድን ውይይት በማድረግ፣ እንደ ግምገማ ሰነዶች፣ ቃለ ጉባዔዎች፣ ውሳኔዎችና የሕዝብ ቅሬታዎች ያሉ ሰነዶችን በመመርመርና መጠይቅ በመበተን፣ ለሦስት ወራት ያህል ሥራዎቹን እንዳከናወነ አመልክተዋል፡፡

በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተካ ገብረ ኢየሱስ የጥናቱን ውጤት አቅርበዋል፡፡ ጥናቱ ከተመለከታቸው ዘርፎች መካከል የመሬት ጉዳይ አሁንም ከፍተኛ የሆነ የመልካም አስተዳደር ዕጦት የሚስተዋልበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከኪራይ ሰብሳቢነት፣ ከቡድንተኝነት፣ ከውሳኔ ሰጪነት፣ ከተጠያቂነት፣ ከመረጃ አያያዝና ከአቅም ጋር የተገናኙ ችግሮች የዘርፉ መገለጫዎች መሆናቸውን ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

‹‹የሊዝ አዋጅ ቁጥር 721 ከወጣ በኋላ የመሬት ወረራና መሰል ችግሮችን የቀረፈ ቢሆንም፣ አዋጁን ተንተርሰው የወጡ ችግሮች መኖራቸው በሁሉም ክፍሎች በታዩ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ዘርፍ ተስተውሏል፤›› ያሉት አቶ ተካ፣ በተለይ በጨረታ መሬት ማቅረብን በተመለከተ ያለው አሠራር ጥቂቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ዘርፉ በሕገወጥ ደላሎች ተፅዕኖ ሥር ያለ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ይባስ ብሎም በቡድንተኝነት መንፈስ የአንድ አካባቢ ሰዎችን ብቻ ተጠቃሚ የማድረግ አሠራር እንደሰፈነበት አስገንዝበዋል፡፡ ተጠያቂነትን ማስፈን አዳጋች እንደሆነ ሲያስረዱም፣ ያጠፉ ሰዎች እንደ ሹመት ከቦታ ቦታ መዘዋወራቸውም በተደጋጋሚ ማጋጠሙን ጠቅሰዋል፡፡

ከመሬት አስተዳደር ጋር የተገናኘ ኃላፊነት ባላቸው ተቋማት አመራር ብቃት ላይ ክፍተት እንዳለ ያመለከቱት አቶ ተካ፣ ‹‹በትምህርት ዝግጅትም፣ በዕውቀትም፣ በልምዳቸውም በጣም ዝቅ ያሉ ሰዎች አንዳንድ ተቋማትን ሲመሩም ታይተዋል፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው በጥናቱ የተዳሰሰው ዘርፍ ኢንቨስትመንት ሲሆን እንደ መሬት ሁሉ ተመሳሳይ ችግር እንደተስተዋለበት ጠቁመዋል፡፡ በተለይ መሠረተ ልማቶች ባልተሟሉበት ሁኔታ በሕጉ መሠረት በስድስት ወራት ውስጥ ግንባታ አልጀመራችሁም በማለት አመራሮች በገንዘብ እንደሚደራደሩ አመልክተዋል፡፡ የአሠራርና የሕግ ግንዛቤ ክፍተትም በዘርፉ እንደሚታይ ጠቁመዋል፡፡ የባለድርሻ አካላት ቅንጅትና የሕዝቡ ተሳትፎ ጉድለት የሚታይበት እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡

ጥናቱ በንግድ፣ በፍትሕ ሥርዓት፣ በአዲስ አበባ ትራንስፖርት፣ በውኃና ፍሳሽና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይም ተመሳሳይ ችግሮች መስተዋላቸውን ይዘረዝራል፡፡ ንግድን በተመለከተ ግልጽነት አለመኖርና የተጠያቂነት ችግር ቁልፍ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ በተለይ ደንቦችና መመርያዎች ሁሉም ላይ እኩል ተፈጻሚ እንደማይደረጉ ተወስቷል፡፡

አቶ ተካ ለእነዚህ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ጥናቱ በመፍትሔነት ያስቀመጣቸውን ጉዳዮችም ጠቅሰዋል፡፡ የመጀመርያው የመፍትሔ ሐሳብ ለኪራይ ሰብሳቢነት ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎችን መዋቅርና አመራር ሙሉ በሙሉ መፈተሽ ነው፡፡ ‹‹የማፅዳትና የማሸጋሸግ ሥራ መሠራት አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ሁለተኛው የመፍትሔ ሐሳብ ቅሬታ የፈጠረ አመራር ላይ ዕርምጃ ተወስዶ ግብረ መልስ ለሕዝቡ መስጠት አለበት የሚል ነው፡፡ ‹‹ኅብረተሰቡ ምን ዓይነት ዕርምጃ እንደተወሰደ ማወቅ አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ሦስተኛው የመፍትሔ ሐሳብ በየደረጃው ያሉ የሕዝብ አደረጃጀቶችና ሚዲያ በዚህ ሥራ ላይ ግልጽ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው በተደራጀ አኳኋን እንዲንቀሳቀሱና ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ ማድረግ አስፈላጊ ነው የሚል ነው፡፡ አራተኛው የመፍትሔ ሐሳብ የአመራር ብቃት የሚመዘንበት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራር መኖር አለበት የሚል ነው፡፡ አቶ ተካ ‹‹የስብሰባ ሥርዓት መመርያ ሊወጣለት ይገባል፡፡ የስብሰባ ብዛት ችግር እየፈጠረ እንደሆነ ብዙ ሕዝብ ቅሬታ እያቀረበ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ውይይቱ

በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አማካይነት ከተላለፈው ፕሮግራም ለመረዳት እንደሚቻለው ያልቀረቡት ያልተዳሰሱ ጉዳዮች አሉ፡፡ በማብራሪያውና በጥያቄዎቹ መካከል የታለፉ መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና በርካታ ሚኒስትሮች በታደሙት ውይይት ችግሩ በጥናቱ ከቀረበውም በላይ ጥልቅ እንደሆነ ስምምነት ላይ የደረሱ ይመስላል፡፡ እርግጥ እንደ የቤቶችና ከተማ ልማት ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ያሉ ባለሥልጣናት ሪፖርቱ ያላገናዘባቸውን ጉዳዮች በመዘርዘር በድጋሚ እንዲታይ የጠየቁም ነበሩ፡፡ የፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬም በክልሎች የቀረበውን ችግር ተቀብለው የፌዴራል መንግሥቱ ላይ የቀረበው ዝርዝር የሚጎለው ነው ብለዋል፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣና ዋና ዳይሬክተር አቶ በከር ሻሌ ያቀረቡት አንድ ቅሬታ ግን ለየት ያለ ነበር፡፡ ጥናቱ በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞች ቶሎ ቶሎ ይለቃሉ በሚል ለቀረበው ችግር፣ መሥሪያ ቤታቸው በአንድ ዓመት ብቻ ከ1,000 በላይ ሠራተኛ ማባረሩን ለአብነት ይጠቀሳል፡፡ የዚህ ችግር ምንጭም የባለሥልጣኑ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሠራተኞች አስተዳደር ደንብ ሲሆን፣ ይኼው ደንብ በአንቀጽ 37(2) ላይ ዋና ዳይሬክተሩ ሙስና ፈጽሟል ያሉትን ሠራተኛ በጥርጣሬ ብቻ ያለ ማስረጃ ማባረር እንዲችሉ ሥልጣን ይሰጣቸዋል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለት እንደማይቻል ይደነግጋል፡፡ ይህ አንቀጽ በሕገ መንግሥቱ የተሰጡትን ይግባኝ የማለትና የመዳኘት ሥልጣን እንደሚጋፋ በብዙ ምሁራን ቅሬታ ይቀርባል፡፡ የባለሥልጣኑ ሠራተኛ የነበሩት በዚሁ ደንብ መሠረት የተባረሩት አቶ ኢብራሒም ሞሐመድ ጉዳዩ ሕገ መንግሥቱን ይጥሳል በማለት ለፌዴራል የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ትራይቡናል አቅርበው፣ ትራይቡናሉም ጉዳዩን ወደ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ መርቶት ነበር፡፡ ጉባዔው በየካቲት ወር 2002 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ ድንጋጌው ከሕገ መንግሥቱ ጋር አይጣረስም ማለቱም ይታወሳል፡፡

አቶ በከር ይህ ቅሬታ በተለያዩ አካላት መቅረቡን አስታውሰው በመንግሥት አካላት ጭምር በተከታታይ መቅረቡ ግን እንዳልተዋጠላቸው አመልክተዋል፡፡ ‹‹ይኼ አንቀጽ የተካተተው ተቋሙን ከአደጋ ይታደጋል በሚል ነው፡፡ አፈጻጸሙ ላይ ግን ችግር አለ፡፡ ሁሉም አካል ይኼን አሠራር ይኮንናል፡፡ በዚህ እንደ ተቋም በጣም ተቸግረናል፡፡ አሁን ጥያቄ እያነሱብን ያሉት የመንግሥት አካላት ናቸው፡፡ የምናስፈጽመው የመንግሥት ደንብ ነው፡፡ ከተስማማን ሊቀየር ይችላል፡፡ አደጋው ግን የከፋ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ መተኮር ያለበት ለተፈጠሩት ችግሮች በር የሚከፍቱ የአሠራር ግድፈቶችን ለማስተካከል መንቀሳቀስ ላይ መሆን አለበት ብለዋል፡፡ ‹‹ከሰዶ ማሳደድ ይልቅ ሥርዓቱን አስተካክለን ብንሄድ ነው የሚሻለው፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል አስተባባሪ አቶ ዓባይ ፀሐዬ ችግሩ ሥር የሰደደ በመሆኑ በዘመቻ መፍታት ስለማይቻል ሥርዓት መዘርጋት በአስቸኳይ መፈጸም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ‹‹እኛ በመተማመን ነው እየሠራን ያለነው፡፡ መሬት ላይ ያሉት ነገሮች እኛ እንደምናስባቸው አይደሉም፡፡ አመለካከት እስኪቀየር ሥርዓት ሳንዘረጋ የምንጠባበቅ ከሆነ እንበላለን፤›› ብለዋል፡፡

ከአቶ ጌታቸውና ከአቶ ዓባይ በተለየ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከሉ ኃላፊ አቶ በረከት ስምኦን የግንዛቤ ማስጨበጥና የዘመቻ ሥራው ሥርዓት ከመገንባት ሥራው ጋር ጎን ለጎን መሄድ አለበት ብለዋል፡፡

አቶ መኩሪያ ባለሙያዎች ከሠለጠኑበት ዘርፍ ውጪ ተመድበው መሥራታቸው ትልቅ እንቅፋት መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ በአመራሩ አቅምና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ላይ ማመዛዘን ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙክታር ከድር ጥናቱ መልካም አስተዳደር ለማስፈን መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያጠናክር አቅጣጫ ያስቀመጠ ነው ብለዋል፡፡ የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ያዕቆብ ያላ የመንግሥት አካላት የቅንጅት ጉድለት እርስ በርስ ከመካሰስ ያለፈ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደመጣ አመልክተዋል፡፡ አቶ በረከት ጥናቱ በናሙና የተሠራ ቢሆንም፣ በመላው አገሪቱ በችግሩ ላይ ያለው ልዩነት ምን ያህል እንደሆነ የጠቆመ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል የኮሙዩኒክሽንና መረጃ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሴኮቱሬ ጌታቸው፣ ‹‹ጥናቱ የችግሩን ጥልቀት መቶ በመቶ ይገልጻል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በመሬት ላይ ያለው ችግር የከፋ ነው፡፡ ሕዝቡ የሚሰማው አካል እንደሌለ ነው የሚገልጸው፡፡ ሰብስበው ቢያናግሩንም መፍትሔ የለም ነው የሚለው፤›› ብለዋል፡፡ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ምክትል ኃላፊ አቶ አለበል ደሴ የባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነት የወንጀል ምርመራ ሥራን ሁሉ እያቋረጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

መሬት ላይ ያለውና የተጠቀሰው ችግር ስፋት አሳሳቢ ቢሆንም፣ ከገዢው ፓርቲና ከመንግሥት አቅም በላይ የሆነ ችግር እንዳልሆነ የገለጹት የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ አስቴር ማሞ ናቸው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ወሳኝነት የታየበት መድረክ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ አገሪቱ ይኼ ነው በሚባል ሁኔታ ወደኋላ ከመቅረት ይልቅ ለውጥ መምጣቷ ቢቀጥልም፣ ውሳኔ ሰጪነቱን የሚቀናቀኗቸው ቡድኖችና ግለሰቦች እንዳሉ ግን ሲነገር ነው የቆየው፡፡ በዚህ መድረክ በዚህኛው አምስት ዓመት ዋናው ወሳኝ አካል ‹‹እኔ ነኝ!›› ያሉበት ነበር፡፡

አቶ በከር ሻሌ በጥናቱ ላይ አመራሩ የሚሠራውን ሥራ አያውቅም የሚለው ጅምላ ፍረጃ አግባብ እንዳልሆነ ተናግረው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ቅሬታ ሲመልሱ፣ ‹‹አስተያየቱን ተገቢ ነው ብለን ብንወስድ ያስተምረናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ መሥሪያ ቤታችንን ከደላላ መንጋጋ ማላቀቅ ካልቻልን፣ በጥቅም ከተሳሰረ አሠራር ማላቀቅ ካልቻልን፣ መሥሪያ ቤታችንን እናውቃለን ብሎ ደፍሮ መናገር የሚቻል አይደለም፡፡ ለችግሩ የፖለቲካ መፍትሔ መስጠት እንችላለን፡፡ ባለሙያዎቹ የመሰላቸውን የመፍትሔ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ የተነሱት ነገሮች እውነት ናቸው ወይ የሚለው ነው ዋናው ነገር፤›› ብለዋል፡፡

ከወራት በፊት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር በአድዋ ለመገንባት ላሰቡት ፕሮጀክት ከክልሉ ትብብር እንዳላገኙ ቅሬታ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ በውይይቱ ወቅት አቶ ሴኮቱሬ ይህን ጉዳይ አንስተው ጉዳዩ ለአራት ዓመት ተኩል በእንጥልጥል መቅረቱ የመልካም አስተዳደር እጥረቱ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጊዜ የሕወሓት ምክትል ሊቀ መንበርና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ ‹‹የአድዋ ባለሀብት የተባለውን ጉዳይ እኔም አውቀዋለሁ፡፡ ሕገወጥ ሥራ ሲሠራ ማስቆም አለብን፡፡ ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ አይገባህም ከተባለ አይገባህም ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ‹‹ሴኮን እንደተረዳሁት ባለሀብቱ ትክክለኛ ነው አላለም፡፡ ምላሽ ስለመስጠት ነው ያነሳው፤›› በማለት አርመዋቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመቅረፍ በሥርዓት ግንባታ ላይ ያነጣጠሩ ባለሥልጣናትንም አርመዋል፡፡ ‹‹እንደ አዲስ የምንፈጥረው ነገር የለም፡፡ ምርጥ የመሬት ሪፎርም አዘጋጅተን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥርዓት ገንብተናል፡፡ የሪፎርም ፕሮግራሞቻችን እኮ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ የያዝነውን ፕሮግራም ተግባራዊ ሳያደርግ ነው እንዴ ወደ ሌላ ሥርዓት የምንሸጋገረው?›› ብለዋል፡፡

በመልካም አስተዳደር ዕጦትና በመፍትሔዎቹ ላይ ከዚህ ቀደም በርካታ ውይይቶች መደረጋቸውን ያስተወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አዲሱ ጥናት ከመፈክር የዘለለ መፍትሔ የሰጠ፣ የችግሩን ጥልቀት አመራሩ በአግባቡ እንዲያየው ያደረገና በውስጡ ድንጋጤ የፈጠረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ሁሉም የጥናቱን ውጤት ከልቡ ይቀበለዋል ማለት እንዳልሆነም አመልክተዋል፡፡ ‹‹በሽርደዳ ከሆነ የምንቀበለው ጥረታችን መውደቁ አይቀርም፡፡ ይኼ ከባድ አደጋ አለው፡፡ ጥናቱ ያመጣቸውን እውነቶች ጠራርገን መፍታት አለብን፡፡ ኅብረተሰቡ ውስጥ እውነት የሆኑና በአመለካከት ደረጃ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ካላቃለልን ለኅብረተሰቡ እስከ መቼ ነው ይፈታሉ እያልን የምንቀጥለው?›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጨረሻም የቡድንተኝነት ስሜት በፓርቲያቸው እንደሚንፀባረቅ ይፋ አድርገዋል፡፡ ‹‹እዚህ አገር ያለ ከባድ ፈተና እዚህ እናወራለን እንጂ፣ ከወጣን በኋላ የተለያየ የራሳችን መረብ እንዳይነካብን እንከላከላለን፡፡ ይኼ አንዱ ትልቁ በሽታ ነው፡፡ ብቻችንን ቆመን አቋም የምንወስድበት ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ የእኛ ነው የምንለውን ሰው ለመደበቅና ለመሸፈን ብቻ የምንሄድ ከሆነ ለውጡ አይሠራም፡፡ በብሔር፣ በአብሮ አደግነት፣ በተለያየ ጥቅም ትስስር የምንሠራና የምንከላከል ከሆነ አይሠራም፡፡ መፍትሔው የሚመሠረተው በከፍተኛ አመራሩ ቁመና ነው፡፡ ይህን ለመለወጥ ትክክለኛ የሕዝብ ተሳትፎ ላይ ሊሠራ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረውን አሰልቺ አካሄድ መከተል በሕዝብ ዘንድ ሊኖር የሚችለውን አመኔታ ያሳጣል፣ የሕዝቡንም ሞራል ይሰብራል በማለት የሕዝብ ተሳትፎ ጉዳይን መመርመር እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡ በሥርዓቱ ውስጥ የነገሠውን የደላላ ተፅዕኖ በቁርጠኝነት መታገል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -