– በዚህ ሳምንት በማዕከል የሚደረገው ለውጥ ይፋ ይሆናል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለክፍላተ ከተማና ለወረዳዎች 1,600 አመራሮችን ሾመ፡፡ ለተሿሚዎቹ ባለፈው ሳምንት ለሦስት ቀናት የቆየ የፖሊሲ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሙስናና በብልሹ አሠራር ገምግሞ ካሰናበታቸው አመራሮች በተጨማሪ፣ ከዲፕሎማ በታች የትምህርት ደረጃ ያላቸውን አመራሮች አንስቷል፡፡ በእነዚህ ተሿሚዎች ምትክ ለአሥሩ ክፍላተ ከተሞችና ለ116 ወረዳዎች የተሾሙት 1,600 አመራሮች ከመጀመሪያ ዲግሪና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ናቸው ተብሏል፡፡
እነዚህ ተሿሚዎች አዳዲስና ከዚህ ቀደም በአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች በተለያዩ ደረጃዎች ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ተሿሚዎች ባለፈው ሳምንት ከማክሰኞ ጥቅምት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት የቆየ የፖሊሲ ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ታውቋል፡፡
የፖሊስ ማብራሪያውን የሰጡት የአዲስ አበባ አቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ይስሐቅ ግርማይና የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተወልደ ገብረ ፃድቃን ናቸው፡፡
በፖሊሲ ማብራሪያው እነዚህ ተሿሚዎች በከተማው መልካም አስተዳደር ማስፈን፣ የፀረ ሙስና ትግል በብቃት ማካሄድ እንዳለባቸውና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት መሥራት እንደሚኖርባቸው፣ በፖሊሲ ማብራሪያው ማሳሰቢያ እንደተሰጣቸው ከአቅም ግንባታ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተለይ አቶ ይስሐቅ በሥልጠና ወቅት እንደተናገሩት፣ ከዲፕሎማ በታች የትምህርት ደረጃ ያላቸው ከኃላፊነት የተነሱ አመራሮች በቀጣይ ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበት አሠራር ይፈጠራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የተነሱት የቀድሞ አመራሮች በጥቃቅንና በአነስተኛ ማኅበራት ተደራጅተው የተለያዩ ሥራዎችን እንዲያካሂዱ ይደረጋል ሲሉ አቶ ይስሐቅ በሥልጠናው ወቅት መግለጻቸው ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በክፍላተ ከተሞችና በወረዳዎች ሲያካሂድ የቆየውን ሹም ሽር በማጠናቀቅ፣ ትኩረቱን በማዕከል ደረጃ በሚያካሂደው ለውጥ ላይ አድርጓል፡፡ በዚህ ሳምንት መጨረሻ በማዕከል ደረጃ የሚያካሂደውን የመዋቅርና የባለሥልጣናት ሹም ሽር ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡