እስቴር ሶምሎ የሚባል የጀርመን ሊቅ እንዲህ ይላል፣ እያንዳንዱ ሰው ሌላውን ሰው ሁሉ አጥቅቶ ለብቻው እንደ ፈቃዱ እንዲኖር ይወዳል፡፡ መንግሥት ግን በግዛቱ ውስጥ የሚኖሩትን ኃይለኞች ሁሉ እርስ በርሳቸው እንዲተፋፈሩ የግድ ይላቸዋል፡፡ የመንግሥት ጥረቱ ሕዝቡን ሁሉ አስማምቶ በመካከላቸው ሰላም ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም መንግሥት የተሻለውን ሥርዓት እያወጣ፣ ያወጣውንም ሥርዓት እንዳይፈርስበት ባለቤቱ ይጠብቃል፡፡ ሥርዓት አውጪውም ዳኛም መንግሥት ራሱ ነው፡፡ ከዳኝነቱ በቀር ሕዝቡን ከፍ ወዳለው የዕውቀትና የሀብት ደረጃ እንዲደርስ የማስተዳደሪያ ደንብ እያወጣ ባወጣውም ደንብ ሕዝቡን በሥርዓት ያስተዳድራል፡፡ ሕዝቡንም ማስተዳደር ማለት ጥንት የቆየውን የሕዝብ ጥቅም እንዳይጠፋ መጠበቅ ነው፡፡ ሌላውንም አዲስ ጥቅም አዘጋጅቶ አውጥቶ በግድ ማስፈጸም ነው፡፡ የሕዝብ ሐሳብና ሀብት ሲሰፋ መንግሥት ሐሳቡን ለማስፈጸም የበለጠ ኃይል ያገኛል፡፡
እንግዲህ እንደ ሊቁ ቃል ከሄድን ዘንድ፣ በመንግሥቱ ውስጥ የሚያድር ሕዝብ ዕውቀት የሌለውና ደሃ የሆነ እንደሆነ መንግሥቱ ኃይል ሊያገኝ አይችልም፡፡ እንኳን በውጭ አገር ሊታፈር የገዛ ሕዝቡም ቢሆን አያፍሩትም፡፡ በአገሩ ውስጥ ሽፍታ፣ ወንበዴና ሌባም ይበዛበታል፡፡ ሕዝቡ ዕውቀት ሲያድርበት ግን መንግሥት አዋቂዎች፣ ሠራተኞችንና ሹማምንቶችን ያገኛል፡፡ ሕዝቡም ሲበለፅግ መንግሥት በግብር የሚያገኘው ገንዘብ እየበዛ ይሄዳል፡፡
- ገብረሕይወት ባይከዳኝ ‹‹መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር›› (1916)